በየዓመቱ መስከረም ወር የኦሮሞ ተወላጆች ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት የኢሬቻ ክብረ በዓል ሥርዓት ላይ፣ በርካቶች መሞታቸውን በመቃወም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተቃውሞ ተቀሰቀሰ፡፡
ይህ ክስተትም ጋብ ብሎ የነበረውን የኦሮሞ ክልል ተቃውሞ ዳግም እንዲያገረሽ እያደረገው መሆኑን፣ በአዲስ አበባ ዙሪያና በሌሎች ትልልቅ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞና ግጭት ማሳያ ነው፡፡
የደረሰው አደጋ እንደተሰማ በአምቦ ከተማ ተቃውሞ መቀስቀሱንና እስከ መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት አለመረጋጋቱን፣ ወደ አምቦ የሚወስዱ መንገዶች መዘጋታቸውንና ትራንስፖርት መቆሙን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በአርሲ ኢተያ፣ በዝዋይና በመቂ ከተሞች ተመሳሳይ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን፣ በተለይ በመቂ ከተማ የከተማው መስተዳድር ሕንፃ ለተቃውሞ በወጡ በእሳት መያያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በከተማው ውስጥ በሆቴሎችና የንግድ መደብሮች ላይ ቃጠሎ ደርሷል፡፡
በምዕራብ ኦሮሚያ ሙገር የሚገኘው የናይጄሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጐቴ የሲሚንቶ ፋብሪካም ጥቃት ደርሶበታል፡፡
አራት እያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ማሽኖች፣ የጥሬ ዕቃ ማጓጓዣ ማሽኖችና ሲሚንቶ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች በቃጠሎ መውደማቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ፋብሪካው ሥራውን ለጊዜው እንዲያቆም ተገዷል፡፡
በአደጋው ማግሥት የኢሬቻ ክብረ በዓል የሚከበርባት የቢሾፍቱ ከተማ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ሐዘኗን ስትገልጽ መዋሏን ከአካባቢው ነዋሪዎች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ከቢሾፍቱ ከተማ ወጣ ብላ የምትገኘው ድሬ የተባለች ገበሬ ማኅበር ነዋሪዎች የሆኑ ስምንት ወጣቶች በአደጋው በመሞታቸው የተቆጡ የገበሬ ማኅበሯ ነዋሪዎች፣ በነጋታው ቁጣቸውን ሊገልጹ ቢሾፍቱ ከተማ እንደተገኙም ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ በፀጥታ ኃይሎች መበተናቸውንና ይህንንም ተከትሎ በቢሾፍቱ የሚገኙ ሱቆችና የንግድ ተቋማት ተዘግተው ከተማዋ ያለእንቅስቃሴ መዋሏን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና ሁከት ፍርድ ቤት፣ ጉምሩክ፣ ፖሊስ ጣቢያ መቃጠላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስር ቤት በእሳት እንዲያያዝ ተደርጐም እስረኞች እንዲያመልጡ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የመንግሥት ተሽከርካሪዎችም ተቃጥለዋል፡፡ በቡሌ ሆራ ከተማ ቁጥራቸው ባይገለጽም ሰዎች በግጭቱ ወቅት ተገድለዋል፡፡
በሐረርጌ አካባቢ በጭሮና በአወዳይ በተመሳሳይ ተቃውሞ እንደነበር የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በምዕራብ ወለጋ በደምቢ ዶሎ፣ በሻሸመኔ ሲካሄዱ መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በብሔር ላይ ያነጣጠሩ ንብረቶችን የማውደም እንቅስቃሴ እንደነበርም የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በተቀሰቀሰው ግጭት ያዘለ ተቃውሞ የሞቱ መኖራቸው እየተነገረ ቢሆንም፣ በይፋ ቁጥራቸው አልታወቀም፡፡