Tuesday, December 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ፓርላማው የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ይዘጋጅ!

 የአምስተኛው ፓርላማ ሁለተኛው የሥራ ዘመን በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል፡፡ በአገሪቷ አጠቃላይ ሕይወት ላይ የወሳኝነት ሚና ያለው ፓርላማ ከሥራ አስፈጻሚው ከሚቀርብለት ዕቅድና ሪፖርት በተጨማሪ፣ በሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ያገኙ ዘንድ ከፍተኛው ሥልጣን አለው፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራበት ዕውነታ ነው፡፡ ምክንያቱም የፓርላማ አባላት ተጠሪነታቸውና ታማኝነታቸው ለወከላቸው ሕዝብ፣ ለሕገ መንግሥትና ለሕሊናቸው በመሆኑ ነው፡፡ የአንድ አገር የሥልጣን የመጨረሻ አካል የሆነው ፓርላማ በአገር አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ወሳኝነት የሚኖረውም ለዚህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ሁለተኛ የሥራ ዘመኑን ሲጀምር ዋነኛ ተግባሩ ሊሆን የሚገባውም ላለፉት አሥር ወራት ለሕይወት መጥፋት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለንብረት ውድመትና ለአገሪቱ ህልውና ሥጋት ለሆነው ችግር የጋራ መግባባት የሚፈጥር መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠለትን ሥልጣኑን መጠቀም አለበት፡፡ ሕዝብ እየጠበቀ ነው፡፡

አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ከሕዝብ ለተነሱ መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ተደምጧል፡፡ ይህ ምላሹ የፓርላማውን ውሳኔ የሚጠብቅ ከሆነ፣ ፓርላማው ለዚህ አንገብጋቢ ብሔራዊ ጉዳይ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ የሚነሱ ለዓመታት ሲንከባለሉ የነበሩ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ በፀጥታ አስከባሪዎች ዜጎች እንዳይገደሉ፣ በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባትም ሆነ እርቅ ለማምጣት የሚረዱ የውይይት መድረኮች በአስቸኳይ እንዲዘጋጁ፣ የተዘጋጋው የፖለቲካ ምኅዳር በፍጥነት እንዲከፈት፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል አሳማኝ በሆነ መንገድ እንዲሰፍን፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ ነፃነት እንዲንቀሳቀሱ፣ ሕገወጥነትና የኃይል ተግባር ቆሞ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ያለአድልኦ የሁሉንም ድምፅ እንዲያስተጋቡ፣ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች ትልቅ ትኩረት እንዲሰጥ፣ ወዘተ የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦች ቀርበው ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በመሠረቱ በየትኛውም ዴሞክራሲ ባለበት አገር ፓርላማ ሦስት መሠረታዊ ኃላፊነቶች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው አዳዲስ ሕግጋት መደንገግ፣ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎችን ማሻሻል ወይም መለወጥ፣ እንዲሁም የማያስፈልጉ ሕጎች ከተገኙ መሻር ናቸው፡፡ ሁለተኛው በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ የዜጎችን ፍላጎትና ምኞት ለማሟላት የሕዝብ ውክልናን በአግባቡ መወጣት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ለሕዝብ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ባለበት መንገድ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ብርቱ ቁጥጥር ማድረግ ሲሆን፣ የመንግሥት አሠራርም ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች በብቃት ለመከታተልና ተግባራዊነታቸውን ለመቆጣጠር ደግሞ ፓርላማ ጠንካራ፣ ውጤታማና ብቁ መሆን ይኖርበታል፡፡ ብሔራዊ የልማት አጀንዳዎች የሚሳኩት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ጥረት የሚቀላጠፈውና የሕዝብ ፍላጎት የሚሟላው ፓርላማው በሚጫወተው ወሳኝ ሚና ነው፡፡ ፓርላማው የሕዝብ ተጠሪ እንደመሆኑ መጠን በፖሊሲዎችና በአፈጻጸሞች ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና የሕዝቡን ጥቅም ለማስከበር ሥር ነቀል ዕርምጃ እስከ መውሰድ ድረስ ይሄዳል፡፡

በአገራችን ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ መጓደልና የሙስና ጉዳዮች በተደጋጋሚ ቢወሱም በጥልቀትና በዝርዝር ሲገባ የተከማቹ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በእነዚህ ችግሮች ላይ ከልብ መነጋገር ከተቻለ ሁሉንም ዜጎች ማዕከል ያደረገ ሰላማዊ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል፡፡ ከሥልጣን ጉጉት በላይ የአገርና የሕዝብ ህልውና ጉዳይ ቅድሚያ ከተሰጠው የማይፈታ ችግር የለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚታሰብ ከሆነ ግን ችግር ሌላ ችግር እያስከተለ ሰላማዊው መንገድ ይዘጋጋና መነጋገሪያው የጠመንጃ ቃታ ይሆናል፡፡ ይኼ ደግሞ ለሕዝብ ዕልቂትና ለአገር ውድመት ካልሆነ በስተቀር በፍፁም አማራጭ ሊሆን አይችልም፡፡ በጋራ መነጋገር፣ መደማመጥ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና የሕዝብን ፍላጎት ማርካት የሚቻለው ከኃይል ይልቅ ዴሞክራሲያዊው መንገድ ሲመረጥ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ትግል የመጨረሻ ግቡ ሥልጣን ቢሆንም የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ያላደረገ ሥልጣን መቼም ቢሆን ተረጋግቶ አይቀጥልም፡፡ ይልቁንም አገርንና ሕዝብን ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ ፓርላማው እንዲህ ዓይነቱን ግንዛቤ በመጨበጥ ለሕዝብና ለአገር የሚበጅ ውሳኔ ይጠበቅበታል፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዴሞክራሲ በጣም መሠረታዊ ከሚባሉ ፍላጎቶች ተርታ የሚመደብ እንጂ፣ እንደ ቅንጦት እየታየ በተራዘመ ጊዜ የሚገኝ የተስፋ ዳቦ አይደለም፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ባይተዋርነት ሳይሰማቸው በአገራቸው አጠቃላይ ጉዳዮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመሳተፍ መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት በሚገባ ተከብሮ በውስጡ የሠፈሩ መሠረታዊ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ሊረጋገጡላቸው ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ሊታሰሩ አይገባም፡፡ በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነታቸው ተረጋግጦ በነፃነት ሐሳባቸውን መግለጽ አለባቸው፡፡ የመደራጀት መብታቸው ተከብሮ የፈለጉትን የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት፣ መሳተፍና መደገፍ የመቻል ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው በተግባር እንዲረጋገጥ መደረግ አለበት፡፡ በመላ አገሪቱ በፈለጉት ሥፍራ የመዘዋወር፣ ሀብት የማፍራትና የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው በተግባር መከበር ይገባዋል፡፡ በሕግ ፊት ሁሉም ዜጎች እኩል መሆናቸው በገቢር መታየት አለበት፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት መሠረታዊ መብቶች ባለመከበራቸው ምክንያት የተፈጠረው የሕዝብ ቁጣ ምላሽ እንዲያገኝ፣ ፓርላማው ትልቅ ኃላፊነት ስላለበት በብርቱ ማሰብ ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል በአገሪቱ የተፈጠሩ ችግሮች ሰላማዊ እልባት እንዳያገኙና ሕዝቡ በሥጋት ውስጥ እንዲኖር አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የሚረባረቡ ወገኖችም ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የአገሪቱን ዙሪያ ገብ ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት አፍራሽ ሚና ከመጫወት ይልቅ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ጠቃሚ ሐሳቦችን ለማበርከት የሚረዱ መድረኮች እንዲፈጠሩ አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡ ሰላማዊው ዕድል እንዲያመልጥ የሚረዱ አውዳሚ መንገዶች እንዲፈጠሩ መሥራት አገርን ወደ ፍርስራሽነት፣ ሕዝብን ደግሞ ወደ ዕልቂትና ስደት ከመምራት ውጪ ፈፅሞ አይጠቅሙም፡፡ እልህና ጥላቻን ብቻ በማራገብ ሁሉን አቀፍ የሆነ የጋራ መፍትሔ እንዳይመጣ ቅስቀሳ ማድረግ፣ የአገሪቱን ታሪካዊ ጠላቶች ከማገዝ የተለየ ፋይዳ የለውም፡፡ ይልቁንም ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ወገኖች በእኩልነት የሚነጋገሩበት ብሔራዊ መድረክ እንዲኖር የበኩላቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት ይወጡ፡፡ በጥላቻና በመፈራረጅ ላይ ብቻ የተመሠረተ የቧልት ፖለቲካ ማብቃት አለበት፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ቅን ዜጎች ሁሉንም ወገን የሚያግባባ አማካይ በሚፈልጉበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ ፓርላማውም የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ራሱን ያዘጋጅ!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...