Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየማስፈጸም አቅም ውስንነት ለእግር ኳሱ አደጋ ሆኗል ተባለ

የማስፈጸም አቅም ውስንነት ለእግር ኳሱ አደጋ ሆኗል ተባለ

ቀን:

የእግር ኳሱን ልማት ማስፋፋትና ማሳደግ ይቻል ዘንድ የአቅምና የአመለካከት ችግሮች፣ እንዲሁም ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ችግሮቹን ለማቃለል በሚመለከተው የመንግሥት አካልም ሆነ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚጠኑ ጥናቶችና የሕግ ማዕቀፎችን ወደ መሬት በማውረድ ማስፈጸም አለመቻል በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ ይኽም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፖርቱ አካባቢ ለሚፈጠሩ ሁከቶችና አለመግባባቶች መንስዔ እየሆነ መምጣቱ በውይይቱ ተመልክቷል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባባር ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ለእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት ችግሩን የተመለከተ ዳሰሳ ጥናት አቅርበው ነበር፡፡ በሚኒስቴሩ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አምበሳው እንየውና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በተገኙበት በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በቀረበው ዳሰሳ ጥናት፣ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ በክለቦችና ብዙኃን መገናኛውን ጨምሮ በየደረጃው በሚገኙ ባለድርሻ አካላት ላይ ያሉትን ውስብስብ የአደረጃጀትና የአሠራር ችግሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ መድረኩም ችግሮችን ከመፍትሔው ጭምር አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2009 ዓ.ም. መርሐ ግብር ጥቅምት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ይጀምራል ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት፣ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልን መነሻ አድርጎ የቀረበው ዳሰሳ ጥናት፣ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ በክለቦች እንዲሁም በስፖርቱ ብዙኃን መገናኛና በሌሎችም ባለድርሻ አካላት የሚስተዋለውን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አመላክቷል፡፡ ይሁንና አፈጻጸሙን በተመለከተ ግን አሁንም ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች ነበሩ፡፡

እንደነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ከሆነ፣ የዚህ ተመሳሳይ ጥናት ከዚህ በፊት በነበሩ የውድድር ዓመታት ተደርጓል፡፡ ሌላው ቀርቶ በ1990 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣው ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲ፣ ‹‹ኅብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሠራበት ሁሉ ሕፃን፣ ታዳጊ፣ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ አዛውንትና አካል ጉዳተኛ ሳይል የጾታ፣ የዘር የቀለም፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ ልዩነት ሳይኖር ሁሉም ኅብረተሰብ አቅሙ በፈቀደ መጠን እንደ ፍላጎቱ የሚፈለገውንና ስሜቱ የመራውን የስፖርት ዓይነት በመምረጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ መሆኑን ይደነግጋል፤›› እንደሚል አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ግን እግር ኳስ ከስፖርታዊ ይዘቱ ይልቅ ፖለቲካ ይዘቱ እያመዘነ የመጣበት ሁኔታ ላይ መገኘቱን ያስረዳሉ፡፡

የቀረበው ጥናት በማጠቃለያው፣ ከብሔራዊ ፌዴሬሽን እስከ ክለብ አመራሮችና በተዋረድ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም ሆኑ ባለሙያተኞች በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ከኅብረተሰቡም ሆነ ከባለድርሻ አካላቱ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ሲቀርቡባቸው ቢደመጡም የአስፈጻሚ አካላትን ትኩረት እንደማያገኙ ነው ያስረዳው፡፡ ጥናቱ ሲቀጥልም እግር ኳሱ ይመለከታቸዋል በሚባሉ በሁሉም አካላት የአደረጃጀትና የአሠራር እንዲሁም የማዘውተሪያ ቦታ የግንኙነት ችግሮች እንዳሉበትም ተመልክቷል፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት ደግሞ በሁሉም ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከእግር ኳሳዊ ውይይቶች ይልቅ ፖለቲካዊ ውይይቶች ሚዛን እየደፉ ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት እየሆነ መምጣቱም በጥናቱ ታምኖበታል፡፡

እንደ ብዙዎቹ ተወያዮች ከሆነ፣ የአገሪቱ እግር ኳስ ችግሮችና መፍትሔውም በዚህ መልኩ መቅረቡ የሚደገፍ ሆኖ ሳለ በአስፈጻሚው አካል ላይ ያለው የአቅምና የቁርጠኝነት ጉዳይ ግን አሁንም ሊታሰብበት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...