Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሰነድ አልባ ባለይዞታዎችን ለማስተናገድ የወጣው ሰርኩላር ወደታች አለመውረዱ ቅሬታ ቀሰቀሰ

ሰነድ አልባ ባለይዞታዎችን ለማስተናገድ የወጣው ሰርኩላር ወደታች አለመውረዱ ቅሬታ ቀሰቀሰ

ቀን:

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሰነድ አልባ ባለይዞታዎችን ለማስተናገድ የወጣውን መመርያና በተገቢው የመንግሥት አካል ሳይፈቀድ ቦታ የያዙ ሕገወጥ ባለይዞታዎችን ለማስተናገድ የወጣውን መመርያ ለማሻሻልና ለማብራራት ያወጣውን ሰርኩላር፣ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ወደ ክፍላተ ከተሞች ባለማውረዱ ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡

ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በ1988 ዓ.ም. ጂአይኤስና በ1997 ዓ.ም. መስመር ካርታ ላይ የማይታዩ ይዞታዎች የሚስተናገዱበት አዲስ ሰርኩላር ለይዞታ አስተዳደር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ በግልባጭ ደግሞ ለከንቲባ ድሪባና ለምክትል ከንቲባ አባተ ስጦታው ልኮ ነበር፡፡

ነገር ግን የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ሰርኩላሩን ለክፍላተ ከተሞች ባለማውረዱ፣ ነዋሪዎች መንግሥት በሰጣቸው ዕድል መጠቀም እንዳላስቻላቸው እየገለጹ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሰነድ አልባ ባለይዞታዎችን ለማስተናገድ የወጣው መመርያ ቁጥር 17/2006 እና አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ የተያዙ ይዞታዎችን ለማስተናገድ የወጣው መመርያ ቁጥር 18/2006 በደብዳቤ በተላለፈ ሰርኩላር እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ በተግባር ላይ ከዋሉ ሦስት ዓመታት ያስቆጠሩት መመርያዎች እንዲሻሻሉ የተደረገው የከተማው አስተዳደር ሕጋዊ እንዲሆኑ ዕድሉን የሰጣቸው ባለይዞታዎች መስተናገድ ባለመቻላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 1997 ዓ.ም. ድረስ ያሉ ባለይዞታዎችን ሕጋዊ ለማድረግ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በመመርያ ቁጥር 17/2006 በተደነገገው መሠረት፣ እነዚህ ባለይዞታዎች የሚስተናገዱት በ1988 ዓ.ም. በተነሳው ጂአይኤስ ላይ የሚታይ ቤት ካላቸው፣ ከሌላቸው ደግሞ ስለግንባታው መንግሥታዊ በሆነ ተቋም ከግንቦት 1988 ዓ.ም. በፊት የተሰጠ ሰነድ ማቅረብ፣ ግንባታውም ከ1988 ዓ.ም. በፊት ተገንብቶ በእጃቸው የሚገኝ መሆኑን በወረዳው አስተዳደር ተረጋግጦ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ዋና ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይለ ተፈርሞ የወጣው ሰርኩላር እንደሚለው፣ ‹‹በመመርያው ላይ መንግሥታዊ በሆነ ተቋም የሚሰጥ ሰነድ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አልተቀመጠም፤›› ይላል፡፡

ሰርኩላሩ ከዚህ በተጨማሪም በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ሥር የሚገኘው የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለአሥሩም ክፍላተ ከተሞች በቁጥር ይአስ/34407 በጻፈው ደብዳቤ የግብር ደረሰኝ ተቀባይነት እንደሌለው፣ እንዲሁም የቤት ግንባታ የተመለከተበት የቀድሞ ካርታ መቅረብ እንዳለበት ማመልከቱን ሰርኩላሩ አስታውቋል፡፡

‹‹በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፤›› በማለት ሰርኩላሩ ይገልጻል፡፡ በሰርኩላሩ መሠረት ከግንቦት 1988 ዓ.ም. በፊት የተቆረጠ የመኖሪያ ወይም የድርጅት ቤት የግብር ደረሰኝ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወይም በሥሩ ባሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በኩል፣ ወይም በመንግሥት ፋይናንስ ተቋማት እንዲረጋገጥ ተደርጎ የግብር ደረሰኙ ከመንግሥታዊ ተቋም የተሰጠ ሰነድ ሆኖ አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሰርኩላሩ የተደረገው ማሻሻያ በቀድሞ ካርታ ላይ የቤት ግንባታ የተመለከተበት ካርታ መቅረብ አለበት ተብሎ ለተሰጠው ማብራሪያ፣ በወቅቱ ካርታው በሕጋዊ መንገድ እስከተሰጣቸው ድረስ በካርታው ላይ የቤት ግንባታ ቢመለከትም ባይመለከትም ሕጋዊነታቸውን የሚያሳጣቸው ባለመሆኑ፣ ቀደም ሲል በሕጋዊ መንገድ ካርታ የተሰጣቸው ግለሰቦች ኦርጅናል ካርታቸውን ማቅረብ ከቻሉ፣ ከመንግሥታዊ ተቋም እንደተሰጠ ሰነድ ሆኖ ተቀባይነት ማግኘት እንዳለበት ደንግጓል፡፡

ሰርኩላሩ አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ በተያዙ ቦታዎች ላይም ማሻሻያ አድርጓል፡፡ አግባብ ካለው አካል ሳይፈቀድ የተያዙ ቦታዎች የባለቤትነት መብት ሊፈጠርላቸው የሚችለው በ1997 ዓ.ም. በተሰጠው መስመር ካርታ ላይ የሚታይ ቤት፣ ከሌላቸው ደግሞ ስለቤቱ መንግሥታዊ በሆነ ተቋም ከሚያዚያ 1997 ዓ.ም. በፊት የተሰጠ ሰነድ ማቅረብና ቤቱ ከ1997 ዓ.ም. በፊት ተገንብቶ በእጃቸው የሚገኝ እንደነበር በወረዳው አስተዳደር ተረጋግጦ መቅረብ እንዳለበት መመርያ ቁጥር 18/2006 አንቀጽ 5(5.1.1) እና (5.13) ያመለክታሉ፡፡

በዚህ መሠረት ወደ መስተንግዶ ሲገባ የወረዳው አስተዳደር ቤቱ በወቅቱ ተገንብቶ በእጃቸው የነበረ መሆኑን አረጋግጦ የሚልክ ቢሆንም፣ ስለቤቱ መንግሥታዊ በሆኑ ተቋማት ከሚያዚያ 1997 ዓ.ም. በፊት የተሰጠ ሰነድ ማቅረብ ባለመቻላቸው በርካታ ባለይዞታዎች አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን እየገለጹ መሆኑን፣ ከሚቀርቡ አቤቱታዎች መረዳት መቻሉን ሰርኩላሩ ያስታውሳል፡፡

ሰርኩላሩ፣ ‹‹ይሁን እንጂ ስለቤቱ መንግሥታዊ በሆነ ተቋም ከሚያዚያ 1997 ዓ.ም. በፊት የተሰጠ ሰነድ እንዲያቀርቡ የተፈለገው የወረዳው አስተዳደር ቤቱ በወቅቱ ተገንብቶ በእጃቸው የነበረ መሆኑን በሚያረጋግጥበት ወቅት አጋዥ ሰነድ ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ ነው እንጂ፣ ይህ ሰነድ ካልቀረበ አገልግሎቱ አይሰጥም ማለት አይደለም፤›› ይላል፡፡

ከግንቦት 1988 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 1997 ዓ.ም. የባለቤትነት መብት በፈጠራ እንዲከናወንላቸው እየተደረጉ ያሉት ባለይዞታዎች፣ አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድላቸው በሕገወጥ መንገድ ቦታ የያዙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ቦታ ለያዙት አካላት ደግሞ ከ1997 ዓ.ም. በፊት ውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ መስመር ማስቀጠል ወይም የግንባታ እድሳት ፈቃድ መስጠት ይቻላል ተብሎ አይገመትም፡፡

በዚህ የተነሳ ከ1997 ዓ.ም. በፊት ቤት ገንብተው እየኖሩበት መሆናቸውን የወረዳው አስተዳደር አረጋግጦላቸው እያለ፣ ቤታቸው በ1997 ዓ.ም. መስመር ካርታ ላይ የማይታይ በመሆኑ ከ1997 ዓ.ም. በፊት ከመንግሥታዊ ተቋም የተሰጣቸው ሰነድ ማቅረብ ባለመቻላቸው አገልግሎቱን እንዳያገኙ ተከልክለዋል፡፡

በዚህ መሠረት ሰርኩላሩ መንግሥታዊ በሆነ ተቋም ከሚያዚያ 1997 ዓ.ም. በፊት የተሰጠ ሰነድ ያላቸው ባለይዞታዎች ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን፣ የሌላቸው ደግሞ ሰነዱ እንደ ቅድመ ሁኔታ ሳይቆጠር ቤቱ ከ1997 ዓ.ም. በፊት ተገንብቶ በእጃቸው የሚገኝ እንደነበር በወረዳው አስተዳደር ተረጋግጦ ከቀረበ ተገቢው መስተንግዶ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ ሰለሞን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለማድረግ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...