የአዲስ አበባና የዙርያው የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ አሁን መልኩን ቀይሯል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በወልቃይት የማንነትና የወሰን ለውጥ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ከ2008 ዓ.ም. አጋማሽ በኋላ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የበርካቶችን ሕይወት ከቀጠፈ በኋላ መልኩን ቀይሮ፣ የተለያዩ የአማራ ከተሞችና አካባቢዎች በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሟቸው ተሰምቷል፡፡
ከ60 በመቶ በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክሉት እነዚህ ሁለት ክልሎች የተቃውሞ አንድነት በመፍጠር አንዱ ጋ ጋብ ሲል በሌላው በኩል እየተቀጣጠለ ተቃውሞው እየተሰማ ይገኛል፡፡
በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች አንፃራዊ መረጋጋት በሚስተዋልበት በአሁኑ ወቅት፣ በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች የተቀሰቀሰው ግጭትና ተቃውሞ ማሳያ ነው፡፡
ባለፈው እሑድ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪውን በሚያመሰግንበት የኢሬቻ በዓል ላይ የተገኙ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች በስፋት ያስተጋቡት ተቃውሞን ተከትሎ፣ የደረሰው አሳዛኝ የወጣቶች ሕይወት ሕልፈት በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የንብረት ውድመትን እያደረሰ ያለ ሌላ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡
በኢሬቻ በዓል ላይ ለመታደም የተገኙ በአንድ ድምፅ ‹‹ወያኔ በቃን››፣ ‹‹ኦሕዴድ በቃን›› እያሉ በአንድነት በማስተጋባት ጥያቄያቸው ምን እንደሆነ በትክክል ለማስገንዘብ ሞክረዋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ ሥርዓትን ተጠቅመው ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ በበርካታ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ታዳሚዎች ለመበተን የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ በተኮሰው አስለቃሽ ጭስ በመደናገጥ በተፈጠረው መገፋፋት፣ በርካቶች ገደል ውስጥ ገብተው መሞታቸው በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የበለጠ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዚህ ቁጣ ወደ አደባባይ የወጡ ወጣቶች የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን ንብረት ከማውደም በላይ ብሔር ተኮር ጥቃቶች እየደረሱ ነው፡፡
ተቃውሞው ከተቀሰቀሰ ከዓመት በላይ ያስቆጠረ ከመሆኑ ባሻገርም ስፋቱ እየገዘፈ ይገኛል፡፡
የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተቃውሞዎች በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተቀጣጠለበት በነሐሴ ወር ላይ ተሰብስቦ የችግሩ መንስዔ ናቸው ያላቸውን መለየቱ ይታወሳል፡፡
ማዕከላዊ ኮሚቴው ነሐሴ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫም፣ ‹‹ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግሥትን ሥልጣን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ከማዋል ይልቅ፣ የግል ኑሮን መሠረት አድርጐ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅምን ማስቀደም ይታያል፤›› ብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሕዝብ ፍላጎትና የሥራ አጥነት ችግርን በፍጥነት አለመፍታት፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለተንሰራፋው የሕዝብ ተቃውሞ ምክንያቶች መሆናቸውን ገምግሟል፡፡
በተጨማሪም ከሥራ አስፈጻሚው ጀምሮ የትምክህተኝነትና የጠባብነት አስተሳሰብና ጥገኝነት መኖራቸውን፣ እነዚህንም በጥብቅ በመታገል እንዲተጉ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችን ማዘጋጀቱን በመግለጫው መግለጹ ይታወሳል፡፡
‹‹እነሆ ዛሬ ድርጅታችን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ መሠረታዊ መንስዔዎች በሌላ በማንም ሳያሳብብ በመንግሥትና በድርጅት ማዕቀፍ የሚታይ ቀዳሚ ችግር እንደሆነ ተገንዝቧል፤›› የሚለው ይኸው መግለጫ፣ ‹‹ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሚጠበቁ የለውጥ ፕሮግራሞች ተጠናክሮ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል፤›› ብሏል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ትኩረት የተደረገው በገዥው ፓርቲ ላይም ሆነ በመንግሥት መዋቅር አስፈጻሚዎች ላይ ሹም ሽርና የሽግሽግ ለውጥ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ለውጥ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ብቃት ላይ መሠረት ያደረገ ምደባ ማድረግን፣ ለዚህም የፓርቲ አባልነት ቦታ እንደማይኖረው ተገልጿል፡፡
ይህ ሹመትና ሽግሽግ ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ፓርላማው ሥራ ከጀመረ በኋላ በቀጣዮቹ የፓርላማው መደበኛ ስብሰባዎች የሚጠበቅ ነው፡፡
ኢሕአዴግ የሕዝቡን ጥያቄ ተረድቶታል?
ብሉምበርግ (Bloomberg) የተባለው የአሜሪካ ሚዲያ የኢትዮጵያ ወኪል ጋዜጠኛ በመሆን ከአምስት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ሲከታተልና ሲዘግብ የቆየው በዜግነቱ እንግሊዛዊ የሆነው ዊሊያም ዴቪሰን፣ በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ የሚዲያ ተቋማት በተሻለ ተቃውሞ በተካሄባቸው አካባቢዎች በመገኘት እንቅስቃሴዎችን በገለልተኝነት ተከታትሏል፡፡
ከሙያው ጋር በተገናኘ በተጓዘባቸው አካባቢዎች የተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን እንዴት እንደተረዳቸው ሪፖርተር ላቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፣ ‹‹ደካማ የሕዝብ አገልግሎት፣ መልስ የማይሰጥ የተኛ ቢሮክራሲ፣ በአግባቡ የማይሠሩ ፍርድ ቤቶች፣ የባለሥልጣናት ሙሰኛ መሆን፣ ያልተመጣጠነ የካሳ ክፍያና በመናር ላይ የሚገኝ የኑሮ ዋጋ (ግሽበት) ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ አማረውታል፤›› ብሏል፡፡
ከዚህ የሕዝብ ምሬት ጋር የተቀላቀሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መኖራቸውን እንደታዘበ የሚገልጸው ጋዜጠኛ ዊሊያም የዴሞክራሲ ዕጦት፣ የትግራይ (የሕወሓት) የበላይነትን አስመልክቶ የተፈጠረ እምነት (Perception)፣ የኦሮሞ ሕዝብ መገለል፣ የአማራ ወሰን ለትግራይ ተላልፏል የሚል ክስ ከላይ ከተጠቀሱት ጋር ተዋህደው በኢትዮጵያ አሁን ያለውን የፖለቲካ ቀውስ ፈጥረውታል የሚል አረዳድ እንዳለው ጠቁሟል፡፡
መንግሥት የገጠመውን ቀውስ ለመፍታት የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ሙስናን መታገልና ባለሥልጣናትን የማንሳት እንቅስቃሴና የአገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር ላይ ያሉትን ችግሮች ለማሻሻል ዕቅድ ቢኖረውም፣ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ፈጣንና ትልቅ ለውጥ ማምጣት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት እነዚህ ጉዳዮች ላለፉት በርካታ ዓመታት የመንግሥት ትኩረት አቅጣጫ የነበሩና ያልተሳኩ በመሆናቸው፣ የሕዝብ ተቃውሞን በመቀነስ ረገድ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል ብሎ እንደማያምን ይገልጻል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ናሁሰናይ በላይ፣ መንግሥት የሕዝብ ተቃውሞን አስመልክቶ ያደረገው ግምገማ ቁንፅል ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እንዲሁም የፓርቲው አባላት በተናጠል ባደረጉት ውይይት፣ የተቃውሞዎቹ መነሻ መሠረታዊ ምክንያቶችን አስመልክቶ የደረሱባቸው ድምዳሜዎች የችግሩ አካል ይሁኑ እንጂ ፓርቲው ሕመሙን አልተረዳውም ይላሉ፡፡
‹‹የችግሩ አረዳድ ላይ ነው ችግሩ፤›› የሚሉት አቶ ናሁሰናይ፣ ‹‹ፓርቲው የገጠመው የቅቡልነት ቀውስ (Legitmacy Crisis) ነው፤›› ብለዋል፡፡
ነፃ ፍርድ ቤት፣ ጤነኛ ፓርላማ፣ በቅጡ የሚሠሩ ኮሚሽኖች ተፈጥረው ሥራ አስፈጻሚውን ሥርዓት ማስያዝ ሲገባቸው የተገላቢጦሽ ሙሉ በሙሉ አንድ ፓርቲ ለሚቆጣጠረው መንግሥት ተገዥ እንደሆኑ፣ ይህም የሥልጣን መባለግ መፍጠሩን አቶ ናሁሰናይ ገልጸዋል፡፡
‹‹በአጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ሕገ መንግሥቱን ባለመምሰሉ ፓርቲው ሕዝባዊ ቅቡልነቱን አጥቷል፤›› ብለዋል፡፡
የሚጠበቀው ሹም ሽርና ሽግሽግ መፍትሔ ይሆናል?
ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በ2009 ዓ.ም. ሊከናወኑ ስለሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ለመንግሥት በሚሰጡት አቅጣጫ መደበኛ ጉባዔውን የሚጀምረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በቀጣዮቹ ቀናት በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀውን የካቢኔ አባላት ሹም ሽርና ሽግሽግ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህ የካቢኔ ሹም ሽርና ሽግሽግ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውሱን ለመፍታት ገዥው ፓርቲና መንግሥት ቃል ከገቡት መሠረታዊ ከሚባሉት መፍትሔዎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ሹም ሽርና ሽግሽግ፣ እንዲሁም በብቃት ላይ የተመሠረተ እንጂ የኢሕአዴግ አባልነት ላይ ያላተኮረ የካቢኔ ምሥረታ ፋይዳው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
ሪፖርተር በዚህ አዲስ የካቢኔ አወቃቀር ፋይዳ ዙሪያ ያነጋገራቸው መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ሌሎች መሠረታዊ የፖለቲካና የሕግ ማሻሻያዎች አብረው ካልተደረጉ፣ ‹‹የዓለም ምርጥ ብሩህ አዕምሮዎች ካቢኔውን ቢሞሉትም ለውጥ አይመጣም፡፡ አስቀድሞ ለቴክኖክራቶች አስቻይ ሁኔታዎች ሊዘጋጁ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ካልተፈጠረ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ካልተረጋገጠ፣ ሕግ ከፓርቲ አሠራር የበላይ ካልሆነ፣ በፖለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መሠረታዊ ማሻሻያዎች ካልተደረጉ ለቀውሱ መፍትሔ ይመጣል የሚል እምነት የላቸውም፡፡
አቶ ናሁሰናይም ተመሳሳይ አቋም ያንፀባርቃሉ፡፡ የችግሩ መሠረታዊ መነሻ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ሥርዓት ሕገ መንግሥቱን አለመምሰሉ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ናሁሰናይ፣ መልሱም ሕገ መንግሥቱን የሚመስል ፖለቲካዊ ሥርዓት መፍጠር መሆኑን ያሳስባሉ፡፡
ሹም ሽርና ሽግሽግ እንዲሁም ብቃት ላይ የተመሠረተ የካቢኔ አወቃቀር መፍጠር ቁንፅል መፍትሔ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡
ከሁሉም በላይ ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግሥት ያጣውን ሕዝባዊ ተቀባይነት በድጋሚ ለማግኘት መሥራት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
ይህም ማለት የዜጐችን ተቋማዊ አቅም መገንባት፣ የፖለቲካ መብታቸውን ያለ ገደብ እንዲተገብሩ ማድረግ፣ እንዲሁም መተማመንን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ፡፡
እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች በፍጥነት እየመለሱ መሄድ ካልተቻለ ግን ማንኛውም ዓይነት ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡