– አዲስ የመልሶ መቋቋሚያ ዕቅድ አቅርበዋል
በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደሮች ያቋቋሙት ኮሚቴ መንግሥት እንዲያነጋግረው ጠየቀ፡፡
የተፈናቀሉት አርሶ አደሮች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፉ ረጋሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን ዳግም ለማቋቋም ዕቅድ ቢያወጣም፣ ወደ ተግባር መሸጋገር ባለመቻሉ አርሶ አደሮች ለከፋ ችግር እየተዳረጉ ነው፡፡
ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን ዳግም ለማቋቋም ኃላፊነት የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ነው፡፡ ቢሮው ይህንን ሥራ ለመሥራት ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁሟል፡፡
አቶ ተስፉ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ወደ ተግባር ከመሸጋገር ይልቅ የሕግ ማዕቀፎች በማውጣት፣ ለአርሶ አደሮች ሥልጠና ለመስጠት ካሪኩለም በመቅረጽና በመሳሰሉ ቢሮክራሲ አራዛሚ ሥራዎች ላይ ተጠምዷል፡፡
‹‹አርሶ አደሩ የሚፈልገው ገንዘብና መሬት ነው፡፡ አርሶ አደሩ አሁን ሥልጠና አያስፈልገውም፡፡ እስካሁን የኖረውም በራሱ ዕውቀት ነው፡፡ የቢሮክራሲ ሰንሰለት እየፈጠሩ ገንዘብ ማባከን አይገባም፤›› በማለት አቶ ተስፉ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የአርሶ አደሮቹ ኮሚቴ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም ይበጃል ያለውን ሐሳብ አጥንቶ አቅርቧል፡፡ በቀረበው ጥናት ተፈናቃይ አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራቸውን የሚተካ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ አርሶ አደሮች ወደ ንግድ ዓለም ተደራጅተውም እንዲገቡ ወይም በግል እንዲሠሩ ሕንፃ የሚገነቡበት ቦታ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
‹‹በልማት ምክንያት የተነሱ አርሶ አደሮች የሚገነቡትን ሕንፃ ሊነግዱበት፣ ወይም አከራይተው ሊሠሩበት ይችላሉ፤›› ይላል የቀረበው የአርሶ አደሮች ጥናት፡፡
ጥናቱ በመቀጠልም በበሽታና በእርጅና ምክንያት መሥራት ለማይችሉ ከተወሰደው መሬት ላይ ከሚሰበሰብ ግብር ላይ 20 በመቶ ያህሉ እየተጠራቀመ፣ የጡረታና ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ገቢ ተደርጎ በኤጀንሲው በኩል እንዲከፈላቸው ይጠይቃል፡፡
ተደራጅተው የሕንፃ ባለቤት ሆነው መሥራት ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች ከራስ አሥር በመቶ ከመንግሥት 90 በመቶ ገንዘብ በብድር እንዲቀርብ በማድረግ በአገልግሎት መስጫ፣ በምርት መሸጫ፣ በወተት፣ በሥጋ ውጤቶች፣ በዘመናዊ የሥጋ ዶሮና እንቁላል ዕርባታ፣ በጅምላ ንግድ፣ በንግድ ድርጅትና በመኖሪያ ቤት ኪራይ አገልግሎትና በመሳሰሉት ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችሉ ዕቅዶችን አውጥቷል፡፡
ከአሥር ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ 27 ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት ነበሩ፡፡ በዚህ ወቅት አርሶ አደሩ ራሱን በራሱ ያስተዳድር ነበር፡፡ በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የሥልጣን ዘመን ይህ የገበሬ ቀበሌ ማኅበር መዋቅር ፈርሶ በከተማ አስተዳደር ሥር እንዲተዳደር መደረጉን አቶ ተስፉ ያስታውሳሉ፡፡
በከተማው መጠነ ሰፊ የልማት ሥራዎች በሚካሄዱበት ወቅትም አርሶ አደሩ ያለ በቂ ምትክ ቦታና ካሳ ሲፈናቀል መቆየቱ ይታወቃል፡፡
‹‹በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለተነሳው ችግር የመልካም አስተዳደር ዕጦት ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ አርሶ አደሮች ላይም የመልካም አስተዳደር ዕጦት ተንሰራፍቷል፡፡ መንግሥት ቢሮክራሲውን ከማርዘም ይልቅ መፍትሔ ላይ ቢሠራ መልካም ነው፤›› በማለት አቶ ተስፉ ተናግረዋል፡፡