Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ‹‹ታሪካዊ›› ምርጫ አከራክሯል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ የሦስት ዓመት ሪፖርቶችን በአንድ አጠቃሎ ያቀረበበትን ጉባዔና ንግድ ምክር ቤቱን ለቀጣዩ ሁለት ዓመታት የሚመሩ የቦርድ አባላት ምርጫም አካሂዷል፡፡ የዘንድሮው ጠቅላላ ጉባዔ ለተከታታይ ዓመታት ከተካሄዱት የተለየም ነበር፡፡

መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄው የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት የታደሙት አባላት ቁጥር ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በርካታ ሲሆን፣ ይህም የዘንድሮውን ጉባዔ የተለየ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ከሌላው ጊዜ በተሻለም የንግዱን ዘርፍ የሚወከሉ አባላት በብዛት የተገኙበት ነበር፡፡ በዕለቱ ከ1,377  በላይ የምክር ቤቱ አባላት በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት መገኘታቸው ብቻም ሳይሆን ከአሥር ዓመታት ወዲህ በንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ በርካታ አዳዲስ አባላት የታዩበት መሆኑ፣ የዘንድሮውን ጠቅላላ ጉባዔ ለየት እንዳደረጉት ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው የኢንተርኮንትኔታል የስብሰባ አዳራሽ በመሙላቱ አባላት በሌላ ተጨማሪ አዳራሽ ውስጥ ስበሰባውን በስክሪን እንዲከታተሉ፣ አንዳንዶችም ቦታ አጥተው በቁማቸው የተሳተፉበት አጋጣሚ መታየቱ የዘንድሮውን ጉባዔ ለየት አድርጎታል፡፡

አከራካሪ ሆኖ የቆየናውና ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ምን ያህል ድምፅ ወይም የአባላት ቁጥር ያስፈልገዋል? የሚለው ጉዳይ  ይታወሳል፡፡ በዘንድሮው ስበሰባም 500+1 ወይም አብላጫው አባላት ከተገኙ ምልአተ ጉባዔ ይሆናል በሚለው አሠራር መሠረት ምልአተ ጉባዔ በመሙላቱ ስብሰባው ተካሂዷል፡፡ በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይና የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ አስተዳደሩ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር በጋራ ለመሥራት ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡ በተግባርም የአዲስ አበባ አዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ሴንተር ግንባታ ለማካሄድ ለሽያጭ ካቀረበው አክሲዮን ውስጥ ግማሽ ያህሉን በመግዛት ለከተማው የንግድ ኅብረተሰብ አጋር መሆኑን ያሳየበት ተሳትፎ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

የዕለቱ ጠቅላላ ጉባዔ በቀጥታ ያመራው የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ገነቴ የሦስት ተከታታይ ዓመታት ሪፖርታቸውን ወዳቀረቡበት ምዕራፍ ነበር፡፡ በንግግራቸውም ንግድ ምክር ቤቱ አከናውኗል ያሏቸውን ተግባራት የገለጹ ሲሆን፣ በተለይ የንግድ ኅብረተሰቡ ጥያቄዎችን በመንተራስ ከመንግሥት ጋር በተደረገ ውይይት አስቸጋሪ የተባሉ ሕግጋት እንዲሻሻሉ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃም ከከተማው አስተዳደር ጋር የምክክር መድረክ ለመፍጠር ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

 ንግድ ምክር ቤቱ ስለከወናቸው ሥራዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ኤልያስ፣ ያቀረቡትን የሥራና የሦስት ዓመታት የኦዲት ሪፖርት ጠቅላላ ጉባዔው አጽድቆላቸዋል፡፡ በውይይቱ ወቅትም ተሳታፊዎች አስተያየቶችንና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከተነሱት ሐሳቦች ውስጥ ወቅታዊውን አገራዊ ጉዳይ የተመለከቱም  ይገኙበታል፡፡ ሦስት ተሳታፊዎች በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውን የሰነዘሩ ሲሆን፣ አሁን ያለው ችግር እንዲፈታ ንግድ ምክር ቤቱ አስተዋጽኦ ያበረክት ዘንድ ጠይቀዋል፡፡ ይህንኑ የተሳታፊዎች አስተያየት በመመልከት አቶ ኤልያስ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ጉዳዩ በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ እንደሚያሳስባቸው፣ ንግድ ምክር ቤቱም ይህ ችግር እንዲፈታ ለማድረግ የሚችለውን አስተዋጽኦ ከአገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤት ጋር በመምከር ምን ይደረግ በሚለው ላይ እንወያያለን ብለዋል፡፡

ከዚህ ውጭ ንግድ ምክር ቤቱ አከናውኗቸዋል ከተባሉት ተግባራት በተቃራኒው አሁንም የሕግ ጥሰት እየፈጸመ ነው የሚለው አስተያየት ተስተጋብቷል፡፡

ወደ ምርጫው ሲገባም የንግድ ምክር ቤቱ ለዓመታት ሲተችበት የነበረው ጉዳይ መልኩን ቀይሮ ዳግም የመጣ አስመስሎታል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን የሚፃረሩ ሒደቶች ታይተዋል ያሉም አሉ፡፡ ከምርጫው ጋር በተገናኘ የሕግ ጥሰት ተከስቷል በማለት አስተያየት ከሰነዘሩት ውስጥ የቀድሞው የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ተሾመ በየነ ይጠቀሳሉ፡፡

 በዕለቱ ለፕሬዚዳንትነት በዕጩነት የቀረቡት ተወዳዳሪ አንድና ብቸኛ ብቻ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ለንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት እንዴት አንድ ዕጩ ብቻ ይቀርባል? የሚለው ጥያቄም የበርካቶች ነበር፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ በተፈጠሩ ውዝግቦች ምክንያት ለሁለት ዓመታት እንዲያገለግል የተመረጠው የቀድሞው አመራር ለሁለት የምርጫ ዘመን ወይም ከአራት ዓመታት በላይ ማገልገል እንደማይችል እየታወቀ፣ ከፕሬዚዳንቱ ሌላ ለቦርድ አባልነት በዕጩነት ከቀረቡት አንዳንዶቹ ድጋሚ በዕጩነት መቅረብ አልነበረባቸውም ተብሏል፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ብቸኛ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ንግድ ምክር ቤቱን ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ ሲመሩ የቆዩት አቶ ኤልያስ ገነቴ ናቸው፡፡

የዕጩዎችን ጥቆማ ሲያስተባብር የነበረው ኮሚቴ ሌላ ዕጩ ያልቀረበ በመሆኑ ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት አቶ ኤልያስ ገነቴ ብቻ መሆናቸን በመግለጽ እሳቸውን ብቻ ለጥቆማም ለምርጫም ይዞ ቀርቧል፡፡ ይህ አጋጣሚ በንግድ ምክር ቤቱ ታሪክ ያልታየ አዲስ ክስተት እንደሆነ የሚገልጹት፣ እስከዛሬ የተደረጉ ምርጫዎች አንዳንዶቹም የቱንም ያህል አወዛጋቢ ቢሆኑ እንኳ በየትኛውም የንግድ ምክር ቤቱ የምርጫ ታሪክ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ የቀረበበትን ሒደት አናስታውሰውም ያሉም ነበሩ፡፡ የምርጫ አመቻች ኮሚቴውም ሆነ አቶ ኤልያስ ሲመሩ የቆዩት ቦርድ ወደ ዕለቱ ምርጫ ከመምጣታቸው በፊት ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት አንድ ግለሰብ በብቸኝነት እንደሚቀርቡ ያውቁ ነበር በማለትም ምርጫውን ኮንነዋል፡፡ በመሆኑም ምርጫ ተብሎ አንድ ተወዳዳሪ ማቅረብ ዴሞክራሲያዊ ስለማይሆን፣ ቢያንስ በዕለቱ ከተሰበሰበው ጉባዔተኛ ተጠቁሞ ምርጫው ውድድር ቢታከልበት ይሻላል በማለት አካሄዱን የነቀፉም ነበሩ፡፡  

ብቸኛው ዕጩና ያለ ማንም ተቀናቃኝ አሸናፊነታቸው የተረጋገጠው አቶ ኤልያስ፣ እሳቸው ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸው ቅር እንዳሰኛቸው ቢገልጽም ሒደቱ ግን አልተለወጠም፡፡ ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃም አባላት የዕጩ ጥቆማ እንዲያካሂዱ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ቅስቀሳ ተደርጓል፡፡ በሚዲያዎችና በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ ጥሪ ተላልፏል በማለት ገልጸዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ያነጋገርናቸው አባላት፣ ምክር ቤቱ የተሻለ ጠቅላላ ጉባዔ ያካሄደ መሆኑን ባይክዱም አሁንም ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከችግር የፀዱ አለመሆናቸውን ታይቷል ይላሉ፡፡

ምክር ቤቱ ከችግር አለመውጣቱን የሚያመለክተው ሌላው ትዕይንት፣ የንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መጣሱ ነው ተብሏል፡፡ አቶ ተሾመ ጉዳዩ ሊፈተሽና ሊመረመር ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

አንድ ተመራጭ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ ማገልገል እንደሌለበት እየታወቀ ከአንዳንድ አባላት በቀደሙትም ሆኑ በአሁኑ ምርጫ ከሁለት ዘመን በላይ ያገለገሉ ሆነው ሳሉ በድጋሚ እንዲመረጡ ተደርጓል፡፡ ይህ የሕግ ጥሰት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ በዘንድሮው ምርጫ ከተካተቱት የቦርድ አባላት ውስጥ አንዳንዶቹ በሕግ ከተቀመጠው ውጭ ሲሆኑ አንዳንዶቹም ተመላልሰው ወደ ኃላፊነት የወጡ ናቸው፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና ሌሎች የቦርድ አባላት ለሁለት የምርጫ ዘመን ብቻ ያገለግላሉ ቢልም፣ እየታወቀ አቶ ኤልያስ ግን ለሁለት የምርጫ ዘመን በቦርድ አባልነት፣ ለሁለት የምርጫ ዘመን በፕሬዚዳንትነት መመረጣቸው የሕግ ጥሰት ነው ተብሏል፡፡

አቶ ኤልያስ ንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነትና በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በምርጫ ዘመምን ሲሰላ ከሁለት የምርጫ ዘመን ላይ በሥልጣን መቆየታቸውን ያሳያል፡፡ አስተያየት የሰጡ ወገኖች እንደሚገልጹ አቶ ኤልያስ ለፕሬዚዳንትነት ብቻ በሁለት ጠቅላላ ጉባዔዎች ተመርጠዋል፡፡ በቦርድ አባልነት ደግሞ በአንድ የምርጫ ዘመን ተመርጠው ሠርተዋል፡፡

ስለዚህ ለድጋሚ ውድድር እንዴት ይቀርባሉ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ በእርግጥ አቶ ኤልያስ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ ለአንድ ዓመት ካገለገሉ በኋላ ንግድ ምክር ቤቱ በፍርድ ቤት ታግዶ ምርጫው በመሰረዙ በድጋሚ በተደረገው ምርጫ ሊመረጡ ችለዋል፡፡ በመስከረም 27ቱ ምርጫም ብቸኛው ተወዳዳሪ ሆነው በድጋሚ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ ስለዚህ በሦስት ጠቅላላ ጉባዔዎች የተመረጡ በመሆናቸው፣ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ አገልግለዋልና በድጋሚ መመረጥ የለባቸውም በማለት ክርክር የሚያነሱ ቢኖሩም፣ ለቀጣዩ ሁለት ዓመታት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ከመሆን አልገደባቸውም፡፡

 አቶ ኤልያስ ምንም የሕግ ጥሰት እንዳልተፈጸመ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በቦርድ አባልነት ተመርጬ ሁለት ዓመት አገልግያለሁ፡፡ በ2006ቱ ምርጫ በፕሬዚዳንትነት ብመረጥም በፍርድ ቤት ታግዷል፡፡ በ2007 ዓ.ም. በባላደራ ቦርዱ በተደረገው ምርጫ አሸንፌያለሁ፡፡ ስለዚህ በፍርድ ቤት የተሻረው እንዴት ይቆጠራል?›› በማለት በጥያቄ መልሰዋል፡፡ ‹‹ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደርኩት ለሁለተኛ የምርጫ ዘመን በመሆኑ፣ በሕጉ የተቀመጠውን ደንብ አልተላለፍኩም፤›› ሲሉም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር አስገራሚ የተባለው የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ምርጫ ነበር፡፡

በዕለቱ ያለ ተወዳዳሪ የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት አቶ አበባው መኮንን ናቸው፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር ከዘርፍ የሚወከሉት በቀጥታ ምክትል ፕሬዚዳንት ስለሚሆኑ በዕለቱ ለቦታው የተደረገ ውድድር አልነበረም፡፡ ብዙዎችን ያነጋገረው ግን ባለፉት አሥር ዓመታት የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እየተፈራረቁ የተሰሙት አቶ አበባውና ትናንት የተኳቸው አቶ ታደሰ መሸሻ ናቸው፡፡

አቶ አበባው ለሁለት የምርጫ ዘመን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ተሰይመዋል፡፡ አቶ አበባው በአገር አቀፉ ንግድ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም በዘርፍ ምክር ቤቱ የቦርድ አባል በመሆን ከአንዱ ወደ ሌላኛው እየተዘዋወሩ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታውን ይዘው ቆይተዋል፡፡ ይህ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታ በሁለቱ ግለሰቦች ብቻ በፈረቃ መያዙ ከሚነሳበት የሕግ ጥያቄ ባሻገር ምክር ቤቱን ሌላ ተመራጭ የሌለው አስመስሎታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች