እሑድ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ በሆራ አርሰዲ ሊከበር በነበረው የኢሬቻ በዓል፣ በበርካታ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው ሞት ጥልቅ የሆነ ሐዘናችንን እንገልጻለን፡፡ ለሟቾች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም መጽናናትን እንመኛለን፡፡ በወቅቱ በደረሰባቸው አደጋ ጉዳት ያጋጠማቸው ወገኖቻችንም ከጉዳታቸው ያገግሙ ዘንድ ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለዘመናት በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የደረሰው ይህ አደጋ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ሐዘኑ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በንፁኃን ዜጎች ላይ የደረሰ ሞትና የአካል ጉዳት በጭራሽ ሊደገም አይገባውም፡፡
አሁን አገሪቱ በልጆቿ ሞት ምክንያት ታላቅ ሐዘን ላይ ናት፡፡ ይህ ከልብ የማይወጣ ጥልቅ ሐዘን ዳግም በዚህች አገር እንዳይከሰት አገራቸውን የሚወዱ ዜጎች በሙሉ አንድ ላይ መቆም አለባቸው፡፡ ይህንን መሪር ሐዘን በጋራ ከመወጣት በተጨማሪ ለወደፊቱ ምን መደረግ አለበት የሚለው ላይ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ንፁኃን ወገኖቻችን እንደወጡ ቀርተው አገሪቱ ማቅ በለበሰችበት በዚህ ጊዜ፣ እንዲህ ዓይነቱ አሰቃቂ ነገር ዳግም እንዳይከሰት ምን መደረግ አለበት? በአገራችን ኢትዮጵያ ለዓመት ያህል አልበርድ ያለው አለመረጋጋት ምን ዓይነት መፍትሔ ያስፈልገዋል? ለመነጋገርና ለመደማመጥ አሻፈረኝ ያለው የአገሪቱ የፖለቲካ ዓውድ ምን ዓይነት ለውጥ ያስፈልገዋል? በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተፈጠረው ቅራኔ እንዴት ይፈታ? ሥልጡንና ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች እየተገፉ በዚህ ሁኔታ የት ድረስ መጓዝ ይቻላል? ሕዝባችንስ እስከ መቼ በሥጋት ውስጥ ይኖራል? ወዘተ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አንስቶ መፍትሔ መፈለግ የግድ ይሆናል፡፡
ከኅዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ አለመረጋጋቶች የበርካታ ወገኖቻችን ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ አሁን ደግሞ በኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ በርካታ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ መፍትሔ አመንጭቶ ተግባራዊ ለማድረግ ዳገት የሆነበት የአገሪቱ የፖለቲካ ጎራ አሁን ለይቶለት መወነጃጀል ውስጥ ገብቷል፡፡ ከወገኖቻችን አማሟት እስከ ቁጥራቸው ድረስ እየተደረገ ያለው ሙግት ከመባባሱም በላይ፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች ለተጨማሪ ሕይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል፡፡ መንግሥት የጥፋት ኃይሎች የሚላቸው ባቀነባበሩት ሴራ ምክንያት አደጋው መድረሱን ደጋግሞ በመናገር ላይ ሲሆን፣ ተቃውሞውን በማኅበራዊ ሚዲያ በመምራት ላይ ያሉት ደግሞ ኃላፊነቱን ለራሱ አሸክመውታል፡፡ በዚህ መሀል ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦች ጠፍተው አገሪቱ ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለመውጣት ቸግሯታል፡፡ ሐዘኑም ከፍቷል፡፡
አሁን ወቅቱ የመፍትሔ መሆን አለበት፡፡ መፍትሔ ፍለጋ የሚጀመረው የችግሩን ጥልቀት በሚገባ ከማወቅ ነው፡፡ ስለዚህ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱት አደጋዎች እንዲቆሙ ከተፈለገ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ መፍትሔ እንዲያመነጩ ዕድል ይሰጣቸው፡፡ በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርባቸው መድረኮች ተዘጋጅተው ሕዝቡ ምን እንደሚፈልግ በግልጽ ይታወቅ፡፡ መንግሥት ባለበት ኃላፊነት መሠረት የሕዝቡ ጥያቄ በትክክል እንዲደመጥ ያድርግ፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ በጋራ የሚመክሩበትና መግባባት ላይ የሚደርሱበት ሁኔታ ይመቻች፡፡ አገሪቱ በጣም አሥጊ ሁኔታ ውስጥ ገብታ ሕዝቡ ጭንቅ ላይ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ፈጣን የሆኑ ዕርምጃዎች ካልተወሰዱ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ ይህንን አደጋ መቀልበስ የሚቻለው ሁሉንም ወገኖች የሚያስማማ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ተቃውሞው የበለጠ እየተጋጋመ ሲሄድ ከሚገመተው በላይ የሆነ ችግር ይገጥማል፡፡ ለበለጠ ዕልቂትና ውድመት የሚያጋልጥ ችግር ከተከሰተ ደግሞ መልሶ መጠገን አይቻልም፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ የገባችበት ቀውስ አንፃራዊውን ሰላምና መረጋጋት አናግቷል፡፡ ይህ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝና ሁሉን አቀፍ የሆነ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ ይህ መፍትሔ በጋራ መግባባት ላይ መመሥረት አለበት፡፡ የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የጋራ መግባባት ካልተፈጠረ፣ አገሪቷንና ሕዝቡን እያስመረረ ያለው ሞት ይቀጥላል፡፡ ሰላምና መረጋጋቱ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ያመራል፡፡ በብዙ አገሮች እንደታየው ተቃውሞዎችና ግጭቶች ካልቆሙ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ይቀየራሉ፡፡ በሰሜን አፍሪካ ለሊቢያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ለሶሪያና ለየመን ውድመት ምክንያት የሆኑት ችግሮች በጊዜ ባለመፈታታቸው ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ምላሽ ባላገኙ ቁጥር ተቃውሞ እየበረታ ይሄዳል፡፡ ለተቃውሞው የሚሰጠው ምላሽ ኃይል ከሆነ ደግሞ ውጤቱ የከፋ ይሆናል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደገና እያገረሸ ያለው ተቃውሞ መፍትሔ ካልተፈለገለት አድማሱን እያሰፋ የበለጠ አደጋ ይፈጥራል፡፡ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ ወደነበሩበት ለመመለስ ያዳግታል፡፡
ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦችን አሰባስቦ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት መቻል ያስፈልጋል፡፡ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ቃል የገባው መንግሥት በፍጥነት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ የሕዝብ ብሶት ገደቡን ጥሶ ከወጣ በኋላ በኃይል ለማቆም መሞከር የበለጠ አደጋ መፍጠር ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝቡን ጥያቄዎች በአግባቡ የሚመልሱ ተግባራዊ ዕርምጃዎች በፍጥነት ይታዩ፡፡ የተዘጋጋው የፖለቲካ ምኅዳር በፍጥነት ይከፈት፡፡ በሕግ ዋስትና ያገኙ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በተግባር ይረጋገጡ፡፡ ሕዝብን ለምሬት የሚዳርጉ አሠራሮች በአስቸኳይ ይወገዱ፡፡ የዜጎችን ነፃነት የሚጋፉ ድርጊቶች ይቁሙ፡፡ የፍትሕ አካላት ገለልተኝነትና ነፃነት ይከበር፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ መገናኛ ብዙኃን የሁሉም ወገን ድምፅ ይሰማባቸው፡፡ በዚህች አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት የሚረዱ ዜጎች አስተያየቶች በሙሉ ይደመጡ፡፡ ከራስ ጋር ብቻ መነጋገር ቆሞ ሕዝብ የሚፈልገው በግልጽ ይታወቅ፡፡ በፍጥነት መልስ ያግኝ፡፡ ካሁን በኋላ የኃይል ተግባር ተወግዶ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ብቻ ይፈቱ፡፡ ሁሉም ወገኖች ከጥፋት መንገድ ይልቅ ቀናውን ጎዳና በመምረጥ ለተሻለች ኢትዮጵያ ይትጉ፡፡ ይህ ዕድል ካመለጠ አይገኝም፡፡
እስካሁን ድረስ የበርካታ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ የወገኖቻችን ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ሊያንገበግበን ይገባል፡፡ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታም በጣም ሊያሠጋን ይገባል፡፡ የሕዝባችንም ህልውና ጉዳይ እንዲሁ፡፡ መንግሥት በኢሬቻ በዓልም ሆነ ከዚያ በፊት የደረሱ የሕይወት ሕልፈቶችን በተመለከተ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በማቋቋም ለሕዝቡ በግልጽ ማስታወቅ አለበት፡፡ በዜጎቻችን ሕልፈት ሳቢያ የተፈጠረው ቅራኔ ረገብ ብሎ በምክንያታዊነት መነጋገር ካልተቻለ፣ ሰላም ማስፈን አዳጋች ከመሆኑም በላይ የዜጎች ጉዳት ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ የሕዝብ ደመ እየፈሰሰ የፖለቲካ ቁማር መቆመር ለማንም የማይጠቅም በመሆኑ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ መፍትሔ ወዲህ ይበሉ፡፡ ለአገርም የሚበጀው መፍትሔ እንጂ መወቃቀስ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ወገኖቻችንም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው አይጠቅምም፡፡ አገሪቱ ከገባችበት አጣብቂኝ የምትወጣው የጋራ መግባባት የተደረሰበት መፍትሔ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችንን የምንወድ ሁሉ ከጥፋቷ ይልቅ ለሰላሟ መፍትሔ እንፈልግ፡፡ መፍትሔ! መፍትሔ! መፍትሔ! በኢሬቻ በዓል ለሞቱ ወገኖቻችን አሁንም ጥልቅ ሐዘናችንን እንገልጻለን!