Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአራቱ የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳዎች

አራቱ የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳዎች

ቀን:

   በዘለዓለም እሸቴ (ዶ/ር)

ዛሬ ኢትዮጵያ አስከፊ ችግር ውስጥ ወድቃለች፡፡ ነገር እይተባባሰና የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ልጆቿ አደጋ ላይ ሳይወድቁ ይህን ክፉ ጊዜ የምታልፍበት መውጫ ቀዳዳ ያጣች ትመስላለች፡፡ መውጫ ቀዳዳዎች ከአንድም አራት አሉላት ይባል ይሆናል፡፡ መውጣትም አይቀሬ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ያልፋልና፡፡ ግን ዋናው ጉዳይ በአንደኛው መውጫ ቀዳዳ እንደምንም ብሎ መውጣቱ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ልጆቿ ኖረውላት፣ ፍቅርን አትርፈውላት፣ ታሪክን ሠርተውላት፣ በዓለም አንገቷን ቀና እንድታደርግ አድርገውላት፣ በድልና በክብር ካለችበት አደጋ የሚያስፈተልካት መውጫ ቀዳዳው የትኛው እንደሆነ ለይቶ ማወቁና መተግበሩ ላይ ነው፡፡

ታዲያ ለዚህ ፈውስን በሚያመጣው መውጫ ቀዳዳ በኩል ኢትዮጵያን የሚያስመልጡ ጀግናዎች ያስፈልጉናል፡፡ ለመሆኑ ታዲያ ኢትዮጵያ የጀግና አገር ናትን? መልሱ አንድ ሳይሆን ሁለት ነው፡፡ ያውም ተቃራኒ የሆኑት አዎና አይ ናቸው፡፡ እንግዲህ የዚህን ጭብጥ ለመረዳት ወደ ዝርዝሩ እንለፍ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ዕርምጃ እንዲወሰድ!›› እያሉ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎች ሽምግልና ቦታ የለውምና ‹‹አትደራደር!›› እያሉ ሲጮሁ ይሰማል፡፡ በዚህ መሀል ሽምግልና ቦታ ይሰጠው ብለን የምናቀነቅን ሰዎች ሁለቱም ወገን እንዲሰማን ስንሟገት እንገኛለን፡፡ በዚህ ግርግር ቆም ብለን ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ምኞትና ፍላጎት ምን ይሆን?›› ብለን እንድንጠይቅ ግድ ሊለን ይገባል፡፡

ሽምግልና መፈለግ የደካማነት ምልክት ሳይሆን የእውነተኛ ጀግንነትን ጥበብ የሚያመላክት ነው፡፡ ምክንያቱም ማሸነፍን ብቻ ሳይሆን ከማሸነፍ በስቲያም ማሸነፍን ያረጋግጣልና፡፡ ይህች ቀጭንና ጠባቧ መንገድ ናት፡፡ እንደሚታወቀው ሁለት ዓይነት የሽምግልና አካሄዶች አሉ፡፡ አንድም አድሏዊ የሆነ ከኃይለኛው ጋር የወገነ የይስሙላ ሽምግልና ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ አድሏዊ ያልሆነ ከማንም ያልወገነና እውነተኛ ሽምግልና ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ የምናየው ሽምግልና ፋይዳ የማይሰጠውን የይስሙላ ሽምግልና ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ካለችበት አጣብቂኝ እንድትወጣ ድልድይ የሚሠራውን እውነተኛውን ሽምግልና ነው፡፡ የዚህ እውነተኛ ሽምግልና ግብና ዓላማ በውይይትና በመግባባት አገሪቱን በሰላማዊ መንገድ ወደ ዘላቂ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ዕድገት የሚያመራውን ሒደት ለመፍጠር ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡

ሽምግልናን በተመለከተ መንግሥት ሁለት ምርጫዎች አሉት፡፡ አንድም በመግባባት መንገድ መሄድ፣ አለበለዚያ በእንቢተኝነት ዘራፍ ብሎ ‹‹ደምስሰው!›› እያለ መገስገስ፡፡ አማራጭ ኃይሎችም ሁለት ምርጫዎች አሉዋቸው፡፡ አንድም በመግባባት መንገድ መሄድ፣ አለበለዚያ ዘራፍ ብሎ ‹‹ገርስሰው!›› እያሉ መጓዝ፡፡ መንግሥትና ተቃዋሚዎች የሚመርጡዋቸው ምርጫዎች ኢትዮጵያን ከአራቱ አንዱን አካሄድ እንድትያዝ ያደርጋታል፡፡ እያንዳንዳቸውን በየተራ ለመመልከት እንድንችል እነዚሁ አራቱ የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳዎች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፡፡

  1. ተቃዋሚ ሽምግልናን ፈልጎ መንግሥት ግን ሽምግልናን ባይፈልግ፣
  2. መንግሥት ሽምግልናን ፈልጎ ተቃዋሚ ግን ሽምግልናን ባይፈልግ፣
  3. ሁለቱም ወገን ሽምግልናን ባይፈልጉ፣
  4. ሁለቱም ወገን ሽምግልናን ቢፈልጉ፣

አንደኛው የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ

መንግሥት ሽምግልናን ባይፈልግና ተቃዋሚዎች ሽምግልናን ቢመርጡስ?

አንድም ዘርፈ ብዙ የሆኑትን አማራጭ ኃይሎችን መግባባት እርስ በርስ ያቀራርባቸዋል፡፡ አንድ ድምፅ ይሰጣቸዋል፡፡ ልዩነታቸውን እንዲያጠቡ ያበረታታቸዋል፡፡ አንድነት ኃይል ይሆንላቸዋል፡፡ ጥያቄው ሕዝብ ያሸንፋል ወይ? አይደለም፡፡ ሕዝብ ሁልጊዜ አሸናፊ ነው፡፡ ግን እንዴት ያሸንፋል? ነው ጥያቄው፡፡ መግባባትን ለመረጠ አማራጭ ኃይል፣ ሕዝብ ሥልጣኑን ቢሰጠው የሕዝብ መንግሥት ለመሆኑ የተረጋገጠ ይሆናል፡፡ ቁምነገሩ እዚህ ላይ ነው፡፡ ከማሸነፍ ባሻገር ማሸነፍ አለ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ከማሸነፍ ባሻገር ያለው ማሸነፍ ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ማየት ነው፡፡ ይህም ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ መከራ ይበቃታል፡፡ እርስዋ እየደማች ተራ በተራ ንጉሦች የሚፈራረቁባት ጊዜ ያክትም፡፡ ልባችንን መጣል ያለብን ኢትዮጵያ ታሸንፍ ዘንድ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ‘ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ’ እንዳይሆን መግባባትን ዛሬውኑ ጓደኛ ማድረግ የሚበጀው፡፡

ደግሞም አማራጭ ኃይሎች መግባባትን ዕድል ቢሰጡትና መንግሥት እንቢ ብሎ ኃይሉን ብቻ ማፈርጠም ቢቀጥል፣ ይህ አካሄድ መግባባትን እንቢ ያለውን መንግሥት ብቻውን እንዲቀር ያደርገዋል፡፡ ሕዝብን ሁሉ አንድ ወገን አድርጎ እምቢተኛውን መንግሥት ያጋልጠዋል፡፡ እንቢተኝነቱ እርሱን የሚደግፉት ሁሉ እንዲክዱት ያደርጋል፡፡ ይህን አደጋ ለማምለጥ ምንም መላ አያገኝም፡፡ ሌላውን አጥፍቶ ሳይሆን እንዲሁ ብቻውን ራሱ ራሱን አጥፍቶ ታሪክ አልባ ሆኖ ሥፍራውን ይለቃል፡፡

ሁለተኛው የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ

መንግሥት ሽምግልና ቢፈልግና ተቃዋሚዎች ለሽምግልና ቦታ ባይሰጡትስ?

መንግሥት መግባባትን በሥራ ላይ ለማዋል መድረኩ በእጅ ነው፡፡ እንደሚገባ ኃላፊነቱን በዚህ ረገድ መወጣት የመሪነቱ ግዴታ ነው፡፡ ጊዜ ከወሰደ ዕድሉ ከእጁ እያፈተለከ እንደሆነና ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እየጣላት እንደሆነ ማወቅ አለበት፡፡ ነገር ግን ነገ ሳይል ዛሬ ሽምግልናን ቢቀበል ታሪክ ሠሪ መንግሥት ሆኖ በታሪክ መዝገብ ሊታወስና አዲስ ጅማሬን ለኢትዮጵያ የማውረስ አጋጣሚ አለው፡፡ መንግሥት መግባባትን ሲመርጥ፣ ለሚያልፍ ጊዜ ሥልጣን ላይ መቆየት ላይ ያነጣጠረ ራዕይ ሳይሆን፣ ራዕዩን አስፍቶ ፈር ቀዳጅ ድርጊትን አድርጎና ለታሪክ የሚቀር አሻራ ትቶ እንዲያልፍ ያሳስበዋል፡፡ ሕዝብ ብሎ በሥልጣን ቢቆይም በክብር፣ ሕዝብ ብሎ ሥልጣን ቢለቅም በክብር ይሆንለታል፡፡ ላስተዋለው እንዲህ ያለ ታሪክ ሠሪነትን በጀማሪነት የሚታደል አንዱ ጀማሪ ብቻ ነው፡፡ ይህን ዕፁብ ድንቅ የሆነውን ዕድል የሚቀናጀው የመግባባትን ጥሪ በእውነት ሲቀበል ነው፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት የመግባባትን ሰላማዊ ጥሪ ለሁሉም ቢያቀርብና ተቃዋሚዎች ለሰላሙ ጉዞ ሥፍራና ቦታ ካልሰጡ፣ ጉዳያቸው ስለኢትዮጵያ ሳይሆን መንግሥትን አውርዶ ራስን ዙፋኑ ላይ የማስቀመጥ ሩጫ መሆኑ ይታወቅባቸዋል፡፡ ተሳክቶላቸው እንኳን መንግሥት ቢለቅ፣ መግባባትን ንቆ በዘራፍ ቤተ መንግሥት የደረሰ አማራጭ ኃይል ሁሉ አንድነትን ፈጥሮ ለመጓዝ ያስቸግረዋል፡፡ ባሳለፍነው ታሪክም ያየነው እንደማይቻል ነው፡፡ በመግባባት የዛሬውን ልዩነት ዛሬ መፍታት እንቢ ብሎ ለይደር ያስቀመጠ፣ ያኔ ሥልጣኑ ተይዞ ልቡ ከየት ይመጣል? ያው አንዱ እንደተለመደው ደግሞ ሥልጣኑን ይይዝና ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም›› እንዲሉ ለኢትዮጵያ ጠብ የሚል ምንም ነገር ላይፈጠር ይችላል፡፡ እንዲያውም ‘ከድጡ ወደ ማጡ’ እንዲባል የባሰ ቢመጣ ምን የሚያስገርም ነገር አለ?

ሦስተኛው የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ

ሁለቱም ወገን ሽምግልናን ዓይን ላፈር ብለው በዘራፍ ጎዳና መንገድ

ለዚህ ምንም ማብራሪያ መስጠት አያስፈልገውም፡፡ ሁሌም ለዘመናት ያየነው ታሪካችን ነው፡፡ ለውጭ ጠላት ያሳየነው ‹‹እውነተኛ ጀግንነት›› ብዬ ስጠራ፣ ለእርስ በርስ ባለብን ግጭት አፈታት ላይ ያሳየነው ዘራፍነት ‹‹የክስረት ጀግንነት›› ብዬ እፈርጃለሁ፡፡ ምክንያቱም በውጭ ጠላት ላይ ባሳየነው ዘራፍነት ኢትዮጵያ አሸንፋለችና እውነተኛ ጀግንነት ነው፡፡ በሌላ በኩል እርስ በርስ ባለን ግጭት ላይ ያሳየነው ዘራፍነት ኢትዮጵያ ከስራለችና የክስረት ጀግንነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምን ከሰረች ቢባል፣ ዴሞክራሲና እኩልነት ለሕዝቡ ያላስገኘ ድርጊት ስለነበረ ነው፡፡ ለዚህም ነው እርስ በርስ ባለው የውስጥ ችግር ኢትዮጵያ እውነተኛ ጀግንነትን ለማየት እስካሁን አልታደለችም ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚቻለው፡፡

አራተኛው የኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ

ሁለቱም ወገን ሽምግልና ቢፈልጉስ?

ጉዳዩ በእውነት ስለኢትዮጵያ እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ መሪዎች ከራሳቸው የሥልጣን ጥማት ይልቅ የሕዝቡን የልብ ትርታ አዳመጡ ይባላል፡፡ ቁምነገሩ መንግሥትን በሥልጣን ማቆየት ሳይሆን፣ ወይም ደግሞ መንግሥትን ከሥልጣን ማውረድ ሳይሆን፣ የሕዝብ መሻት እንዲሆን ሁለቱም ወገኖች ራሳቸውን ለሰላም መንገድ መስዋዕት አድርገው ሊሰጡ መወሰናቸው ነው፡፡

ሁለቱም ወገኖች በሥልጣን ላይ ያለውም ሆነ፣ ወደ ሥልጣን ልምጣ ባዩ ቁጭ ብለው የሚደራደሩት ስለየራሳቸው የሥልጣን ዕጣና ፈንታ ሳይሆን፣ ስለሕዝብ ስንል ምን እናድርግ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነው፡፡ የመደራደሩ ውጤት የሕዝብን የበላይነት ለማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ነው እውነተኛ ጀግንነትን የሚጠይቀው፡፡ ይህ ነው ጥበበኛ የሚያሰኘው፡፡ ይህ መንገድ ነው እስካሁን በእውነተኛ ጀግንነትን የሚጠይቀው፡፡ ይህ ነው ጥበበኛ የሚያሰኘው፡፡ ይህ መንገድ ነው እስካሁን በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ውስጥ ያልታየው፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...