Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢሕአዴግን በማደስ አገርን ማዳን ወይስ…?

ኢሕአዴግን በማደስ አገርን ማዳን ወይስ…?

ቀን:

   በገመቹ ዘለዓለም

ከ2008 ዓ.ም. ማጠቃለያ ቀናት አንስቶ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ በመላው አገሪቱ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ››፣ ስብሰባና ግምገማ ተቀጣጥሏል፡፡ ከአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል (የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ) አንስቶ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራር፣ መምህራንና የትምህርት ዘርፍ አመራሮች፣ ወላጆችና የተማሪ ተወካዮች በስብሰባ ተወጥረዋል፡፡ ሲቪል ሰርቪሱም ቢሆን በመስከረም መጨረሻ የሚካሄደውን የመንግሥት ማዋቅር ማሻሻያ ከመጠበቅ ባለፈ በውስጥ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ላይ መጠመድ መጀመሩ በስፋት እየተወራ ነው፡፡

ግን ይህ ሁሉ ከፍተኛ የአገር ሀብት ወጥቶ ድካሙ ሁሉ ፍሬ የሚያፈራ ካልሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በተመጣበት መንገድ ለማሻሻል መሞከር የሚቻል አይሆንም፡፡ በተለይ አሁን በሁሉም መድረኮች በድፍረት እየተነሱ ካሉ መሠረታዊ ጭብጦች አንፃር፣ የራሱ የድርጅቱ አባላትና አመራሮች ጭምር በድፍረት አደባባይ ያወጡትን ችግር ወደ ጎን ማለት ከወድቀት አያድንም፡፡

ከዚህ አንፃር በዚህ ጸሐፊ እምነት እንደ ሕዝብና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኢሕአዴግን ጥልቅ ተሃድሶ በዝምታ ልናልፈው አንችልም፡፡ አቅማችን በፈቀደው መጠንም አገሪቱን ከቀውስ፣ ሕዝቧንም ከችግር የሚያወጣ ፖለቲካዊ ሥነ ምኅዳር ለመፍጠር የየድርሻችን መወጣትም ይኖርብናል፡፡

ግን ሁላችንም የየድርሻችን የምንወጣው ‹‹ኢሕአዴግን በማደስ አገርን ማደስ? ወይስ ኢሕአዴግን በማፍረስ አገርን ማንገራገጭ? አልያም ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ መፍትሔ በማፈላለግ የጋራ መፍትሔ ማምጣት?›› የሚለውን ማጤን ተገቢና አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር ለውይይት የሚረዱ ነጥቦችን በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ መድረኮች ከሚነሱባት ገጽታ አንፃር ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

ሙስናና ጥገኝነትን እንደምን መግታት ይቻላል?

ራሱ ገዢው ፓርቲ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት እንደገለጸው በሥርዓቱ ውስጥ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሚባለው አስተሳሰብ በተለይ በከተሞች እየጎመራ መጥቷል፡፡ ለዚህ ያልሠሩበትን የማጋበስ አስተሳሰብና ተግባራዊው መነሻ ደግሞ ሥልጣንና የ‹‹ሕዝብ አደራ›› እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ኢሕአዴግ በአገሪቱ ለማስፈን የሚፈልገው ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› የተባለው የምሥራቅ እስያ ተሞክሮ እንደመሆኑ መንግሥት ዋነኛው የማኅበረ-ኢኮኖሚው ተዋናይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህም በየትኛውም የመንግሥት እርከን ላይ የተቀመጠ ኃላፊም ሆነ ባለሙያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቅ በሚባል የአገር ሀብት ላይ የማዘዝና የመወሰን ዕድል አለው፡፡ ደርግ አገሪቱ እንዳትሆን አድርጎ ትቶ ሲሸሽ በመንግሥት ካዝና ውስጥ የተገኘው ከ33 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ገንዘብ ነበር፡፡ አሁን ግን ለአንድ ሜጋ ፕሮጀክት (ታላቁ የህዳሴ ግድብን መውሰድ ይቻላል) እስከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር መበጀት የቻለች አገር ተገንብታለች፡፡

ይህ ነገር ታዲያ ባለሥልጣናትና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሙያዎች በቢሊዮን ብር የሚገመት ተጫራጮችና የውጭ ኩባንያዎችን እንዲደራደሩ ይላካሉ፡፡ በከፍተኛ ሀብት የመንግሥት ግዢም ሆነ ሽያጭ ይፈጸማል (በተለይ የኮንትራት ግዢ ከሚገመተው በላይ ነው)፡፡ የጉምሩክና የግብር ሥርዓቱ፣ መሬትን ዋነኛ የሀብት ማዕከል ያደረገው ኃይል የሚራኮትበት ሁኔታ ሁሉ ለሙስናና ለብልሹ አሠራር ተጋልጦ ቆይቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወይም በፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቀምጦ ሳይፈርም በስልክ ትዕዛዝ ብቻ ሀብት ሲያካብት የከረመው ኃይል ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለ የሕዝብ መሬት ተቀራምቶ፣ ሕንፃና ዘመናዊ ቪላ እስከ መገንባትና የንግድ ድርጅት እስከ ማቋቋም የደረሰው፤ ከዚያም አልፎ የውጭ አገር ባንኮች ውስጥ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያስቀመጠው የመንግሥትና የኢሕአዴግ ሰው ቁጥሩ ትንሽ እንዳልሆነ እየተደመጠ ይገኛል፡፡

አሁን በተለያዩ መድረኮች ተሳታፊዎች እየተነሳ እንዳለው ‹‹ሌባ›› ከየትኛውም ብሔር ቢመጣ የመጣበትን ሕዝብ ሊወክል አይችልም፡፡ በግላዊ ፍላጎት የሕዝብ መስብን ገልብጦ የበላ ቀማኛ እንጂ፡፡ ይሁንና ስንቶች መስዋዕት ሆነውበታል የሚባለውን ኢሕአዴግ መከታ አድርገው የዘረፉ፣ ያዘረፉና ያቀባበሉም መጠየቅ እንዳለባቸው ጥርጥር የለውም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ቅሬታ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ዝንባሌዎች በግልጽ ታይተዋል፡፡ በተለይ ከመከላከያ፣ ከደኅንነትና ከቢሮክራሲው የወጣ አብዛኛው ጥገኛ በተለያዩ ክልሎች፣ ውስጥ በመግባት በላቡ ከመሥራትም ባለፈ የአቋራጭ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ በተለይ በምዕራብ ኢትዮጵያ ‹‹በእርሻ ሥራ›› ስም ተሰማርቶ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚሊዮኖች ብር ብድር ተመቻችቶለታል፡፡

በዚህም አገርን ለልማት (በተለይ በማካናይዝድ እርሻ) አሳድጎ ወደ ልማታዊነት ከመቀየር ይልቅ በጥገኝነት የተገኘን የሕዝብ ሀብት ሕንፃ ሠርቶ ለማከራየት፣ የግንባታ ማሽነሪ ከታክስ ነፃ አስገብቶ ኪራይ ለመሰብሰቢያ መሣሪያ ማድረግ የለየለት ሌብነትና ጥገኝነት ነው፡፡ ያለጥርጥርም ዘረፋ ነው፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ላይ በርካታ ባለሀብቶች (በዘኢኮኖሚስት መጽሔት ሚሊየነሮች እየጎረፉባት ያለች አገር ተብለናል) ተፈጥረዋል፡፡ ይሁንና እነዚሁ ወገኖች ሕንፃም ይሥሩ የንግድ ኩባንያ በምን መንገድ ተለወጡ የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ምንም እንኳን የሚሸማቀቁበትና የሚደናገጡበት ሁኔታ ይፈጠር ባይባልም፣ በተለይ በሥልጣን ላይ ከነበረው ጥገኛ ኃይል ጋር ተጣብቀው የሕዝብ ሀብት ዘርፈው የከበሩ ካሉ ሊጋለጡና ሊገቱ የግድ ይላል፡፡ በመሠረቱ ከአንዳንድ ባለሀብቶች ስም ጀርባ ሕዝብ የሚያነሳቸው ሕንፃዎችና ኩባንያዎች ወይም የንግድ ድርጅቶች ጉዳይም ተፍረጥርጦ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

በድምር ‹‹የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን›› የሚባለው ልግመኛ መሥሪያ ቤት የባለሥልጣናትንና የተመራጮችን ሀብት መዝግቦ ተኝቶበታል፡፡ ቢያንስ አሁን ግን በእንዲህ ዓይነቱ የተሃድሶና የጥልቅ መሻሻል ለሚባልላት ጊዜ መረጃው ሊያግዝ ይገባል፡፡ በተጨባጭም ሥርዓቱ ሙስናን የሚፀየፍና ሕዝባዊ መሆኑን ሊያረጋግጥ የሚችለው፣ ይኼ አገርና ሕዝብ ያወቀውን ወቅታዊ ፈተና አብዮታዊ በሆነ ዕርምጃ መሻገርና ከሕዝብ ጋር መተማመንን ሲፈጥር ብቻ ነው፡፡

መንግሥታዊ ቸል ባይነትና የፈጠረው የቅንጦት ገደል

ይኼ መንግሥት መታደስና እውነተኛ መሻሻል ማድረግ ካለበት በዋናነት፣ በገዢው ፓርቲና በመንግሥት መዋቅሩ ውስጥ ያለው ስንፍና፣ ሕዝባዊነት ማጣትና የጥቅም መካፈል አደጋ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ እንደተናገሩት፣ የመንግሥትን ሥልጣን የግል ጥቅም ማካበቻና ምቾት ማረጋገጫ ያደረጉ ብዙዎቹ ሹመኞች፣ በተለይ ብሔርንና የውሸትም ቢሆን የድርጅቱ አባልነትን ተጠቅመው ተገልግለውበታል፡፡

እነዚህን አባባሎች በማሳያ ለማብራራት ለምሳሌ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች ጉዳይ ወዳልሆነ ፉክክር የተገባባቸውና ጥቅም ማስከበሪያ ሆነዋል፡፡ ትናንት በሚኒስትሮች፣ በሚኒስትር ዴኤታዎች፣ በአማካሪዎች፣ በኮሚሽነሮች፣ ወዘተ እጅ ያየናቸው  (እስከ ስምንት ሚሊዮን ብር ያወጣሉ) ዛሬ በአዲስ አበባ የክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ እጅ ደርሰዋል፡፡ ዘመናዊ ላንድክሩዘርና ዘመናዊና ራዶ ተሽከርካሪን ያልያዘ የመንግሥት ባለሥልጣንም ፈጽሞ ማግኘት አይቻልም፡፡

እንግዲህ አስቡት ገና የሕዝቡ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ600 ዶላር በታች በሆነባት አገር፣ 22 ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት በታችና ከዚህ ውስጥ 17 ሚሊዮን ሥራ አጥ ለተሸከመ አገር ይኼ ምን ማለት ነው!? ሌላው ይቅር ልመናው፣ ሴተኛ አዳሪነቱ፣ ስደቱ፣ ድርቁና ችግሩ አልቆጠቁጣችሁ ያለን ለምንድነው!? መባል አለበት፡፡ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች ያለው የተሽከርካሪ የቅንጦት አጠቃቀም የሚያስገርም ነው፡፡ አንዳንዱ የካቢኔ አባልም ካለልምምድ ላሽከርክር እያለ በሚሊዮን የሚገመት ሀብት ዶጋ አመድ ሲያደርግ ማየት ተራ ነገር ሆኗል፡፡ ይኼ ሁሉ እንዝህላልነት ገደብና ጣሪያ ሊበጅለት ግድ ይላል፡፡ ቢያንስ የደርግን ያህል እንኳን ደረጃ ማውጣትና ሕዝባዊ ተቆርቋሪነትንም ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ እነ ህንድ፣ ቻይናና ኮሪያን የመሳሰሉ አገሮች ደግሞ ለመንግሥት ኃላፊዎቻቸው ከአገር ውስጥ ምርት ውጪ እንዲጠቀሙ አያስደርጉም፡፡

የእኛ አገር አስፈሪ የባለሥልጣናት ባህሪ ደግሞ ከወረዳ አመራር ጀምሮ ተሽከርካሪውን በጥቁር ስቲከር እየሸፈነ ከሕዝብ ተደብቆ መውጣትና መግባቱ ነው፡፡ ሚኒስትሩና ሥራ አስፈጻሚው እሺ ‹‹ለደኅንነቴ›› ይበል እንዲያው የክፍለ ከተማ ካቢኔና ስሙ እንኳን በአግባቡ የማይታወቅ የጽሕፈት ቤት ኃላፊን ማን እንዳይነካው ይሆን!? ነው ሕዝብን ሽሽት? አገልጋይነትን መግፋት? ወይም ራስን ከፍ ከፍ ለማድረግ? በነገራችን ላይ ባለሥልጣናቱ የሚጠቀሙበት በር፣ የቢሮ ዕቃዎችና የቅንጦት ዕቃዎች ሁሉ የተገልጋይነት ፊውዳል ባህሪ የፈጠረው የቢሮ ትምክህተኝነት መሆኑ ሊመረመር ግድ ይለዋል፡፡

አሁን የሕዝቡ ቁጣ ጣሪያ ነክቶ ኢሕአዴግን እንደ ሥርዓት ከዳር ዳር መቃወም ሲጀምር ‹‹መንግሥታዊ ሥልጣንን ለኑሮ ማመቻቻና ለመጠቃቀሚያ ያደረጉ ኃይሎች አሉ›› እያለ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆኑት የአዲስ አበቤዎቹ አስተዳዳሪዎች ኔትወርክ ነው፡፡ ብዙዎቹ በኔትወርኩ አማካይነት በቤተሰብ ጭምር ተሳስረዋል፡፡ አንዳንዱ የአስተዳደሩም ሆነ የድርጅቱ ተሿሚ በተለያየ መንገድ የያዘውን ሁለትና ሦስት የመንግሥት ቤት በሕገወጥ መንገድ ጨብጦ ኪራይ እየለቀመበት ነው፡፡

በብልጣ ብልጥ ሙያተኞች (አንዳንድ አመራሮች) የተመቻቸን የውጭ ጉዞ ያለምንም ዓላማ መመላለሻ ያደረጉ ‹‹ተሿሚዎች›› ጥቅማቸው እየጎለበተ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የዓላማ ሰዎችና የሕዝብ ጥቅምን ያስቀደሙ ጀግኖች የሞሉበት እንዳልነበረ፣ እየተሞዳሞደ የአገር ሀብት የሚከፋፈል በእጅጉ እየከበበው መጥቷል፡፡ እንግዲህ ይቺ የተፈጠረችውን የተሃድሶ የመጨረሻ ዕድል የሚታዩ ግልጽ ዝርክርክነቶችን ለማረም መጠቀም ግድ ይለዋል መባሉም ለዚሁ ነው፡፡

አገር እያስጨነቀ ያለ ጠባብነት

ኢሕአዴግና መንግሥት በአገሪቱ ጠባብነት አለ ሲል የማይነጥለው ትምክህትም ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ዝንባሌዎች በሌሎች አገሮችም ያሉና የነበሩ ናቸው፡፡ በኢትዮጽያ ሁኔታም ምንም እንኳን ለዘመናት የዘለቁ ቢሆኑም፣ ከፌዴራል ሥርዓቱ መጀመር ጋር ተያይዘው ብቅ ጥልቅ እያሉ መምጣታቸው አይካድም፡፡

በእኔ እምነት አሁን የአገሪቱን አየር የሞላው ግን በዚያም ሆነ በዚህ እየተቀጣጠለ ያለው ጠባብነት (Narrow Nationalism) እና መንደርተኝነት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲስ አንዳንዶች በአገራቸው ጉዳይ ለመጠቀምና ለመሳተፍ ከመሻት ይልቅ ‹‹ምንነቴ›› በሚሉት ብሔር ቋንቋና ሠፈር ዙሪያ መኮልኮል ይዘዋል፡፡ ለዘመናት አብሯቸው የኖረውን የተጋቡትንና የተወለዱትን የሌላ ብሔር ሳይቀር እንደ ባዕድና የሩቅ ሰው መቁጠሩንም ገፍተውበታል፡፡ (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእገሌን ቤት ማፍረስ፣ እነእገሌ ይውጡልን ምን ያህል እየበረታ እንደመጣ መገንዘብ አያዳግትም፡፡)

ለዚህ ጠባብነትም ቢሆን ዋነኛ ተጠያቂዎቹ የገዢው ፓርቲ መሪዎች መሆናቸው ግን ግልጽ ነው፡፡ ገና ከመነሻው ከፌዴራልም ሥርዓት ባህሪ ልዩነትን እንጂ አንድም የጋራ እሴትን ማስገንዘብ አልተቻለም፡፡ ትውልዱ በራሱ ቋንቋ መማሩና መዳኘቱ ጥሩ ሆኖ ስለሌለው ቋንቋና ማንነት ያለው አረዳድ የተዛባ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ (ኦሮሚያ ክልል አማርኛን ‹‹የገዢ መደብ›› ቋንቋ አስመስሎ በእነዚያ ኋላቀርነት የተሞላበት ቅስቀሳ አማርኛ ችሎ የሚናገር ወጣት ጠፍቷል፡፡ ይህም የክልሉ ምሩቃን በፌዴራል መንግሥቱ የመቀጠር ዕድላቸውን ጎድቶታል፡፡)

ኢትዮጵያውያን ለጋራ ሰንደቃቸውና ኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ያላቸው ክብርና ፍቅርም የተደበላለቀ ነው፡፡ ምንም እንኳን ለ25 ዓመታት ‹‹አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ተገንብቷል›› ሲባል ቢከርምም በአንዲት ቃል ወይም ኅትመት ስህተት ጥቅሜ ተነካ ብሎ ድብልቅልቅ የሚያወጣ ትውልድ መጥቷል፡፡ ከ40 ሺሕ ሔክታር በማትበልጠው የግጮውና አካባቢው ይዞታ መዘዝ ለዘመናት የኖሩት የጎንደርና የምዕራብ ትግራይ ነዋሪዎችን ቅያሜና ቅሬታ ውስጥ ከትቷል፡፡ በክልሎቹ አስተዳዳሪዎች ማናለብኝነትና ችግር የመፍታት ድክመት የልዩነት ደውሉ ከልክ በላይ ጮኾ ተደምጧል፡፡

ኢትዮጵያውያን አገራችን ከድህነት ወጣች፣ ዜጎች ሀብት እያፈሩ ነው ሳይሆን የሚያስጨንቃቸው ‹‹እነእገሌ በለፀጉ›› የሚለው ጉዳይ ሆኗል፡፡ የአንድ አገር ዜጎች ተባብረውና ተሳስበው ሌባውን እየነጠሉ እንዳይመቱ የሚያደርግ መደበቂያ የብሔር ባርኔጣ ውስጥ እየተበጀ ነው፡፡ እንኳን የአክሲዮን ማኅበር ይቅርና ዕድርና ሠፈር በብሔር የሚደራጅበት አገር መፈጠሩ ባለፉት 25 ዓመታት ጠባብነት ይበልጥ እንዲባባስ በር ከፍቷል፡፡ ይህን መጥፎ በሽታ ደግሞ መንግሥትና መዋቅሩ አለመከላከላቸው አደጋውን ይበልጥ አስፈሪ ያደርገዋል፡፡

አብዮታዊነት የራቀው ኢሕአዴግ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በትጥቅ ትግል የቀድሞውን አምባገነን ሥርዓት አሸንፎ በአገሪቱ አዲስ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሥርዓት የዘረጋ ነው፡፡ በዚህም ሥር ነቀል ለውጥ የማምጣት ባህሪ እንዳለው ይታመናል፡፡ ይሁንና ድርጅቱ በአንድ በኩል እስካሁን ድረስ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ መሆን አልቻለም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ከጊዜ ወደጊዜ ደግሞ የአራቱ አባል ፓርቲዎቹ አብዮታዊነት ሲዳከምና ሲሸረሸር ታይቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ለተፈጠሩት ቀውሶች እየተነገሩ ያሉ ምክንያቶችን ለሚመረምር በአብዛኛው ከጋራ መርህ ውጪ መንቀሳቀስ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ አንዱ ጋ ሙስና ሲበረታታ፣ ሌላው ዘንድ ጠባብነት ወይም ትምክህት ይጎላል፡፡ በውስጥ መደማመጥና መከባበር የለም፡፡ የእኩልነት መንፈስ እየተዳከመ ከመሄዱም ባሻገር፣ የአንዱ ድርጅት አባል የሌላውን የሚያበጠለጥል ኃይል እየሆኑ ነው፡፡

የአብዮታዊነት አንዱ መገለጫ ሕዝባዊነት ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ገዢው ፓርቲ ፈጥኖ ካላስተካከለው ከሕዝቡ የተነጠለባቸው የተለያዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በአንዳንዱ አካባቢ የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ በሌላው የዴሞክራሲ መሸራረፍ፣ ወይም ሥራ አጥነትና ድህነት ቅር የሚያሰኛቸው ዜጎች ቁጥር ትንሽ አይደሉም፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በጣም በርካታ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ እነዚህ ሳንካዎች ደግሞ ድርጅቱ ይቅርታ ጠይቆ ወደ ሕዝቡ እንዲወርድ ያስገድዱታል፡፡

ወደ ሕዝቡ ለመውረድ መሠረታዊው ጉዳይ ደግሞ የተሿሚዎች ቀለም መቀየር ወይም ወንበር ማዟዟር ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሌባና ሕገወጡን በሕግ መቅጣትና የሕዝብ ሀብት ማስመለስ፣ በፖለቲካ መዘዝ የታሰረን መልቀቅ፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ማስፋት ብሎም ወደተጠናከረ የልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባር መግባት ይኖርበታል፡፡

በአጠቃላይ ኢሕአዴግን በማሻሻልና በማደስ የአገሪቱን ጉዞ አጠናክሮ ማስቀጠል ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ የብዙኃኑ የአገሪቱ ሕዝብ ፍላጎትም ቢሆን ከዚህ የተለየ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም ከሰላማዊና ከዴሞክራሲያዊ መንገድ ውጪ በኃይል የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት መሞከር አገርን የሚበታትን ነው፡፡ በተለይ አሁን የአገሪቱ ሕዝቦች ላይ ባንዣበበው ጠባብነትና የመለያየት ስሜት ውስጥ አገርን ለመገነጣጠልም ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ የመጨረሻው የማስጠንቀቂያ ደወል ተሰጥቶትም ቢሆን ኢሕአዴግ በጥልቀት እንዲታደስ ዕድል እንስጠው፡፡ የአቅማችንንም እንተባበረው ለማለት እወዳለሁ፡፡ ይህ ሲሆን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መከባበርና ለሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን መፍትሔ ለማምጣት መንገዱን መጥረግ ይቻላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...