Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በቁም ከማለቅ ይሰውራችሁ!

 ሰላም! ሰላም! ይኼውላችሁ የአሮጌው ዓመት በጀትና የአጠቃቀም መርሐ ግብሩ መጠናቀቁን አስመልክተን እኔና ማንጠግቦሽ አዲሱን ዓመት እንዴት እንደምንዘልቀው መመካከር ጀመርን። ማንጠግቦሽ ታዲያ እንደ ሰይጣን ንፋስ ብድግ ብላ፣ ‹‹የለም ምክክሩ ወደ ክርክር መድረክ መቀየር አለበት። ካልተፋጨን በሐሳብ ካልተዳቆስን ምኑን ዴሞክራሲያዊ ሆነው?›› ብላ ክችች አለች። ‹‹ምክክራችን ሳያልቅ ክርከሩ ለምን አስፈለገ?›› ብዬ ስጠይቅ እኔ ራሴ የጠየቀችውን መድረክ መፍቀዴን አላወቅኩትም ነበር። አንድ ስል አንድ ስትል፣ አንድ ስል አንድ ስትል ዶናልድ ትራምፕና ሒላሪ ክሊንተንን ሆነን አረፍነው። ይኼ ከሆነማ ብዬ የባሻዬን ልጅ ግራ ቀኝ አድምጦ ነጥብ እንዲሰጥ ለዳኝነት ጠራሁት። ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመንና ቆስጣ ለወር ይሸመቱ ለሳምንት? ሽንኩርትና ቅመማ ቅመም በስድስት ወር ይሸመቱ? ወይስ ዕለት ተዕለት? ስንባባል እግዜር ይስጠው በትዕግሥት ሲያዳምጠን ዋለ። በኋላ ውጤቱን አሳውቅ ስንለው፣ ‹‹ከትዝብቴ ስጀምር ነጥብ በነጥብ የመከራከር ክህሎታችሁ አርክቶኛል፤›› አለ።

አበጀህ ስንለው፣ ‹‹እንደ ትራምፕና ሒላሪ ክሊንተን ክርክር ስሜት ስለመቆጣጠርና ስላለመቆጣጠር የሚወራበት ሳይሆን፣ ስላነሳችኋቸው ዓበይት ዓበይት ጉዳዮች የተሻለ ዕቅድ ስታብራሩ በመስማቴ ውጤት ተኮር ክርክር አድርጋችኋል፤›› ሲለን ግን ሁለታችንም ስሜታችንን መቆጣጠር አልቻልንም። ማንጠግቦሽ እልልታዋ እንደ ባህር ዕጣን ሽቅብ ወደ አርያም ወጣ። እኔ ዝላይ ጀመርኩ። የባሻዬ ልጅ ያበድን መስሎት የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቶ ሲዋልል ቡፌው ጠርዝ ላይ የተቀመጠ የማንጠግቦሽ የልጅነት የፎቶግራፍ ፍሬም ጥሎ መስታውቱን አነከተው። መስታወቱ ሲነክት እኛ ጋብ ስንል አንድ ሆነ። ‹‹ምነው?›› ቢለን፣ ‹‹ምን ምነው?›› አልነው፡፡ ‹ያሰብኩት ተሳካ ያለምኩት ደረሰ› አለ ጥላሁን ገሠሠ። ይኼ ታይቶት እኮ ነው አልነው። ‹ምኑ?›› አይለን መሰላችሁ? ደግሞ እኛም ወጉ ደርሶን ለአሜሪካ የምርጫ ክርክር አርዓያ መሆናችን ነዋ። ቂቂቂ!

‹ሃይማኖት ታረደ ደሙን ውሻ ላሰው፣ መቼም ልብ ለልብ አልተገናኘም ሰው› ያለው ማን እንደነበር ዛሬ ተዘነጋኝ። ለምን አመጣኸው ብትሉኝ ግን በዚህ በቴክኖሎጂ የፈጠነ ዘመን ሰው በዚህም በዚያም ምናባዊ ገጽ ተፈላልጎ አልጠፋፋ እንደማለቱ፣ ልብ ለልብ አለመገናኘቱ ስለሚያስገርመኝ ነው። ልብ ለልብ ለመገናኘት ኤኮ ለነገሩ መጀመርያ ዓይን ለዓይን መተያየት ያስፈልጋል። ‹ወግ በዓይን ይገባል› አይደል እንዴ የሚባለው? መቼም እኔ ደላላነት ሙያዬ ባይሆን ወይም በሆነ ተዓምር በዚህ ዘመን ድጋሚ ተፈጥሬ ቢሆን ምን እንደማደርግ ታውቃላችሁ? ‹ወግ በዓይን ይገባል› ከሚለው አባባል ተነስቼ አንድ ልዩ ‹አፕሊኬሽን› ሳልፈለስፍ እንቅልፍ ባይኔ አይዞርልኝ ነበር። ይኼን ብለው የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ስካይፒ ስለማታውቅ ነው፤›› አለኝ። ‹‹ምነው እናንተ የምታውቁት ታዲያ አልተዋወቅ አላችሁ? ምነው ልብ ለልብ አልነጋገር አላችሁ?›› ስለው ፀጥ አለ።

አዎ። በበበኩሌ ገና አይበቃም ባይ ነኝ። የተፈለሰፉት እነዚህ ዘመናዊ መግባቢያዎች አላረካኝ ብለዋል። አታዩም እንዴ የተረፈንን? ባይሆን እንደ ድሮው እንደ ጥንቱ ሰው ተናግሮ እስኪጨርስ የማናዳምጥ አደረጉን እኮ። ኧረ ‹ትራምፒዝም› አስቸገረን እናንተ? እውነቴን ነው እኮ። ‹ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ› በቃ የዛገና ጊዜው ያለፈበት ነገር ሆኖ እንዲያው እንዳመጣለት የሚለጥፍና የሚወረውር መንገዱን ሞላው። ‹‹ምን እዚህ ብቻ አንበርብር? ሠለጠንን ያሉትን አርዓያችሁ ነን ቅብጥርሶ የሚሉንን አሜሪካኖችን አታይም እንዴ? ክርክር፣ ውይይት፣ ኤክስፐርት፣ ሳይንቲስት ጠፍቶባቸው በመሰዳደብና በመዘረጣጥ ጊዜ እያጠፉ ታሪክ ሲደግሙ፤›› ይሉኛል ባሻዬ ሲያገኙኝ። እኔም ሳላቋርጣቸው እስኪጨርሱ አዳምጣቸዋለሁ። ዓለም በቆርቆሮ የታጠረች ይመስል ስንጯጯህ አብዳ አሳበደችን ጎበዝ!

ዛሬ ለጨዋታችን ድምቀት ሰውዬው ደመቅ ያሉ ሰለሆኑ አነሳናቸው እንጂ (ዶናልድ ትራምፕን ማለቴ ነው)፣ ዋናውን ጉዳይ ትቶ ስለአሰስ ገሰሱ ማውራት፣ ከመረጃና ሳይንሳዊ ድምዳሜ ርቆ በስሜት የመቀባጠር አባዜ ዘንድሮ በየሄዳችሁበት  ነው። በቀድም አንድ ቪላ ቤት ከአንድ ደላላ ወዳጄ ጋር ለሁለት ልናሻሽጥ ደንበኛችንን ይዘን እንሄድላችኋለን። መጀመርያውንም ቤቱን ፈልጎ ያገኘው ወዳጄ ነውና ቀደም ቀደም አላልኩም። ግቢው ተከፍቶልን ከገባንባት ደቂቃ አንስቶ ወዳጄ አንዲህ ይላል። ‹‹ይኼ ቤት ገዳም ነው። ባለቤቶቹ ውጭ ናቸው። አሜሪካ ምን የመሰሉ ሦስት ቤቶች አሉዋቸው። አንዲት ሴት ልጅም አለቻቸው። ልማቱና ዕድገቱ አጓጉቷቸው አገራቸው ናፈቃቸውና ሊኖሩ ቢመጡ ልጅቷ ልታስኖራቸው መሰለህ? አይታሃት የለም እንዴ አንበርብር? ምን ዝም ትላለህ? ተናገር እንጂ?›› ይለኛል።

‹‹ምንድነው የምታወራው ለምን ስለቤቱ ይዞታ አታብራራም?›› ብዬ ሹክ ብለው እንዳልሰማ ሆኖ ወደ ደንበኛችን ዞሮ፣ ‹‹የዘንድሮን ልጅ ታውቀዋለህ መቼም። መውለድ አያስፈልግም እኮ የዘመኑን ልጆች ለማወቅ። ኧረ ኧረ ኧረ! እሳት ናት ብታያት። እሳት! በቃ ከወዳጅ ዘመድ አላገናኛቸው አለች። ሐሺሽ ነው። ጫት ነው። ሲጋራ ነው። ሌሊቱ እስኪነጋ ነይ አብረን እናውጋ ሆነና ‹ላይፏ› በመጡበት እግራቸው ይዘዋት ተመለሱ፤›› ሲለው ደንበኛችን፣ ‹‹ታዲያ ይኼ ነው ጉዱ?›› አለው። ‹‹የለም። መች ጨረስኩ? እነሱ እንደሄዱ የሆነ ሰው ተከራየው። በተከራየው በዓመቱ ምን የመሰለች ልጅ አገባ። አቤት ውበት። በዚያ ላይ የራሷ ምርጥ መኪና ያላት። በዓመቱ ወለዱ። ይኼው የራሳቸው ቤት ሠርተው ለቀቁት። ለዚህ  ነው ባለቤቶቹ ለመሸጥ የወሰኑት፤›› ሲል እኔ ምኑን ከምን እንደሚያገናኘው አልገባኝ ብሎ አቀርቅሬ አዳምጣለሁ። ‹ቢገጥም ባይገጥም› ነዋ ዘመኑ። ዋናው ጮክ ብሎ መድረኩን በድፍረት መቆጣጠር ሆኗል። ይኼ ነው ዘመኑ!

እናላችሁ ባልተጨበጠና ምንም በማይገናኝ ነገር እየፈተልን የምንለብሰው የሕይወት ሸማ በዝቶ ይኼው የምንጠራው ስብሰባ በዝቷል። በምን ቀን ይሆን ካንተ ጋር የገጠምኩት እያልኩ በልቤ ያን ደላላ ወዳጄን ዓይኑን ላለማየት ስሸሽ ሳለሁ ባሻዬ ደወሉ። ‹‹አቤት?›› ስል ‹‹ና ወዲህ›› ተባልኩ። ስደርስ በወቅታዊ ጉዳዮችና የአገራችን ሁኔታ ላይ ነዋሪው ራሱ በራሱ አነሳሽነት የጠራው ስብሰባ ይዘውኝ ሄዱ። በአገር የመጣ ነውና ማፈግፈግ የለም። እንኳን ሐሳብ ለማዋጣት ሕይወት ለመገበር ይዘመት የለም ወይ? አገር እኮ! ታዲያስ! ስብሰባው እንደተጀመረ ምን ልበላችሁ? እንደ ‹ኤልክላሲኮ› ሆነ። በእግር ኳሳችን ለማየት ባያድለንም በነገር ሜዳችን ላይ እውነቴን ነው የምላችሁ ብዙ ሜሲዎችና ሮናልዶዎች እያሠለፍን ነው።

አንዱ ማይኩን ተቀብሎ እንዲህ አለ። ‹‹ደግሞ ለመናገር ቱ! ወደ ተግባር ቀይረው አትበሉኝ  እንጂ መናገሩንማ ግጥም አድርጌ ነው የምናገረው፤›› ሲል ‹ቅኔ እኮ ነው! ቅኔ እኮ ነው› እየተባባለ ነዋሪው ያጨበጭባል። ‹‹ባሻዬ ዕውን ቅኔ ነው?›› ስላቸው ዘወር ብዬ፣ ‹‹ኧረ ተወኝ እባክህ ለራሴ ዞሮብኛል፤›› ይሉኛል። ተናጋሪው ቀጠለ፣ ‹‹መንግሥት እንደ መንግሥት፣ ሕዝብ እንደ ሕዝብ (ባሻዬ ወይ የዘንድሮ አማርኛ እያሉ ጉዴ ይላሉ) ሊሠራ የሚገባው አንድ ነገር አለ። ሁላችንም ተባብረን፣ ተቻችለን፣ ተመከካክረን፣ አንተ ትብስ አንቺ ተባብለን መኖር አለብን። ስሙኝ ብቻ። አለበለዚያ ግን ነገ ምን አለ ትሉኛለችሁ። አለበለዚያ ግን ይኼ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ አካሄዳችን የሚያዛልቀንም የሚያወላዳንም አይደለም፤›› ሲል ሌላ ጭብጨባ። እኔም አንድ የምሳሌ መጽሐፍ ልጻፍና ‹ከአዳራሹ ጣራ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም› ብሏል አንብርብር የሚባልበት ቀን ይመጣ ይሆን? ነው ወይስ ተቀድሜያለሁ?

በሉ እንሰነባበት። ስብሰባው እንዳለቀ ሁሉም ደመራውን ሊለኩስ ይሯሯጥ ጀመር። ‹‹ይኼ በዓመት በዓመት ሳይነጋገሩ ተቀጣጥሮ እሳት የመለኮስ ባህል በየት በየት አድርጎ ሃይማኖታዊ እንደሆነ አላውቅም፤›› ብሎ አንዱ ችቦው እንደተለኮ መተቸት። ሕፃናትና አዋቂዎች ሳይቀሩ እየተቀባበሉ የስድብ ናዳ አወረዱበት። ይኼኔ ባሻዬ ተቆጡ፣ ያላወቀን እንደማስረዳት በመስቀሉ ጌታ፣ በተሸከመው መስቀል ስም፣ ከመስቀሉ በወጣው የፍቅር ሕግ ስም ተሰባስባችሁ እንዴት ለስድብና ለቁጣ ታድማላችሁ?›› ብለው እሪ አሉ። ቢዚያ በኩል እሳቱ ይንቦገቦጋል። በዚህ በኩል ባሻዬ ራሳቸው ይንቦገቦጋሉ። ልጃቸው፣ ‹‹ቆይ ረጋ በል እስኪ፤›› እያለ ያቆራርጣቸዋል። ‹‹እንዴት ረጋ እላለሁ? የጠየቀ ሲሰደብ፣ ሲገደል፣ ሲታደምበት፣ ሲገለልና ሲወገዝ እያየሁ እንዴት ረጋ እላለሁ? ነገራችሁ ሁሉ ያለ ዕውቀት መሆኑ ሳያንስ በጥላቻና በስድብ ጽንፍና ጽንፍ የሚከናዳው እስከ መቼ ነው? ንገረኝ በል እስኪ?›› አሁን ሲሉት የባሻዬ ልጅ ወደኋላ አፈገፈገ። ባሻዬ ሰሞኑን ብሶባቸዋል። የግለሰብ የአስተሳሰብ፣ የአቋምና የእምነት ነፃነት በየመንደሩና በየጓዳው ባይጨፈለቅ ውሎ አድሮ የአገር  ሸክምና ራስ ምታት አይሆንም ባይ ናቸው። እኛም እንስማማለን። ፍቅር የልዩነታችን ሁሉ ማሰሪያ ሲሆን ትርፉ ብዙ ነው። አለበለዚያ ግን ‹እንደ አንድ እናስብ፣ እንደ አንድ እንልበስ፣ እንደ አንድ እንጉረስ› የሚሉት ነገር ያደበላልቀናል እንጂ አያዋጣንም። ዘንድሮ የለኮስነው ደመራ ወዴትም አልወደቀም። ነዶ ነዶ በቁሙ አልቋል። እኛም ወደየፊናችን፣ ወደየቤታችን ተበታትነናል። በቁም ከማለቅ ይሰውራችሁ! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት