Friday, May 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከቀብር መልስ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ስድስት ከባድ ተሽከርካሪዎች ተቃጠሉ

ከቀብር መልስ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ስድስት ከባድ ተሽከርካሪዎች ተቃጠሉ

ቀን:

– የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምንም የፀጥታ ሥጋት የለም አለ

በኢሬቻ ክብረ በዓል ወቅት ሕይወታቸው ያለፈ የሁለት ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት በዓለም ገና አካባቢ ከተፈጸመ በኋላ በተነሳ ተቃውሞ፣ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ቢራ ለመጫን የሄዱ አምስት የወኪል አከፋፋይ ተሽከርካሪዎችና ንብረትነቱ የሚድሮክ ደርባ የሆነ ከባድ ተሽከርካሪ በእሳት ተቃጠሉ፡፡

ተቃውሞውን ተከትሎ በተለይ ጀሞ ቁጥር ሁለት ከሚባለው ሥፍራ ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወደ ሰበታ የሚወስደው መንገድ የሕዝብ ትራንስፖርት ቆሞ እንደነበር፣ ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ ለማስተዋል ችሏል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶችና የንግድ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው ውለዋል፡፡

- Advertisement -

ከፉሪ-ጀሞ ዓለም ገና ያለው መንገድ በፀጥታ ኃይሎች ከመወጠሩም በላይ፣ ንብረትነቱ የሚድሮክ ደርባ የሆነ ባለተሳቢ ተሽከርካሪ ዓለም ገና ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በእሳት ሲቃጠል ታይቷል፡፡ ሪፖርተር በሥፍራው በደረሰበት ወቅት ተሽከርካሪው በመቃጠል ላይ ነበር፡፡ የአድማ በታኝ የደንብ ልብስ የለበሱ ሁለት ፖሊሶች አጠገቡ ይታዩ ነበር፡፡

በፉሪ፣ ኬንተሪና ዓለም ገና አካባቢ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ከሁለቱም አቅጣጫ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቢሆንም፣ በዕለቱ የነበረው እንቅስቃሴ ከወትሮው በተለየ አነስተኛ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ ተሽከርካሪዎች በሁለቱም አቅጣጫ ሲንቀሳቀሱ የተስተዋሉ ሲሆን፣ አድማ በታኝ ፖሊሶች ከኬንተሪ እስከ ሰበታ የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ድረስ በስፋት ታይተዋል፡፡

ከዓለም ገና እስከ ሰበታ በሚደርሰው በጎዳና ላይ መንገዶች ቀደም ብለው በድንጋይ ተዘግተው እንደነበርና በኋላም የፀጥታ ኃይሎች መንገዱን ማስከፈታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ነገር ግን ተቃውሞው እስከ ምሽት የዘለቀ ነበር ተብሏል፡፡

ከሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ምርት ለመጫን ወደ ሰበታ አቅንተው የነበሩ የወኪል አከፋፋዮች ንብረት ናቸው የተባሉ 20 የሚደርሱ የጭነት ተሽከርካሪዎች ቆመው የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አምስቱ ሙሉ ለሙሉ በእሳት መውደማቸውንና ሌሎችን ማትረፍ መቻሉን አንድ የፋብሪካው ሠራተኛ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የፋብሪካው ሠራተኞች መውጣት ባለመቻላቸው እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመቆየት ተገደዋል፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ በመሄድ ለተቃውሞ የወጡ ሰዎችን በኃይል በመበተን ሠራተኞች ወደ ቤታቸው ለመሄድ ችለዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ፋብሪካው ከግማሽ ቀን በኋላ ሥራ ማቆሙን ሪፖርተር ከምንጮች ማወቅ ችሏል፡፡

በዓለም ገና የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ አዲስ አበባ እንዳይስፋፋ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች ኦሮሚያን ከከተማዋ በሚለየው የጀሞ አደባባይ በተጠንቀቅ ቆመው ተስተውለዋል፡፡

በተመሳሳይም በርከት ባሉ ሥፍራዎች ይህ ነው የሚባል ግጭት ባይኖርም፣ በነዋሪዎች ላይ መደናገር በመፈጠሩ የንግድ ቤቶችና አገልግሎት ተቋማት ተዘግተው ታይተዋል፡፡

በአየር ጤና፣ ካራ ቆሬ፣ አሸዋ ሜዳ፣ ከአስኮ ወደ ቡራዩ በሚወስደው መንገድ ተመሳሳይ ችግር ተስተውሎ ነበር፡፡ በርከት ያሉ ነዋሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው በእግር ሲጓዙ ታይተዋል፡፡ ከነዋሪዎች በተገኘ መረጃ መሠረት ለትራንስፖርት አገልግሎቱ መቋረጥ ምክንያት የሆነው ቀደም ብሎ ቡራዩ አካባቢ ተከስቶ የነበረው የአደባባይ ተቃውሞ ነው፡፡ በዕለቱም በዚሁ በቡራዩ አካባቢ አንድ ተሽከርካሪ በእሳት መጋየቱን ከዓይን እማኞች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

አስኮ የሚገኘው መናኸሪያ ወደ አምቦ መስመር የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች መንገድ በመዘጋቱ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው መንገደኞች ተቸግረው ውለዋል፡፡

ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ በኅብረተሰቡ መሀል ከተፈጠረው ውዥንብር ባለፈ ምንም የተከሰተ የፀጥታ ሥጋት አለመኖሩን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ከፍርኃት ባለፈ በኅብረተሰቡ ላይ የፀጥታ ችግር አልተከሰተም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ