Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየፌስቡኩ ሜዳ

  የፌስቡኩ ሜዳ

  ቀን:

   ሕፃኗ ወደዚህ ዓለም ከመጣች ገና ሰዓታት ቢቆጠሩ ነው፡፡ ዓይኗን በቅጡ አልገለጠችም፡፡ ሕፃናት እንደተወለዱ ያላቸው ደም የመሰለ የፊት ገጽታዋም አልተለወጠም፡፡ በቀዶ ሕክምና የወለደቻት እናቷም ሙሉ በሙሉ ከሰመመን የነቃች አይመስልም፡፡ ይህ የአንድ ቤተሰብ ግላዊ የሆነ ቅጽበት ፎቶ ተነስቶ ፌስቡክ ላይ ተለቋል፡፡ ፎቶውን የተመለከተችው ወ/ሮ ስንዱ መሓሪ በሁኔታው ማዘኗን ትናገራለች፡፡ ሰዎች ከቅርብ ወዳጆቻቸው ውጭ ከማንኛውም ሰው ጋር ሊጋሯቸው አይገባም የምትላቸው መረጃዎች ፌስቡክ ላይ ተለቀው ስትመለከት የመጀመርያዋ አልነበረም፡፡

        ወደ አሥር ዓመት ገደማ ፌስቡክ ተጠቅማለች፡፡ ሰዎች የግላቸውን እንዲሁም የቤተሰባቸውን ፎቶዎች መለጠፋቸው አግባብ አይደለም ከሚሉት ጎራ ናት፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ በሩቅ የምታውቀው ሰው ለሴት ጓደኛው የጋብቻ ጥያቄ ሲያቀርብ የሚያሳይ ፎቶ ለቀቀ፡፡ በእሷ እምነት ፎቶው የጥንዶቹ ብቻ መሆን ነበረበት፡፡ ጥንዶቹ ቅጽበቱን ትርጉም ባለው መንገድ ከማሳለፍ ይልቅ ፌስቡክ ላይ ለሚለቋቸው ፎቶዎች የተጨነቁ ይመስላል፡፡ ከአገራችን ወግና ሥርዓት አጥባቂነት አንፃርም ቤተሰቦችን ያላማከለ የጋብቻ ጥያቄ ፌስቡክ ላይ መልቀቅ ተገቢ አይደለም ትላለች፡፡

  በፌስቡክ እያንዳንዱ እንቅስቃሴውን በመግለጽ ስታተስ አፕዴት የሚያደርግም ጓደኛ አላት፡፡ ያለበትን ቦታ፣ የሚሄድበትን እየወሰደ ያለውን ሥልጠናና ስለ ሥራ ሁኔታው በሰዓታት ልዩነት ይጽፋል፡፡ ወ/ሮ ስንዱ፣ ‹‹እነዚህን ሁሉ ግላዊ መረጃዎች በፌስቡክ መልቀል አስፈላጊነቱ አይታየኝም፤›› ትላለች፡፡

  በእሷ እምነት፣ ሰዎች ያሉበትን ስሜት በግልጽ የሚያሳዩና ሕይወታቸውን በአደባባይ የሚተነትኑ መረጃዎች መልቀቅ የለባቸውም፡፡ ፖስት የሚደረግ መረጃ በሰው ግላዊ ሕይወት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ ከግምት መግባት አለበት፡፡ ከመረጃው ባለቤት ውጪ ለሌሎች ሰዎች ትርጉም የማይሰጥ ነገርም መልቀቅ አይገባውም፡፡

  እሷ ሁለት የፌስቡክ ገጽ አላት፡፡ አንደኛው ከቤተሰቦቿና ዘመድ አዝማዶቿ ጋር የምትገናኝበት በቤት ስሟ ያወጣችው ሲሆን፣ ሌላው ከትምህርት ቤት ጓደኞቿና ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር የምትጋራው ነው፡፡ በሁለቱም ገጿ በአካል የምታውቃቸው ሰዎች ወይም ከሥራዋ ጋር የተገናኘ መረጃ ሊያቀርቡላት ከሚችሉ ሰዎች ጋር ብቻ ጓደኛ ናት፡፡ እነዚህም ከ200 አይበልጡም፡፡ ከፕሮፋይል ፎቶዋ ባለፈ የባለቤቷንም ይሁን የልጆቿን ፎቶዎች አትለቅም፡፡ ስለ ግላዊ ሕይወቷ የሚገልጽ መረጃ ፌስቡክ ላይ ባለመኖሩ፣ ‹‹ከፌስቡክ ገጼ ስለኔ ማወቅ አይቻልም፤›› ትላለች፡፡

  ሼር የምታደርጋቸው ነገሮች ውስን ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ኮሜንት ከማድረግም ትቆጠባለች፡፡ ፌስቡክ ላይ አስተያየቷን የምትሰጥባቸው ነገሮች አንዳች ነገር እንዳያስከትሉባት ስለምትሠጋ በተለይ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አትሳተፍም፡፡ ፌስቡክ የተጋነነና በስሜት የተሞላ መልዕክት የሚተላለፍበት የማኅበረሰብ ድረ ገጽ በመሆኑ በጥንቃቄ እንደምትጠቀም ትናገራለች፡፡

  ፖስት ከምታደርጋቸው ነገሮች ባሻገር ሰዎች ከሷ ጋር ያሳለፉትን ጊዜ ሼር እንዲያደርጉም አትፈልግም፡፡ ከቤተሰቦቿ ወይም ከጓደኞቿ ጋር ሆና የምታደርገው ማንኛውም ነገር በፌስቡክ እንዲውል አትሻም፡፡ ፍቃደኛነቷን የሚጠይቁ ግን የሉም፡፡ ሰዎች ሲበሉ፣ ሲጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ሲያደርጉ የሚያሳይ ፎቶ ያለፈቃዳቸው ፖስት ባይደረግ ይመረጣል ትላለች፡፡

  ‹‹ሰዎች በሚዝናኑበት ወቅት የሚያደርጉት ነገር ግላዊ ነው፡፡ ትልልቅ ተቋማት የሚመሩ እንዲሁም የቤተሰብ ኃላፊዎች በእረፍት ጊዜያቸው መጠጥ ሊጠጡ ይችላሉ፡፡ ይህንን በፌስቡክ መልቀቅ በቤተሰባቸውና በሥራ ቦታቸው የሚያስከትለው ተፅዕኖ መታሰብ አለበት፤›› ትላለች፡፡ ወ/ሮ ስንዱ ሠርግ ላይ ወይም ለበዓላት ከቤተሰቦቿ ጋር የተነሳችውን ፎቶ እህቶቿና ወንድሞቿ ታግ አድርገዋት ሲለጥፉ ደስተኛ አይደለችም፡፡ ቅሬታዋን ግን ደፍራ አትነግራቸውም፡፡ ሰዎች ፌስቡክ ላይ ስለሚለጥፉት ነገር ከቀልባቸው ሆነው ገደብ ቢያበጁ ትላለች፡፡

  በሐሳቧ ሙሉ በሙሉ የማይስማማው አቶ ዮናታን ለይኩን እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን፣ ስሜቱንና አስቱያየቱን በየደቂቃው ፌስቡክ ላይ ፖስት ያደርጋል፡፡ በፎቶ፣ በቪዲዮ ወይም በጽሑፍ ስሜቱን ከመግለጽ ወደኋላ አይልም፡፡ ግላዊ የሚላቸው መረጃዎች የሉም፡፡ ፌስቡክ ገጹ ላይ በልጆቹ፣ በእናቱና በአባቱ ስም የፎቶ መዝገብ አለ፡፡ ልጆቹ ከልጅነታቸው እስከ ወጣትነታቸው በተለያየ አጋጣሚ የተነሱትን ፎቶ በየጊዜው ፖስት ያደርጋል፡፡ ቤተሰቦቹም በወጣትነታቸውና በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች የተነሱት ፎቶ በፌስቡኩ ይገኛል፡፡ የሥራ ባልደረቦቹና ጓደኞቹም ይካተታሉ፡፡

  አቶ ዮናታን ሲናደድ፣ ሲደሰት፣ የበላውን፣ የሄደበትንና ሊሄድ ያሰበበትን ለማወቅ ፌስቡኩን መመልከት በቂ ነው፡፡ ሼር የሚያርጋቸው ነገሮች ላይ ገደብ ሳያስቀመጥም ስለአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች፣ ቴክኖሎጂ ወይም ኪነ ጥበብ ስሜቱ ያጫረውን ነገር ባጠቃላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያሰፍራል፡፡ ‹‹ፌስቡክ ላይ ካሉኝ 890 ጓደኞቼ አብዛኞቹን በአካል አውቃቸዋለሁ፡፡ አንዳንዴ ፖስት የማደርገው ነገር በጣም ግላዊ ነው ብለው ስለሚያስቡ ይህንን ሼር አታድርግ ይሉኛል፡፡ ለኔ ግን ፌስቡክ ስሜቴን ያለገደብ የምገልጽበት ሚዲያ ነው፤›› ይላል፡፡

  ፌስቡክ ላይ የሚሰፍሩ መረጃዎች ገደብ ሊኖራቸው ይገባል ከሚሉ ሰዎች ጋር አይስማማም፡፡ የድረ ገጹ ዓላማ ሰዎች ስሜታቸውን እንዲጋሩ በመሆኑ መልካሙንና ክፉውንም ጊዜ በግልጽ ቢያሰፍሩ መልካም ነው ይላል፡፡ የሱን ሕይወት ከሀ እስከ ፐ ለማወቅ ፌስቡክ ገጹን መመልከት ብቻ የሚበቃ በመሆኑ ቅር አይሰኝም፡፡ ‹‹ፌስቡክ ገጼ ማለት እኔ ነኝ፤›› ይላል፡፡

  በቅርቡ የነፍሰጡር ጓደኛውን ልጅ ስሪዲ አልትራሳውንድ ፎቶ ፖስት አድርጓል፡፡ እናቱ በወጣትነታቸው ከጓደኞቻቸው ጋር ቢራ ሲጠጡ የሚያሳይ ፎቶ ለጥፎ እንዲያነሳ ቢጠይቁትም ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ ከቀድሞ ባለቤቱ ጋር ሲፋታ መጀመርያ ያደረገው ነገር ፌስቡክ ስታተሱን መቀየር ነበር፡፡ ከነዚህም ነገሮች በላይ ሰዎች ግላዊ የሚሏቸው ነገሮችን በገጹ ሲለቅ ፍቃዳቸውን አይጠይቅም፡፡ መጠየቅ አለብኝ ብሎም አያምንም፡፡ ጓደኞቹ ቢያንስ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሲሰጥ እንዲጠነቀቅ ቢነግሩትም አልተቀበለም፡፡

  በወ/ሮ ስንዱና አቶ ዮናታን መካከል ያለው የአመለካከት ልዩነት የብዙዎች ነው፡፡ ከሁለቱ ጎራ በአንዱ ሆነው፣ ፌስቡክ ላይ ግላዊ መረጃዎችን ያለገደብ መልቀቅን የሚነቅፉ የሚደግፉም አሉ፡፡ ፌስቡክ በቀላሉና በፍጥነት መረጃ ለመለዋወጥ የተመቸ እንደመሆኑ ጥቃቅን የሚባሉ ነገሮችን ሳይቀር ፌስቡክ ላይ የሚለቁ አሉ፡፡ አንዳንዴም ሰዎች ስሜታቸውንና ፍላጎታቸውን ለመላው ተከታዮቻቸው የሚያሳውቅ መረጃ ይለቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ አንድ ቦታ ላይ አብረዋቸው የነበሩ ሰዎችን ግላዊ ነፃነት በሚጋፋ መልኩ የሰው መረጃ መለጠፍን ሊያካትት ይችላል፡፡

  በፌስቡክ የሚለቀቁ መረጃዎች መስመር ምን መሆን አለበት? የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን ያጠያይቃል፡፡ ሰዎች ምን ዓይነት ጉዳያቸውን ወይም ሐሳባቸውን በፌስቡክ ማስፈር አለባቸው? የሚለው ጥያቄም ይነሳል፡፡ ከግል መረጃ ባሻገር የሌሎችን ጉዳይ ፌስቡክ ላይ ማስፈርስ ተገቢ ነው? ሲሉ የሚጠይቁም አሉ፡፡

  በሚጥስር ሊያዝ የሚገባ ነገርን በፌስቡክ ፕሮፋይልና በስታተስ አፕዴት ለሰው ማካፈል ተገቢ አለመሆኑን የሚያምኑ አሉ፡፡ በሌላ በኩል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በግልጽ አስተያየት መስጠትም አቋምን የሚያስገምት በመሆኑ መቅረት አለበት የሚሉ አይታጡም፡፡ ለምሳሌ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ጽንፍ የወጡ አስተያየቶች ሊያስከትሉ የሚችሉት ተፅዕኖ ሳይታሰብ እንደሚለጠፍ የሚገልጹ አሉ፡፡ ለምሳሌ በዚህ ረገድ ሰዎች እንደ ቀነኒሳ በቀለ ያሉ ሯጮችና እንደ ሰማኸኝ በለው ያሉ ድምፃውያንን በተመለከተ የሚሰማቸውን በግላቸው መያዝ እንዳለባቸው የሚገልጹ አስተያየት ሰጪዎች ይጠቀሳሉ፡፡

  ፌስቡክ ተጠቃሚዎቹ በየጊዜው ግላዊ መረጃዎችን ፖስት እንዲያደርጉና ስታተስ አፕዴት እንዲያደርጉም ያበረታታል፡፡ ተጠቃሚዎች ሌሎች ሰዎች ፖስት ያደረጉትን ከመመልከትና ሼር ከማድረግ ባለፈ የየግል አስተያየታቸውን እንዲያሰፍሩም ያበረታታል፡፡ የፌስቡክ መሥራቹ ማርክ ዙከርበርግ ስለጉዳዩ ባለፈው ዓመት ለፌስቡክ ተጠቃሚዎች  የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፎ ነበር፡፡ መልዕክቱ ‹‹ፀጉራችሁን ስትቆረጡም ይሁን በየትኛውም ቅጽበት የተሰማችሁን ነገር ሼር አድርጉ፤›› የሚል ነበር፡፡ ቪዲዮውን አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ አይተውታል፡፡ ፌስቡክ ተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃ እንዲያካፍሉ ከሚያደርግባቸው መንገዶች መካከል የሰዎችን ልደት፣ በዓላትና ያለፉ ዓመታት ፖስቶችን ማስታወስ ይጠቀሳል፡፡

  ወ/ት ሶፊያ አሊ የግል ሕይወቷና አመለካከቷን ከሚያሳዩ መረጃዎች መካከል ፌስቡክ ላይ የምታወጣቸው ለራሷ የምታስቀራቸውም አሉ፡፡ ፌስቡክን የተቀላቀለችው ከሰባት ዓመት በፊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለች ነበር፡፡ በቀላሉ ከሰው ጋር መግባባት ስለሚቸግራት ጓደኞች ለማፍራት ፌስቡክን መረጠች፡፡ በፌስቡክ የጓደኝነት ጥያቄ የላኩላትን ባጠቃላይ ትቀበል ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ሰዎች የሚለጥፉት ነገር ትርጉም አልባ እየሆነባት ስለመጣ ብዙዎቹ ከጓደኝነት ሰረዘቻቸው፡፡

  ‹‹ፌስቡክ ጥሩ ጓደኞች ያገኘሁበት ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች ፖስት የሚያደርጉት ነገር የማኅበረሰብ ድረ ገጽን እርባና ቢስ ያደርገዋል፤›› ትላለች፡፡ በእሷ እምነት፣ ሰዎች ከራሳቸው ባለፈ የሌሎችን ግላዊ ነፃነት የሚነካ ነገር መለጠፍ የለባቸውም፡፡ እርቃናቸውን የሆኑ ሕፃናትና የጎዳና ተዳዳሪዎች ፎቶ መለጠፍ እንዲሁም የታዋቂ ሰዎችን ግላዊ እንቅስቃሴ መጻፍና የልጅነት ፎቷቸውን መለጠፍ ግላዊ ነፃነታቸውን መጋፋት ነው፡፡

  እሷ ከከተማ ስትወጣ የምትነሳቸውን ፎቶዎች ፖስት ታደርጋለች፡፡ የቃልኪዳን ቀለበት ስታስርም ፎቶዋን በፌስቡክ ለቃለች፡፡ እንደ ሙዚቃ፣ ፎቶግራፍ፣ ኮሚዲ ያሉ መዝናኛዎችንም ሼር ታደርጋለች፡፡ ፌስቡክን ፖስት የምታደርጋቸው ፎቶዎችና ሊንኮች እንዳይጠፉባት ጭምርም  እንደምትጠቀም ትናገራለች፡፡

  ብዙ ጊዜ ሰዎች ስሜታዊ ሆነው ፖስት የሚያደርጓቸው ነገሮች ያሉበትን ሁኔታ ስለሚገልጹ ጥንቃቄ ቢወስዱ መልካም ነው ብላ ታምናለች፡፡ ለምሳሌ ከፍቅር ጓደኞቻቸው ጋር ሲጣሉ ስለ ሰዎች ባህሪ የሚገለጽ ጥቅስ የሚጽፉ ወይም ስታተስ የሚቀይሩም ታስተውላለች፡፡ ፌስቡክ ላይ የሚለቀቁ መረጃዎችን ቆይቶ ማጥፋት ቢቻልም፣ በተለቀቁበት ጊዜ ምን ያህል ሰው እንደሚመለከታቸው ስለማይታወቅ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ትላለች፡፡

  የፌስቡክ ገጿ ስለማንነቷ በከፊል ቢገልጽም፣ ሐሳቦቿን ባጠቃላይ የምታሰፍርበት አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ፌስቡክ ላይ ግላዊ አመለካከታቸውን  ሲያሰፍሩ በሚጽፉበት ጉዳዩ ዙሪያ  ጥልቅ መረጃ ያላቸው ከመሰላት ትከታተላለች፡፡ ሚዲያው ስላለ ብቻ ስለሁሉም ነገር አስተያየት የሚሰጡትን ደግሞ ትቃወማለች፡፡ የሰውን ግላዊ ነፃነት በመጋፋት ያለ ፈቃድ ታግ የሚያደርጉና መልክዕት የሚልኩ ሰዎችንም አትደግፍም፡፡

  በፌስቡክ የሚለቀቁ መረጃዎች ከማኅበረሰቡ ባህል አንፃር መታየት አለበት የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ገጥመውናል፡፡ ግላዊ የሚባሉ ነገሮች እንደየማኅበረሰቡ ይለያያሉና በሌሎች አገሮች ያሉ ፌስቡክ ተጠቃሚዎች የሚለቀቁትን ዓይነት መረጃ በሙላ መልቀቅ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሁኔታ ውስጥም ያስኬዳል ማለት አይቻልም፡፡

  የፌስቡክ ጉዳይ በሌሎች አገሮችም ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የመኖሪያ አድራሻ፣ ከሥራ ጋር የተያያዙ መረጃዎች፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ የግል ጤና፣ የፍቅር ወይም የወሲብ ግንኙነት በፌስቡክ ላይ ማስፈርን የሚቃወሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ተቃውሟቸውን በተለያዩ ጽሑፎች ያሰፈሩም ይገኛሉ፡፡ ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን የግል መረጃዎች የሚጠብቅበት ሁኔታ ስለማያስተማምናቸው ፕሮፋይላቸውን የማይጽፉ አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ፌስቡክ የሰዎችን ግላዊ መረጃ ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ በመስጠት የተጠረጠረባቸው ጊዜዎችም ነበሩ፡፡

  በቅርቡ አሳፋሪ የልጅነት ፎቶዎቿን በፌስቡክ ለቀው አላጠፋ ያሏት ቤተሰቦቿን ፍርድ ቤት ያቆመችው አውስትራሊያዊት ወጣት የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስባለች፡፡ ወጣቷ ዳይፐር ሲለወጥላትና ፖፖ ላይ ስትፀዳዳ የሚያሳዩ ፎቶዎቿን ፌስቡክ ላይ ያዩ 700 ጓደኞቿ እየተቀባበሉት ነው፡፡ የ18 ዓመቷ ታዳጊ የግል ሚስጥሬ የምትላቸው ወደ 500 የሚሆኑ የልጀነት ፎቶዎችን ቤተሰቦቿ ፍቃዷን ሳይጠይቁ ለጥፈዋል፡፡ እሷም የፍትሕ ያለህ እያለች ሲሆን፣ በብዙ አገሮች የሰዎችን ሚስጥራዊ መረጃ ያለፈቃዳቸው ፌስቡክ ላይ መልቀቅ በሕግ ያስቀጣል፡፡

  ግሩም አዳነ ፌስቡክ ላይ ግላዊ የሚባሉ ነገሮችን የሚለጥፉ ሰዎች የጎላ ጉዳት እስካላደረሰባቸው ፖስት ማድረጋቸው ችግር የለውም ብሎ ያምናል፡፡ እሱ ልደት፣ ምርቃት፣ ሠርግና በዓል ላይ የሚያነሳቸው ፎቶዎችን ይለጥፋል፡፡ ከሰው ሲጣላ፣ በሥራ ቦታው አንዳች ነገር ሲገጥመው ወይም ስሜቱን መግለጽ ሲፈልግ በቀጥታ ባይጽፍም ጥቅሶች ፖስት ያደርጋል፡፡ አገር ውስጥም ይሁን ውጪ ያሉ ጓደኞቹ ፖስቱን ላይክ ሲያደርጉ ወይም አስተያየት ሲሰጡትም ደስ ይለዋል፡፡

  አንዳንዴ ግን በመረጃው ባለቤት ብቻ መቅረት ያለባቸው ሚስጥሮች አደባባይ ሲወጡ ይገርመዋል፡፡ ስለ እናቱና አባቱ አሟሟት ‹‹ለማንም ያልነገርኩት ሚስጥር›› ብሎ ፌስቡክ ላይ ጽሑፍ የለቀቀ ጓደኛውን ይጠቅሳል፡፡ ከጓደኛው የቀድሞ እጮኛ ጋር ድብቅ የፍቅር ግንኙነት የጀመረ ወዳጁ ነበር፡፡ አንድ ምሽት ላይ ከልጅቷ ጋር ግንኙነታቸውን በሚያሳብቅ መልኩ የተነሱትን ፎቶ የሥራ ባልደረቦቹ ፌስቡክ ላይ ይለቁታል፡፡ ሁለቱ ጓደኞቼ እንዴት እጮኛዬ ከነበረች ሴት ጋር ግንኙነት ትጀምራለህ በሚል እስከወዲያኛው ተቆራርጠዋል፡፡ ሲጋራ እንደሚያጨስ ቤተሰቦቹ እንዲያውቁበት ያልፈለገ ጓደኛውም ተመሳሳይ ነገር ገጥሞታል፡፡ ከጓደኞቹ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ እየጠጡ ሲያጨስ የሚያሳይ ፎቶ ፌስቡክ ላይ ወንድሙ ተመልክቶ ከቤተሰቡ ተጋጭቷል፡፡

  አንዳንድ ተቋሞች የሠራተኞቻቸውን የፌስቡክ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ይሞክራሉ፡፡ ሠራተኞቻቸው የማኅበረሰብ ድረ ገጽ እንዳይጠቀሙ የሚያግዱም አሉ፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው ከሌሎች ሰዎች ጋር ቢጋሯቸውም ጉዳት የሌላቸው የሚመስሏቸው መረጃዎች የተቋማቸውን ስም እንዳያበላሹ ይሠጋሉ፡፡

  ፌስቡክን በአግባቡ ለመጠቀም ወስነው ከተቀላቀሉ በኋላ የፌስቡክ ድባብ መስመራቸውን እንዳሳታቸው የገለጹልን ነበሩ፡፡ ፌስቡክ ላይ ፖስት ማድረግ እንደ ሱስ ሆኖባቸው ተገቢ የሆነውና ያልሆነውን ሳይመርጡ የሚለቁም ጥቂት አይደሉም፡፡ ፌስቡክን ጠቀሜታ ላለው ነገር ብቻ እያዋሉ እንዳሉና ግላዊ ሕይወታቸውን እንዳልነካ የሚናገሩም አሉ፡፡

  በ1996 ዓ.ም. ከአሜሪካው ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተነስቶ በመላው ዓለም የተስፋፋው ፌስቡክ ወደ 1.23 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት፡፡ አምና ከተጠቃሚዎቹ 17.97 ቢሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡ ዓለም ላይ በፌስቡክ አማካይነት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ንቅናቄ የታየባቸው አገሮች አሉ፡፡ በንግዱና በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የተጠቀሙበት ግለሰቦችም ይጠቀሳሉ፡፡ በአንፃሩ ፌስቡክ በግልና በማኅበራዊ ሕይወታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረባቸውም ጥቂት አይደሉም፡፡

  ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን ደኅንነት ለመጠበቅ ብዙ ድንጋጌዎች አውጥቷል፡፡ ተጠቃሚዎች የሚለጥፉት ነገር በግለሰቦች ወይም በማኅበረሰቡ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቀነስም መርሆች አሉት፡፡ መርሆቹን የጣሱ ተጠቃሚዎች ፖስት የሚያደርጉትን ነገር ከማንሳት አካውንታቸውን ሪሙቭ እስከማድረግ ይደርሳል፡፡ ቢሆንም ግለሰቦች በገዛ ፍቃዳቸው የሚለጥፏቸው ግላዊ መረጃዎች የራሳቸው ኃላፊነት እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ ሌሎች የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ወይም ማኅበረሰቡን እስካልጎዳ ድረስም ጣልቃ አይገባም፡፡  

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ‹‹ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

  የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን...

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡...

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...