Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአደባባይ ምስጢሮች

የአደባባይ ምስጢሮች

ቀን:

 ፀጥ ረጭ ባለው ክፍል ውስጥ ስምንት የቴሌቪዥን ስክሪኖች ተሰቅለዋል፡፡ ሁለቱ ስክሪኖች አልተከፈቱም፡፡ የተቀሩት ስድስት ስክሪኖች ግን የሕንፃውን የተለያዩ ክፍሎች በሚያሳዩ ቪዲዮዎች ተሞልተዋል፡፡ የተለየ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን የሕፃናት መጫወቻ ሥፍራዎች፣ ቲኬት መቁረጫና የመኪና ማቆሚያ ያሉ ቦታዎችን ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ሰፋ አድርገው (ዙም አድርገው) ያሳያሉ፡፡

የክፍሉ ሠራተኛ የሆኑት ሁለት ወጣቶች በየስክሪኖቹ የሚታዩትን እንቅስቃሴዎች በንቃት ይከታተላሉ፡፡ ድንገት የተለየ ነገር የተመለከቱ ሲመስላቸው ስክሪኑን በማስፋት ጉዳዩን በአትኩሮት ይከታተላሉ፡፡ የሚያመልጣቸው ነገር ያለ አይመስልም፡፡ ያልተገባ ነገር ሲፈጽም የተመለከቱት ሰው ሲኖር አልያም አደጋ የደረሰበት፣ በአፋጣኝ በቅርበት ወደሚገኙ ጥበቃዎች በሬዲዮ መልዕክት በማስተላለፍ ችግሩ እንዲፈታ እገዛ ያደርጋሉ፡፡

የደኅንነት ካሜራ የተሠራው እ.ኤ.አ. በ1942 በጀርመናዊው ኢንጅነር ዋልተር በሩች ሲሆን፣ አገልግሎት ይሰጥ የነበረውም እንደዛሬው በየንግድ ማዕከላቱና ተቋማቱ ሳይሆን መከላከያ ዘርፍ ብቻ ነበር፡፡ ቴክኖሎጂው ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት የሰጠው እ.ኤ.አ. በ1944 ወደ ህዋ በመጠቀችው ቪቱ በተሰኘች የጀርመን ሮኬት ላይ በመገጠም ነበር፡፡ በተለያዩ ዘርፎች በሥራ ላይ የዋለው ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ነው፡፡ በስፋት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ቴክኖሎጂው እውን ከሆነ ከ20 ዓመታት በኋላ በኒውዮርክ ነው፡፡ በከተማው የሚገኙ የንግድ ተቋማት በተለይም ባንኮች የደኅንነት ካሜራው ቀዳሚ ተጠቃሚዎች ነበሩ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በወቅቱ ስለደኅንነት ካሜራ የነበረው ግንዛቤ ዝቅተኛ ስለነበር ከትልልቅ የንግድ ተቋማትና አንዳንድ ድርጅቶች በስተቀር ካሜራዎቹን የሚጠቀም አልነበረም፡፡ ቴክኖሎጂውን ይጠቀሙ የነበሩ ተቋማት ቁጥርም ውስን ነበር፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የደኅንነት ካሜራ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ መጣ፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ወቅት 25 ሚሊዮን የሚሆኑ የደኅንነት ካሜራዎች በዓለም ዙሪያ ተሰራጭተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ቴክኖሎጂው በስፋት ከመሰራጨቱ አንፃርም አንድ ሰው በቀን በአማካይ 300 ጊዜያት ያህል በተለያዩ የደኅንነት ካሜራዎች እንደሚቀረጽ ይነገራል፡፡

67 በመቶ የሚሆኑት የወንጀል ድርጊቶችም በደኅንነት ካሜራ አማካይነት እንደሚጋለጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ፈገግ የሚያሰኘው ጉዳይ ግን እነዚህን ካሜራዎች ወንጀለኞችም የሚጠቀሙበት አጋጣሚ መኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ወንጀለኞች የኤቲኤም ማሽኖች ላይ የደኅንነት ካሜራ በመግጠም ማሽኖቹን የሚጠቀሙ ሰዎችን የሚስጥር ቁጥር በካሜራው ይቀዳሉ፡፡ ከዚያም ሰዎቹ አገልግሎቱን ጨርሰው ቦታውን ሲለቁላቸው የሚስጥር ቁጥሩን በማስገባት ገንዘብ ይዘርፋሉ፡፡

ከአምስት አሥርታት በላይ በዓለም ላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ይህ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ ከገባ ጥቂት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ከአንዳንድ ትልልቅ ተቋማት ውጪ ቴክኖሎጂውን የሚጠቀሙ ብዙ አልነበሩም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር የተለያዩ ድርጅቶች እነዚህን ካሜራዎች በየሕንፃቸው አስገጥመው እየተገለገሉባቸው ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል ቦሌ መድኃኔዓለም ፊት ለፊት የሚገኘው ኤድና ሞል አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ 80 የደኅንነት ካሜራዎችን በየፎቁ በመግጠም የሕንፃውንም ሆነ በሕንፃው የሚገለገሉ ሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ጥረት ያደርጋል፡፡ መርዕድ ኪሮስ በኤድናሞል የሲሲቲቪ ኦፕሬተርና ሱፐርቫይዘር ነው፡፡ በሥራው ከተሰማራ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

‹‹ወደዚህ የሚመጡ ሁሉ መዝናናትን አስበው ነው ማለት አይቻልም፡፡ ሌላ አጀንዳ ኖሯቸው የሚመጡ አሉ፤›› የሚለው መርዕድ፣ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ከሕንፃው መግቢያ ጀምሮ እስከ መውጫው ድረስ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ግድ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የደኅንነት ሥጋት አለባቸው ተብለው በሚገመቱ አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የተለየ ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሕፃናት መጫወቻ ሥፍራ አንዱ ነው፡፡ ቦታው የተለየ ክትትል የሚያስፈልገውም አንድም ሕፃናቱ በሚጫወቱበት ጊዜ የመውደቅና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ቢደርሱባቸው ፈጥኖ ለመድረስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌባ ለመከላከል ነው፡፡

‹‹በሚጫወቱበት ጊዜ አደጋ ቢደርስባቸው የመጀመሪያ የሕክምና ዕርዳታ የሚሰጡ ነርሶች አሉ፡፡ እነሱ ደርሰው የሕክምና ዕርዳታ እንዲያደርጉላቸው እናደርጋለን፡፡ በሕፃናት መጫወቻ ክፍል ውስጥ ገብተው የሚሰርቁ አዋቂዎችና ዕቃ የሚያነሱ ትንንሽ ልጆችም ያጋጥሙናል፡፡ ለዚህም ነው የሕፃናት መጫወቻ ቦታው በተለየ ትኩረት በደኅንነት ካሜራዎቹ የሚጠበቀው፤›› ይላል፡፡

ተመሳሳይ ትኩረት የሚደረግባቸው ቦታዎች የትኬት መቁረጫና የሲኒማ መግቢያ ቦታዎች ናቸው፡፡ በሲኒማ መግቢያዎች ላይ ግፊያና መጨናነቅ ሲኖርና አጋጣሚውን ተጠቅመው ከሰው ኪስ ውስጥ የሚገቡ ያጋጥማሉ፡፡ ስለዚህም በእነዚህ ቦታዎች ላይ የሚገጠሙ ካሜራዎች የሚቀዷቸውን እንቅስቃሴዎች በንቃት በመከታተል መሰል ድርጊቶችን በሚፈጽሙ ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋሉ፡፡ አንዳንድ ሕገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ የድርጅቱ ሠራተኞችን ለመቆጣጠርም በትኬት መቁረጫ ቦታዎች ልዩ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡

ከቀናት በፊት በተወሰደ አንድ ቪዲዮ አንድ ትኬት ቆራጭ ከሌላ የድርጅቱ ሠራተኛ ጋር በመመሳጠር ለድርጅቱ ገቢ መሆን የነበረበትን ገንዘብ ወደ ራሳቸው ኪስ ሲያስገቡ መታየታቸውንና ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጽሙ የድርጅቱ ሠራተኞች ከሥራ እስከመባረር ቅጣት እንደሚጣልባቸው መርዕድ ይናገራል፡፡

በከተማው የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የደኅንነት ካሜራዎች ቢያስገጥሙም፣ በየእንቅስቃሴያቸው የደኅንነት ካሜራ መኖሩን ተገንዝበው አንዳንድ ያልተገቡ ድርጊቶችን ከመፈጸም የሚቆጠቡ ጥቂት መሆናቸው፣ እንደ መርዕድ ላሉ የደኅንነት ካሜራ ላይ የሚሠሩ ሰዎች የሥራ ውሏቸው በገጠመኞች የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

መርዕድና ጓደኛው ሥራቸውን አጠናቀው ወደየቤታቸው የሚገቡት ሌሊት ስድስት ሰዓት ገደማ ነው፡፡ የእነሱ የዕለቱ ሥራ አበቃ ማለት ግን ቀረጻውም ይቆማል ማለት አይደለም፡፡ የተገጠሙት ዲጂታል ካሜራዎች 24 ሰዓት የሚሠሩ ናቸው፡፡ በጨለማ የመቅረጽ አቅም ስላላቸውም የሚቀራቸው ነገር የለም፡፡

ነገር ግን ይህንን አውቀው የሚጠነቀቁ በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው፡፡ የሥራ ሰዓት አብቅቶ የድርጅቱ ሠራተኞች ከወጡ ከ11 ሰዓት በኋላ ‹‹ማንም አያየንም›› በሚል ወደ ሕንፃው የላይኛው ክፍል በመውጣት ወሲብ ለመፈጸም የሚሞክሩ ጥንዶች ጥቂት አይደሉም፡፡ የተለያዩ አደንዛዥ ዕፆችን ደብቀው ለመግባት የሚሞክሩ ታዳጊዎችም አሉ፡፡ እርቃናቸውን ሆነው ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ፎቶግራፎችን የሚነሱም ያጋጥማሉ፡፡

‹‹አልፎ አልፎም አንዳንድ ትንንሽ ልጆች ከቤታቸው ለብሰው የወጡትን ልብስ እዚህ መጥተው በሌላ በተራቆተ ይቀይራሉ፤›› የሚለው መርዕድ፣ ሥራው ከተለያዩ ሰዎች ጋር የሚያገናኘው እንደሆነ፣ ከጥበቃ ጀምሮ ያሉ አንዳንድ የድርጅት ሠራተኞች፣ የቅርብ ጓደኞቹ ጭምር ያልተገባ ነገር ሲያደርጉ በደኅንነት ካሜራው ተመልክቶ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው አድርጐ እንደሚያውቅ ይናገራል፡፡

ከዚህም ሌላ አንዳንድ ከበድ ያሉ ጉዳዮችም ያጋጥማሉ፡፡ ከአንድ ወር በላይ ሲከታተሉት የቆዩት ወጣት ነው፡፡ ቢያንስ በቀን አንዴ ሕንፃውን ሳይጐበኝ አይውልም፡፡ የነመርዕድን ትኩረት የሳበው ግን በየቀኑ በመመላለሱ አልነበረም፡፡ በንግድ ማዕከሉ የሚሰጡትን አንዳችም አገልግሎቶች አለመጠቀሙ፣ የሕንፃውን ክፍሎች ማጥናት ሥራዬ ማለቱ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጥበቃዎችና ከሌሎች የድርጅቱ ሠራተኞች ጋር መግባባት መቻሉ፣ እንዲሁም ደኅንነት ነኝ በሚል ሰበብ መታወቂያውን ሳያሳይ ሕንፃ ውስጥ መመላለሱ ነበር፡፡ ለወር ያህል በዚህ መልኩ ከቆየ በኋላ በተደረገበት ክትትል ግለሰቡ ደኅንነት አለመሆኑ ተረጋገጠ፡፡ ጉዳዩን ፖሊስ እንዲከታተለው ተደረገ፡፡

የደኅንነት ካሜራዎች ዓላማ የሰዎችን ድብቅ ባህሪ ማጋለጥ እስኪመስል ድረስ ያልተጠበቁ ሰዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዲታዩ እያደረገ ይገኛል፡፡ ‹‹ግላዊነቴን ተጋፋኝ›› አይሉ ነገር ካሜራዎቹ የሚገጠሙት የደኅንነት ሥጋት በሚኖርባቸው ልዩ ቦታዎችና የሕዝብ መገልገያ አካባቢዎች በመሆኑ ያልተገባ ነገር ሲፈጽሙ የተቀረጹ ‹‹ምን አቀበጠኝ፤›› ብሎ በራስ ከመጸጸት ባለፈ ምንም ማድረግ የሚችሉት ያለ አይመስልም፡፡

በከተማው በሚገኝ በአንድ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ የሚሠሩት ወ/ሮ አስቴር ለማ፣ ማኅበረሰቡ ስለደኅንነት ካሜራዎች ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ የመጣ ቢሆንም፣ አሁንም አንዳንድ ክፍተቶች እንደሚታዩ ይናገራሉ፡፡ በድርጅቱ ለ16 ዓመታት ያህል የደኅንነት ካሜራዎችን በመቆጣጠር ሥራ ቆይተዋል፡፡ ድርጅቱ 150 የሚሆኑ የደኅንነት ካሜራዎች በመኪና ማቆሚያ፣ በኮሪደሮች፣ በሴልስ፣ በሊፍቶችና በመሳሰሉት አስገጥሟል፡፡

በሰው ኃይል ሊጠበቁ የማይችሉ ቦታዎች ላይ የደኅንነት ካሜራዎችን በመጠቀም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክፍተቶችን ለመሸፈን ይሞክራሉ፡፡ ‹‹እኛ ሰው እንዲጠነቀቅ አንፈልግም፡፡ እንደ ልቡ እንዲዝናና ነው የምንፈልገው፤›› የሚሉት ወ/ሮ አስቴር፣ ድርጅቱ ሰዎች የደኅንነት ካሜራ መኖሩን አውቀው እንዳይጨነቁ ሲል ‹‹በካሜራ ዕይታ ሥር ነዎት፤›› የሚለውን ማስታወቂያ አለመለጠፉን ይናገራሉ፡፡

ሐሳቡ ባይከፋም አንዳንድ ሰዎች ጥበቃ ሠራተኞች አይደርሱባቸውም ብለው በሚያስቧቸው ቦታዎች ማድረግ የሌለባቸውን ነገር እንዲያደርጉ መንገድ የከፈተላቸው ይመስላል፡፡ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ገብተው አንዳንድ የተሽከርካሪ ክፍሎችን ለመስረቅ ሙከራ የሚያደርጉ፣ መኪና ውስጥ ወሲብ እስከመፈጸም የሚደርሱ፣ አጥር የሚዘሉ ሌቦች በየጊዜው ያጋጥሟቸዋል፡፡ አልፎ አልፎም ግርምት የሚያጭሩ ክስተቶች እንደሚያጋጥሙ ወ/ሮ አስቴር ይናገራሉ፡፡ በአንድ ወቅት ካጋጠማቸው መካከልም አንዱን እንደዚህ አስታውሰዋል፡፡

በጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ የሚመስል አንድ ሰው፣ ወደ ሆቴሉ የገባው ቀይ መርሴዲስ መኪና እየነዳ ነበር፡፡ አመጣጡም በሆቴሉ በተዘጋጀ አንድ ትልቅ ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ነው፡፡ የመጣበት ፕሮግራም እንደተጠናቀቀ ወደ መፀዳጃ ክፍል ገባ፡፡ ከቆይታ በኋላ ከመፀዳጃ ቤቱ ሲወጣ ግን ባዶ እጁን አልነበረም፡፡ በመፀዳጃ ቤቱ የነበረውን የሶፍት መስቀያ (ሮለር) ይዞ ነበር፡፡

‹‹ሮለሩ ወርቃማ ቀለም ስለነበረው ምናልባት ወርቅ ይሆናል ብሎ መውሰዱ ነበር፤›› ያሉት ወይዘሮዋ፣ ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ብዙ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ ድንኳን ሰባሪዎችም ያጋጥማሉ፡፡ እንደዚህ ያሉት በደኅንነት ካሜራ የተቀዱ ቪዲዮዎች ምናልባት በሕግ ጉዳዮች እንደ አንድ መረጃ ሊያስፈልጉ ስለሚችሉ ቅጂዎች ሳይሰረዙ እስከ ስድስት ወራት ድረስ እንዲቆዩ እንደሚደረግ ወ/ሮ አስቴር ተናግረዋል፡፡

በደኅንነት ካሜራ ከሚታዩ በርካታ ኬዞች መካከል በሱፐር ማርኬቶች የሚያጋጥሙ ስርቆቶች ዋነኛው ነው፡፡ ማንም አያየንም በሚል እምነት በትልልቅ ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ ገብተው ዕቃ የሚያነሱ ጥቂት አይደሉም፡፡ እንደዚህ የሚያደርጉት ብዙዎቹ የተቸገሩ ሰዎች ሊሆኑ ቢችሉም አመል ሆኖባቸው ዕቃ የሚያነሱ ሰዎች እንደሚያጋጥሙ፣ አንዳንዶቹን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ እንደሚያደርጉ፣ አንዳንዶቹን ደግሞ በይቅርታ እንደሚያልፏቸው፣ ሳይያዙ የሚያመልጡም እንዳሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአንድ ሱፐር ማርኬት ማናጀር ገልጸዋል፡፡

የደኅንነት ካሜራዎች የመስረቅ አመል ያለባቸውን እንደ ዝነኛዋ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ብርትኒ ስፒርስና ሌሎች ታዋቂ የሆሊውድ አክተሮችንም አጋልጧል፡፡

ጓደኛው ሞባይል ስልክ ሲሰርቅ በደኅንነት ካሜራ የያው ሙሉቀን (ስሙ ተቀይሯል) ‹‹አጋጣሚው በጣም ነበር ያሳቀቀኝ፡፡ በጣም አሳፋሪ ነው፤›› ይላል፡፡ የደኅንነት ካሜራዎች ወንጀልን በመከላከልና በሌሎችም ትልቅ ፋይዳ ቢኖራቸውም ግለኝነትን ይጋፋሉ ሲሉ አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡ በዚህ ረገድ በጌት ፋም ሆቴል የሴፍቲ ኤንድ ሴኪዩሪቲ ማናጀር አቶ ካህሳይ ኃይለ፣ ካሜራዎቹ የሚገጠሙት በሕዝብ መገልገያና ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች እስከሆነ ድረስ ግለኝነትን አይጋፋም ሲሉ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የግላዊነት ጥያቄ መነሳት ያለበት የደኅንነት ካሜራዎች በሻወር፣ በመፀዳጃ ቤት እንዲሁም በሬስቶራንቶችና በመኝታ ክፍሎች ሲገጠሙ ነው፡፡ በመግቢያና በመውጫ፣ በመኪና ማቆሚያ፣ በሊፍት፣ እንዲሁም በሌሎች ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች የደኅንነት ካሜራ መግጠም ለድርጅቱ ደንበኞች፣ ሠራተኞችና ለተቋሙ ደህንነት ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን በካሜራ እይታ ሥር ነዎት የሚል ማስታወቂያ መለጠፍ ያስፈልጋል፡፡

‹‹የካሜራዎቹ መኖር ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ለመከላከልና ከሆኑ በኋላ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ይረዳል፤›› የሚሉት አቶ ካህሳይ፣ ካሜራዎቹ በሕዝብ መገልገያ ቦታዎች እስከተገጠሙ ድረስ ግላዊነትን ይጋፋሉ የሚለው አመለካከት ቦታ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...