በአገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ የኢኮኖሚውን አውታሮች ባለመንካቱ፣ በኢትዮጵያ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አላሳደረም ሲል መንግሥት ገለጸ፡፡ በዚህ ዓመት የአገሪቱ ዓመታዊ ዕድገት 8.5 በመቶ እንደሚሆን ይጠበቃል ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በየዓመቱ የሚያወጣውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ሪፖርት ይፋ ባደረጉበት ወቅት ተጠይቀው ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ፣ ወቅታዊው የፖለቲካ ችግር የምርት አውታሮች ላይም ሆነ የምርት ውጤቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት ባለመኖሩ በኢኮኖሚው ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደማያደርስ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ስታስመዘግብ የቆየችው ባለ ሁለት አኃዝ ዓመታዊ ዕድገትም ባለፈው ዓመት በተከሰተው ድርቅና በዓለም በተከሰተው የሸቀጦች ዋጋ መውደቅ ምክንያት፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ወደ ነጠላ አኃዝ ዝቅ ማለቱን ዓመታዊው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በሪፖርቱ የቀረቡትን ምክንያቶች ያልተቀበሉት አቶ አህመድ፣ አጥኚዎቹ ገና ለገና ይደርሳል ብለው ባሰቡት ጉዳት ምክንያት የአገሪቱን ዕድገት ወደ ታች ማውረዳቸው ትክክል እንዳልነበር በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡ ይሁንና የአገሪቱ ዓመታዊ ዕድገት ወደ 8.5 በመቶ ዝቅ ሊል እንደሚችል ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
መንግሥት በአምስት ዓመት ዕቅዱ መሠረት በአማካይ በየዓመቱ የ11 በመቶ ዕድገት እንደሚኖር ቢያቅድም፣ ከ8.5 እስከ ዘጠኝ በመቶ ባለው ክልል ውስጥ እያደገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በአንፃሩ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ይፋ አድርጎት በነበረው ትንበያ መሠረት፣ የአገሪቱ ዕድገት ወደ 4.5 በመቶ ዝቅ ማለቱ አይዘነጋም፡፡ በመጪው የአውሮፓውን ዓመት ኢኮኖሚው በሰባት በመቶ ሊያድግ እንደሚችልም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በተመድ አፍሪካ ሪፖርት መሠረት የአፍሪካ አገሮች ከዚህ ቀደም ያስመዘግባሉ ተብሎ ከሚጠበቀው መጠን ይልቅ ቅናሽ መደረጉ ታይቷል፡፡ ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ያድጋል ተብሎ የሚጠበቀው ከአራት በመቶ በላይ ቢሆንም፣ በዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በሸቀጦች ዋጋ መውደቅ ሳቢያ ዕድገቱ ወደ 3.6 በመቶ ዝቅ መደረጉን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ይህ መጠን ግን የዓለም ኢኮኖሚ ያድጋል ተብሎ ከሚጠበቅበት ከ3.1 በመቶ አኳያ ሲታይ፣ አፍሪካ አሁንም ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ ቀጣናዎች እስያን ተከትላ በሁለተኛነት እንድትመራ አስችሏታል ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ በበኩሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመላው ዓለም የታየው መቀዛቀዝ፣ የአገሮችን ዕድገት ይበልጥ ወደ ታች መጎተቱን ያመለክታል ብሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው ሪፖርት እንደሚጠቁመው፣ የአፍሪካ ዕድገት ወደ ሁለት በመቶ ዝቅ እንደሚል የሚጠቁም ነው፡፡