Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርእውን በኢትዮጵያ ሴም የሚባል ሕዝብ አለ?

እውን በኢትዮጵያ ሴም የሚባል ሕዝብ አለ?

ቀን:

በብርቱካን ወለቃ

በዓለም ላይ  የሥነ ሰብ ተመራማሪዎች የዓለምን ሕዝብ ጥቁር፣ ነጭ፣ ቢጫ፣ቀይ ከማለት አልፈው ሴም፣ ኔግሮይድ፣ ከውኮሴድ እያሉ ይመድቧቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ደግሞ የኖኅ ልጆች በመባል የሚጠሩት ሴም፣ ካምና ያፌት ይባላሉ፡፡ ከካም ልጆች ኩሽ ጥቁር ሕዝቦች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ አሠፋፈራቸውም አፍሪካና አካባቢው መሆኑ ይነገራል፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ ሃይማኖታዊ ትውፊትና የሥነ ሰብ ምርምር ውጭ የተለያዩ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የፖለቲካ አጥኚዎች በተለያየ ጊዜ ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች የተሳሳተና የተዛባ መረጃዎችን በማደባለቅ ሲጽፉና በቤተ እምነቶች ጭምር ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡

ሌላ ሌላውን ትተን በ13ኛው ክፍለ ዘመን በመጀመሪያ በግሪክ ቋንቋ ቀጥሎ በዓረብኛ ቀጥሎ ወደ ጀርመን ከዚያ ወደ ግዕዝ በቅብብሎሽ የተጻፈውና የተተረጎመውን ጸሐፊዎች የራሳቸውንና የንጉሣቸውን ፍላጎት እየጨማመሩ የጻፉት ክብረ ነገሥት (Glory of Kings) የሚባለው የተረት መጽሐፍ፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የተዛባ የማንነት ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት ከሆኑት ምንጮች አንዱ ነው፡፡ ይህ የተረት መጽሐፍ የግሪኩ ትርጉም ከዓረብኛው፣ የዓረብኛው ከጀርመኑ፣ የጀርመኑ ከግዕዙ እጅግ የተለያየ ነው፡፡ ለምን ተጻፈ፣ በማን ተጻፈ የሚለውን በሌላ ጊዜ የምመልስበት ሆኖ በዋናነት ግን ሥልጣንን ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰለሞናዊው ተብየ ሥርወ መንግሥት በሐሰት ለማስተላለፍ የተጻፈ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ሃይማኖታዊ ዲስኩር የተጨመረበት ሥልጣን በእግዚአብሔር ጭምር ለተፈቀደላቸው የእስራኤል ወገን ለሆኑት የሰለሞን ዘሮች ብቻ የተሰጠ ነው በሚል የአገው ሕዝቦች መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን አስረክበው አለት በመቆርቆር ቤተ ክርስቲያን ማነፃቸውን ተያያዙት፡፡ የንግሥት ሳባ የንጉሥ ሰሎሞን ጥበብ ለማየት ጓጉታ ለጉብኝት በሄደችበት ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት በንጉሡ ተደፍራ እንድታረግዝና ወንድ ልጅ እንድትወልድ ተደርጎ የተተረተው ተረት እውነት ሆኖ ሳይሆን፣ የግድ የነጮችና የዓረቦች ተንኮል ኢትዮጵያን ከአናቷ በመቆጣጠር ዓባይ ያለምንም ከልካይ ወደ ግብፅ እንዲፈስ ለማድረግ የተሸረበ ሴራ ነበር፡፡ ለዚህ ዓለማቸው ያግዝ ዘንድ በክርስትና ማስፋፋት ስም የኢትዮጵያን ማንነት ከኩሽ ወደ ሴሜቲክ መቀየር የግድ አስፈላጊ ነበር፡፡ ዓረብና እስልምና እንዳይቀላቀልባችሁ፡፡

ለዚያ ይረዳ ዘንድ ሳባ በሰሎሞን መደፈር ነበረባት፡፡ ከዚያ ወንድ ልጅ መውለድ ነበረባት፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ያ ከሰለሞን ተወለደ የሚባለው ‹‹ቀዳማይ ምንሊክ›› ከ20 ዓመት በኋላ ወደ አባቱ አገር መሄድ ነበረበት፡፡ ከዚያም ከእስራኤል ወገን የሆኑ 12 ሺሕ አጃቢዎች የራሳቸውን ታቦተ ጽዮን ሰርቀው ወደ ኢትዮጵያ  መምጣት ነበረባቸው፡፡ንጉሥ ሰለሞን በማይገዛት አገር ኢትዮጵያ ልጁን ‹‹ንጉሠ ነገሥት ሞዓ አንበሳ ዘ ዕምነ ነገደ ይሁዳ›› ብሎ መሾም ነበረበት፡፡ አስቡት ይህ የሰለሞን ልጅ ተብየው መሾም እንኳ ካለባት የመሾም ሥልጣን ያላት ንግሥት ሳባ እንጂ፣ ንጉሥ ሰለሞን ሲጀመር በኢትዮጵያ ልጁን ንጉሥ አድርጎ ለመሾም ምንም ዓይነት ሥልጣን አልነበረውም፡፡ የውሸቱ የካብ ድርድር ከዚህ ላይ ይናዳል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን የሴም ምድር የማድረጉ ዘመቻ ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ እምንት ድረስ ተሰበከ፡፡ የሰሜኑ ኩሽ ሕዝብ (አገው) እየተንደረደረ ራሱን ከኩሽ ወደ ሴሜቲክ ‹‹ቀይሬያለሁ›› በማለት በውሸት ጉራ ተነፋ፡፡ ሴሚቲክ ነኝ ማለት ምድራዊ ሥልጣን በር ከማስከፈት አልፎ ሰማያዊ ቤተ መንግሥትም ወራሾች እኛ ብቻ ነን እንዲሉ አስባላቸው፡፡ ይህን የውሸት ማንነት ያልተቀበለውን ሕዝብ ከቦታው በማፈናቀል ማፍለስ ተያያዙት፡፡ የኢትዮጵያ መሬት ከባለቤቱ ወጥቶ በቤተ መንግሥትና በቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በሰሜንና በሰሜን ምዕራብ የሚገኙ ሕዝቦች ሙሉ በሙሉ በማንነት ቀውስ ውስጥ ወደቁ፡፡ የውሸት ማንነት ቀድመው የወሰዱት ባልተቀበለው ላይ የስድብ ናዳ ማውረድ ጀመሩ፡፡ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሰው ‹‹ከእንጨት ተገኘ›› በማለት በቤተ ክርስቲያን ጭምር ተሰበከ፡፡ የጽድቅን በር ቁልፍ በእነሱ እጅ የተያዘ እስኪመስል ድረስ ማንነቱን ያልቀየረ ሕዝብ ገሀነም ገቢ ነው ብለው አስተማሩ፡፡

ከመሬታቸው የተፈናቀሉ አገዎች ‹‹ፈላሻ›› ተብለው መሬት አልባ በመደረጋቸቸው በብረት ቅጥቀጣ፣ በሸማ ሥራ፣ በሸክላ ሥራ በመሰማራት ኑሯቸውን እንዲገፉ ተገደዱ፡፡ ማንነታቸውን ቀይረው መሬታቸው ያልተነቀሉትም ቢሆን በጭሰኝነት እንዲማቅቁ ተደረገ፡፡ ጎንደር ቋራ፣ ወገራ፣ አርማጭሆ የነበሩ የአገው ክፋይ የሆኑ ሕዝቦች የዚህ ታሪካዊ በደል ሰለባ እንዲደረጉ ሆነ፡፡  በደንቢያ፣ በአለፋ፣ በቋራ፣ በአርማጭሆ በከፊል ጭልጋ በጐንደር ዙሪያ በበለሳ ይኖሩ የነበሩ ቅማንቶች ሳይወዱ በግድ ሴሜቲክ ነኝ ብለው በመሬታቸው እንዲቀመጡ ሲደረግ ማንነታችን እንቀይርም ያሉ ከጐንደር በከፊል ተገፉ፡፡ በመሬታቸው ላይ አስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ጭሰኛ እንዲሆኑ ተደረጉ፡፡ በተለምዶ ቤተ እስራኤል የሚባሉ የአገው ሕዝቦች ፈላሻ ተብለው በመጨረሻ ከእናት ምድራቸው ጐንደር እንዲለቁና ወደማያውቁት አገር እንዲሰደዱ ተገደዱ፡፡

የሰሜንና የሰሜን ምዕራብ ሕዝቦች በውሸት የበላይነትና የበታችነት ቀውስ ውስጥ ተዘፈቁ፡፡ ቀድሞ ክርስትናን የተቀበለው ባልተቀበለው ላይ ጦርነት አወጀ፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ ዘመተ፣ ወንድም ውንድሙን ናቀው፡፡ ኢትዮጵያን ዘንግተው ገዥዎችና ተከታዮቻቸው እኛ ‹‹ከእስራኤል ወገን የሆን ሴማዊ ነን›› ብለው ታበዩ፣ ሌላውን ሕዝብ ናቁ፡፡ የጎጃምና የበጌ ምድር ጋፋት ሕዝቦች ቀድመው ማንታቸውን ከለወጡትና በሌላው ሕዝብ ላይ የበታችና የበላይ የሚል ስብከታቸውን ተያያዙት፡፡ በተለይ ጋፋቶች ቀድመው ቤተ ክርስቲያን ውስጥና ቤተ መንግሥት በመሰግሰግ በአገው ሕዝቦች ላይ ይቅር የማይባል ግፍ ፈጸሙ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ ቆመው የአገው ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅ አያገኝም አሉ፡፡

ይህ የማንነት ቀውስ ዛሬም ድረስ በመቀጠሉ አንድን ሕዝብ ሌላኛው በመናቅ በመሳደብ ቀጥሏል፡፡ በዚህ የማንነት ቀውስ ውስጥ ያልወጡ ቡድኖች ዛሬም ወገናቸውን ከማሳደድ አልተመለሱም፡፡  ሲፎክሩና ሲያቅራሩ እንትን ገዳይ፣ የእንትን ዘር እንትን ገዳይ፣ እንትን በሊታ በማለት ሳይፈሩ ይናገራሉ፡፡ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ጐንደር ላይ በግልጽ በሐምሌ 2008 ዓ.ም. በግልጽ በአደባባይ ተነግሯል፡፡ እነዚህ ሰዎች ዛሬም ሳያፍሩ በሕዝብ ላይ ጸያፍ ንግግር ይናገራሉ፡፡

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶለሳ የሚባሉ ግለሰብ በኢትዮጵያ ሴም የሚባል ሕዝብ እንደሌለ ከስንት ዓመት በኋላ ይህን ሀቅ ለመጻፍ ተንደረደሩ፡፡ ‹‹ሴሜቲክ የሚባል ሕዝብ በኢትዮጵያ ምድር የለም፡፡ ሁሉም የኩሽ ዘር ነው›› አሉ እኚህ ግለሰብ ፈረንጆች  ከመቅረት መዘግየት ይሻላል እንደሚሉት አባባል ሀቁን መናገራቸው መልካም ቢሆንም፣ ድሮ የሚያውቁትን ሀቅ በዚህ ወቅት መጻፍ የፈለጉበት የራሳቸው ፖለቲካዊ አጀንዳ ያነገበ ለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ቢሆንም እንኳንም እየመረራቸውም ቢሆን ሀቁን ተናገሩት፡፡ አስታውሳለሁ እኚህ ፕሮፌሰር በአንድ ወቅት በ2004 ዓ.ም. አካባቢ በኢትዮ ሚዲያ ድረ ገጽ የጻፉት ጽሑፍ መቼውንም ቢሆን አልረሳውም፡፡ አንድን ብሔር ለይተው ‹‹አገር አቅኝ›› ሌላው ግን መጤና ተጠማኝ፣ ይህ እሳቸው የሚያሞግሱት ሕዝብ የሚናገረው ቋንቋ ምርጥ፣ ሲናገሩት ጉሮሮ የማይከረክርና የማይከብድ አድርገው የጻፉት ጽሑፍ አሁን ካሳተሙት መጽሐፍ ጋር ምንም የማይገናኝና አሁን የጻፉት መጽሐፍ ለምን ታስቦ እንደተጻፈ መገመት አያዳግትም፡፡ ግን እንኳንም ጻፉት፡፡

ዞሮ ዞሮ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ የተሰበከው የተሳሳተ የማንነት ቀውስ ዘመን ተሻግሮ ዛሬ ድረስ  ኢትዮጵያን እያተራመሳት ይገኛል፡፡ በተለይ በሰሜን አካባቢ የሚነሱ ተደጋጋሚ የእርስ በርስ ጦርነቶች ምንጫቸው በውጭ ኃይሎች የሚደገፍ የዚህ የማንነት ቀውስ ውጤቶች ናቸው፡፡ ኤርትራ ለመገንጠል እንደ ምክንያት የተጠቀመችበት የማንነት ቀውስ የወለደው ‹ዓረባዊ አፍሪካዊ›› አስተሳሰብ ጭምር ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አገር ጠንካራ ሆና ለመቀጠል በመጀመሪያ ደረጃ ይህ የማንነት ቀውስ ሊስተካከል ይገባል፡፡ ከዚያ በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሲርቅ የአንድ የአዳም ልጆች፣ ሲቀርብ ደግሞ የአንድ ቤተሰብ የኩሽ ልጆች መሆናቸውን በመገንዘብ አንዱ በማንነት ቀውስ ተዘፍቆ ሳይታበይ ወይም ሳይጠብ በጋራ በፍቅር መኖር ይቻላል፡፡

ለዚህ ደግሞ መንግሥት ትክክለኛ የሕዝቦች ታሪክን ለአዲሱ ትውልድ በማስረጽ የኢትዮጵያን አንድነት በጠነከረ መንገድ ማስቀጠል ይቻላል፡፡ ያለፉ የመናናቅ ታሪኮችና የሃይማኖት ስብከቶች ሊስተካከሉ ይገባል፡፡ የታሪክ ትምህርት ክፍሎችን በመዝጋት ሕዝብን ታሪክ አልባ ከማድረግ ይልቅ ትክክለኛ የሕዝብ ታሪኮችን ማስተማር የበለጠ መቀራረብን ያመጣል፡፡ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ሕዝቦች ያላትና ሰፊ ታሪክ ያላት ቢሆንም፣ ይህ ሀቅ ተዛብቶ ሲተረት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ማስተካከል ግን ይቻላል፡፡

በሌለ ማንነት ከመኮፈስ ይልቅ እውነተኛ ማንነትን ተገንዝቦ ኅብረት መፍጠሩ መልካም ነው፡፡ እንደ ሕዝብ ሴም የሚባል ሕዝብ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ባይኖርም የዓረብ የሚመስሉ ‘ኤለመንቶች’ ግን በኢትዮጵያ ምድር ላይ ይታያሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ንጉሣችን አጼ ኃይለ ሥላሴ አሉ እንደሚባሉት እኛ ሴም ነን ማለት እንዳልሆነ ሁሉም ሆዱ ያውቀዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...