Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በኢንቨስትመንቶች ላይ የደረሱ ውድመቶችን የሚያጣራ ቡድን ሊላክ ነው

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በኢንቨስትመንቶች ላይ የደረሱ ውድመቶችን የሚያጣራ ቡድን ሊላክ ነው

ቀን:

 በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ሳቢያ በሙሉና በከፊል ውድመት የደረሰባቸውን ኢንቨስትመንቶችና ተያያዥ ንብረቶች የሚያጠና ቡድን፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ክልሎቹ እንደሚያሰማራ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በበኩሉ በሁለቱ ክልሎች ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት በአገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ያደረሰውን የጉዳት መጠን ለመለየትና ለማጥናት፣ የፌዴራልና የክልሎቹ መንግሥታት በጋራ እየገመገሙ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጌታሁን ነጋሽ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹በኦሮሚያ በመጀመሪያው ዙር ጉዳት የደረሰባቸው ባለሀብቶች እንዲጠናላቸው በጠየቁት መሠረት አጥንተን ጨርሰን፣ ለደረሰባቸው ጉዳት ማካካሻ ለመክፈል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበን ውሳኔ እየተጠበቀ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እንደደረሰ ለባለሀብቶች መከፈል ይጀምራል ሲሉም አክለዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች በተነሱት ተቃውሞዎች በአገር ውስጥና በውጭ ኢንቨስትመንቶች ላይ የደረሱ የውድመት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ የደረሰውን አደጋ በሚመለከት ጥቅል የሆነ ድምዳሜ ላይ ባለመደረሱ በቀጣይ ይታያል ተብሏል፡፡

በመጀመሪያ ዙር በኦሮሚያ ክልል የደረሱ ጉዳቶችን አስመልክቶ በተደረገው ጥናት መሠረት ለሰባት ባለሀብቶች ካሳ እንደሚከፈል የገለጹት አቶ ጌታሁን፣ በኦሮሚያ ክልል በድጋሚ በደረሱ ጉዳቶች የሁለተኛ ዙር ጥናት ይካሄዳል ብለዋል፡፡ እንዲሁም በቅርቡ በአማራ ክልል በተመሳሳይ የደረሱ ጉዳቶችን ለማጥናት የሚያጣራ ቡድን ይላካል፡፡ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በመገኘት መረጃዎችን አጠናቅሮ ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በራሱ ከሚያካሂዳቸው ቀጥተኛ የግምገማና የጥናት ሥራዎች በተጨማሪ ክልሎቹ በራሳቸው ገምግመው የደረሱበት የምርመራ ግኝት አለ፡፡ እንዲሁም ከባለሀብቶቹ መካከል በራሳቸው የደረሰባቸውን ውድመት አጠናቅረው ያቀረቡ እንዳሉም ኃላፊው ጨምረው አስረድተዋል፡፡ በተለይ ባለሀብቶቹ ያቀረቧቸውን ማስረጃዎች የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አይቶና ገምግሞ ለኮሚሽኑ እንዲያቀርብ ውሳኔ ላይ መደረሱንም ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ባለሀብቶቹ ባቀረቡት መረጃና ቅሬታ መሠረት፣ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች እስከ ረቡዕ መስከረም 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ አጥንተው መመለሳቸውንም አብራርተዋል፡፡

‹‹የዚህን የጥናት ድምዳሜ ኮሚሽኑ በራሱ ከመረመረና በልማት ባንክ በኩል በድጋሚ ታይቶ አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ የሚገኘው ውጤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቦ ሲፀድቅ የካሳ ክፍያውን እንከፍላለን ብለን እናስባለን፤›› ሲሉም አቶ ጌታሁን አስረድተዋል፡፡

እስካሁን የጉዳቱ መጠን ተጠንቶ ያለቀው የኦሮሚያ ክልል የሰባቱ ባለሀብቶች ብቻ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የመጨረሻ ውሳኔ ከሚጠብቀው በተጨማሪ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የኦሮሚያ ተቃውሞ ከጀመረበት አንስቶ የአማራ ክልል ተቃውሞ እስከተከሰተበት ባለው ጊዜ ውስጥ አጠቃላይ የውድመትና የጉዳት መጠኑን መገመት እንደሚያስቸግር ጠቁመዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ላይ እስካሁን የደረሰው ውድመትና በፍሰቱ ላይ ያመጣው ተፅዕኖ ምን እንደሚመስል በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያው ዙር በኦሮሚያ ክልል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተረጋግጦላቸዋል የተባሉት የሰባቱን ባለሀብቶች ዝርዝር ሁኔታና እነማን እንደሆኑ እንዲገልጹ ሪፖርተር ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ‹‹ለጊዜው ቢያንስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እስኪታወቅ ድረስ ለመግለጽ ያስቸግራል፤›› በማለት አቶ ጌታሁን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለባለሀብቶች ይሰጣል ስለተባለው የካሳ ዓይነትና መጠን ሲያስረዱም፣ ‹‹ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ጥናት የካሳው መጠንና ዝርዝር የጉዳት ዓይነት ተካቶበታል፡፡ ነገር ግን የግድ በቀረበው ልክ ይፀድቃል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ መጠነኛ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲታይ ባለሀብቶች ባቀረቡት ዝርዝር መሠረት ሙሉ ለሙሉ ካሳ ላይከፈላቸው ይችል ይሆናል፡፡ የካሳ ክፍያው የደረሰባቸውን ጉዳት ሊጠግን የሚችልና መልሰው መቆም የሚያስችላቸው ጉልበት ይሰጣቸዋል ተብሎ ይታመንበታል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...