Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክሚኒስትሮችን የመሾሚያ መሥፈርቶች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት

ሚኒስትሮችን የመሾሚያ መሥፈርቶች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት

ቀን:

   በውብሸት ሙላት

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች የተነሱትን ተቃውሞና ዓመጾችን ተከትሎ፣ በመፍትሔ መልክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የካቢኔ (የሚኒስትሮች) ሹም ሽር እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ ቀደምት የኢሕአዴግ ታጋዮችና ባለሥልጣናት የሆኑት አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ በረከት ስምኦን፣ ዶ/ር ካሱ ኢላላና አቶ አባ ዱላ ገመዳ፣ በኢትዮጵያ ብሮድካቲንግ ኮርፖሬሽን ቀርበው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት በሰጡበት ወቅትም፣ ፓርላማው ሥራውን ሲጀምር የተለያዩ ማስተካከያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ በረከት የሚኒስትርነት ዋና መሥፈርቱ ብቃት እንደሚሆን ሲገልጹ፣ ዶ/ር ካሱ በበኩላቸው የብሔር ተዋጽኦም ከግምት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ፣ የሚኒስትር መሾሚያ መሥፈርቶች ምን ምን እንደሆኑ ሕገ መንግሥቱን፣ አተገባበሩን፣ ንድፈ ሐሳቦችንና የሌላ አገሮችን ልምድ ዋቢ በማድረግ ምጥን ትንተና ማቅረብ ነው፡፡ በተለይም የብቃትንና የብሔር ውክልና ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡

መንደርደሪያ

በንጉሠ ነገሥት፣ በፕሬዚዳንት ወይንም በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን በማቋቋም መንግሥታዊ ተግባራትን ማከናወን ከጀመርን፣ እንደ አገር መቶ ዓመት አልፎናል፡፡ ቀጣይነት ያለው የታወቀ አሠራርን አለመከተል፣  መርሆችን አለማዳበር፣ ከምክር ቤቶቹ ሰብሳቢ ጋር ያላቸው ግንኙነት ግልጽ አለመሆን፣ የሚኒስተርነት መመልመያና መለማመጃ ሥርዓት አለመኖርና የመሳሰሉት ጉድለቶች ሚኒስትሮቻችንና ምክር ቤቱንም የተጣለባቸው ብሎም መሻገር ያልቻልናቸው ችግሮች ናቸው ማለት እንችላለን፡፡

የብዙ ነገሩ ማጠንጠኛ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ አወቃቀር ከመሠረትን ሩብ ምዕት ዓመት ሞላን፤ የሽግግር ዘመኑ ሲጨመር፡፡ ፌዴራላዊ አወቃቀር፣ ራስ ገዝነታቸውን መጠበቅ የሚፈልጉ ክፍሎች በጋራ በማዕከላዊው መንግሥት መሳተፍ በሚያስችል መልኩ አገርን የማቋቋምና የማስተዳደር ጥበብን የሚከተል አሠራር ነው፡፡ ማዕከላዊውን መንግሥት የሚዋቀረው ደግሞ በፌዴሬሽኑ መሥራቾች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደ ሌሎች ፌዴራላዊ አገሮች መሥራቾቹ ክልሎች ሳይሆኑ፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡ ሁሉም አካላት የየራሳቸው ክልል ስለሌላቸው ነው የልዩነቱ መነሻ፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፌዴራላዊ አስተዳደር ሥርዓት ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደራቸው ባለፈ የጋራ በሆነው፣ በኅብረት በመሠረቱት ፌዴሬሽን ውስጥም የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡ የጋራ የሆኑትን ተቋማት በጋራ ይመራሉ፤ በጋራ ያስተዳድራሉ፡፡ በመሆኑም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39(3) መሠረት እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፌዴራሉ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የመወከልና የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ካሉት ተቋማት ውስጥ የፌዴሬሽን፣ የሕዝብ ተወካዮችና የሚኒስትሮች ምክር ቤቶች፣ የዳኝነት ተቋሙ እንዲሁም ሌሎችም  ይገኙበታል፡፡

    

ሚኒስትሮችንም ይሁኑ ሌሎች ተሿሚዎች፣ ውክልናቸው በቀጥታ በሕዝቡ ባይሆንም ውክልና ግን አላቸው፡፡ በፌዴራል መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት አጽዳቂነት ስለሚፈጸም በተዘዋዋሪ ወኪሎች ሆኑ ማለት ነው፡፡ ብሔሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናትን መምረጥ ባይችሉም፣ በተለያዩ የሹመት እርከኖች ላይ ፍትሐዊ በሆነ ስልት ተወክለው ማየትን ግን ይፈልጋሉ፡፡ በተለይም ለፌዴራሉ መንግሥት ተለይተው የተሰጡት ሥልጣኖች ለሁሉም የጋራ ስለሆኑ ሁሉም የራሱ ወኪል እንዲኖረው ይፈልጋል፤ መፈለጉም ትክክል ነው፡፡

በቀደሙ ሥርዓቶች ተገልለናል፣ ተገፍተናል፣ ከኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ በረከቶች ተቋዳሽ አልሆንም የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች (ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሊሆኑ ይችላሉ) በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ውክልናን አጥብቀው እንደሚፈልጓት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ቀዳሚው ምክንያት ውክልና የመመካከሪያ፣ የመሳተፊያና የልምድ መለዋወጫ መድረክ ስለሆነ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከዕለታዊና ከዋናው የፖለቲካ ተዋጽኦና ውይይት ውጭ የሆኑ ቡድኖች በእንደነዚህ ዓይነት ተቋማት ካልተሳተፉ በስተቀር መቼም ሰሚ አይኖራቸውም፡፡ በመሆኑም ከመገለልና ጭራሹንም ከመረሳት የሚድኑበት ሥርዓት ነው፡፡ ሦስተኛው ቅቡልነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ወኪሎች የተለየ ሙያና ልምድ ሊኖራቸው ስለሚችል እሱን በመጠቀም ከቡድናቸው ባለፈ ለብዙኃኑ መጥቀሙን ሲረዱ፣ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች አዎንታዊ አመለካከትን ያዳብራሉ፤ የወከለው ክፍልም ተሰሚነት እንደፈጠረ ስለሚያምን ሥርዓቱን የመቀበል አዝማሚያውን ይጨምራል፡፡

ካቢኔያዊ ሥልጣን መጋራትና ውክልና

የሥልጣን መጋራት ከውክልናም ያልፋል፡፡ መጋራት ወሳኝና ቁልፍ የፖለቲካ ቦታዎችን መካፈል፣ አብሮ መወሰንንም ይጨምራል፡፡ በመሆኑም የሥልጣን መጋራቱ የሚፈጸምባቸው ተቋማትና የሥልጣን ቦታዎች፣ የተለያዩ አመለካከት፣ ጥቅምና ፍላጎት ያላቸውን አካላት ወይንም ቡድኖች አካታችነቱና የሚከፋፈሏቸው ወይንም የሚጋሯቸው ሥልጣኖች በእውነትና የምር ሥልጣኖች መሆናቸው ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ የመጨረሻዋ ነጥብ አጨቃጫቂ ናት፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ አንድን ብሔር የፕሬዚዳንትነቱ ቦታ፣ ለሌላው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቢሰጠው በእውነት የሥልጣን መጋራት ተካሂዷል ማለት ያስቸግራል፡፡ በርካታ ብሔሮች ወይንም የተለያዩ ፍላጎቶችንና ጥቅሞችን የሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገኙባቸው አገሮች የተለያዩ ሥልቶችን በመጠቀም ከፍተኛ የሹመት ቦታዎችን አካታችና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ፡፡ የእኛ ሕገ መንግሥት ስለ ሚኒስትሮች የመመልመያ መሥፈርት ምን እንደሚል እንመልከት፡፡

ስለ ሚኒስትሮች የሹመት፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ ሐሰሳ ብናደርግ ሁለት መሥፈርቶችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው፣ አንቀጽ 74(2) ላይ የተቀመጠው ‹‹ብቃት›› ነው፡፡ ሁለተኛው በቀጥታ ሚኒስትርነትን የሚመለከት ባይሆንም እንኳን፣ አንቀጽ 39(3) የተገለጸው የብሔሮች በፌዴራል ተቋማት ‹‹በሚዛናዊነት የመወከል መብት›› የሚለው ነው፡፡ ምናልባት በሦስተኛነት የሴቶች ፖለቲካዊ ውክልናን ሊጨመር ይችላል፡፡

ብቃት

ሚኒስትሮች በተናጠልም ይሁን በጋራ በርካታ ኃላፊነትና ግዴታዎች አሉባቸው፡፡ በዋናነት ሕግ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መጠበቅ፣ ፓርላማው የሚያወጣቸውን ሕጎች ሥራ ላይ ማዋል፣ ረቂቅ ሕጎች ማዘጋጀት፣ ፖሊሲዎች መንደፍ፣ ደንብና መመሪያ ማውጣት፣ የእያንዳንዱን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መምራትና በዚያ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማማከርና ሌሎች በርካታ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እነዚህን ተግባራት ለመወጣት አቅምና ብቃት ያላቸው የሕዝብ ተወካዮች ወይንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የሆኑ፣ ወይንም ደግሞ ሌላ ማንኛውንም ሰው ሚኒስቴር ሊሆን ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የምልመላ መሥፈርታቸው በዋናነት ይሄው መሆን አለበት ማለት ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ላይ ቢቀመጥም ባይቀመጥም ከላይ የገለጽናቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በትምህርትና በልምድ የታገዘ አቅምና ብቃት መኖር ግድ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ልማታዊ መንግሥትን እንደ ፖሊሲ የሚከተል አገር ብቃት ያለው ሚኒስቴር መኖር መለያ ባሕርይው ነው፡፡ የግሉን ዘርፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን እንቅስቃሴም ጭምር የልማት ተሳትፎና አቅጣጫቸውን ያስቀምጣል፡፡ መንግሥት ብዙውን ነገር ስለሚመራና ስለሚደግፍ፣ እያንዳንዱ ሚኒስትር በበርካታ ገንዘብ ላይ ውሳኔ ስለሚሰጥ፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ተግዳሮት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ብቃትና አቅም የሌለው ሚኒስትር ራሱ ሙስና ውስጥ ባይገባ እንኳን ሥርዓት መዘርጋት ስለማይችል፣ ሕግና ፖሊሲን የመገንዘብና ተንትኖ መተግበር ስለሚያዳግተው፣ አዳዲስ ሐሳብና ቴክኖሎጂ ማመንጨት ስለሚሳነው ሚኒስትራዊ ሥራውን በአግባቡ መወጣት አይችልም ማለት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንካራና አቅም ያለው ከሆነ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምቹ ስለሚሆን የሶፋ መንግሥት (Sofa Government) ይሆናል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ሲባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ይሆናል፡፡  ይህ ደግሞ ለአገር የሚጠቅም አይደለም፡፡

ሚዛናዊ ውክልና

ኢትየጵያም ሌሎች ባለብዙ ብሔር አገሮች ከፍተኛውን የፖለቲካ ሥልጣን መጋራትን በተመለከተ ከሚቸገሩት የተለየች አይደለችም፡፡ አገሮች የራሳቸውን ቀመር ወስነዋል፡፡ በየጊዜውም ይለዋወጡታል፡፡ የማንንም አገር ቀጥታ በመገልበጥ ለሌላው ማልበስ አይቻልም፡፡ አንዱ ከሌላው ድክመትና ጥንካሬ በመማር ልምድ ሊቀስምበት ግን ይችላል፡፡ የስዊዘርላንድ ከህንድ አይገጥምም፤ የቤልጂየም፣ የካናዳና የስፔን የየቅል ናቸው፡፡ የናይጄሪያ ከደቡብ አፍሪካ ፈጽሞ ይለያል፡፡ በእርግጥ የሚያመሳስላቸውም የተወሰኑ ሥርዓቶችና ተቋማት ያላቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡

ኢትዮጵያ የፖለቲካው ቁንጮ ላይ የሚቀመጡትንና የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑትን ሰዎች የብሔር ዳራቸውን ስናይ መቼም ቢሆን ሁሉን አካታችና አሳታፊ ሆኖ ታይቶ አይታወቅም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተወሰኑ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም የዳግማዊ ሚኒሊክ፣ የአጼ ኃይለ ሥላሴ፣ የደርግ፣ አሁንም በዘመነ ኢሕአዴግ፣ የብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦችን ተወካዮች ከማካተትና ሥልጣንን ከማጋራት አንፃር አሁን የተሻለ ቢሆንም በርካታ ጉድለቶች አሉበት፡፡ ከሽግግር ዘመኑ ብንነሳ ርዕሰ ብሔሩ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩና ጸሐፊው ከአንድ ብሔር እንዳይሆኑ በሽግግር ቻርተሩ ተከልክሏል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም የብሔር ተዋጽኦን ከግምት ማስገባት እንዳለበት የሕግ መሠረት ነበረው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ በኋላ ግን እንደዚህ ዓይነት ሕግ ጠፋ፤ የሕጋዊ መሠረቱ እየተጠናከረ መሔድ ሲገባው ከሕግ ይልቅ በተግባር በፓርቲ ደረጃ እንዲወሰን ሆነ፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ  (የሕወሓት፣ የብአዴን፣ የኦሕዴድና የደሕዴን ጥምርና በአምስቱ ክልሎች ያሉ አጋር ፓርቲዎችን ይዞ) ካለፉት አራት ምርጫዎች እንደታዘብነው ከአራቱ ፓርቲዎች ከሚውጣጡ ሚኒስቴሮች ሌሎች ቁልፍ ቦታዎችን ይደለድላል፡፡ ከዚያ የተወሰኑ (የተለመዱት ሁለት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች) ከሶማሊያና ከአፋር ፓርቲዎች ለሚወከሉ ይሰጣሉ፡፡ ላይ ላዩን ስናየው በፓርቲው አወቃቀር መሠረት አራቱ ክልሎች እንጂ ቀሪዎቹ አምስቱ በኢሕአዴግ አይመሩም፡፡ ነገር ግን ከምርጫ በፊት በሚደረግ ወይንም በተደረገ ስምምነት አጋር ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር በጥምረት አገሪቱን እየመሩ ነው፡፡ ስለዚህ አምስቱ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር በሚያደርጉት ስምምነት መሠረት ብቻ በፌዴራሉ ካቢኔና ሌሎች ቁልፍ የሥልጣን ማማዎችን ይይዛሉ፤ እንደ መብት ለመጠየቅ አንሶኛል ወይንም ሌላው በዝቶበታል ለማለት ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በጥቅል እንደ መርሕ ከተቀመጠው ውጭ በአዋጅ የተደነገገ አሠራርና የድልድል ቀመር የለም፡፡

በእርግጥ የሕገ መንግሥቱና የፓርቲው አሠራር ተቃርኖ ያለውም ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፌዴራል ተቋማት ውስጥ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ይወከላሉ ሲል የፓርቲው አተገባበር ግን የትግራይ (ሕወሓት)፣ የአማራ (በእርግጥ አገው ኻምራዎች በተወሰነ መልኩ እየተሳተፉ ቢሆንም)፣ የኦሮሞና የደቡብ (56 ብሔረሰቦች) በጥቅሉ የሚወከሉበት ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ዓላማና ግብ ግን የአገሪቱ መሥራቾች፣ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች ከዚህ የሥልጣን በረከት ሁሉንም ተቋዳሽ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ መርሕ ነው፡፡ የፓርቲያዊም ይሁን ሌሎች አሠራሮች ደግሞ ይህንን ለማሳካት የሚደረጉ መሆን አለባቸው፡፡

የችግሩ እምብርት ያለው እንዴት ሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሚኒስትርና በሌሎች የካቢኔና ቁልፍ የሥልጣን እርከኖች ላይ ይሳተፉ? የሚለው ነው፡፡ ከሰማንያ በላይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሉም፡፡ ሚኒስትርነትም ቢሆን ብቃት፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ታማኝነትን ስለሚጠይቅ እነዚህን አቻችሎ ሁሉም በፍትሐዊነት እንዴት ይወከሉ የሚለውን መመለስና ተቋማዊ መሠረት ማስያዝ ነው፡፡ ጉዳዩን የበለጠ ለመረዳት በርካታ ብሔረሰቦች የሚገኙባቸው አገሮች ሥልጣን እንዴት መከፋፈል እንዳለበት የሚያሳዩትንና ታዋቂ የሆኑትን የሁለት ምሁራኖችን ንድፈ ሐሳቦች አቀርባለሁ፡፡

ሊፕሃርትና ሆሮዊዝ ስለ ካቢኔያዊ የሥልጣን መጋራት

ከሦስት ደርዘን በላይ የሚሆኑ አገሮችን የዴሞክራሲ ሒደት ያጠናው ኔዘርላንዳዊው ምሁር አረንድ ሊፕሃርት (Arend Lijphart) ኮንሶሻሽናል ዴሞክራሲ በማለት የሚጠራውን የሥልጣን መጋራት ዘዬ አራት አላባውያን ሲኖሩት አንደኛው ጥምር መንግሥት ምሥረታ (ካቢኔያዊ ሥልጣን መጋራት) ነው፡፡ የንድፈ ሐሳቡ እሳቤዎች የተረጋጋ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባትና እኩልነትን ማስፈን ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ መነሻ ግምቱ ደግሞ እነዚህ የሚመጡትና የሚሰፍኑት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በሚወክሉ ልሂቃኖች መካከል በሚደረግ ትብብርና መግባባት ነው የሚል ነው፡፡ እንደ ሊፕሃርት አመለካከት የካቢኔያዊ ሥልጣን መጋራት የተለያዩ ብሔሮችን የሚወክሉ ፓርቲዎች ሥልጣን የሚጋሩበት ዘዴ ነው፡፡ ካቢኔው ተፅዕኖ ያላቸውን የተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍና ማኅበራዊ መሠረት ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ማካተት አለበት ይለናል፡፡ የተለያዩ ፓርቲዎች ባይኖሩም እንኳን ብሔሮች ወጥ የሆነ የሥልጣን መከፋፈያ ሥልት እንዲኖር ይመክራል፡፡

በአንፃሩ አሜሪካዊው ምሁር ዶናልድ ሆሮዊዝ ከላይ የቀረበውን የሥልጣን መጋሪያ ሥልትን በማጣጣልና በማንኳሰስ አዋሃጃዊና አካታች የሆነ ሥልትን እንጂ ይበልጥ ከፋፋይ አካሄድን ይቃወማል፡፡ ከብሔር ይልቅ ዜጎችንና መልክዓ ምድራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሲመሠረቱ የተለያዩ ብሔሮችን በማቀፍ መሆን አለበት እንጂ አንዱ የራሱን፣ ሌላውም እንዲሁ የራሱን እየመሠረቱ ክፍፍሉን ማስፋት የለባቸውም፡፡ ድርድርና የጥምር መንግሥትም ሆነ ቅንጅታዊ አሠራር ከምርጫ በኋላ ነው መከናወን ያለበት፡፡ ሆሮዊዝ ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝምን አይመክርም፤ መልክዓ ምድራዊን እንጂ ግትርና ደረቅ የሆነ ቀድሞ በሕግ የታሰረ አሠራርን ይቃወማል፡፡ እነ ደቡብ አፍሪካና ማሌዥያን ሲመክርም ይህንኑ ነው ያቀረበው፤ የተገበሩትም እንደዚሁ፡፡ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሠራረት፣ የካቢኔያዊ አወቃቀርና የመሳሰሉት ሁሉም ብሔሮችን በአንድ አድርጎ ያቀፈ፣ አንድነትን የሚያሳልጡ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ በአንዳንድ አገሮች ብሔርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ፈጽሞ አይፈቀድም፤ ተቋቁመው ቢገኙም ይፈርሳሉ፡፡ ምክንያቱም በታኝና አገር አፍራሽ ተደርገው ስለሚታዩ ነው፡፡ 

ሊፕሃርት በብሔርና በሌሎች ምክንያቶች ክፍፍል ለሚስተዋልበት አገር ፓርላሜንታዊ መንግሥት ቀዳሚ ምርጫው ሲሆን፣ ፕሬዚዳንታዊ ከሆነ ደግሞ ፕሬዚዳንቶቹ ከየብሔሮቹ ሊፈራረቁ ይገባል፤ ለካቢኔያዊ የሥልጣን ክፍፍል ደግሞ የሕግ ዋስትና መኖር አለበት፤ ለሆሮዊዝ ግን ፕሬዚዳንታዊ መንግሥትና በስምምነት ላይ የተመሠረተ ካቢኔዊ የሥልጣን መጋራት ተመራጭ ነው፡፡ ከላይ ከተገለጹት አንፃር የኢትዮጵያን ስንመለከተው ከሊፕሃርት ፓርላሜንታዊ መንግሥትን፣ ከሆሮዊዝ ደግሞ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ የካቢኔያዊ አወቃቀርን ወስዷል ማለት ይቻላል፡፡ የሥልጣን ማጋሪያ መሥፈርቱም ብሔርን መሠረት ያደረገ ስለሆነ ፓርቲዎችም በዚሁ ሁኔታ ሊመሠረቱ ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የካቢኔ የሹመት ሁኔታ ሲፈተሸ

የተለያዩ አገሮች የተለያዩ አሠራሮች እንዳዳበሩና ሕጋዊ እንዳደረጓቸው እንረዳለን፤ የደቡብ አፍሪካን ስናይ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ከአምስት በመቶ በላይ መቀመጫ ካለው በካቢኔ ውስጥ ይወከላል፤ በቤልጂየም ደቾቹና ፍሌሚሾቹ በፌዴራሉ ካቢኔ ውስጥ እኩል አባላት አላቸው፡፡ ቤልጂየም የሁለት ብሔሮች አገር ስለሆነች ይሆናል፡፡ በኮሎምቢያ ሁለቱ ዋና ዋና ፓርቲዎች የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ በመፈራረቅ ነው የሚይዙት፡፡ በሊባኖስ ደግሞ በቋሚነት ፕሬዚዳንትነት ለአንድ ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ደግሞ ለሌላ የተሰጠ ነው፡፡ ለማሳየት የፈለግኩት አንድ ዓይነት ቀመር ለሁሉም የማይሠራ መሆኑን ነው፡፡

እነ ሊፋርትም ይሁኑ ሌሎች የዘርፉ ምሁራን የፕሬዚዳንት (በፓርላሜንታዊ ሥርዓትም ቢሆን)፣ የጠቅላይ ሚኒስትር፣ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቦታዎችን እንደ ቁልፍ ሥልጣን በመውሰድ ለተለያዩ ብሔሮች መከፋፈል አለባቸው ይላሉ፡፡ የሊባኖስና የቆጵሮስ አሠራር ወደዚሁ የተቀራረበ ነው፡፡ የእኛን ታሪክ ከ1987 ጀምሮ የነበሩት ምርጫዎች በኋላ የብሔር ተዋጿቸውን ከላይ ከተቀመጡትና ሥልጣኖች አንፃር በተጨማሪም የፖለቲካ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ የሆኑትን የውጭ ጉዳይና የአገር ውስጥ/የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዲሁም የመከላከያ አዛዥና የደኅንነት ኃላፊውን ጨምረን እንያቸው፡፡

በ1999 ዓ.ም. በተደረገው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት መሠረት ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኦሮሞ 36.2%፣ አማራ 25%፣  ሶማሌ 6.3%፣ ትግሬ 5.5%፣ ሲዳማ 4.6% እና ወላይታ 2.3% ናቸው፡፡ ሶማሌ በቁጥር ከትግራይ ቢበልጥምና በሕገ መንግሥቱ እኩል መብት ቢኖረውም፣ ኦሮሞ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ከ1/3ኛ በላይ ቢሆንም በተግባር ግን ሦስቱም በፍትሐዊነት ተወክለዋል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙዎች በንግግራቸውም ይሁን በጽሑፋቸው የኢትዮጵያ አስተዳደሪ (ገዥ) ሕወሓት/ኢሕአዴግ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የአንድ ብሔር የበላይነት ለመኖሩም የመከላከያ አዛዦችን፣ የደኅንነት ኃላፊዎችን፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሳይኖራቸው በአማካሪ ስም የሚኒስትርነት ሥልጣን ኖሯቸው ወይንም ሳይኖራቸው በየዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያማክራሉ ተብለው የሚታሰቡትን በመጨመር ነው ይህ የአንድ የብሔር የበላይነት የሚነሳው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቢሯአቸው የሚያማክሯቸው ሰዎች እንደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ነገር ግን ፊት ለፊት ስለማይታይ ፈረንጆቹ የጓዳ ካቢኔዎች (Kitchen Cabinet) ይሉታል፡፡ በመሆኑም አማካሪ ሚኒስትሮችም እንዲሁ በሕዝቡ እንደ ካቢኔ ለዚያውም ወሳኝ ሥልጣን እንዳለው ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡

በጣም ቁልፍ የሚባሉትንም ይሁን ሌሎች የሥልጣን ቦታዎች እየተፈራረቁ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚያገኙትም ሊሆን ይገባል፡፡ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ብቻ አገር በሚመራበት ወቅት፣ የተለያዩ ብሔሮች ሊወከሉ የሚችሉበትን መርሕ ማስቀመጥና አሠራሩንም ማዳበር ብሎም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ ካልተቻለ፣ አንድን ወይንም ከዚያ በላይ የሆኑ ክልሎችን ሌላ ፓርቲ በምርጫ ቢያሸንፍ፣ አሁን ባለው የፖለቲካ ባህል፣ በዚያ ክልል የሚኖሩ ብሔሮች ሊወከሉ የሚችሉበት ሕጋዊ አሠራር የለም፡፡ ይህ ደግሞ የግጭት መነሻ ነው፡፡ ለዚያውም የብሔር ግጭት!

ማጠቃለያ

ሚኒስትርነት እጅግ ብዙ ሙያዊና ፖለቲካዊ ተግባራት የሚከናወኑበት ሥልጣን ነው፡፡ በርካታ አገሮች በፓርላማ የተሻለ መቀመጫ ያለው ተቃዋሚ ፓርቲ በመንግሥት ወጪ፣ የጥላ ሚኒስትር (Shadow Minister) በመሰየም የገዥው ፓርቲን እንከን ያጋልጣሉ፣ ይተቻሉ፣ ራሳቸውም ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ክህሎት ያዳብራሉ፡፡ ሲያሸንፉ የሚሠሩትን በአግባቡ ያውቃሉ፣ አቅማቸውንም ያሳድጋሉ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደ ጠላት በሚታይበት አገራችን ይህንን ማሰብ አዳጋች ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ፓርቲም ውስጥ ቢሆን በተናጠል ስለሚመሯቸው ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ዕውቀትና ልምድ የሌለውን ሰው መሾም ሕገ መንግሥቱ ላይ የተደነገገውን የብቃት መሥፈርት መጣስ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሹመቶችን ሲያጸድቅ የተሿሚዎችን ብቃት የሚለካበት መሥፈርት ሊያሳድግ ይገባዋል፡፡ የጤና ባለሙያን ስለ ፌዴራሊዝም፣ ስለ ሕገ መንግሥት፣ ስለ ግጭት አፈታት ጥልቅ ዕውቀት የሚጠይቀው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ፋይናንስና ልማት ጉዳይን የሚመራው ሚኒስትር በእነዚህ ጉዳዮች ላይ  ልምድና ዕውቀት ከጎደለው አገራዊ ኪሳራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ማንኛውም ተሿሚ፣ ሚኒስትርም ይሁን ሌላ፣ ሲሾም ሁሉንም ነገር አዋቂ የሆነ ይመስለዋል፡፡ በርካታ የዕውቀት ዘርፍ የሚዳስሱ የመንግሥት ፖሊሲዎችን ከበርካታ የትምህርት ዘርፍ የተውጣጡ ለዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሳይቀር፣ የሚያወላዳ ዕውቀት ባይኖረውም ባለሥልጣን በመሆኑ ብቻ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ይህንን ሁኔታ የሚከተሉት የባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ ስንኞች የበለጠ ይገልጹታል፡፡

‹‹ላም እሳት ወለደች በሬ ቀንድ አወጣ፣

በሥልጣን ሊቅ መሆን ይህም አለ ለካ፤››

የአገሪቱ አብዝኃኛው ጉዳይ እንደ መንግሥት የሚወሰነውና የሚከናወነው፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ስለሆነ ቦታውን ሊመጥን የሚችል ልምድና ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ብቃት ያስፈልጋል፡፡ የግሉን ዘርፍና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ጭምር የሚመራ ልማታዊ መንግሥት ሲኖር ደግሞ የብቃት አስፈላጊነት የበለጠ ይጎላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ፣ ለሚኒስትርነትም ቢሆን ሚዛናዊ የብሔረሰብ ውክልና መኖር እንዳለበት ደንግጓል፡፡ እንደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ 77፣ እንደ ሕዝብና ቤት ቆጠራ 85፣ ብሔረሰቦች ባሉባት ኢትዮጵያ፣ ሚዛናዊው ውክልና እንዴት ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ግልጽ የአሠራር መርሆችን የሕግ ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ሊፕሃርት ሐሳብ ቁርጥ አድርጎ በፐርሰንትና በቁጥር ማስቀመጥ ለእኛ አገር ሁኔታ የሚመች አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ብሔሮች በመያዝ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ከብዙዎች አትለይም፡፡ ፓውፓ ኒው ጊኒያ ወደ 800፣ ናይጄሪያ ወደ 400፣ ሩሲያ ወደ 185 የሚጠጉ ብሔረሰቦች አሏቸው፡፡ ብቃት ከሚዛናዊ ውክልና ጋር የሚጣጣምበትን መፍትሔ መሻት ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ከወቅታዊ የፖለቲካ ፍጆታ በመውጣት ሕግና ሥርዓት ማስፈን ነው፡፡    

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...