Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሐዘን ያጠላበት ኢሬቻና የገዳ የዩኔስኮ ጥያቄ

ሐዘን ያጠላበት ኢሬቻና የገዳ የዩኔስኮ ጥያቄ

ቀን:

ለወትሮው ወደ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ የሚወስደው ጎዳና ኢሬቻን ለማክበር ከተለያዩ አካባቢዎች በተሰባሰቡ እድምተኞች ኅብረ ዝማሬ ይደምቅ ነበር፡፡ አደይ አበባና ለምለም ቄጤማ የያዙ እንስቶች ‹‹መሬ ሆ›› እያሉ ወደ ሐይቁ ሲወርዱ ወንዶችም በራሳቸው ዜማ ያጅቧቸዋል፡፡ ዘንድሮ ይህን መሰል ድባብ አልተስተዋለም፡፡ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ የተቃውሞ ድምፅ ይስተጋባ ነበር፡፡

ከክረምት ወደ ብራ መውጣትን ምክንያት በማድረግ የሚቀርብ ምስጋና ሳይሆን መንግሥትን የሚቃወሙ መፈክሮች ተደምጠዋል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ለመጪው ጊዜያት መልካም ምኞቱን የሚያሳልፍበት ኢሬቻ፣ የሐዘን ድባብ አጥልቶበታል፡፡

ከማለዳ አንስቶ በሆራ አርሰዲ ሐይቅ የተሰባሰቡ የበዓሉ አክባሪዎች ለሰዓታት የቀጠለ ተቃውሞ ያሰሙ ነበር፡፡ ለዓመታት በአካባቢው ይደረግ እንደነበረው አባገዳዎች ሕዝቡን አልመረቁም፡፡ በኢሬቻ ዕለት ከአባገዳዎች ምርቃት በመቀበል የተጀመረ ትዳር መልካም ይሆናል ተብሎ ይታመናልና ቀድሞ በቦታው ብዙ ጥንዶች ይገኙ ነበር፡፡ ዘንድሮ የተገኙት በጣት የሚቆጠሩ ጥንዶች አልተሞሸሩም፡፡ በተቃራኒው አካባቢው በለቅሶና በዋይታ ተውጧል፡፡

ረፋድ ላይ ተቃውሞው ይጋጋል ጀመረ፡፡ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሆኑና አካባቢው በአስለቃሽ ጭስ ተሸፈነ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የሆራ አርሰዲ ሐይቅ አቅራቢያ ሕይወታቸው ባለፈ የበዓሉ አክባሪዎች ተሞላ፡፡ ቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸው የሞቱባቸውና የተጎዱባቸው ሰዎች ዋይታ ልብ ይሰብራል፡፡ የዘንድሮው ኢሬቻ አሳዛኝ ገጽታ በማኅበረሰብ ድረ ገጽ የተሰራጨው በፍጥነት ነበር፡፡ ሕዝቡ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ከመግለጹ ባሻገር ከመስረከም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ታውጇል፡፡

የሐዘን ድባብ ያጠላበት ኢሬቻን በተመለከተ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የገዳ ሥርዓትን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ላይ የማስመዝገብ ሒደትን የተመለከተ ነበር፡፡ በእርግጥ የብዙ ሰዎች ሕይወት መቀጠፉ እየታዘነ ባለበት ወቅት ጥያቄው መነሳትም የለበትም የሚሉ አካሎች ጥቂት አይደሉም፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ፣ በሚኒስቴሩ ስም የጠለቀ ሐዘናቸውን አስተላልፈው፣ ስለ ዩኔስኮ ጉዳይ መግለጫ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን የገዳ ሥርዓትን በዓለም ቅርስ አስመዝጋቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ገዛኸኝ ግርማ፣ መጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ፓሪስ ለሚገኘው የዩኔስኮ ጽሕፈት ቤት ገዳ በዓለም አቀፍ የወካይ ቅርስ መዝገብ ላይ እንዲሰፍር ጥያቄ መላኩን አስታውሰው፣ በዘንድሮ ኢሬቻ የተፈጠሩ ሁኔታዎች መመዝገቡ ላይ ተፅዕኖ እንደማይኖራቸው ገልጸዋል፡፡

የገዳ ሥርዓት ዩኔስኮ የሚጠይቃቸውን መሥፈርቶች በማሟላቱ፣ ከኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚካሄድ ከሚጠበቀው 11ኛው የዩኔስኮ የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶችን የሚመለከተው ኮሚቴው ስብሰባ በኋላ በዓለም ወካይ ቅርስነት ለመመዝገብ ያለውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ገዛኸኝ ግርማ ገለጻ፣ ስለ ገዳ ሥርዓት የሚገልጹ ጽሑፎች ዘጋቢ ፊልሞችና ፎቶዎች እንዲሁም የሕዝቡን ይሁንታ የሚያሳይ የፊርማ ዝርዝር ለዩኔስኮ ተልኳል፡፡ በገዳ ዙሪያ ከድርጅቱ ለተነሱ ጥያቄዎችም መልስ ተሰጥቷል፡፡ ሥርዓቱ በዩኔስኮ መዝገብ ላይ መስፈር የለበትም ብለው የሚከራከሩ አካሎች አሉ፡፡ እነዚህ አካሎች የአፍሪካ ናይሎቲክና ኦሞቲክ ሕዝብ ጥምረት (The Alliance of Nillotic and Omotic People of Africa-NOPA) ሲባሉ ለዩኔስኮ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ ባለሙያው በበኩላቸው፣ የገዳ ሥርዓት በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገብ እንዳለበት አሳማኝ ማስረጃ መቅረቡን ያስረዳሉ፡፡ ዩኔስኮም ማስረጃዎቹን ከፈተሸ በኋላ ተቃውሞውን ያነሱ አካሎች ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡ ዩኔስኮም የመጨረሻ ውሳኔውን የሚያስተላልፈው በዘንድሮው ኢሬቻ ብቻ ሳይሆን በቀደሙት ዓመታት በተላኩ ሰነዶች በመሆኑ የመመዝገብ ተስፋውን ያለመልመዋል ብለዋል፡፡ ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት መገለጫዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

አቶ ገዛኸኝ አባተ እንደገለጹት፣ ገዳ በዩኔስኮ ላይ ስለመመዝገቡ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም፣ እስካሁን ከዩኔስኮ የተገኙ ምላሾች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ በእርግጥ በሆራ አርሰዲ ሐይቅ የሚከናወነውን ሥርዓት ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቁ የነበሩት የዩኔስኮ ተወካዮች በተቃውሞው ምክንያት በቦታው አልተገኙም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣኖችና አባ ገዳውም አልነበሩም፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ትኩረትም የአገሪቱ አለመረጋጋት ጉዳይ ነው፡፡

ኢሬቻ በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙዎች ከሚከበሩ በዓሎች አንዱ እንደመሆኑ በተፈጠረው ሁኔታ ስሜታቸው የተነካ በርካቶች ናቸው፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በሐዘኑ ምክንያት ገዳን በዩኔስኮ የማስመዝገብ ጥያቄን በአሁን ወቅት ማንሳት ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ገዳን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ አድርጎ የማስመዝገብ ነገር አብቅቶለታል የሚሉ አካሎችም አሉ፡፡

አቶ ገዛኸኝ አባተ፣ ‹‹ያለነው በሐዘን ድባብ ውስጥ ቢሆንም ኅብረተሰቡ ላይ ውዥንብር እንዳይፈጠር ስለምንፈልግ ገዳን በዩኔስኮ ላይ የማስመዝገብ ጉዞ እንደማይገታ እንገልጻለን፤›› ብለዋል፡፡ የገዳ መገለጫ ከሆኑ ሥርዓቶች በአንዱ ኢሬቻ የተፈጠረው እልቂት በእጅጉ ቢያሳዝንም፣ የገዳ ሥርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገሩ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡

በአቶ ገዛኸኝ ግርማ ገለጻ፣ ገዳን በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ለማስመዝገብ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተዋል፡፡ ስለ ገዳ ሥርዓት ምንነት፣ ታሪካዊ አመጣጥና ለኦሮሞ ሕዝብ ያለው ጠቀሜታ ተሰንዶ ቀርቧል፡፡ ገዳ በአገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡም ለዩኔስኮ ተገልጿል፡፡ ገዳን የመመዝገብ ሒደት ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ደረጃዎች በማለፉ በዘንድሮው የኢሬቻ ክስተት ዩኔስኮ ወደኋላ ተመልሶ ገዳን እንዲመዝን እንደማያደርገው እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዩኔስኮ የሚያተኩረው ያቀረብነው ሰነድ ላይ ነው፡፡ ገዳን ጠብቆ ለማቆየት የሚደረጉ ጥረቶችና ቅርሱ ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች የማይፃረር መሆኑን አሳውቀናል፤›› ብለዋል፡፡

በገዳ ምዝገባ ዙሪያ በቢሾፍቱ ከተማ መስከረም 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥናትና ጥበቃ አስተባባሪ አቶ ስንታየሁ ቶላ የዩኔስኮን የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በተመለከተ በውይይቱ ላይ ባቀረቡት ጥናት መሠረት፣ ገዳ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቃላዊ ትውፊት (ኦራል ትራዲሽን ኤንድ ኤክስፕረሽን) መስፈርትን ያሟላል፡፡

እንደ ፉከራና ውዝዋዜ ያሉት የሥርዓቱ አካሎች አንድ ቅርስ ክውን ጥበባትን (ፐርፎርሚንግ አርትስ) ማካተት አለበት የሚለውን መስፈርት ያሟላሉ፡፡ በተጨማሪም በኢሬቻ ባህላዊ ክንውን ላይ የሚስተዋሉ ልማዶችም (ሪችዋል) የመስፈርቱ አካል ነው፡፡ የገዳ ሥርዓት ውስጥ በየስምንት ዓመቱ የሚካሄደውና አንድ ሰው ከአንድ እርከን ወደ ሌላው ሲሸጋገር ያለው ባህላዊ ሥርዓትም ይጠቀሳል፡፡

የገዳ ሥርዓት የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖሩና አገር በቀል ዕውቀት (ኢንዲጅንየስ ኖሌጅ) መተግበሩ ይንፀባረቅበታል፡፡ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴን ለማከናወን የሚውሉ የዕደ ጥበብ ውጤቶች (ትራዲሽናል ክራፍትስማንሽፕ) በሚል በዩኔስኮ የተቀመጠውን መስፈርትም ያሟላል፡፡ ሴቶች መብታቸውን የሚያስጠብቁበት የሲንቄ ሥርዓትም ተጠቃሽ ነው፡፡

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ፣ የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ መመዝገብን ከአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥርን ከመጨመር አንፃር ይገልጹታል፡፡ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተውጣጣ  ባህልን የሚያንፀባርቅ የጎዳና ትርዒትና ሩጫ በቢሾፍቱ የተዘጋጀው ለዚሁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የጎዳና ትርዒቱና ሩጫው መስከረም 20 እና 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በከተማዋ ተካሂዷል፡፡ ከነዚህ ክንውኖች በኋላ ግን ኢሬቻ ላይ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ገጽታቸውን ለውጠዋል፡፡

ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የኦሮሞ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት የሚከናወንበት ገዳን በዩኔስኮ የማስመዝገብ እንቅስቃሴና የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የተፋጠጡ ይመስላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...