Thursday, September 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊተማሪዎች ወደየተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መሄድ አልቻሉም

  ተማሪዎች ወደየተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መሄድ አልቻሉም

  ቀን:

  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደ ተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ለመጓዝ መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው አውቶቡስ ተራ ቢገኙም በትራንስፖርት ችግር ጉዟቸው ተስተጓጉሏል፡፡

  ሐሮማያ፣ ጂማ፣ አሰላ፣ መቱ፣ ዲላ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ አርባምንጭ፣ ጅግጅጋና መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡት በርካታ ተማሪዎች ጉዞ የተስተጓጐለው ሰሞኑን እየተደረገ ያለውን ተቃውሞ ተከትሎ በተከሰተው የትራንስፖርት እጦት ምክንያት ነው፡፡

  በዕለቱ በመናኸሪያው ከተገኙት ተማሪዎች ከፊሎቹ ቲኬት እንቆርጣለን በሚል ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ሲሆን፣ እኩሎቹ ደግሞ በየቲኬት መቁረጫ ክፍሎች በራፍ ላይ በመሆን መረጃ ለማግኘት ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ ዕቃቸውን ይዘው ከመናኸሪያው ውጭ ቆመው የነበሩም ብዙ ነበሩ፡፡

  በሐዋሳና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ አንዳንዶች አማራጫቸውን ለመሞከር ወደ ቃሊቲ መናኸሪያ በሃይገር ባስ ተሳፍረው ሲጓጓዙ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የተወሰኑ ተማሪዎች ወደቃሊቲ የሚሄዱት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማደሪያ አዘጋጅቶላችኋል ስለተባሉ እንደሆነ ገልጸውልናል፡፡ ይህንን ያሏቸው የሕዝብ ትራንስፖርት የመናኸሪያ አስተዳደር፣ ስምሪት፣ አገልግሎትና ክትትል ቡድን መሪ መሆናቸውን ከተማሪዎቹ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

  ከመናኸሪያው የቲኬት መቁረጫ ክፍል ያገኘናቸው የግል አውቶቡስ ባለሀብቶች ማኅበር ሠራተኞች ችግሩ የአውቶቡስ እጦት ሳይሆን የትራንስፖርት ፀጥታ መደፍረስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሁኔታዎች ከተስተካከሉና በስምሪት ላይ አስተማማኝ ሰላም ከሰፈነ ለመንቀሳቀስ ወደኋላ የሚሉበት ምክንያት እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡

  እስካሁን አምስት አውቶቡሶች በስምሪት ላይ እንዳሉ ሙሉ ለሙሉ መቃጠላቸውን፣ በበርካታ አውቶብሶች ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ የውድመትና ጉዳት የደረሰባቸው አውቶቡሶች በባንክ ብድር የተገዙና ዕዳቸው ተከፍሎ ያላለቀ እንደሆነ ገልጸው የዕዳና የወለድ ክፍያው ላይ መንግሥት አስተያየት ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

  በጉዳዩ ዙሪያ ትምህርት ሚኒስቴርን፣ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣንና የመናኸሪያው አስተዳደርን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img