Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መሠረተ ልማትን ማኅበረሰቡ እንዲጠብቀው የጂቡቲው ፕሬዚዳንት አደራ አሉ

የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መሠረተ ልማትን ማኅበረሰቡ እንዲጠብቀው የጂቡቲው ፕሬዚዳንት አደራ አሉ

ቀን:

ባለፈው ረቡዕ መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀውን የአዲስ አበባ ጂቡቲ ዘመናዊ የባቡር መሠረተ ልማት የሁለቱ አገር ሕዝቦች ንብረት መሆኑን በመጥቀስ፣ የሁለቱም አገር ሕዝቦችና ማኅበረሰቦች ከጉዳት እንዲጠብቁት የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ይፋዊ የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው በለቡ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባቡር ጣቢያ ነው፡፡ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጉሌ ከሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ታድመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ላይ የነበሩት የቶጐው ፕሬዚዳንት ፍሬ ኢሶዚማ አጋጣሚውን ተጠቅመው በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ የቻይና ፕሬዚዳንት ልዩ መልዕክተኛም የፕሬዚዳንት ዥ ጂንፒንግ መልዕክት ለማስተላለፍ ተገኝተው ነበር፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግራቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጉሌ ኢትዮጵያንና ጂቡቲን ከ119 ዓመታት በፊት ያስተሳሰረው በአፍሪካ የመጀመሪያው የባቡር መሠረተ ልማት መሆኑን ጠቁመው፣ የሁለቱ አገሮች ሕዝብና መንግሥት በድጋሚ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን በኤሌክትሪክ የሚሠራ ዘመናዊ የባቡር ፕሮጀክት ዕውን በማድረግ ትስስራቸውን ዳግም እንዳደሱ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ትስስር እየላቀ መምጣቱን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ዘመናዊው የባቡር መሠረት ልማት የበለጠ ፋይዳ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢኮኖሚያዊ ውህደት የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ነው፤›› ሲሉ እርግጠኝነታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያደረጉትን ንግግር እንዳጠናቀቁም፣ ‹‹ይህ መሠረተ ልማት የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ንብረት ነው፤›› በማለት በአማርኛ ቋንቋ መናገር ሲጀምሩ በሥርዓቱ የታደሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንግዶች በአግራሞት ግር ተሰኝተው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ጉሌ ያደጉትና ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሁለቱን አገሮች ያስተሳሰረው የቀድሞው የባቡር መስመር በቆረቆራት ድሬዳዋ ከተማ በመሆኑ፣ አማርኛን አቀላጥፈው መናገር ይችላሉ፡፡

‹‹የሁለቱም አገር ሕዝቦች የባለቤትነት መብት ያለበት መሠረተ ልማት ስለሆነ ሁላችንም እንጠብቀው፤›› ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

አንድ ክፍለ ዘመን ሙሉ ሁለቱን አገሮች ያገናኘው የቀድሞው የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር አሁን አገልግሎቱን ቢያቆምም የማይረሳ ታሪካዊ አሻራውን አስቀምጧል፡፡ ይህንን የባቡር መስመር መዘርጋት ተከትሎ የተመሠረተችው ድሬዳዋ ከተማም ታሪካዊው አሻራ ያረፈባት በቀዳሚነት የምትጠቀስ ከተማ ነች፡፡

ታሪካዊው የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር የቆረቆራት ድሬዳዋ የኦሮሞና የሁለቱንም አገሮች የሱማሌ ብሔር ሕዝቦች ያስተሳሰረና ያዋለደ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

ኢትዮጵያ ብሔርን መሠረት ያደረገ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ብትከተልም፣ ድሬዳዋ ከተማ የዚህ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ልዩ ክስተት ሆና ራሷን በራሷ የምታስተዳድር በቻርተር የተቋቋመች የፌዴራል መንግሥት አካል ሆና ቀጥላለች፡፡

በዕለቱ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በታሪካዊው የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር መሠረተ ልማትን ተከትላ የተቆረቆረችው ድሬዳዋ፣ የደመቀች የንግድ መናኸሪያነቷንና የመሠረተ ልማቱ እስትንፋስ እንደነበረች አውስተዋል፡፡

አዲሱና ዘመናዊው የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መሠረተ ልማትም ለድሬዳዋ ደግሞ ተመሳሳይ ዕድልን ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ብቻ ሳትሆን አዳማና ደወሌ ደግሞ ዕድሉ ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡

የቻይና ፕሬዚዳንትን መልዕክት ያሰሙት ልዩ መልዕክተኛውም ፕሮጀክቱ የቻይና አፍሪካ ወዳጅነት መገለጫ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ለሁለቱ አገሮች ብልፅግና የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

ባቡሩ የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ ወደ ሥራ ሲገባ ኢትዮጵያን ከጂቡቲ ወደብ በፍጥነት የሚያገናኝ እንደሚሆን፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጌታቸው በትሩ ገልጸዋል፡፡ ባቡሩ ሥራውን በይፋ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው በያዝነው ዓመት አጋማሽ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር በመጓዝ አዲስ አበባን ከጂቡቲ ጋር በሰዓታት ውስጥ የሚያገናኝ ዓለም የደረሰበት ቴክኖሎጂን ያካተተ መሠረተ ልማት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቱ በጋራ የአገልግሎት አስተዳደር እንደሚከናወን፣ ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት አገልግሎትና ጥገናውን እንዲመሩ ሁለት የቻይና ኩባንያዎች እንደሚቀጠሩም ገልጸዋል፡፡ በዚህ የአገልግሎትና የጥገና ማኔጅመንት ሥራ ላይ 2,200 ኢትዮጵያውያንም የሥራ ዕድል እንደሚያገኙ ዶ/ር ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ 3.4 ቢሊዮን ዶላር የፈጀ ግዙፍና ትልቅ ሀብት የፈሰሰበት መሆኑን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዶ/ር ጌታቸው፣ ‹‹በባቡር መስመሩ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን መሠረተ ልማቱን እንድትንከባከቡትና እንድትጠብቁት እማፀናለሁ፤›› ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...