የአሜሪካው ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ከተቀናቃኛቸው ሒላሪ ክሊንተን ጋር በነበራቸው ክርክር፣ ሁለተኛ ተመራጭ ሆነው እንደነበር የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
የሕግ ባለሙያ ለሆኑትና በአሜሪካ የፖለቲካ ታሪክ ሥፍራ ያላቸው ሒላሪ ክሊንተን፣ ቱጃሩን ዶናልድ ትራምፕ በንግግር በልጠውና አጀንዳዎች ልቀው መታየታቸው ብዙም ትኩረት ባይስብም፣ የትራምፕን ታክስ አለመክፈል አስመልክተው የነሱት ነጥብ ግን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ባለሀብቱ ትራምፕ ላለፉት 20 ዓመታት ታክስ አልከፈሉም ብሎ ማሰብ፣ ግብር በመክፈል አቋማቸው ለሚታወቁት አሜሪካውያን አነጋጋሪ ቢሆንባቸውም፣ ጉዳዩ ግን እውነት መሆኑን ኒውዮርክ ታይምስ ይዞት የወጣው ዘገባ ያሳያል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1995 ብቻ የ916 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ገጥሞኛል በማለት ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ የገቢ ግብር ሳይከፍሉ ለሁለት አሥር ዓመታት መቆየታቸውን ያተተው ዘገባው፣ አያይዞም ይህን ያህል የንግድ ኪሳራ ሪፖርት ማቅረብ አንድን ኩባንያ በሕጋዊ መንገድ ለብዙ ዓመታት የገቢ ግብር ሳይከፍል እንዲቆይ ያስችለዋል ብሏል፡፡
ክሊንተን ያነሱትም ትራምፕ ሕጋዊ አስመስሎ የኪሳራ መረጃ በማቅረብ ከ20 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የገቢ ግብር ሳይከፍሉ መቆየታቸውን ነበር፡፡ ዛሬ በምረጡኝ ዘመቻቸው ላይ ጥላ ሳያጠላ በፊት ትራምፕ ተመላሽ የሆነላቸውን የገቢ ግብር እንዲከፍሉ፣ በፖለቲካ ተንታኞችም ሆነ በክሊንተን በራሳቸው ሲነገራቸው የከረመ ቢሆንም፣ ግብሩን ለመክፈል ግን ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ብቅ በማለትና ክሊንተን ለአሜሪካ ባለሥልጣናት ከተቀመጠው መሥፈርት ወጣ በማለት በግል ሰርቨር ኢሜይል መጠቀማቸውን በማንሳት፣ ‹‹ያጠፋቻቸውን 33 ሺሕ ሚስጢራዊ ኢሜሎች ታሳይ፣ እኔም ተመላሽ ታክሴን እከፍላለሁ፤›› በማለት ነበር የሚከራከሩት፡፡ ታክስ ያለመክፈላቸው ጉዳይ ግን ለትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ እንቅፋት መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ ትራምፕን አስመልክቶ ሦስት ገጽ ካለው የግብር ሪፖርት ላይ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ትራምፕ ደርሶብኛል ባሉት የንግድ ኪሳራ ልክ ላለፉት 20 ዓመታት ታክስ ለሚከፍሉባቸው አገልግሎቶች ባለመክፈል ሲያጣጡ ቆይተዋል፡፡
ሲኤንኤን ትራምፕ ስላልከፈሉት ታክስ በራሱ አለማረጋገጡን ቢገልጽም፣ ‹‹እኔ የአሜሪካን የተወሳሰበ የታክስ ሕግ ከማንም ለፕሬዚዳንትነት ከተወዳደረ ግለሰብ በላይ አውቀዋለሁ፡፡ ይህንን ችግር መፍታት የምችለውም እኔው ብቻ ነኝ፤›› ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ማስፈራቸውን ዘግቧል፡፡
የተሳካላቸው አሜሪካዊ ነጋዴና ጠንካራ ሠራተኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ትራምፕ፣ ላለፉት 20 ዓመታት ታክስ አለመክፈላቸውን ተንተርሰው የሚወጡ መረጃዎች፣ ‹‹ሰውየው ውስብስብ የሆኑ የአካውንቲንግ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙና ብዙዎች ደግሞ ይህን ባለመጠቀማቸው መውደቃቸውን ያሳያሉ›› ተብሏል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡ ኤክስፐርቶች በአሜሪካ የግብር ሕግ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የንግድ ኪሳራ አንድን ነጋዴ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የፌዴራል ታክስ እንዳይከፍል ከለላ ይሰጣል፡፡ ሆኖም የትራምፕን አነጋጋሪ ያደረገው፣ ሌሎች ነጋዴዎች ታክስ ላለመክፈል ያጭበረብራሉ ብለው ሲወቅሱና ሲወተውቱ መኖራቸው ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2012፣ ‹‹ከአሜሪካ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ የገቢ ግብር አይከፍልም፤›› ብለው የተናገሩት ትራምፕ፣ አያይዘውም ለሁሉም አሜሪካዊ የታክስ ቅነሳ ይደረግ ብለው ጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹ኮንዘርቫቲቭ ታክስ ፋውንዴሽን›› የታክስ ቅነሳው ሀብታሞች በሚሊዮን እንዲያተርፉ ያደርጋል በሚል አስተያየቱንም ሰንዝሮ ነበር፡፡
ትራምፕ የታክስ ቅነሳ ማድረግን አንድ አጀንዳ አድርገው በቅስቀሳ ወቅት እየተጠቀሙበትም ይገኛሉ፡፡ በአሜሪካ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ረዥም ሰዓት እየሠሩ ታክስም መከፈላቸው ትራምፕን ብቻ ሳይሆን ሴናተር በርኒ ሳንደርስንም ያናገረ ጉዳይ ነበር፡፡ ‹‹ሕዝቡ የትምህርትን፣ የመሠረተ ልማትን፣ የወታደሩን ህልውና ለማስጠበቅ ግብር ይከፍላል፡፡ ቢሊየነሮቹ ግን አያደርጉትም፡፡ ዜሮ የግብር ከፋይ ናቸው፤›› ሲሉም ሳንደርስ ለኤቢሲ ተናግረዋል፡፡
‹‹እኔ ቢሊየነር ነኝ፡፡ የተዋጣልኝ የንግድ ሰውም፡፡ ነገር ግን ታክስ አልከፍልም፡፡ የሚከፍሉት በሰዓት 15 ዶላር የሚያገኙት ናቸው፤›› የሚሉት ትራምፕ፣ ቢመረጡ ለአገሪቱ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጡ ተናግረዋል፡፡
በሰጡት መግለጫም ክህሎቱ ያላቸው ነጋዴ፣ ለንግዳቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ ሠራተኞቻቸው በሕግ ከሚጠየቀው ውጪ ተጨማሪ ታክስ እንዳይከፍሉ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ይናገራሉ፡፡
ትራምፕ የንብረት ባለቤትነት የሽያጭ፣ የኤክሳይስ፣ የሪል ስቴት፣ የሲቲ፣ የፌዴራልና የሠራተኛ ታክሶችን የሚከፍሉ ሲሆን፣ የማይከፍሉት የትርፍ ግብር ነው፡፡
ትራምፕ 916 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ውስጥ ገብቻለሁ ብለው እ.ኤ.አ. በ1995 በማሳወቃቸው ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት የፌዴራል የገቢ ግብር ሳይከፍሉ ከመቆየታቸውም ባለፈ፣ ለምርጫ ሲወዳደሩ የግብር ሪከርዳቸውን ባለማሳወቃቸው ይተቻሉ፡፡ ትራምፕ፣ ‹‹የግብር ሪከርዴን የማሳውቀው ሒላሪ ያጠፋቻቸውን 33 ሺሕ ሚስጥራዊ ኢሜሎች ስታሳውቅ ነው›› ቢሉም፣ በመራጮች ዘንድ ግን ተቀባይነትን አላገኙም፡፡
የታክስ ውዝግቡ የትራምፕን ፕሬዚዳንት የመሆን ዕድል ያጨልማል ወይ? የሚለውን ለመመለስ ወቅቱ ገና ቢሆንም፣ አብዛኛቹ መራጮች ዕጩ ፕሬዚዳንት የግብር ታሪኩን ማሳወቅ እንዳለበት ያምናሉ፡፡
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ባለፈው ወር በሞንማውት ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ የሕዝብ አስተያየት ስለታክስ ማሳወቅ ከተጠየቁት መራጮች 62 በመቶ ያህሉ የግብር ታሪክን ማሳወቅ ወሳኝ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
የታክስ ታሪክን ግልጽ አለማድረግ የተወሳሰበ የፖለቲካ ጉዳይ የሚያስነሳ ቢሆንም፣ ትራምፕ ሒሳባቸው ኦዲት እየተደረገ በመሆኑ በሒደት ላይ እያለ ማሳወቅ እንደማያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በሕግ አማካሪያቸው የተነገራቸውም፣ ‘የሒሳብ ሥራው ያላለቀለትን የግብር ሒሳብ መግለጽ የዋህነት’ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ሆኖም በኦዲት ላይ እያለም የነበራቸውን የታክስ ሪከርድ መግለጽ ምንም የሕግ ተጠያቂነት እንደማያስነሳ ተዘግቧል፡፡
የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ክሊንተን ቢልየነሬውን ሪፐብሊካን ትራምፕ ግብር ካለማሳወቅና ካለመክፈል ጋር አያይዘው ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡ ትራምፕም የፌዴራል ገቢ ግብር ግልጽ ላልሆኑ ጊዜያት አለመክፈላቸውን ተናግረው፣ ይህም የእሳቸውን ብልጥነት እንደሚያሳይና ከፍለው ቢሆን ኖሮ የፌዴራል መንግሥት ያጠፋው እንደነበር በመግለጽ ‹‹ትክክለኛ ውሳኔ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹ትራምፕ ለአሜሪካውያን ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌለው ሰው ነው፤›› ሲሉም ተችተዋል፡፡