Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኢኮኖሚው ያልታደገው ዓይነስውርነት

ዶ/ር ፍጹም በቀለ፣ ከጎንደር ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ዶክትሬት አግኝተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት በዓይን ሕክምና ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሲሆን፣ በለንደን ስኩል ኦፍ ሐይጂን በኮሙዩኒቲ አይ ሔልዝ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በህንድ፣ በአሜሪካና በሌሎችም አገሮች አጫጭር ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡ በሥራ ዓለምም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኘው ጨንቻ ሆስፒታል ተመድበው አገልግለዋል፡፡ በአዲስ አበባና በመቐለ የሚገኙ ፍጹም ብርሃን ስፔሻላይዝድ አይ ሴንተሮች መሥራች፣ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ታደሰ ገብረማርያም በማኅበሩ እንቅስቃሴና በዓይን ሕክምና ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለማኅበሩ አጠር ያለ ማብራሪያ ቢሰጡን?

ዶ/ር ፍጹም፡- የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ወይም የዓይን ሐኪሞች ማኅበር ከተቋቋመ 18 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ወደ 150 የሚጠጉ የዓይን ሐኪሞች አባላት አሉት፡፡ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የዓይን ሐኪሞች አንድ ዓይነት የሙያ ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ልዩ ልዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ለአባላቱ አቅም ግንባታ ሥልጠና ልዩ ትኩረት የተሰጠውም፣ በትምህርት ቤት ደረጃ እኩል ቢሠለጥኑም፣ እኩል ላይሠሩ ስለሚችሉ ነው፡፡ ይህንን ማሻሻል የሚቻለው በየጊዜው ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ነው፡፡ በየዓመቱም አዳዲስ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና በአገር ውስጥ ይሰጣቸዋል፡፡ ለምሳሌ ‹‹በኮርኒያና አያያዙ፣ ወይም ሬቲናና አያያዙ›› በሚሉና ‹‹አዲስ በገባው የጨረር ሕክምናና አዲስ ዓይነት ቀዶ ሕክምና›› የሚሉ ጉዳዮችን እያነሳን፣ እናሠለጥናለን፡፡ እንዲሁም ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ የመጡ ሳይንሶችን እንዲያውቁ ይደረጋል፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡት ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች ቢሆኑም፣ በአብዛኛው ግን ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከህንድና አፍሪካ ውስጥ ደግሞ ከናይጄሪያ የሚመጡ ሙያተኞች ናቸው፡፡ ሙያተኞቹም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው ይመጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡-  በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የዓይን በሽታ ለመከላከል እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ላይ የማኅበሩ ድርሻ ምንድነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የዓይን በሽታ አስመልክቶ ማኅበሩ በጥናት ላይ ይሳተፋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ምን ያህል ዓይነስውርነት አለ? ለዓይነስውርነት መነሻ የሆኑትስ ምን፣ ምን ናቸው? በሚሉት ዙሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ላይም ማኅበሩ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ በዚህም ተሳትፎው ጥናቱ እንዴት መካሄድ እንዳለበት የሚጠቁም ዲዛይን አዘጋጅቷል፡፡ ጥናቱንም ወደ ኅብረተሰቡ ውስጥ ገብተው ያጠኑት የማኅበሩ አባል የሆኑ የዓይን ሐኪሞች ናቸው፡፡ በጥናቱም ላይ ችግሩ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ነው? ግላኮማ ነው? ረቲና ነው? ወዘተ ብለው ዘርዝረውታል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ሰው ዓይነስውር ነው የሚባለው እንዴት ነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው አንድ ሰው ዓይነ ስውር ነው የሚባለው፣ ከሦስት ሜትር በላይ ማየት ከተሳነው ወይም እይታው ከሦስት ሜትር በታች ከሆነ ነው፡፡ ዓይነስውር ማለት ሙሉ ለሙሉ ብርሃኑ የጠፋ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ከ100 ሚሊዮን ሕዝቦች መካከል 1.6 ሚሊዮን ያህሉ ወይም 1.6 በመቶ የሚጠጉ ዓይነስውራን አሉ፣፡ ይህም መጠን በአሁኑ ጊዜ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም የተመዘገበ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዓይነስውርነት ድህነት አስተዋጽኦ አለው?

ዶ/ር ፍጹም፡- በጣም አስተዋጽኦ አለው፡፡ ዓይነስውርነትን ያስከትላሉ ተብለው ከሚታወቁ ችግሮች መካከል ግማሾቹ በተላላፊና በንጽሕና ጉድለት ሳቢያ የሚከሰቱ፣ እኩሎቹ በዕድሜ ምክንያት፣ ከፊሎቹ ደግሞ መታከም ሲገባቸው ሕክምና ባለማግኘታቸው የሚመጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የዓይን ሞራ ግርዶሽን በምንወስድበት ሰዓት ሰው በዓይን ሞራ ግርዶሽ መታወር አልነበረበትም፡፡ በቀዶ ሕክምና የሚድን ነው፡፡ በቂ የሆነ የውኃ አቅርቦት በሌለበትና የትምህርት ደረጃ እጅግ ዝቅተኛ በሆነበት አካባቢ ትራኮማ አገር ያጥለቀልቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ብርሃናቸውን ያጣሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ይህ በሽታ ከድህነት ተያይዞ የሚመጣ ነው፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት ደረጃ መሠረትም ትራኮማ ‹‹የድህነት በሽታ ነው›› በሽታው ሕክምና ስላገኘ አይደለም የሚድነው፣ ንጽሕናው የተጠበቀ ውኃና ትምህርት በማቅረብ፣ ጥሩ ግንዛቤ በመፍጠር ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የማከሙ ፋይዳ እስከምን ድረስ ነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- ትራኮማ የያዘው ሰው ዓይነስውር የሚሆነው ትራኮማው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ ይህም ማለት የዓይን ቆዳው ፀጉር ይታጠፍና የዓይኑን መስታወት ይቦጭረዋል፡፡ በዚህን ወቅት ሕመም ይኖራል፡፡ በቀዶ ሕክምና ፀጉሩ ቀና ከተደረገ ታካሚው ከሕመም ይገላገላል፡፡ ስለሆነም ማከሙ እዚህ ላይ ነው የሚጠቅመው፡፡ በትራኮማ ምክንያት ዓይናቸው ፀጉር የበቀለባቸውን ሰዎች ቀዶ ሕክምና አድርጎ ማዳን፣ ወይም ከትራኮማ ጋር የሚመጣን ዓይነስውርነት በዚህ መልኩ መቅረፍ እንደሚቻል ግንዛቤው ሊወሰድ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ አንፃር ከድህነት ብንላቀቅና ሰዎች ንጽሕናቸውን ቢጠብቁ ኖሮ ዓይናቸው ፀጉር ወደ ማብቀል አይደርስም ነበር ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ፍጹም፡- ትክክል ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን ከፍ ቢል፣ በቂና ንጹሕ የሆነ የውኃ አቅርቦት ሊኖር ይችል ነበር፡፡ ትምህርት ሲስፋፋ ደግሞ ስለፊት አስተጣጠብና በአጠቃላይ ስለግልና አካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ማስተማር ይቻል ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ የተማረ ሰውና ትራንስፖርት ይኖራል፡፡ መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ በዚህም ታክሞ እንደሚዳን ግንዛቤው ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ዓይኑ ሳይታወር ይድን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የትራኮማ በሽታ በአገሪቱ በጣም ተንሠራፍቷል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ፍጹም፡- በአገሪቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የትራኮማ ችግር አለ፡፡ እንደውም የትራኮማ ችግር አለባቸው ተብለው ከተፈረጁት ወይም ከተለዩት የዓለም አገሮች መካከል ዋነኛዋ ኢትዮጽያ ናት፡፡

ሪፖርተር፡- በትራኮማ ዓይናቸው ፀጉር የበቀለባቸው ሰዎች ስንት ናቸው? ይህንን ለመቆጣጠር ምን እየተደረገ ነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ወይም የዓይን ፀጉር ያለባቸው ሰዎች አሉ፡፡ ከዓይን ጋር ተያይዞ ያለውን ሥራ የሚያከናውኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች እንዲሁም ጤና ኬላዎችና ጣቢያዎች የተሳተፉበት አንድ ግብረ ኃይል ካለፈው ሦስት ዓመት ወዲህ ተቋቁሟል፡፡ በትራኮማ ሳቢያ ዓይናቸው ፀጉር ለበቀለባቸው ወገኖች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በዘመቻ እየሰጠ ነው፡፡ ለዚህም የሚረዱ መድኃኒቶች እየቀረቡ ናቸው፡፡ የቀዶ ሕክምናው ያስፈለገው እነዚህ ወገኖች ዓይነስውር ከመሆናቸው በፊት እናድናቸው ወይም እንከላከልላቸው ከሚል ቀና አመለካከት በመነሳት ነው፡፡ አገልግሎቱንም የሚሰጡት ዓይን ውስጥ የገባውን ፀጉር በቀዶ ሕክምና የማቃናት ሥልጠና የወሰዱ ነርሶች ናቸው፡፡ ሕክምናው በዘመቻ ከተጀመረበት አንስቶ እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ 300,000 ወገኖች አገልግሎቱን እንዳገኙና ከዓይነስውርነት እንደተጠበቁ ይገመታል፡፡ አገልግሎቱም የሚካሄደው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግላኮማ የተባለው የዓይን በሽታ እንዴት ይከሰታል?

ዶ/ር ፍጹም፡- ግላኮማ የዓይን ግፊት ይጨምርና የዓይናችንን ስር ይጫነዋል፡፡ ሥሩ ሲጫን ደግሞ ቋሚ የሆነና ከዓይናችን ወደ አንጎላችን የሚወሰደውን ኦፕቲክ ነርቭ ይገድለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሰዎች ዓይነብርሃናቸው ይጠፋል፡፡ ‘ግላኮማ የዓይን ብርሃን ሌባ ነው’ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሰውየው አያመው፣ ምን አይለው፣ እንዲሁ ዓይኑ ይጠፋል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ዓይነስውር ሳይሆኑ የምናገኛቸው በምርመራ ብቻ ነው፡፡ ወይም የዓይን ግፊታቸውን ከለካን ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ብቸኛ መፍትሔ ምንድነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- ስለግላኮማ አደገኛነት ማስተማር ሲሆን፣ ሌላው መፍትሔ ደግሞ ዕድሜው ከ40 ዓመት በላይ የሆነ ማንም ሰው የዓይን ግፊቱን መለካት አለበት፡፡ ቤተሰቡ ግላኮማ ያለበት ከሆነ ደግሞ ልዩ ወይም ተጨማሪ ምርመራ ሊደረግለት ይችላል፡፡ ሰው ዓይኑ ሳይጠፋ መታከም ይገባል፡፡ ለዚህም የሚሆን መድኃኒትና ቀዶ ሕክምና አለ፡፡ ግላኮማ በምርመራ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የስኳር በሽታ ከዚህ ጋር እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ፍጹም፡- ዲያቤቲክስ በዓይን ላይ እያስከተለ ያለው ጠንቅ በእጅጉ ከፍተኛ ነው፡፡ ብዙ የስኳር በሽተኞች ሌላው አካላቸው እንደሚጎዳ ሁሉ፣ ዓይናቸውንም እየተጎዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር አንዳንዶቻችን አመጋገባችንን በሥነ ሥርዓት አናካሂድም፣ ስለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለን ግንዛቤና ዕውቀት በቂ አይደለም፡፡ የዓይን ሐኪም የማማከር ልምዳችን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በየቦታው የመድኃኒት አቅርቦትና ሐኪም ያለመኖር ችግር አለ፡፡ እነዚህ ችግሮች ሁሉ ተደማምረው በስኳር በሽታ ቶሎ የመጠቃት ነገር እየታየ ነው፡፡ በዚህም ብዙ የዓይን ጉዳቶችን እያየን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከዓለም አቀፍ መሰል ተቋማት ጋር ግንኙነት አለው?

ዶ/ር ፍጹም፡- የዓይን ስፔሻላይዝድ ከተኮነ በኋላ ሰብ ስፔሻሊስት የሚባል አለ፡፡ ይኼውም የሬቲና፣ የግላኮማ፣ የኮርኒያ ወዘተ ሰብ ስፔሻሊስት ማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሰብ ስፔሻሊስት ሥልጠና በአገር ውስጥ የለም፡፡ አባሎቻችን ሰብ ስፔሻሊስት ሥልጠና የወሰዱት ውጭ አገር ነው፡፡ ይህንንም የሥልጠና ዕድል የሚሰጠው መንግሥት ሳይሆን ኢንተርናሽናል ድርጅቶቹ ናቸው፡፡ ከሆስፒታሎች ወይም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት ፈጥረን አባላት ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት እየሄዱ ጥልቅ ትምህርት ያደርጋሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከዓይን ባንክ ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ፍጹም፡- የዓይን ባንክ የራሱ አካሄድ አለው፡፡ ነገር ግን ማኅበራችን የኮርኒያ ወይም የዓይን መስታወት ነቅለው የሚገጥሙ ስፔሻሊስቶች አሉት፡፡ እነዚህ ስፔሻሊስቶች ከዓይን ባንክ ጋር እየሠሩ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...