Tuesday, April 16, 2024

በኢሬቻ ክብረ በዓል ለደረሰው የንፁኃን ዜጎች ሕልፈት ተጠያቂው ማነው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የምሥራቅ ኦሮሚያዋ ከተማ ቢሾፍቱ ቅዳሜ ምሽት ላይ አሸብርቃ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበትን የኢሬቻ ክብረ በዓል ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች፡፡

ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የመጡ በኦሮሞ ባህላዊ ልብሶች ያጌጡ ወጣቶች እየተዘዋወሩ ብሔሩን የሚያሞግሱ ዜማዎችን ሲያሰሙ ነበር፡፡

በከተማዋ አመሻሹ ላይ የደረሰ እንግዳ በጭራሽ መኝታ አልጋ ሊያገኝ አይችልም ነበር፡፡

ማምሻውን ሁሉም መዝናኛ ቤቶች በደስታና በጭፈራ ተሞልተዋል፡፡ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው የምሽት መዝናኛ ቤቶች ዓመታዊውን የኢሬቻ በዓል ለማክበር ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች ብሔሩን የሚያወድሱ ዘፈኖች፣ እንዲሁም ስለደረሱ ጭቆናዎች የተዜሙ ዜማዎች በሚከፈቱበት ወቅት ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው በኅብረት ያዜሙ ነበር፡፡

ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ሌሊቱን ሙሉ ሲደሰቱ ያሳለፉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለእሑድ አጥቢያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ካረፉባቸው ሆቴሎችና ሌሎች ማረፊያ ቤቶች ወጥተው በቡድን በቡድን እየዘመሩ ክብረ በዓሉ ወደሚከናወንበት ሆራ አርሰዲ ሲተሙ ተስተውሏል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል በሁሉም የበዓሉ ታዳሚ ወጣቶች ላይ ፍተሻ እያደረገ ነበር ወደ ክብረ በዓሉ እንዲገቡ የሚፈቅደው፡፡ በዋዜማው ምሽት መዝናኛ ቤቶች ከነበሩ ጭፈራዎች አዝማሚያ በመነሳት በበዓሉ ላይ ተቃውሞ ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

ለእሑድ አጥቢያ ከንጋቱ 11 ሰዓት በኋላ እጃቸውን በማጣመር የኦሮሞ ሕዝብ የተቃውሞ ምልክት የሆነውን “X” የሚያሳዩ ወጣቶችን አልፎ አልፎ ለመመልከት ተችሏል፡፡

ባህላዊውን የምሥጋና ሥነ ሥርዓት የሆራ ሐይቅን በመባረክና ቄጤማ ወደ ሐይቁ በመንከር የብሔሩ ባህላዊ አመራሮች አባ ገዳዎች ቢያስጀምሩም፣ ጥቂት በዕድሜ ገፋ ካሉት በስተቀር የተከተላቸው አልነበረም፡፡

በአካባቢው የተገኙት ወጣቶች እጃቸውን በማጣመር ተቃውሟቸውን ክልሉን በሚያስተዳድረው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ላይ ሲያሰሙ ነበር፡፡ እንዲሁም ʻወያኔ በቃን፣ ነፃነት እንፈልጋለን፣ የኦሮሞ ሕዝብ የተከበረ ነው፣ ራሱን ማስተዳደር አለበት…ʼ የሚሉ መፈክሮችን በተደጋጋሚ ያሰሙ ነበር፡፡

እጅግ በጣም በርካታ የሚባሉት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ጐን ለጐን በሞባይል ስልኮች ተቃውሟቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች ቡድኖች የሚያደርጉትን ተቃውሞ ሲቀርፁ ተስተውሏል፡፡

በዚሁ በሐይቁ አካባቢ ተቃውሞው ድምቅ ብሎ መቀጠሉ ያሳሰባቸው የልዩ ኃይሉ ፀጥታ አስከባሪዎች ሐይቁን ወደከበቡት ተራራማ ቦታዎች ላይ በመቅረብ መታየታቸው የበለጠ ተቃውሞው እንዲጋጋል አድርጐታል፡፡

አባ ገዳዎች በሐይቁ ዳርቻ ባህላዊ ሥርዓቶችን አከናውነው ወደተዘጋጀላቸው መድረክ ሲመለሱ በዚሁ አካባቢ የልዩ ኃይሉ ፖሊሶች በረድፍ በመቆም ባበጁት የተከለለ ቦታ ላይ፣ ታዳሚዎች በተመሳሳይ ግለት ከንጋቱ 12 ሰዓት የጀመረውን ተቃውሞ በዚህ ሥፍራም ቀጥለውበታል፡፡

‹‹ወያኔ አይበጀንም››፣ ‹‹ኦፒዲዮ በቃን››፣ ‹‹ኦሮሞን የሚያስተዳድረው ኦሮሞ ብቻ ነው…›› የሚሉ መፈክሮችን በኦሮሚኛ ያሰሙ ነበር፡፡

አልፎ አልፎ በአማርኛ ‹‹ወያኔ ሌባ›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በኦሮሚኛ ቋንቋ ‹‹ዲʼኔ – ዲኔ ዲኔ››፣ “ኑገʼኤራ”፣ ‹‹ቢሊሱማ›› የሚሉ መፈክሮችን ያሰሙ ነበር፡፡ የእነዚህ መፈክሮች ትርጓሜም ‹‹እምቢ››፣ ‹‹በቅቶናል›› እና ‹‹ነፃነት እንፈልጋለን›› የሚሉ ናቸው፡፡

አንዳንድ ቡድኖች ወጣት ሴቶችን እንኮኮ አድርገው ሴቶቹ ወጣቶች አባ ገዳዎቹ እንደማይወክሏቸው የሚያሰሙትን መፈክር ይደግሙ ነበር፡፡ በመድረኩ ላይ ከተሰበሰቡት አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች መካከል የቀድሞ አባ ገዳ አሁን ደግሞ ‹‹ዮባ›› ተብለው የሚጠሩትን በዕድሜ ከሁሉም ገፋ ያሉትን ዮባ ስለሺ ዳባ ቱሉ እየሆነ ስላለው ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡

ዮባ ስለሺ ዳባ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት የጀመሩት ስለኢሬቻ በዓል ታሪካዊ ትርጓሜና ፋይዳ በማብራራት ቢሆንም፣ ‹‹ዛሬ እየሆነ ያለው ከየት መጣ? መልዕክቱ ምንድነው? የሚለውን መንግሥት መመርመር አለበት፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢሬቻ ማለት የተጣላው የሚታረቅበት፣ ለተጋደለው ጉማ (ካሣ) ተከፍሎ ለዕርቅ ‹‹መልካ›› የሚወጣበት ቀን መሆኑን የገለጹት አቶ ስለሺ፣ ‹‹መልካ ማለት የፍቅር፣ የመታረቂያ፣ የወደፊት ሰላማችንን መለመኛ ቀን ነው፡፡ ምክንያቱም ታንክና መድፍ፣ ጄት አይደለም ያለን፡፡ ስለዚህ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ሰጥተኸናልና እሷኑ ያዝልን፣ ድንበሯን ጠብቅልን ብለን የምንለምንበት ቀን ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት የአገር ሽማግሌዎችንና የእምነት አባቶችን አሰባስቦ ምንድን ነው ይኼ መልዕክት ብሎ መፍትሔ መስጠት እንዳለበት ያሳሰቡት ዮባ ስለሺ፣ ‹‹መፍትሔ ቶሎ ካልተሰጠው ሌላ መልክ የሚያመጣ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ጠጋ ብሎ ተነጋግሮ መፍትሔ መምጣት አለበት፤›› ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ሪፖርተር ዮባ ስለሺ ዳባን እያነጋገረ በነበረበት ወቅት የታዳሚዎቹ ተቃውሞም ያለማቋረጥ ተጋግሎ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ እየተከናወነ መሆኑን እንጂ ስለሚፈጠረው መገመት ያልቻሉት አዛውንቱ አቶ ስለሺ፣ ‹‹በዚህ በዓል እንደዚህ ዓይነት ነገር ታይቶ አያውቅም፡፡ ቢሆንም ግን ከመታፈን ይሻላል፡፡ ከታፈነ መርዝ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ግን ወጥቷል፡፡ ከወጣ ደግሞ ቶሎ ብሎ መፍትሔ መፈለግ ግድ ይላል፡፡ እኛም አንተኛም፤›› ብለዋል፡፡

ተቃውሞው አሁንም ቀጥሏል፡፡ አንዳንድ የቡድን መሪዎች በልዩ ኃይሉ ከታጠረው ክልል ውስጥ ፖሊሶቹን እያስፈቀዱ ለውጭ የሚዲያ ተቋማት ስለተቃውሟቸው ለመግለጽ ወደ መድረኩ እየተጠጉ ይመለሳሉ፡፡

ከየት አካባቢ እንደመጡ የሚገልጽ ‹‹ባነር›› የያዙ ሁለት ወጣቶች ወደ መድረኩ ወጥተው ሲመለሱም የልዩ ኃይሉ ፖሊሶች በትህትና በኦሮሚኛ በማነጋገር እንዳይደግሙት ከማሳሰብ ውጪ፣ ነገሮችን በጣም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲመሩ ነበር፡፡

በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ባህላዊው የኢሬቻ ሥነ ሥርዓት መከበር አልተጀመረም፡፡ አባ ገዳዎቹ ለምን ሥርዓቱን ለማስጀመር እንደማይሞክሩ ሪፖርተር አንድ የአካባቢውን ተወላጅ ሲጠይቅ ዋናው አባ ገዳ ሰንበቶ የተባሉት አልተገኙም የሚል ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡

በነገሮች መራዘም እንዲሁም የሚጠበቁ አባ ገዳዎች ወይም ባለሥልጣናት መገኘት አለመቻል የተሰላቹት በመድረኩ የተገኙት አባ ገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች መድረኩን ጥለው ለመውረድ ሲሞክሩ የበዓሉ አስተባባሪዎች እንዲቀመጡ አድርገዋቸዋል፡፡

በዚህ ወቅት የበለጠ ተቃውሞው ተቀጣጥሏል፡፡ አባ ገዳዎቹ በበዓሉ ሥነ ሥርዓት መሠረት ምርቃት እንዲካሄድ እንዲጠይቁ በሥነ ሥርዓቱ አስተባባሪዎች በተመከሩት መሠረት፣ ድምፅ ማጉያ ይዘው ድምፅ ማሰማት ቢጀምሩም የሚያዳምጣቸው ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

በልመና እንዲያዳምጧቸው ቢጠየቁም ማንም ሊሰማቸው አልቻለም፡፡ አንድ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ማይክራፎን ተቀብሎ ታዳሚዎች እንዲረጋጉ ቢጠይቅም የሚሰማው አልተገኘም፡፡ ከታዳሚዎች መካከል ቀስ ብሎ መድረኩን የተቀላቀለ አንድ ወጣት ማይክራፎኑን ከሌላው ወጣት አስተናባሪ ሲቀበል ተመሳሳይ የማረጋጋት ሥራ ለመሥራት እንጂ ቀጥሎ ያደረገውን የገመተ ያለ አይመስልም፡፡

‹‹Down Down Weyane›› (ውድቀት ለወያኔ) ‹‹Down Down TPLF›› (ውድቀት ለሕወሓት) የሚል መፈክሮችን በማይክራፎን ማሰማት ሲጀምር፣ ሁሉም ታዳሚዎች በአንድነት ተቀብለው ያስተጋቡ ጀመር፡፡ ይህ ክስተት ሁሉንም አንድ አድርጐ የበለጠ ተቃውሞው ተቀጣጠለ፡፡

ከወጣቱ ላይ ማይክራፎኑን ለመንጠቅ አስተናባሪዎችና ፖሊሶች ተረባረቡ፡፡ አንዳንድ ወጣቶች ይህንን ድርጊት የውኃ ላስቲክ በመወርወር ለመቃወም ሲሞክሩ ሌሎቹ የሚወረውሩትን ሲገስጹ ተስተውሏል፡፡

ነገሮች አስቸጋሪ ሆነው እየተለወጡ መምጣታቸውን ያስተዋለው የልዩ ኃይሉ ኮማንደር፣ ‹‹ባለቤት አብጁለት ባለቤቱ ማነው?›› በማለት ከሌላ ሲቪል ከለበሰ ባልደረባው ጋር በአማርኛ ሲነጋገር ተሰምቷል፡፡

አባ ገዳዎቹና ሽማግሌዎቹ እንዲሁም የእምነት አባቶቹ መድረኩን ለቀው ወጡ፡፡ ከዚህ በኋላ በርከት ያሉ ወጣቶች መድረኩን ተቆጣጠሩ፡፡ ይሁን እንጂ የልዩ ኃይሉ ፖሊሶች በሰላማዊ መንገድ አስወርደዋቸዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሌላ በርከት ያሉ ወጣቶችን የያዘ ቡድን ከስብስቡ ጀርባ በመነሳት አባላትን እያበዛ ሰላማዊ የሆነውን የተቃውሞ መፈክር እያሰማ ዳግም ወደ መድረኩ አመራ፡፡ ይህ ቡድን እጅግ ብዙ ቁጥር ያለው ነው፡፡

ከዚህ በኋላ ነገሮች በዚህ መልኩ እንዲቀጥሉ ባልፈቀዱት የልዩ ኃይሉ ኃላፊዎች ትዕዛዝ መሠረት ፖሊሶቹ አስለቃሽ ጭስ መፈናፈኛ ወዳልነበረበት የሕዝብ ስብስብ ተኮሱ፡፡

በበርካታ መቶ ሺዎች የሚቆጠረውን ታዳሚ የያዘው የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል ማክበሪያ ቦታ በሁለት አቅጣጫዎች ጥልቅ ተፈጥሯዊ ገደሎች እንዳሉት ቢታወቅም በአጥር አልተከለሉም፡፡

በተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ድምፅ ተደናግጦ ራሱን ለማዳን የተነቃነቀው ታዳሚ የፈጠረው ግፊት በገደሎቹ ጠርዝ አቅራቢያ ለነበሩት የበዓሉ ታዳሚዎች አሳዛኝ አጋጣሚን ፈጠረ፡፡ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩት ድንጋያማ ከሆኑት የገደሎቹ ግድግዳዎች እየተጋጩ ቁልቁል ወረዱ፡፡   

እርስ በርስ በመደራረባቸውና በመተፋፈጋቸው መተንፈሻ ያጡት በሕይወት መውጣት አልቻሉም፡፡

ከላይ ያሉት ራሳቸውን ለማዳን ሲሞክሩ ጥቂት ተረጋግተው በአካባቢው የቀሩ ወጣቶችንና የልዩ ኃይሉን እጆች ዕርዳታ አግኝተው ለመትረፍ ችለዋል፡፡

ዕርዳታ ለመስጠት የነበሩት ጥቂት የቀይ መስቀል አምቡላንሶች ቅድሚያ በሕይወት ያሉትን እያስቀደሙ ወደ ሕክምና መስጫ ጣቢያዎች ተራወጡ፡፡ በርካታ አስከሬኖች ከጉድጓዶቹ ወጥተው ሜዳ ላይ ተዘርረዋል፡፡

በተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ተደናግጠው የሮጡት አብዛኛዎቹ ታዳሚዎች ወደ ሥፍራው ዳግም አልተመለሱም፡፡ ይልቁንም ራሳቸውን አረጋግተው ተቃውሞአቸውን ዳግም እያሰሙ ወደ ከተማው መዝለቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተለምዶ ‹‹ሠርክል›› ተብሎ በሚጠራው የቢሾፍቱ ዋና አደባባይ አካባቢ የልዩ ኃይሉ ፖሊሶች በድጋሚ በአስለቃሽ ጭስ እንደበተኗቸው የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ወደዚህ አደባባይ ሪፖርተር በደረሰበት ወቅት የፌዴራል ፖሊስ አድማ በታኝ ፖሊስ አባላት በክፍት መኪና ተጭነው ቅኝት ሲያደርጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ታዝቧል፡፡      

ከተማው ውስጥ የነበረው አብዛኛው ሕዝብ በኢሬቻ ክብረ በዓል ቦታ ስለተፈጠረው አደጋ አያውቁም ነበር፡፡ በየምግብ ቤቱ ደስታና ጭፈራ ይታያል፡፡

ሪፖርተር ቢሾፍቱ ሆስፒታል በደረሰበት ወቅት የሚታየው ነገር ዘግናኝ ነበር፡፡ በሁለት የዩኒሴፍ ድንኳኖች ቤተሰቦቻቸው እንዲለዩዋቸው የተንጋለሉ ከፈን ያልለበሱ በርካታ አስከሬኖች ይታያሉ፡፡ ሪፖርተር ባደረገው አጭር ቅኝት በርካታ አስከሬኖችን ለማየት ችሏል፡፡ አስከሬኖቹ ምንም ዓይነት ጉዳት አይታይባቸውም፡፡ አንድ ወጣት ላይ ብቻ ከአፉ ጐን የደረቀ ደም ይታያል፡፡

ሕይወታቸውን ያጡት ተሳታፊዎች ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በመሆናቸው ጓደኛው የቀረበት ወይም የተጠፋፋ ወደዚህ ሆስፒታል ይመጣል፡፡ እየመጡ ያዩትን ለማመን ከብዷቸው እንዲሁም አቅም ከድቷቸው መሬት ይቀመጣሉ፡፡ አንዳንዶች የተረጋጉት አስከሬኖችን ሲገንዙና ትራንስፖርት ሲኮናተሩ ታይቷል፡፡   

ከቢሾፍቱ ሆስፒታል ውጪ ወደተለያዩ የሕክምና ተቋማት ያመሩ መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በበኩሉ 110 ተጐጂዎችን ማመላለሱን አስታውቋል፡፡

በተፈጠረው አሳዛኝ አጋጣሚ በእጅጉ ማዘኑን የገለጸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሟቾች ቁጥር 55 መሆኑንና ከ100 በላይ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሕክምና ማግኘታቸውን ገልጿል፡፡

ለዕልቂቱ ተጠያቂው ማነው?

አሳዛኝ የዜጐች ሕልፈት በተከሰተበት መስከረም 22 ቀን 2009 ምሽት ላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግሥት ቴሌቪዥን በኩል መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተቃውሞውን ያነሳሱ ባሏቸው ጥቂት ኃይሎች ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል፡፡ በክልሉ መንግሥት በኩልም ሆነ በፌዴራል መንግሥት በኩል ከፍተኛ የፀጥታ ዝግጅት ስለመደረጉ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የፀጥታ ኃይሉ አንዲትም ጥይት አለመተኮሱንና በተሰጠው መመርያ መሠረት ዝግጅት አድርጐ የክብረ በዓሉ ሒደት ሰላማዊ እንዲሆን በማድረጉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ የተከሰተው የሰዎች ሕልፈትም በመረጋገጥና በመተፋፈግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተቃውሞውን በመበተን የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ውጤታቸው ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በወቅቱ የፀጥታ ኃይሉን የሚመሩት ኃላፊዎች ያጤኑት አይመስልም፡፡

በፖሊሶች የተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ቢሆንም ከፍተኛ ፍንዳታ የሚያሰማና በመጀመሪያም ከጭሱ ይልቅ ድንጋጤን የሚፈጥረው ድምፁ መሆኑን በዚህ የተነሳ ምን ይከሰታል የሚለውን በአግባቡ ኃላፊዎቹ የተረዱት አይመስልም፡፡ በዚህ ቅጽበት ውስጥ ለማድረግ የሞከሩትም ስህተታቸውን ተረድተውት የሚመስል ነበር፡፡

በተሽከርካሪዎቻቸው በፍጥነት በመንዳት ‹‹ተረጋጉ በዓላችን ነው ተረጋጉ›› እያሉ ለማረጋጋት ሞክረዋል፡፡ ይህ ሙከራቸው ግን የንፁኃንን ሕልፈት ወደኋላ ተመልሶ ሊታደግ አልቻለም፡፡    

 

     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -