Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየይዞታ ማረጋገጫ ሳይኖረው ከ60 ዓመታት በላይ የቆየው አንበሳ ግቢ ለዕድሳት ተዘጋ

የይዞታ ማረጋገጫ ሳይኖረው ከ60 ዓመታት በላይ የቆየው አንበሳ ግቢ ለዕድሳት ተዘጋ

ቀን:

 ‹‹ፒኮክ ማዕከላዊ ፓርክ የሚዛወሩት አናብስት ግማሾቹ ብቻ ናቸው›› የአዲስ ዙ ፓርክ ዋና ዳይሬክተር

በአራዳ ክፍለ ከተማ ስድስት ኪሎ የሚገኘውና ከ1940 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለይዞታ ማረጋገጫ የሚገኘው በተለምዶ አንበሳ ግቢ በመባል የሚታወቀው አዲስ ዙ ፓርክ ማዕከል፣ ከመስከረም 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ወራት በዕድሳት ምክንያት አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑ ታወቀ፡፡

የ24 ዓመታት ዕድሜ ያለው ጠንክር፣ ልይሽ ሰለሞንና ሰናይት፣ መኮንንና ብርቅዬ፣ መሠረት ደፋር፣ ቀነኒሳ፣ ኃይሌ፣ ጥሩነሽና እጅጋየሁ የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን 12 አናብስትን ጨምሮ 36 የተለያዩ እንስሳት የሚገኙበት ‹‹አዲስ ዙ ፓርክ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ፓርኩ መሀል ከተማ ላይ ቢሆንም፣ ላለፉት 60 ዓመታት ኅብረተሰቡን የሚያረካ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ በተደረገ ጥናት በመረጋገጡ፣ እንዲታደስ ውሳኔ ላይ መደረሱን የአዲስ ዙ ፓርክ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሴ ክፍሎም ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

ፓርኩ ያረፈበት ቦታ 1.2 ሔክታር የነበረ ቢሆንም በመንገድ ግንባታ ምክንያት ተነካክቶ አሁን አንድ ሔክታር ብቻ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለፓርኩ 1509 የሚል የቤት ቁጥር ከመሰጠቱ ውጪ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ፓርኩ እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ክፍለ ከተማውና የከተማ አስተዳደሩ ሲያስተዳድሩት የቆዩ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የነበሩበት፣ በዜጎች መካከል ልዩነት የተፈጠረበትና ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋልጦ የቆየ እንደነበር ዶ/ር ሙሴ አስረድተዋል፡፡

ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ አስተዳደሩ በወሰደው ዕርምጃ መባረር የሚገባቸውን ሠራተኞች ማባረር፣ በሕግ መጠየቅ የሚገባቸውን በሕግ እንዲጠየቁ ማድረጉን የገለጹት ዶ/ር ሙሴ፣ በግቢው ውስጥ ትንሽ ቦታ የተከራዩ በወር ከ35 ሺሕ ብር በላይ ሲከፍሉ፣ መብራትና ውኃ እየተከፈለላቸው ሰፊ ቦታ የተከራዩ ደግሞ አሥር ሺሕ ብር ብቻ የሚከፍሉበት አሠራር እንዲስተካከል በመደረጉ፣ ዕርምጃውን ተቃውመው ወደ ሕግ የሄዱም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

ለከተማው ነዋሪዎች በተለይ አቅም ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተዳደሩ መዝናኛ ቦታዎችን በማዘጋጀት በተለይ ሕፃናት በሀብት ክፍፍል የድርሻቸውን እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለበት የተናገሩት ዶ/ር ሙሴ፣ ለአንድ ዓመት 100 ለሚሆኑ ሰዎች መጠይቅ በማቅረብ፣ ኅብረተሰቡ በመዝናኛ ማዕከሉ የሚያገኘውን እርካታ በመረዳት ለማደስ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡ በየስድስት ወሩ በተረገ የመጠይቅ ምዘና የኅብረተሰቡ እርካታ ከ63 በመቶ እንደማይበልጥ በመረጋገጡ፣ በበጀት ዓመቱ በተመደበለት 11.3 ሚሊዮን ብር መደበኛና 40.9 ሚሊዮን ብር የካፒታል በጀት ሙሉ በሙሉ ዕድሳቱን እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

አስተዳደሩ ፓርኩን ለማሳደስ ባወጣው ጨረታ በርካታ ድርጅቶች የተሳተፉ ቢሆንም፣ የቴክኒክ ግምገማውን ያለፉ ሁለት የኮንስትራክሽን ድርጅቶች መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ሙሴ፣ የፋይናንሻል ግምገማውን ደግሞ ዮት ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ4,506,918 ብር ማሸነፉንና የኮንትራት ውል መስከረም 20 ቀን 2009 ዓ.ም. መፈራረማቸውን አስታውቀዋል፡፡

ፓርኩ ታድሶ ሲጠናቀቅ 12 ሱቆች፣ የልጆች መጫወቻዎች፣ የመጻሕፍት መደብር፣ ደረጃውን የጠበቀ ሬስቶራንት፣ ትልቅ ፋውንቴንና ሌሎችም መዝናኛዎች እንደሚኖሩት ዶ/ር ሙሴ ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚተዳደሩት አዲስ ዙ ፓርክ ማዕከልና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 የሚገኘው 36 ሔክታር ስፋት ያለው ቦሌ ፒኮክ ማዕከላዊ ፓርክ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ሙሴ፣ ቦሌ ፒኮክ በሁለት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረው ግንባታ ላለፉት አራት ዓመታት አለመጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

በ91,202,354 ብር ኮንትራት ግንባታውን የጀመረው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለግንባታው አለመጠናቀቅ ምክንያቱ የከተማ አስተዳደሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ግንባታው የተጀመረው በስሜት እንጂ በዕውቀት እንዳልነበረ የሚናገሩት ዶ/ር ሙሴ በቦሌ ፒኮክ የሚገነቡ 12 የሥነ ምኅዳር መገለጫ ግንባታዎች ያሉ ቢሆንም፣ ወደ ሥራ ሲገባ ማስተር ፕላኑን ብቻ ተሠርቶ ዲዛይኑ ሳይሠራ፣ ከቦታው ለሚነሱ ነዋሪዎች አመቺ ሁኔታ ሳይዘጋጅና ግንባታውን ሊቆጣጠሩ የሚችሉ የሲቪልና የኤሌክትሪካል መሐንዲሶች፣ አርክቴክቶች ሳይሟሉ በመሆኑ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ይህም ችግር የኮንትራክተሩ ሳይሆን የአስተዳደሩ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ስድስት ኪሎ ከሚገኘው አዲስ ዙ ፓርክ ማዕከል ወደ ፒኮክ ማዕከላዊ ፓርክ የሚዛወሩት አናብስት ግማሾቹ ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አዲስ ዙ ፓርክ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጠው አመልክቶ እየተጠባበቀ መሆኑን፣ እስካሁን ድረስ ፓርኩ በዓመት ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኝ፣ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ በሚያውቀው ደረሰኝ የሚሰበስብ በመሆኑ በገቢ ረገድ ችግር አለመኖሩን ዶ/ር ሙሴ ገልጸዋል፡፡ ፓርኩ 18 ቋሚና አምስት ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዳሉትና ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ ኢንሹራንስ እንደተገባላቸው አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...