Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአገር አማን ነው ወይ?

አገር አማን ነው ወይ?

ቀን:

 (ወቅታዊ አጭር ግምገማ)

በገነት ዓለሙ

ከትጥቅ ትግል ታሪክ አንስቶ የኢትዮጵያን ትግል በትክክለኛ አቅጣጫ የመራሁት እኔ ነኝ የሚለው ኢሕአዴግ ዛሬም የኢትዮጵያን ሕዝቦች በህዳሴ እየመራሁ ነን ባይነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ‹‹አውራ ፓርቲ›› የሚባል ነገርን ያስተዋወቀንም እሱው ነው፡፡ በዛሬው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ጌታው ፓርቲ ከፍተኛ የአባላት ብዛት ያለውና ከዳር ዳር መዋቅሩን የዘረጋጋው፣ ለሁሉም እኩልና ነፃ ባልሆነ ሜዳ ላይ ‹‹እየተወዳደረ›› በምርጫ ‹‹የሚያሸነፈውም›› እሱው ነው፡፡ ያም ሆኖ ‹‹መሪነቱም›› አውራነቱም በምርጫ አሸናፊነቱም በመዋቅርና በ‹‹እኖር ብዬ›› ገመድ መያዝን እንጂ፣ እውነተኛ የሕዝብ ድጋፍን የሚናገር አይደለም፡፡ ባለኮከቡ የኢትዮጵያ ባንዲራ በኢሕአዴግ ዓይን ከመታየት ወጥቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ለመሆን የሚያበቃ ልባዊ ተቀባይነት ማግኘት አልሆንለት ሲል ቅጣት በሚያስከትል ሕግ አማካይነት ነው ሊከበርና ሊዘወተር የበቃው፡፡ እንደዚያም ሆኖ፣ ዛሬም ኢሕአዴግን የመቃወም እንቅስቃሴ ባንዲራውን ባለመያዝም አማካይነት መገለጹ ገና አልቀረም፡፡

ይህ ድምዳሜ የሚጓጉጣቸው ቢኖሩ የባሰም አለላቸው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ከኅዳር አንስቶ እስከ 2009 ዓ.ም. መባቻ ድረስ የታየውን የተቃውሞ አስተዳደግና አሰፋፍ ስናስተውልና ትንሽ ለቀቅ ቢደረግ ምን ሊያስከትል ይችል እንደነበር ስንመዝን፣ ኢሕአዴግም ሆነ የቤት ውስጥ ተቃዋሚዎቹ እውነተኛ የፖለቲካ መሪነት ሚና ጭራሽ  እንደሌላቸው ወለል ብሏል ማለት ይቻላል፡፡ ይህንኑ ድምዳሜ በጥያቄ መልክ ላቅርበው፡፡ የኢሕአዴግ  መንግሥት  25 ዓመት በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በኮንፈረንስና በሥልጠና ሲያጎርፍ  በኖረው ፖለቲካው የሕዝብን ልብ አነጋግሮና ተደማጭነት አግኝቶ ተቃውሞውን ከነቁጣው ማብረድና ማስቆም ይቻለው ነበር? የአገር ውስጥ ተቃዋሚዎችስ ቢሆኑ ‹‹እርቅ››፣ ‹‹ሰላማዊ ንግግር››፣ ‹‹የኃይል ዕርምጃ አይበጅም››፣ ‹‹መንግሥት የሁሉንም ሕዝብ ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት›› የሚሉ ዓይነት መግለጫዎች ባለፍ ገደም ከመስጠት ፈቀቅ ቢሉ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የዜና አቀባይ  ዓይነት ሚና በመጫወት፣ ከዚያም ዘለል ያሉ ቢኖሩ ነጭናጫ ቅሬታ በማሰማት የተገደቡ አልነበሩም?

ለአሥር ወራት ያህል ሄድ መለስ ቱግ ቱግ እያለ የቆየው የሕዝብ ቅዋሜ መሪ ማን ነበር ታዲያ? ዋነኞቹ መሪዎቹ ሁለት ናቸው፡- የኢሕአዴግ መንግሥት አስተዳደርና የሕዝብ ምሬት፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ሳያውቀውና ሳይፈልገው በተንኳሻነት የቁጣ አነሳሽ ሆኖ እንደ መሪ አገልግሏል፡፡ በአሮሚያም ሆነ በአማራም ክልል ውስጥ መንግሥት የሕዝብ አሜነታን በማጣት፣ ለቅሬታዎችና ለጉምጉምታ ጆሮ በመንሳት፣ የሰላማዊ ሠልፍ መብትን በማፈን፣ ቅዋሜዎች ገደብ ፈንቅለው ሲወጡ በሕገወጥነት በመወንጀልና የኃይል ዕርምጃዎች በመውሰድ ለቅዋሜ ትግል ነዳጅ ሲሆን ታይቷል፡፡ የታፈነ ብሶትና ምሬት አንዴ ከፈነዳ በኋላ ድንገተኛ መሪዎችን ከውስጥና ከውጭ እየወለደ የኢንተርኔት ማኅበራዊ መድረኮችንና የሰው በሰው መረቦችን በመረጃ መለዋወጫነትና ትግል በማስተባበሪያነት እየተጠቀመ ተዛምቷል፡፡ ተዳፍኖ የኖረ እልሁን ዘርግፏል፡፡ በደሉ በተባሉ ሰዎችና ንብረቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በዚህ ውስጥ አርቆ አስተዋይነት የጎደላቸው ግለሰቦች የኢንተርኔት ማኅበራዊ መድረኮችንም ሆነ የኢሳት ሥርጭትን በመጠቀም ስሜታዊነትን ለማራገብና ለጥፋት ተጠቅመውባቸዋል፡፡ በአያሌው ‹‹አለቀ! ደቀቀ! ወደኋላ መመለስ የለም! የመጨረሻውም ምዕራፍ ላይ ነን! ወዘተ›› በማለት የሕዝብ ቅዋሜን አስክሮ ፈጣን የፖለቲካ ውጤት የማግኘት ጥማት፣ እንዲሁም ከመደዴ ያልዘለለ የተጠራቀመ ጥላቻን ለማስታወስና ግጭት ለመደወል የሚስማማ ‹‹የወያኔ ጦር! የወያኔ መንግሥት! የወያኔ ጭፍጨፋ! ወዘተ. ወዘተ.›› የሚል አፈራረጅ መድረክ አጣቦ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ሆይ ሆይታው በኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ውስጥ ያለውን ትግራዊ ሥርጭት እስከ መዘርዘር (ጥላቻን እስከ መኮርኮር) ድረስ አዙሮ ማየት ቸግሮት ታይቷል፡፡ እንደዚያም ሆኖ፣ የኢሳት የሬዲዮና የቲቪ ሥርጭት ብዙ ኮምኳሚ ማግኘቱ የኢሕአዴግ መንግሥት እነ ‹‹ግንቦት 7››ን አሸባሪ ብሎና ፀረ ሽብር አዋጅ ዘርግቶ ከሕጋዊ ተቃዋሚና ከሕዝብ ጋር እንዳይደራረሱ የቆረጠበት ብልጠት መቀደዱን ለማስተዋል በቃን፡፡ ከንግዲህ የኢሕአዴግ መንግሥት አሸባሪ ባይ ድንጋጌውን ቀይሮ ዓይኑን መክፈት አለበት፡፡ ወይም መዓት ሕዝብ አዋጅ በመጣስ መክሰስ አለበት፡፡

የሕዝብ ተቃውሞው እየተጋጋለ በተስፋፋበትም ሒደት ውስጥ የመንግሥት አሳባቢነት የኪሳራ ሀብታም መሆኑንም ለመታዘብ ችለን ነበር፡፡ አመፅ በማነሳሳትና በማበጣበጥ ሴራ የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎችን መኮነን፣ በዚሁ የውጭ የማበጣበጥ ሴራ ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ የውስጥ ኃይሎች እያሉ ግለሰቦችን ማደን ሁሉ ራስን በራስ ከማደናገር በምን ይለያል?! ኢሳት ውስጥ ሲፈነጭ ያየነው በመደዴ ስሜቶችና በችኩል ‹‹ትንተናዎች›› የተሞላ ፖለቲካኝነት እዚሁ በአገር ውስጥ በየቤቱ፣ በየመንገዱና በየቡና ቤቱ በሽበሽ ነው!! የኢሳት የሚለየው ከየአቅጣጫው የወሬ መዓት የሚመጣለት መሆኑና ከአንድ ማዕከል እየቀመሙAnchor መልሶ ለመርጨት የመገናኛ ዘዴው የሰጠ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ኢሳት ላይ ከተሰማው የበለጠ በየጓዳ ጎድጓዳው ስንት የሚሰቀጥጥ ሥሌትና የበቀል ስሜት ይፍለቀለቅ የለ!!

ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ ወገንተኛ (ኢሕአዴጋዊ) አገዛዝ እያደረጀ፣ ለመደዴ ፖለቲከኞች ለጥላቻ የሚሆን ማዕድን እንካችሁ እየማሳችሁ ራሳችሁንም ሌላውንም አማቅቁ ብሎ የሰጠ፣ በዚህ ጥፋቱና ዴሞክራሲያዊ ተቃዋሚዎች እንዳይጎለበቱ በማዳቀቅ፣ ከጥላቻ የፀዳና የበሰለ ፖለቲካ በአገሪቱ ውስጥ ሥር እንዳይሰድ የከለከለ፣ የወገንተኛነትና የሙስና መሸሸጊያ ዋሻ በመሆን በራሱ ላይ የሕዝብ ምሬት እንዲከማች ያደረገ፣ በራሱ ላይ አመፅ ከመጥራት ባልተናነሰ ደረጃ ራሱን በራሱ ለመጣል ሲተጋ የኖረ፣ ራሱ የኢሕአዴግ መንግሥት!! ለአመፁም ለውድመቱም በዋነኛነት ተጠያቂ ማድረግ የሚገባው የገዛ ራሱን!! መክሰስና ማሰር ያለበትም የገዛ ራሱን!!!

ከኖረ ጥፋቱና በቅርቡ ከሆነው የሚማር ከሆነ ዕጦቶቹ ምርምር የማይሹ (ዓይኖቹ ሥር የተገሸሩ) ናቸው፡፡

 • ኢሕአዴግ በ25 ዓመት ገዥነቱ ውስጥ ከፊተኞቹ ገዥዎች የትና የት የተሻለ ቁሳዊ ግንባታ ያካሄደ ቢሆንም በሕዝብ ተዓማኒ የመሆን ነገር እስከ ዛሬ ዕጦቱ ሆኖ እንዳለነው፡፡ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ለጎረቤት አገር መሬት አሳልፎ በመስጠት መጠርጠር አልተወገደለትም፡፡ ለኦሮሚያ ቁጣ መዘዝ የሆነው አለመታመኑ ነው፡፡ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ተቃጠለ ሲባል በተቃዋሚም ሆነ በብዙ ሰዎች ውስጥ ወዲያውኑ የደወለው ጥርጣሬ ነበር፡፡ ሲጀመር አንስቶ እስከ ዛሬ ኢሕአዴግ የሚታየው ከፊት ለፊት አንድ ነገር፣ በጓዳ  (በስውር) ደግሞ ሌላ ነገር የሚሠራ ተደርጎ ነው፡፡ ለዓመታት ስንት ገንዘብ እየከሰከሰ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በስብሰባዎች የሚያካሂደው የፖለቲካ አጠባ ሁሉ ይህንን ኪሳራ ለማስወገድ አላስቻለውም፡፡ በኢሕአዴግ መንግሥት ፕሮፓጋንዳ ውስጥ መላ የለሽ ንዝንዝ እስከ መምሰል የደረሰ ነገር ‹‹ሰላም ሰላም ያስፈልገናል›› ባይነት ነው፡፡ ይህ ማንም የሚያቀው ምግብ ለሰው ያስፈልጋል ከማለት የማይሻል ተራ እውነት ነው፡፡ ቁልፏ ጉዳይ ሰላምን ሁሌም የሚያቀዳጁ ነገሮችን የማሳካቷ ነገር ነች፡፡ ‹‹ናሁ›› ቲቪ ከጎዛምን ሆቴል (ደብረ ማርቆስ) ጋር በመተባበር ባካሄደው የአዲስ ዓመት በዓል ዝግጀት ላይ ሁለት ሰዎች የማይረሳ ንግግር ተናግረው ነበር፡፡ አንደኛው ሰላም እንዲኖር ፍቅር ያስፈልገናል፡፡ ሰው ከሰው፣ ብሔር ከብሔር፣ መንግሥት ከሕዝብ ጋር መፋቀር አለበት ሲል ተናገረ፡፡ ሌላው ሰው ፍቅር  የሚኖረው ደግሞ መዋሸት ስንተው ነው፡፡ አንቀደድ፣ ፈጣሪ ከመቀደድ ያውጣን ብሎ አለ፡፡ በዚህ ጥቅል ንግግር ውስጥ፣ በሕዝብ የተወደደና በሕዝብ የታመነ መንግሥት ናፍቆታችን ቁልጭ ብላ ተቀምጣለች፡፡ የኢትዮጵያ ቁልፍ የፖለቲካ ጥያቄ ፖለቲከኝነትን በማይጠይቅ ቀላል ቋንቋ እንዲህ የሚገለጽ ሆኗል፡፡ ለኢሕአዴግ መንግሥት ግን ከብዶታል፡፡
 • የኢሕአዴግ መንግሥት ሚስጥር መሆን የማይገባውን ሁሉ ሚስጥር ማድረግና የሰምና ወርቅ ኅብራዊ ሥራ ስለሚወድ፣ ከዚህም ብሶ ፖለቲካዊ ሎሌነትን በጥቅም የመግዛት ሙሰኛነት ራሱ የለመደበት በመሆኑ ምክንያት የሙስና አባዢ እንጂ ለሙስና ፀር መሆን አልቻለም፡፡ በዚሁ በቅዋሜ ወቅት የተፈጸመ ነገር በምሳሌነት እንጥቀስ፡፡ ብዙ የሕይወትና የአካል ጉዳቶች በደረሱበት፣ እስራትና እንባ በበረከተበት ሁኔታ ውስጥ የአዲስ ዓመት መቀበያ የዘፈን ድግስ አዘጋጅቶ ለማናጠርና ኪስ ለመሙላት ህሊናችን እሺ አይለንም የሚል ነገር በሙዚቃ ሰዎች አካባቢ ብቅ ብቅ ማለቱ (በመንግሥት ላይ ፖለቲካዊ አንድምታ ቢኖረውም) ጤናማ አስተሳሰብ ነበር፡፡ እኔም የኢሕአዴግን መንግሥት ብሆን ኖሮ ከዚሁ ጤናማ አስተሳሰብ ጋር አባሪ ተነባባሪ ሆኜ በየትኛውም ወገን በኩል ለደረሰ የሕይወት መቀጠፍና ጉስቁልና መታወሻ የሚሆን የሙዚቃ ሥራዎች እንዲቀናበሩ አስደርጌ፣ ከተቃዋሚዎችና ከሕዝብ በኩል ቀንድ የሆኑ ግለሰቦች የተሳተፉበት ሐዘንን ከመጋራት ጎን ጥያቄዎች ሁሉ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚመጡበትን አዲስ ምዕራፍ የሚያበስር (እናም የአዲስ ዓመት ቅበላው ‹‹ተመስጌን››ን ያጎናፀፈና ቁጣ የሚያበርድ) እንዲሆን ባደረግሁ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የፈጸመው ግን ‹‹ለዓመት በዓል  ልብስ ተገዛልኝ›› ብሎ ሊያስቀና የሞከረን ልጅ ‹‹እኔም አለኝ›› ብሎ ለመመከት ከሚሞክር የሕፃናት ሥራ የማይሻል ግብዝነት ነበር፡፡ ዘፈን አንደግስም ባይነትን ለማክሸፍ መግቢያ በነፃ ብሎ በግዮን ሆቴል መስክ ላይ የሙዚቃ ትርዒት ማዘጋጀት፣ የነፃ መግቢያ ተጋባዦችን ለመሳብ የቀረበች ጉርሻ ነች ሙስና፡፡
 • የኢሕአዴግ መንግሥት ስንቱን የጉልበት ሥራ፣ የመብትና የሕግ ጥሰት እየፈጸመ እስከ ዛሬ ሥልጣን ላይ መቆየት የቻለው ቆዳዊ የይስሙላ በሆነው የምርጫ ክንዋኔ ሳይሆን ለእሱ እንዲታመን አድርጎ በቀረፀው ወታደራዊ ኃይልና የነጭ ለባሽ አውታር አማካይነት ነው፡፡ በሌላ አባባል የኢሕአዴግ ‹‹ሥልጣን የሰጠኝ ሕዝብ ነው፣ ዴሞክራሲን እየገነባሁ ነው…›› ባይነት ማንንም የማያሞኝ ዓይነ ደረቅነት መሆኑና የመንግሥት አውታሮች ኢሕአዴጋዊነታቸው እንደተጠበቀ ዴሞክራሲ ሊዋቀር እንደማይችል አገር ያወቀው ነው፡፡ የቅዋሜ ሠልፎች ‹‹የተኩስ ዕርምጃን ያዘዘ ሰው ከሥልጣን ወርዶ በሕግ ይጠየቅልን!›› የማይሉት፣ በጋዜጣ ጽሑፍ የምንለቀልቅ ሁሉ ‹‹ግራ አጋቢ ሆኖብናል… ያሳስበናል/ያስጨንቀናል … መደረግ የሌለበት ነው …›› የምንለው ወይም መንግሥትን ለማሳመንና ለማራራት የምንዛክረው ገዥዎቻችንን ከሥርዓተ መንግሥቱ ነጥለንና ለሥርዓተ መንግሥቱ አቅርበን መፋረድ እንደማንችል ስለምናውቅ ነው፡፡
 • መንግሥታዊ አውታራት ከቡድን ታማኝነት ተላቀው በሕዝብ ድምፅ ገዥ የሚወጣና የሚወርድበት ሥርዓት እስካልመጣ ድረስ የሕዝብና የመንግሥት ፍቅር እንደማይኖር፣ የአገሪቱና የሕዝቧ ሰላምና ልማትም ከአደጋ እንደማይወጡ በዚህ ዓመት አደባባይ የወጣው የሕዝብ ምሬት ምስክር ነው፡፡ የቅርቡ ልምድ ሌላ ምስክርነትም ሰጥቷል፡፡ የመንግሥት አውታራት ኢሕአዴጋዊነት እስካልተቋረጠ ድረስ በጭራሽ የብሔሩ ጥፋት ባልሆነ ምክንያት ትግራዊነት ከኢሕአዴግ ገዥነት ጋር ተዛምዶ መታየቱ እንደማይበጠስ፣ እስካልተበጠሰ ድረስም የጥላቻ መፍለቂያው ምንጭ እንደማይደርቅ፣ ጥላቻ እንደሌለ አድርጎ ማላባበስም ሆነ መሸምጥጥ ጥላቻ አድፍጦ እንዲደረጅና የቁጣ ፍንዳታ አጋጣሚ ሲያገኘ እሳት ጭሮ ሕዝብን እንዲያባላ መፍቀድ መሆኑን በቀላሉ ምሮ አሳይቷል፡፡ በገዥነት ውስጥ የዚህ ዓይነት ብልሽት ቀላል አይደለም፡፡
 • ችግሮች ታጅለው ኖረው ፍንዳታ ሲመጣም በተለያየ መልክ የተከሰተ የሕዝብ ቁጣ (ጠመንጃ ይዞ ለጩኸት የወጣ፣ ከዚያም አልፎ የተኮሰ ቢኖር እንኳ) ኃላፊነት የሚሰማውና ሕዝብን የሚያከብር መንግሥት የድፍጠጣ በትር ለመጠቀም አይቸኩልም፡፡ ቁጣን አብርዶ (ከመንገድ አውጥቶ) ወደ ሰላማዊ የውይይት መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችል ማንኛውንም ዘዴ (በሽማግሌና በተቃዋሚ ፓርቲ በኩል መማለድን ጭምር) እስከ መጠቀም ይሄዳል፡፡ ይህ ተራራ ሆኖ፣ ተራ የሕዝብ ቅዋሜና መንግሥት ‹‹ውጊያ›› የያዙ የሚመስል ነገር በአማራ ክልል ውስጥና በደቡብ ሕዝቦች (ኮንሶ) ውስጥ መፈጠሩ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ የኮንሶ ታሪካዊ ቤቶች በእሳት የጋዩበት ጥፋት መድረሱ፣ የደቡብ ሕዝቦች መስተዳደር ቃል አቀባይ ሆነው በአሜሪካ ድምፅ የሰማናቸው ሹም የኮንሶ ተወካይ ነን ያሉ ግለሰቦችን ‹‹ሽፍቶች›› ማለታቸው፣ ጎንደር ቅዳሜ ገበያ አራት መቶ ያህል ሱቆችን ከእሳት ላንቃ ለማዳን ያለመቻል ቅሌት፣ 23 ሰዎች አለቁበት የተባለው የቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ጭምር ተደማምረው ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት አገሪቷ አላት ወይ? የሚል ጥያቄን የሚያጭሩ፣ ኢሕአዴግ ብቻውን በመንግሥትነት ቀጥሎ የኢትዮጵያን ጣጣዎች በብልኃት ለመወጣት የሚያስችል የፖለቲካ አቅም እንደሌለው የሚናገሩ ናቸው፡፡ እንኳን መንግሥት ተራም ሰው እንኳ እሰው አገር ሲገባ የሚያስቀጣና የማያስቀጣውን ነገር የማወቅ ግዴታ ያለበት መሆኑ ፊደል እንደ መቁጠር መሠረታዊ ነገር ሆኖ  በሚታይበት በዛሬው ጊዜ፣ ኢንተርኔት ይህን ዓይነቱን የሀሁ ትምህርት ባቀለለበት በዚህ ዘመን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኤምባሲ ነባር ግንኙነት እያለ፣ ስንት ሕግ አዋቂ ኢትዮጵያዊ እያለ፣ በአሜሪካም ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ተወላጆች እያሉ፣ በአሜሪካ ምድር ውስጥ ሰተት ብሎ እንደ አንድ ሕገወጥ ነጋዴ የሚሊኒየም ግድብን ቦንድ ሲሸጡ የመያዝ ቅሌትን እዚህ ሁሉ ላይ ስናክለው ጭራሽ መንግሥትነት የልጅ ጨዋታ እስከ መምሰል መድረሱን እንረዳለን፡፡  የዛሬዋ ኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በእጅጉ አሳዛኙ ነገር ደግሞ ከዚህ ሁሉ ድክመት ያላቅቃል ተብሎ የታመነበት ሌላ የፖለቲካ ኃይል አገሪቱ ገና የሌላት መሆኑ ነው፡፡
 • የራሱንም የአገሪቱንም ዕጦቶች አጢኖ በሕዝብ ጉስቁልናና ምሬት ሥር ለመንበርከክ የፈቀደ እርማት ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ነው?

የሁለት ዓለምን ኑሮ የሚያቀልጡ አንድ የተረት ባህታዊ ነበሩ አሉ፡፡ አንድ ቀን ወደ ውድቅት ላይ ስካር ያሳስታቸውና ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ማስቀደስ ያምራቸዋል፡፡ ሄዱ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም አልዘለቁ፣ ግቢ ውስጥ አንድ ዛፍ ተደግፈው እንደቆሙ እግራቸው ይከዳቸውና ወደ መሬት ይወርዳሉ፡፡ መቀመጡም አልሆነላቸው ፍንግል ይላሉ፡፡ ነቅተው ልቦናቸውን ሲገዙ ዙሪያቸው ሁሉ ብርሃን ነው፡፡ የሰዎች ድምፅና እግር እንደ ልብ ነው፡፡ እንዴት እንደሆነ ሳይገባቸው በግራ እጃቸው ቡትሌ ጨብጠው በደረታቸው ተዘርረዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ቅሌት፣ ከዚያ ሁሉ የከንፈር መጠጣና ‹‹አበስኩ!…›› ባይነት፣ ከዚያ ሁሉ መዓት ዓይን እንደምን ይገላገሉ? ታምረኛ ናቸው፡፡ ተዓምር ሠሩ፡፡ ዓይናቸውን እንደጨፈኑና የካቲካላ ቡትሌያቸውን እንደጨበጡ ቀጥ ብለው ቆሙና እንደተጨፈኑ ስብከት ጀመሩ፣ ‹‹እውን እግዜርን ልትቀርቡ ንስሐ ልትገቡ መጣችሁ ማለት ነው? ይችን መጠጥ ከፈጣሪ የምታስበልጡ የላችሁም! አሁን በአሁኑስ ለሐሜት ያልቸኮላችሁ ማንኞቻችሁ ናችሁ?…›› ቀጠሉ፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት ማምላጫዬ ብሎ የተያየዘው ዓይን ጨፍኖ መስበክን ነው፡፡ የተዘረጋው ሥርዓት በሕዝብ ድምፅ ሥር ከማደር ይልቅ በሕዝብ ድምፅ ስም የሚነግድ የጥርነፋ አገዛዝ መሆኑ እርቃኑን የቀረ ሀቅ ሆኖ ሳለ ‹‹ሥልጣን የሰጠን ሕዝብ ነው/የመንግሥት አለቃ ሕዝብ ነው›› እያሉ ማለት በእውነታ ላይ ዓይን መጨፈን ነው፡፡ ሕዝብ የተንገሸገሸው በአጠቃላይ ዴሞክራሲ አልባ (ጉልበተኛ፣ አድሎኛና ተንኮለኛ) በሆነው አገዛዝ ሆኖ ሳለ፣ እዚያም እዚያም የተነሱ ማኅበረሰባዊና አካባቢ ገብ ጥያቄዎቸ የግዙፍ ምሬት እፊያዎች መሆናቸውን፣ እፊያዎቹ በተከፈቱ ጊዜ የተከሰተው ሹማምንት የመጠራረግና ባንዲራ የመቀየር ዝንባሌ እየተናገረ ሳለ፣ ችግሩን ‹‹ሥልጣንን የግል መጠቀሚያ የማድረግ›› የግለሰቦች ጉዳይ አድርጎ ማቅረብ ዓይንን መጨፈን ነው፡፡

ኢሕአዴግ እስከ ዛሬ ድርስ በመላ አገሪቱ ባለአንድ ክር (ባለአንድ ድምፅ) ክራር እንዲንቋቋ ሲለፋ የኖረ ሆኖ ሳለ፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ክራሩን ተቃርነው ወደ መንገድ የወጡ ብሶቶችንም በጥይትና በእስራት ሲያስተናገድ ይኸው እየታየ ሳለ፣ ነባር ታጋዮች በመንግሥት መገናኛ የሳሉልን ሥዕል፡-

በአንዳንድ አገር ለውጥ የተወሰነ ርቀት ሄዶ ይገተራል፣ የእኛ ግን ቀጣይ ነው፡፡ የእኛ ለውጥ መንግሥት ቢያሸልብ ሕዝብ ወጥሮ ሞግቶ እንዲባንን የማድረግ አቅም ያለው ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሕዝብ ወጣሪነት ሞጋች ኅብረተሰብ የመፍጠር ትግላችን ፍሬ ነው፡፡ … በደርግ ጊዜ የሁሉም ልዩነት መፍቻ ኃይል ነበር፡፡ እኛ ግን ልዩነቶችን በሰላም ማስተናገድ የሚያስችል መሠረታዊ ለውጥ አምጥተናል፡፡… የቡድንና የግል መብቶች የተከበሩበት፣ ሙሉ ነፃነት ያላቸው ፍርድ ቤቶችና አስተማማኝ ሰላም ያለበት ፌዴራላዊ ሥርዓት ገንብተናል፡፡ እነ አሜሪካ መቶ ዓመት የፈጀባቸው እኛ በአንዴ በተሟላ ሕገ መንግሥት አከናውነናል ባይነት ዓይን ከመጨፈንም ያለፈ ዳግመኛ ዓይን እንዳይከፈት አድርጎ ከማሸግ ጋር የሚተካከል ነው፡፡

ታሪካዊ ሕገ መንግሥትን ለሕዝብ በማቀዳጀት የሚመኩት ገዥዎቻችን መንግሥታዊ አውታራትን የፓርቲ ታማኝ በማድረግና በነፃ የአደባባይ ስብሰባና ሠልፍ የማካሄድ ነፃነትን በመሰነግ ዋናው ሕግ ጣሽ ራሳቸው ናቸው፡፡ ዋና ሕግ ጣሽና አፋኝ ሆነውም አፈናቸውን እምቢ ብሎ የገነፈለ ሕዝብን በሕገወጥነት ሲከሱና የረባ ሰላማዊ መፍትሔን ሳይሞክሩ በኃይል ‹‹ሕግ የማስከበር›› ዕርምጃን ሲያውጁ ኃፍረት በአጠገባቸው አላለፈም፡፡ ዴሞክራሲ ብሶተኛ ለመጮህ ዕድል የሚያገኝበት፣ ጩኸትም ጆሮ የሚያገኝበት፣ አልፎም በወከላቸው ሰዎች አማካይነት ከመንግሥት ጋር እስከ መደራደር አክብሮት የሚያገኝበት ሥርዓት ነው፡፡ በኢሕአዴግ ‹‹ዴሞክራሲ›› ውስጥ ያለው ከሕዝብ ጋር ‹‹መወያየት›› ባህርይው በተለይ ነው፡፡ ከተቃዋዊ ፓርቲዎች ጋር ኢሕአዴግ ቢወያይ አጫፋሪ ፍለጋ ወይም ተቃዋሚዎች ቢሳጡልኝ ብሎ ነው፡፡ በእኩል ደረጃ ከእነሱ ጋር (ማለትም ከኒዮ ሊበራልና ከፀረ ልማት ኃይሎች ጋር) መወያየት/መደራደር ማለት ክቡር ዓላማን  ከማጉደፍ ቁጥር ነው፡፡ ከገነፈለ ተቃውሞ ተወካዮች ጋር መወያየትም ያው ለብጥብጥ መልዕክተኞች መሸነፍ እንደማለት ነው፡፡ ኢሕአዴግና መንግሥቱ የሚወያየው ከ‹‹ሕዝብ›› ጋር ነው፡፡ ያ ደግሞ የመሪና የተመሪ ጉዳይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የሕዝብ ብርሃን ነው፡፡ ሕዝብ ሊሳሳት፣ ሊያጠፋና ጥቅሙ ሊጠፋው ይችላል፡፡ ኢሕአዴግ ያቃናዋል፣ አመለካከቱን እያጠራ ከጥፋት ይመልሰዋል፣ በትክክለኛ መንገድ ይመራዋል፡፡ ኢሕአዴግ ቢዘቅጥና ሕዝብ ጀርባውን ቢያዞርበት እንኳ ኢሕአዴግ በተሃድሶ ፀድቶ መሪነቱን መቀጠሉ ሕዝቡም መመራቱ ታሪካዊ ግዴታ ነው፡፡ ተቃውሞ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኢሕአዴግ ሰዎች ነዋሪዎችንና ወጣቶችን እየሰበሰቡ በቃላት ሲጠዘጥዙ መምራታቸው ነው፡፡ በገፍ ወጣት አስረው ‹‹ንቃት›› ሲሰጡ እንኳ መብት መንካታቸው/ሕግ መተላለፋቸው ሳይሆን የመሪነት ኃላፊነታቸውን ማሟላታቸው ነው፡፡ ዓባይ ፀሐዬ፣ በረከት ስምኦን፣ አባዱላ ገመዳና ካሱ ኢላላ በቃለ መጠየቅ ቅርፅ የቅብብል ዲስኩር በመንግሥት መገናኛ ባደረጉ ጊዜም፣ በየቤታችን ትምህርታዊ ሴሚናር እየሰጡን (አመለካከታችንን እያጠሩልን) ነበር፡፡ ይህን መሳዩ የኢሕአዴግ ‹‹መሪነት›› ገና ለሌላ 25 ዓመታት ያህል ሳያስፈልገን አይቀርም (ልማታዊ መስመር እስኪነግስ ድረስ)፡፡ የተለየ ነገር እስካላሳየን ድረስ ኢሕአዴግ የረዥም ጊዜ ገዥነት ጥበቤ ብሎ የያዘው ይህንን ያረጀ የዓይን ጭፈና ዘይቤን ነው፡፡ ‹‹ሁልጊዜ ተማሪ ነን›› የሚለውም እዚህ ዘይቤ ውስጥ ተዘግቶ እየኖረ ነው፡፡

የሕዝብ ትግል በኃይል እየደቆሱ ሕዝብ ሞጋች እንዲሆንና መንግሥትን ወጣሪ እንዲሆን ሠርተናል ብሎ ማለት ዓይን ጭፈና እንደሆነ ሁሉ፣ የሕዝብን እንቅስቃሴ ከውጭ ጠላቶችና አበጣባጮች ጋር ማያያዝም ያው ነው፡፡ ጠላቶቻችን ብር በጆንያ ዳያስፖራ ውስጥ ላሉ የአመፅና የብጥብጥ ኃይሎች ስለመስጠታቸውና የዚህ ዓይነት ብር ሰላም እያሳጣን ስለመሆኑ ማውራት፣ በሐርመኒ ሆቴል የተሰናዳ የዘፈን ድግስን በአዲስ ዓመት ዋዜማ በቲቪ ቀጥታ ሥርጭት ለቅቆ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ! እንኳን ደስ ያላችሁ!›› በማለት ብሶትንና ግርግርን ከመጋረድ ጋር አንድ ነው፡፡ ዓይን ጭፈና፡፡ ከሐርመኒ ሆቴሉ የቀረበልን የዘፈን ሥርጭት ከትዝብት በቀር ቅንጣት ያሰህል ለፖለቲካ ችግራችን መፍትሔ አዋጥቷል? ጠላቶቻችን አንድ ይቅርና መቶ ጆንያ ብር ቢሰጡስ፣ በአገራችን ውስጥ የተከተሰው ቁጣ መንስዔው ውስጣዊ መሆኑ በእውነት የታመነ ከሆነ፣ የሚበጀን ስለ ውጭ ጠላቶች ሴራ ማውራት ወይስ የውስጥ ችግሮችን ቆርጦ ጠላቶታችንን መንጠላጠያ ማሳጣት? ‹‹እናቶች የሚጠቀሙበትን አምቡላንስ ማቃጠል ምን ይባላል!›› እያሉ በስሜት ላይ የመጫወት ፕሮፓጋንዳ ውስጥ መቅለጥ ይፈይደናል? ወይስ የልማት ሥራዎቻችን ዳግመኛ የቁጣና የእልህ መወጫ እንዳይሆኑ አድርጎ የፖለቲካ ኑራችንን ማስተካከል? እነዚህ ጥያቄዎች በዓይን ጭፈና የመቀጠል ወይም ዓይንን የመክፈት ጥያቄዎች ናቸው፡፡

እዚህም ላይ የኢሕአዴግ መንግሥት ከጭፈና መውጣት አልሆነለትም፡፡ ብዙ ዓይነት ሕዝቦች ባሉበት አገር ውስጥ ሥልጣን የሚያንቅ ጠባብ ጥንቅር ያለው ቡድን ለማኅበረሳበዊ መገኛው የሚተርፍ ጣጣ ያስከትላል፡፡ በማኅበረሰባዊ ማንነታቸው የዋነኞቹ ገዥዎች ወገን የሚባሉ የሕዝብ ክፍሎች በገዥዎቹ ዓይን ለመታየትና ለመጠመድ ይጋለጣሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ገዥው ቡድን ለወገኖቹ በማድላት እንደሚጠረጠር ሁሉ ማኅበረሰባዊ ወገኖቹ በድፍኑ ለገዥው የሥልጣን መሣሪያ በመሆንና ብልጫ ጥቅም በማግኘት ጥርጣሬ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ በሌላው ከመጠመድና ከመጠርጠር ባሻገር፣ ወገኔ የሆነ ለጥቅሜ የቆመ መንግሥት በሚል አስተሳሰብ ራሳቸውም ለመታለል ፈተና ይጋለጣሉ፡፡

ይህ በኢትዮጵያም ታይቷል፡፡ ከሕወሓት/ኢሕአዴግ በፊት የነበረውና በአያሌው በአማሮች የተጣበበ ገዥነት በአማራ ተገዛን የሚል ቅሬታንና አማራ ጠልነት አፍርቷል፡፡ የአማራ ትምክህት የሚባለውም ከአማራ ገዥዎች የበላይነት ተሳስቦ የመጣ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከሞላ ጎደል ትግራዊ ሊባል የሚችል ሠራዊቱን የሥልጣን ኃይል አድርጎ አገር ሲቆጣጠርም ሌላ ነፍጠኛ ገዥ መጣብን የሚል ቅዋሜ ለመከሰት፣ ትግራዊንም በአዲስ መጡ ገዥ ዓይን የማየት ችግር ብቅ ለማለት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ይህንንም በማጠናከርና በማባዛት ረገድ የሚከተሉት ሰበዞች የራሳቸውን ድርሻ አዋጥተዋል፡፡ የኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት በብዙ የትግራይ ተወላጆች ዘንድ ሰፊ ድጋፍ ማግኘቱና የኢሕአዴግን የጀግንነት ዝናን ከአክሱም ታሪክ ኩራት ጋር አዛምዶ የፈተለ ትምክህት ለመቆነን መፍጠኑ፣ እንዲሁም ብሔረሰባዊ መጠቃቀም ከመብት ጋር መሳከሩና የቀድሞ መገፋትን ሒሳብ እንደ ማወራረድ መቆጠሩ ናቸው፡፡ በተቀረ የመንግሥት ሥልጣንን ተገን አድርጎ በመቦጥቦጥም ሆነ የመንግሥት ሹም ተመርኩዞ በንግዱ ዓለም ውስጥ ሀብት የማጋበሱን እሽቅድምድም የትኛውም ጎሰኝነት ሲያቀልጠው ቆይቷል፣ አሁንም እንደዚያው ነው፡፡

ዛሬ የኢሕአዴግ ገዥነትም ሆነ የአገሪቱ ሠራዊት ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር ያገኘ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ በአፍላ ሥልጣኑ ጊዜ ያገኘው ጅምላ ሊባል የሚችል የትግራዊ ድጋፍ ዛሬ የጎደለ ቢሆንም ከዛሬ 25 ዓመት አንስቶ የተተከለው የጠባብ ገዥነት መዘዝ ግን ገና በአግባቡ ተጠናቆ አልተወገደም፡፡ በትግራዊ ላይ የሚታይን ክፉ የጥላቻ አመለካከት የጥቂት ፀረ ሕዝቦች ጉዳይ አድርጎ ማቅረብ ሆድ ሲያቅ የችግሩን ጥልቀት ማድበስበስ ነው፡፡ በውጭም በውስጥም ለ25 ዓመት ሲበራከት የቆየና ፈጣን ማስተካከያ የሚሻ አደገኛ ሻካራ ስሜት በከተማም በገጠርም አለ፡፡ ለዚህም የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እያገለገለ ያለው የመከለከያ ሠራዊቱ፣ የደኅንነቱና የፌዴራል ፖሊስ ዕዝ በሕወሓታዊ ቁጥጥር ውስጥ ነው ሊያሰኝ የሚችል እውነታ ዛሬም ከ25 ዓመት በኋላ መኖሩ ነው፡፡ ትግራዊ የበላይ ገዥነት ለሚባል ፍረጃ መሠረት ሆኖ የቀጠለው ይኸው ከሕወሓት ተያይዞ የመጣ በመከላከያና በፀጥታ ኃይሉ ዘንድ ያለ (ከዚያም ዘሎ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በሚባል የኢንዱስትሪ አውታሮች ውስጥ የተሸጋገረ) መዳፍ ነው፡፡ በመንግሥታዊው ሲቪል ቢሮክራሲ ውስጥ ያሉ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ካድሬዎች የሕወሓት ካድሬዎችን ያህል በራስ መተማን የሌላቸው፣ አንዳንድ የሕወሓት ሰዎች ሲቆጡ ብርክርካቸው ሲወጣ ማየት ብርቅ ያልሆነው፣ ተራው ነዋሪም ለሕወሓት ሰዎች የበለጠ ዕልቅና የሚሰጣቸው ለዚህ ነው፡፡

ይህንን እውነታ ታቅፎ አንድ የትግራይ ክልል በሌሎች ክልሎች ላይ የበላይ ሆነ የተባለ ማስመስል ወይም ልማቱ ሁሉ በየክልሉ የሚካሄድ ነው፣ ሌላ ክልልን ሰበብ ማድረግ ቀርቶ እያንዳንዱ ክልል የየራሱን ብልሽት ያጥራ የሚል ዲስኩር ሆድ እያወቀ ከእኔ ጋር አይናችሁን ጨፍኑ ከማለት የማይሻል ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ሁልህም በየክልልህ ውስጥ ተወሰን (ታጠር) ፌዴራላዊ ቅንብር ላይ ያለውን ብልሽት አትይብን እንደማለትም ነው፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ገዥነት ያለው ትግራይ ውስጥ አይደለም፡፡ ትግራይ ውስጥ ያለው የሕወሓት አመራርም የትግራይ እንጂ የኢትዮጵያ ገዥ አለመሆኑ እውነት ነው፡፡ በየክልል አስተዳደሮች ውስጥ ያለ ሹም ጥፋትና ልማትም በሕወሓት ላይ ሊላከክ እንደማይችል፣ የእያንዳንዱ ክልል አመራር ለሥራው በቀጥታ ኃላፊና ተጠያቂ መሆን እንደሚገባውም መታወቅ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ክልልና የክልል ሕዝብ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለ ፌዴራላዊ ቅንብርን ነቅቶ መከታተል፣ ችግሮቹን መለየትና ማቃናት ኃላፊነቱ ነው፡፡ ምክንያቱም በፌዴራል ደረጃ ያለ ጉብጠትና መቅናት የክልሎችንም ሆነ በአጠቃላይ የአገሪቱን ሕዝቦች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት የመወሰን እምብርታዊ ድርሻ ስላለው፡፡ የዛሬው ‹‹ዴሞክራሲያችን›› መልክ ብቻ ሊሆን የቻለውም ገለልተኛ አውታራዊ ሥሮች ስለሌሉት፣ ኢሕአዴጋዊ ወገንተኛ ተፈጥሮ ባላቸው ወታደራዊና ሲቪል አውታራት ላይ የተለጠፈ የማያኝክ ድድ ነገር ስለሆነ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ያለው አገዛዝ በሙስናና በማናለብኝነት የጠነዛው፣ ሹሞች በሕዝብ ላይ ዘብናናና ደንፊ ሊሆኑ የቻሉት፣ የሕዝብን የድምፅ መተማመኛ እናጣለን፣ ተጋልጠን እንጠየቃለን የሚል ፍርኃት ሳያሰጋ ቅዋሜን በኃይል ለመደፍጠጥ የተደፈረውም ሥር ያለው ዴሞክራሲ ስለሌለ ነው፡፡ መንገሽገሽ የተዘረገፈበት ቅዋሜ ላይ ያደረሱንም ዋነኞቹ ችግሮች፣ ዛሬ የኢሕአዴግ ሰዎች ሲሉ እንደምንሰማው የወጣቱን የሥራ ፍላጎት በአግባቡ የሚሞላ የሥራ ዕድል አለመፈጠርና በአፈጻጸም ላይ የሚደርሱ ጥፋቶች አይደሉም፡፡ ዋነኛውና ለሌሎቹ አለቃ የሆነው ችግር ከላይ እንደተለገጸው ሥርዓታዊ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ዓምዶች በቡድን ወገናዊነት የታነፁ (ማለት ለአምባገነንት የተዘጋጁ) ስለሆኑና የአገሪቱ ሕዝቦች በአምስት ዓመት አንዴ ካርድ ሳጥን ውስጥ ከመክተት በቀር ድምፅ የለሽ (አጨብጭቦ አዳሪ እንዲሆኑ) መደረጋቸው ነው፡፡ ዛሬ ደጅ የወጣውም ሆነ ተደፍኖ የሚትከነከነው የሕዝብ ብሶት ሥራ በመፍጠር ብቻ የማይታጠብ ከዚያ አልፎ የዴሞክራሲያዊ አገዛዝን መቋቋም የሚጠይቅ ነው፡፡

ጥያቄው ዓይንን እየደነቆለ ሳለ፣ የመከላከያና የደኅንነት ጉዳይ ሲነሳ በዚህ ደረጃ ላይ የዳበረ የሙያ አመራር ከሥራ ውጪ ቢደረግ ትልቅ ጉዳት ወይም አደጋ ነው የሚል መከራከሪ ማንሳት ፋይዳ የለውም፡፡ መጀመሪያ ነገር፣ ከሰፋ ጥንቅር ውስጥ ብስል አመራርንና ሙያተኛነትን ፈትኖ ለማውጣት የ25 ዓመት ጊዜ ትንሽ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ነገር፣ የዕዝ ሰንሰለት የማስተካከል ሥራ የግድ የሙያተኛ ቅነሳን ወይም ከሥራ ማራቅን አይጠይቅም፡፡ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) እና ሌሎች ቁልፍ ቦታዎች ሲነሱ፣ ጥያቄው ከሕዝብ ጥቅም አኳያ የሚመጣ ሳይሆን ከኪራይ ሰብሰቢ ፍላጎት (እኔም ተራ ይድረሰኝና ልቦጥቡጥ ከማለት) የመጣ ነው የሚል ክርክር መደቀን፣ ከማደናገሪያነትና ጥያቄን ከማምለጫነት በቀር ችግር ለማስወገድ ምን ይጠቅማል? ከየአቅጣጫው አንድ መዓት የምጥመጣ ቅናትና ረሃብ ይላወሳልና ይህንን እያነሱ መከራከር ምን ይጠበስ ነው? የዚህ ዓይነቱ መከራከሪያ በነበረው መቀጠልን ተገቢና ትክክል ያደርገዋል? ዋናው ጥያቄ እኮ የሕዝብ ሀብት ከየትኛውም ዓይነት ዘረፋ እንዲጠበቅ የሕዝብ ዓይንና ጠያቂነት ውስጥ ይውደቅ፣ ታየሁ አልታየሁ እያለ ተሸማቃቂ ሕዝብ ሳይሆን ሹም ከነምንዝሩ የሆነበት ሥርዓት ይምጣ ነው፡፡

ከዚህ ጥያቄ አኳያ ኢሕአዴግ ‹‹ዴሞክራሲን ማጥለቅ›› የሚላት ነገር ምንድን ነች ፍቺዋ? የኢሕአዴግ ሰዎችን ‹‹ተሃድሶ የማጥለቅ›› ሕዝብ የማገልገል ቃል ኪዳንን የማደስ ጉዳይ ከሆነ፣ ይህ ከሌላው ይበልጥ በሕዝብ ተመራጭና ተከባሪ ለመሆንም ሆነ አሁን የተነሳውን ቁጣ ለማብረድ ብለው የሚያደርጉት ፓርቲዊ ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ እናም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የኢሕአዴግ ተሃድሶ ማለት አይደለምና የዴሞክራሲ ግንባታ ጥያቄ እንዳፈጠጠ ይቆያል፡፡ ኢሕአዴግ በዚያችው የራሱ ተሃድሶ ውስጥ ራሱን በመደበቅ ውስጥ ተወስኖ የሚቀር ከሆነ የሕዝብን ምሬትና ጩኸት ሁሉ ትቢያ የቀላቀለ መርዶ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ቤት ውስጥ የዴሞክራሲ እናት ላትነሳ ሞታለችም ማለት ነው፡፡ የሕዝብንና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተሳትፎና አመኔታ በቆነጠጠ መልክ ዴሞክራሲ የሚሻቸውን የአውታራት ገለልተኝነት የማነፅ ሒደት ውስጥ ለመግባት ኢሕአዴግ የተግባር ቁርጠኝነት ካሳየ ደግሞ ድላችን ብዙ ነውና ነጭ በነጭ እንለብስለታለን፡፡

ለትግራይ ሕዝብ የተረፈ የጥላቻ ስሜት የሚነቀለው በዚህ ሒደት ውስጥ ነው፡፡ ይህ ብቻውን አንድ ድል ነው፡፡ ኢሕአዴግ ኖረም ሄደ ከፓርቲ ፍላጎትና መሃላ ውጪ የሆነ በተጠያቂናትና በሥነ ምግባር የሚገዛ የሕዝብ አገልጋይነት የሚረጋገጠው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን ላይ በወጣ ቡድን ሳይጠለፍ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር በየጊዜው እየተነጋገረ የመሻሻል ተግባራዊ ሕይወት ሊያገኝ የሚችለው፣ በሕዝብ እውነተኛ ውዴታ ላይ ጥንካሬውን የመሠረተ መንግሥት የሚዋጣልንም ይህ ሒደት ሲሳካ ነው፡፡ የአደባባይ ስብስባና ሠልፍ ጥያቄ ሲመጣ መንግሥት ‹‹የቀለም አብዮት›› መጣብኝ እያለ የማይርድበት፣ እንዲያውም እልህን በንብረት ላይ ያለመወጣት ጨዋነትንና ሕግን አክብሮ ድምፅ የማሰማት ምግባርን በማለማመድ ረገድ የሰላማዊ ሠልፍ ጠቃሚነት ወለል የሚልበት ቀን የሚመጣው፣ ኢንቨስተሮችም በቅዋሜ ከመጠቃት ሥጋት የተላቀቀ ሜዳ የሚያገኙት ያኔ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከጭፈናና ከጉልበተኛነት መለስ ብሎ በዚህ ጎዳና ውስጥ ይገባ ይሆን?

አሁን የምናየውና እንዲህ ተደረገ እየተባለ የምንሰማው ነገር ተስፋ ከመስጠት ይልቅ የሚያስደነግጥ ነው፡፡ በኃይል ዕርምጃው ውስጥ እየደረሰ ያለው ጥፋት (ግድያና የእሳት ቃጠሎ) በሕዝብ ድምፅ ሥር ከሚያድር ገዥነት ጋር የሚጋጭና የገዥውን ፓርቲ የሕዝብ ተቀባይነት እንዳልነበር አድርጎ የሚጎዳ ከመሆኑ ሌላ፣ ቁጣን ጭራሽ እያባባሰ አገሪቱን መመላሻ የሌለው ቀውስ ውስጥ እንዳይከትታት እያስፈራ ነው፡፡

 • ኢሕአዴግ የራሱ የፖለቲካ ተሰሚነትና የአገሪቱ መጪ ዕጣ የሚያሳስበው ከሆነ ሊያመጣ ያሰባቸውን ለውጦች በግልጽ አሳውቆ እዚህም እዚያም የተነሳውን ቁጣ ከኃይል ይልቅ በሰላማዊ መንገድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተጋግዞ ለማብረድ መንቀሳቀስ አለበት፡፡
 • ተቃዋሚ ፓርቲዎችም (በቅርብ የተጣመሩት ሆኑ እነ መድረክ)፣ የኃይል መንገድ አገሪቱን መመለሻ የሌለው ምስቅልቅል ውስጥ ሊዘፍቅ የሚችል መሆኑን ካመኑበት መግለጫ ከመስጠት ባለፈ መንፈራገጥና ጉባዔ እንኳ አዘጋጅቶ ድምፅን ማጉላት ትንሹ ኃላፊነታቸው ነው፡፡
 • የተወካዮች ምክር ቤት አባላትም እውነት የሕዝብ ተወካይነት የሚሰማቸው ከሆነ፣ አስፈጻሚውን አካል የመመርመርና የመጠየቅ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን የሚሠሩበት ከሆነ በአፈ ጉባዔው በኩልም ሆነ በአባላት ጥያቄ ዕረፍታቸውን አቋርጠው መሰብሰብና እየሆነ ያለውን ከሰብዓዊ መብቶችና ከአገሪቱ ሕልውና አኳያ መገምገምና ትዕዛዝ መስጠት አልነበረባቸውም? ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንስ ‹‹ቀብረው ሲመለሱ እግዜር ይማርዎ›› ከማለት የተሻለ ድምፅና ሚና የለውም?
 • ተቃውሞ ውስጥ ያሉም ሆኑ ቅሬታ ያላቸው የሕዝብ ክፍሎች ሊሞክሩት የሚገባ ሌላም ሰላማዊ ቀዳዳ አለ፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ሕዝቦች የመረጧቸውን የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እምነት ባጡባቸው ጊዜ መልሶ የመጥራትና የመቀየር መብት አላቸው፡፡ ይኸው መብት በየክልል ሕገ መንግሥቶችም ውስጥ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህንን መብት በተግባር መፈተሽ አገራችን ውስጥ ለዴሞክራሲ ምን ያህ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ እንዳለ ለማጤንም ያስችላል፡፡
 • የኅብረተሰቡ ፍላጎቶች በአንድ ፓርቲ ሊወከሉ እንደማይችሉ፣ ፓርላማው ልዩ ልዩ ፍላጎችን ማንፀባረቅ እንደሚያሻው እነ አባይ ፀሐዬ የነገሩንን ከልብ የሚያምኑበት ከሆነም አመኔታ ያጣን ተወካይ በመሳብ መንገድ ፓርላማውና የክልል ምክር ቤቶች ከወዲሁ ሕይወት ሊያገኙ፣ የፖለቲካ ሜዳችንም ትርጉም ያለው ዴሞክራሲያዊ መሻሻል ሊያሳይ ይችላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...