– የሟቾች ቁጥር ከ600 በላይ ነው አሉ
– ኦፌኮ የደረሰውን ዕልቂት የሚያጣራ ኮሚሽን እንዲቋቋም ጠየቀ
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ገዥ ፓርቲ [ኦሕዴድ] ሥልጣን እንዲለቅ ጠየቁ፡፡
የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር (ኦአነግ)፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር (ኦነአግ)፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ብሔር ፓርቲ (ኦነብፓ) ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ ባለፈው እሑድ የኢሬቻ በዓል ለማክበር የተሰበሰበው ሕዝብ በሰላም ተቃውሞ እያሰማ እያለ በተፈጠረ ግጭት ከ600 በላይ ሰዎች ሕይወት አልፏል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ በተገቢ መንገድ ለመምራት የሞራልም ሆነ የፖለቲካ ብቃት ያጣ በመሆኑ ሥልጣን እንዲለቅ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
‹‹የክልሉ መንግሥት በየዕለቱ ሕዝቡን ከመግደልና ከማስገደል ተቆጥቦ እስከ ዛሬ ድረስ ራሱ በሰጠው ከለላ እየተገደለ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ቢያንስ የገዳዩን ማንነት እንዲረዳ ሥልጣኑን በአስቸኳይ ይልቀቅ፤›› ሲል የአራቱ ፓርቲዎች መግለጫ ይጠይቃል፡፡
ፓርቲዎቹ ባወጡት መግለጫ ከ19ነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጠናቀቂያ ጀምሮ እስከ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዘለቀው የኦሮሞ ሕዝብ ጭቆና፣ ግፍና ግድያ እጅግ ዘግናኝ ቢሆንም፣ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ በሆራ አርሶዲ የኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት በወገኖች ላይ የደረሰው ዕልቂት ወደርና ተምሳሌት የለውም ብለዋል፡፡
‹‹የእልቂቶች ሁሉ ክብረ ወሰን ነው፤›› በማለት ድርጊቱን ገልጸውታል፡፡ መንግሥት ለዕልቂቱ ተጠያቂ ያደረገው እንደተለመደው በተገቢው መንገድ እንዳይከናወን የፈለጉ ጥቂት ፀረ ሰላም ኃይሎች ድርጊት በማለት አልፎታል ያሉት አራቱ ፓርቲዎች፣ ይህንን የመንግሥት መግለጫ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡
‹‹መንግሥት የተጠያቂነት አቅጣጫ ለመቀየር የሚያደርገውን ጥረት አንቀበለውም፤›› በማለት ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት፣ መንግሥት በሰላማዊ ሕዝብ መካከል ያሰፈረውን የጦር ሠራዊት በአስቸኳይ ከክልሉ እንዲያስወጣ፣ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተገቢውን ሰላማዊ ውይይት በማድረግ፣ ለዕልቂቱ ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ ለጉዳቱ ሰለባ ቤተሰቦች በቂ ካሳ እንዲከፈል ጠይቀዋል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በተመሳሳይ፣ ‹‹ሐዘናችን ጥልቅ ቢሆንም በወገኖቻችን መስዋዕትነት ትግላችን ግቡን ይመታል›› በሚል ርዕስ ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. መግለጫ አውጥቷል፡፡
ኦፌኮ በመግለጫው፣ ‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ሕወሓት/ኢሕአዴግ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት የሚያህል ዘመቻ ከፍቷል፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የኦሮሞን ሕዝብ በማሰር በማሳደድ በማዋከብ በመግደል የክልሉን ሀብት ሲዘርፍና ሲያዘርፍ ቆይቷል፤›› ብሏል፡፡
‹‹ኦፌኮ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ያገኝ ዘንድ ለኢሕአዴግ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ሰሚ አላገኘም፡፡ የሕዝብ ትግል ግን እየፋመና እየጋመ እንዳይሄድ የከለከለው አንዳች ነገር የለም፤›› በማለት ኦፌኮ ገልጿል፡፡
ሕዝባዊ ትግሉ እየተፋፋመ ባለበት ወቅት ሕዝቡ ያለበትን ምሬት በአዕምሮ ይዞ ፈጣሪውን ሲማፀን ከሌሎች ብሔር ብሔረሰብ ወገኖች ጋር የኢሬቻን ዓመታዊ ክብረ በዓል ለማክበር ቢሾፍቱ ተገኝቶ እንደነበር ያስታወሰው ኦፌኮ፣ ሕዝብን የጠበቀው ግን የመዝሙር፣ የፀሎት የሰላም አከባበር አልነበረም በማለት ክስተቱን ይገልጻል፡፡
‹‹በዚህ ዕልቂት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ ጉዳዩ የቁጥር መብዛትና ማነስ አይደለም፡፡ ዓመታዊ በዓሉን ለማክበር በወጣው ሕዝብ ላይ ለምን ተቃወምክ በሚል ሰበብ ፈጥሮ የበቀል ዕርምጃ ተወስዶ ታሪክ የማይረሳው ዕልቂት ተፈጽሟል፤›› ሲል ኦፌኮ አስታውቋል፡፡
ኦፌኮ መግለጫውን ሲያጠቃልል ለከዚህ ቀደሙም ሆነ አሁን ላለቁት ዜጎች ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ጠይቋል፡፡