Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ በአመራር መስክ መሻሻል ብታሳይ አሁንም ዝቅተኛው እርከን ላይ እንደምትገኝ የሞ ኢብራሒም ሪፖርት አመለከተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየዓመቱ ይፋ የሚደረገውና የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን የሚያወጣው ሪፖርት፣ ባለፉት አሥርት ውስጥ ኢትዮጵያ በገቨርናንስ ወይም በመልካም አመራር መስክ መሻሻል እያሳየች ብትመጣም፣ በጠቅላላው ያስመዘገበችው ውጤት በዝቅተኛው ደረጃ ላይ እንደሚያስቀምጣት አስፍሯል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሁለት ሦስተኛው የአፍሪካ አገሮች የሚታየው የደኅንነትና የሕግ የበላይነት አዝማሚያዎች እያሽቆለቆሉ መጥተዋል ብሏል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት የነበሩትን የአፍሪካ አገሮችን የገቨርንስ ጉዳዮች የዳሰሰው የፋውንዴሽኑ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ከ54 አገሮች ውስጥ 31ኛ ደረጃ ያሰጣትን ውጤት አስመዝግባለች ብሏል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አገሪቱ ያሳየቻቸው መሻሻሎች ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲነጻጸሩ የሰባት ነጥብ ለውጥ ያስገኙ ሲሆን፣ በጠቅላላው ከመቶ ነጥብ 49 አስገኝተውላት ብሏል፡፡

በሪፖርቱ መሠረት የአፍሪካ አገሮች በሕግ የበላይነት እንዲሁም በፀጥታ ወይም ደግሞ በደኅንነት መስክ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ማሽቆልቆል እያሳዩ እንደመጡና በርካቶቹም ከነበሩበትም ይልቅ እጅጉን እንደተንሸራተቱ ማረጋገጡን ሪፖርቱ አትቷል፡፡ በተለይም በግለሰባዊ ደኅንነትና በብሔራዊ ፀጥታ መደቦች ከግማሽ በላይ አገሮች ወደኋላ እየሄዱ እንደመጡ፣ በይበልጥም በተጠያቂነት መመዘኛዎች ሲቃኙም እጅጉን የከፋ ውጤት ማስመዝገባቸውን የሞ ኢብራሒም ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ በርካታዎቹ አገሮች ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ እንዲህ ያለው ማሽቆልቆል ሊታይባቸው መቻሉን አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡ በዚህ መስክ የኢትዮጵያ ደረጃ ከጠቅላላው አገሮች 27ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ አፍሪካውያኑ ከየትኛውም የገቨርናንስ መመዘኛ ጠቋሚ ነጥቦች የባሰውን ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው የታየ ሲሆን፣ ፐብሊክ ማኔጅመንት፣ የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታዎች፣ መሠረተ ልማት እንዲሁም የገጠር አካባቢዎች እንቅስቃሴን በመመዘኛነት የተጠቀመው የኢኮኖሚ መስክ መሥፈርቱ ኢትዮጵያን በ23ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከቀደሙት ጊዜያትም በመጠኑ ማሽቆልቆል ያሳየች መሆኗን አመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 15 አገሮች በዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች መስክ እያሽቆለቆሉ የመጡ አገሮች ተብለው ተደልድለዋል፡፡ ይሁንና ከ54ቱ አገሮች ሁሉ ከፍተኛውን ነጥብ በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆነችው ሞሮኮ ያስመዘገበችው ውጤት 67 ከመቶ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ውጤት 46 ከመቶ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በሞ ኢብራሒም መመዘኛ መሠረት አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ጥሩ መሻሻል አሳይተውበታል የተባለው መመዘኛ የሰብዓዊ ልማት መስክ ሲሆን፣ በትምህርት፣ በጤናና በኑሮ ደኅንነት መመዘኛ ነጥቦች ሲለካ፣ 87 ከመቶ የሚሆነውን የአፍሪካ ሕዝብ የሚወክሉ 43 አገሮች ለውጥ አሳይተዋል ተብለዋል፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ መስክ ለውጥ ማሳየቷ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መስክ አራት አገሮች ከአሥር ነጥብ በላይ መሻሻል ማሳየት የቻሉ ተብለው ተደልድለዋል፡፡ የኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት መስክ የ14 ነጥብ ያህል ለውጥ አሳይታለች ተብሏል፡፡ በዚህ መሠረት አገሪቱ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች መስክ ያስዘመገበቻቸው ለውጦች መንደርደሪያ መደረጋቸው ለለውጡ ምክንያት ሲሆን፣ አገሪቱ በመሠረተ ልማት፣ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ በጤና መስክ ያሳየቻቸው ለውጦች ተዳምረው የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች በአብዛኛው ለማሳካት ከቻሉ አገሮች ተርታ እንድትመደብ ማስቻላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በጠቅላላው ሲታይ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ አገሮች አሳይተዋል ከተባለው ለውጥ ውስጥ ኢትዮጵያ በጠቅላላው የአምስት ነጥብ ውጤት አምጥተዋል ከተባሉ ዘጠኝ አገሮች ተርታ ተመድባለች፡፡

የሞ ኢምብራሒም ፋውንዴሽን እ.ኤ.አ. በ2006 የተቋቋመና በአፍሪካ አገሮች ፖለቲካዊ አስተዳደራዊ ለውጦች ላይ በማመዘን በየዓመቱ ሪፖርት በማውጣት ዘንድሮ አሥረኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሰኞ፣ መስከረም 23 ቀን ይፋ የተደረገው ሪፖርት ምንም እንኳ በአፍሪካ አገሮች ዘንድ በመልካም አስተዳደር መስክ ለውጦች ቢኖሩም፣ እያሽቆለቆሉ መምጣታቸውንና አገሮቹም ያስመዘገቧቸውን ለውጦች ማስጠበቅ ፈተና እንደሆነባቸው አትቷል፡፡ ሱዳናዊው ቢሊየነር ሞ ኢብራሒም የመሠረቱትና በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ፋውንዴሽን፣ ባለፉት ዓመታት የታዩትን ለውጦች በአብዛኛው አወንታዊ ሲል ቢገልጻቸውም፣ ሞ ኢብራሒም በበኩላቸው አገሮቹ ተቀባይነት ያለው፣ ከነቀፌታና ከብልሹነት ራሱን ያሻሻለ አመራር መገንባት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በአፍሪካ ብልኃት የተሞላው አመራር እንዲስፋፋ የጠየቁት ሞ ኢብራሒም፣ እንዲህ ያለውን ፈተና በማለፍ አገሮች ሲያስመዘግቧቸው የቆዩትን ለውጦችን እንዲያስጠብቁ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች