Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊልብዎ እንዴት ነው?

ልብዎ እንዴት ነው?

ቀን:

 በየዓመቱ መስከረም 19 ቀን ከሚከበረው የዓለም የልብ ቀን ጋር በተያያዘ የተለያዩ መረጃዎችን በመገናኛ ብዙኃን ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች አማካይነት ሲያደምጡ፣ ምናልባትም ልብዎ ምን ያህል ጤነኛ ሊሆን እንደሚችል ለራስዎ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተሜነትን ተከትሎ የመጣው የአኗኗር ዘዬ ለልብ፣ ለስኳር፣ ለስትሮክና ለሌሎችም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

በኢትዮጵያ፣ በአሜሪካ ሜዲካል ሴንተር፣ ኢንተርቬንሽናል ካርዲዮሎጂስት የሆኑት ዶክተር ሰለሞን ገብረማርያም፣ ሕፃናትና ታዳጊ ወጣቶች እንዲሁም ጎልማሶችና በዕድሜ የገፉት ለተለያዩ የልብ ሕመሞች ሊያጋልጧቸው የሚችሉ አጋጣሚዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡

የልብ ሕመም ከድህነት ጋር ተያይዞ በተለይም በልጅነት ጊዜ እንደ ቶንሲል የመሰሉ ለኢንፌክሽን የሚያጋልጡ ሕመሞችን በአግባቡ አለመታከም፣ ለልብ ሕመም ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ ልጆችም በአብዛኛው ቶንሲልን ካለመታከም ጋር ተያይዞ ለሕመሙ ይጋለጣሉ፡፡

በአዋቂዎች ዘንድ ደግሞ፣ ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር ተያይዞ ስብ ማብዛት፣ አልኮልና ሲጋራ ማዘውተር የደም ዝውውርን በማወክ ለልብ ሕመም ያጋልጣሉ፡፡

      በኢትዮጵያ አብዛኛው አርሶ አደር ለችግሩ ተጋላጭ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም ከከተሜነት ጋር ተያይዞ አብዛኞቹ ሥራዎች በቢሮ ውስጥ የተወሰኑ መሆናቸው፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብዙም አለመዘውተሩና ከተማ ውስጥ የተመቻቸ ኑሮ  ያላቸውና የአመጋገብ ሥርዓታቸውን ያላስተካከሉ የችግሩ ተጋላጭ ናቸው፡፡

በዘር የሚተላለፍ የልብ ሕመም ዓይነት ቢኖርም፣ በሁሉም ደረጃ ቅድመ ምርመራ አለማድረግ፣ ሕመሙ ከተከሰተ በኋላ የሕክምና ተደራሽ አለመሆን፣ ችግሩን እንደሚያባብሱት ዶክተር ሰለሞን ይናገራሉ፡፡

ከእርግዝና ወቅት ጀምሮ የፅንሱን የልብ ደኅንነት ማረጋገጥ ለልጁ ቀጣይ ሕይወት መልካም ቢሆንም፣ ይህ በአገሪቱ በስፋት አለመለመዱ፣ በአዋቂዎች ደረጃም ቢሆን የተሟላ የቅድመ ምርመራ አገልግሎት ባለመስፋፋቱ እንዲሁም ግንዛቤው አለመኖሩ፣ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ምርመራ እንዳያደርጉ ምክንያቶች ሆኗል፡፡ ለምርመራ የሚሄዱትም በታመሙ ጊዜ ነው፡፡

እንደ ዶክተር ሰለሞን፣ የልብ ኢመርጀንሲና የመድኃኒት አቅርቦት ውስን መሆን ሕሙማንን ለመድረስ እንቅፋት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለልብ ሕሙማን ‹‹ፔስሜከር›› ለማድረግ አገር ውስጥ አቅሙ ያላቸው ተቋማትና ባለሙያዎች ቢኖሩም፣ ፔስሜከሩን ከውጭ ማስገባት ላይ ችግሮች ስላሉና አንድ ጊዜ ከገባ በኋላ በመሀል ስለሚጠፋ፣ ሕሙማን ወደ ኬንያ፣ ባንኮክና ሌሎች አገሮች እየሄዱ ሕክምናውን እንዲያገኙ አስገድዷል፡፡ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት በመኖሩም ተጠቃሚዎች ውጭ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው መድኃኒቱን ሲያስመጡ ይስተዋላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ለተላላፊ በሽታዎች የበለጠ ትኩረት ሰጥታ መሥራቷ መልካም መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ሰለሞን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ከልብ ሕመም ጋር የተያያዙ ውስንነቶችን በመቅረፍና የተሟላ ሕክምና አገር ውስጥ በመስጠት የውጭ ምንዛሪን አገር ውስጥ ለማስቀረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዕለቱ ትኩረት ባይሰጠውም፣ ሰዎችን በተለያዩ መንገድ ለልብ ችግር ያጋልጣሉ የተባሉ ነገሮችን በሚመለከት የተለያዩ ጥናቶች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ የዓለም የልብ ቀን በተከበረበት ዕለት ይፋ የሆነ ጥናት እንዳተተውም፣ ለሕመም ማስታገሻነት በስፋት የሚወሰዱ መድኃኒቶች ከልብ ሕመም ጋር ከፍተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡

በተመራማሪ ጁኦቫኒ ኮራኦ መሪነት በሚላኖ ቢካካ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው፣ በትዕዛዝም ያለትዕዛዝም የሚወሰዱ እንደ ዴክሎፌናክ፣ ኢቦፕሮፊንና ኢንዶሜታሲን ያሉና ሌሎችም የሕመም ማስታገሻዎች ለልብ ሕመም ምክንያት ይሆናሉ፡፡

ጥናቱ በአራት የአውሮፓ አገሮች ውስጥ እነዚህን የሕመም ማስተገሻዎች በሚጠቀሙ አሥር ሚሊዮን ሰዎች ላይ የተሠራ ነው፡፡ በጥናቱ ከተጠቀሱት የሕመም ማስታገሻዎች ዴክሎፌናክና ኢቦፕሮፊን በአገራችን በብዛት ይወሰዳሉ፡፡ ምንም እንኳ ጥናቱ የሕመም ማስታገሻዎቹ ሰዎችን ለድንገተኛ የልብ ሕመም የማጋለጥ ኃይል እንዳላቸው ቢያረጋግጥም፣ በቀጣይ ጥናቶች መሟላት ያለባቸው ክፍተቶች እንዳሉት ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ እንደሚለው፣ እነዚህን የሕመም ማስታገሻዎች በተለይም በከፍተኛ መጠን መውሰድ፣ ለድንገተኛ የልብ ሕመም የመጋለጥ ዕድልን ከፍ ያደርጋሉ፡፡ ሁለት ዴንማርካዊ ኤክስፐርቶች ደግሞ፣ ‹‹ትንሽ እንኳ ለልብ ጤና ችግር የሚሆን ነገር የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የሚወሰደው የሕመም ማስታገሻ ዴክሎፌናክን፣ አውሮፓ ውስጥ በማንኛውም መጠን (ዶዝ) እንዳይወሰድ፣ የአውሮፓ ካርዲዮሎጂ ሶሳይቲ መቃወሙ፣ በተለያዩ የጤና ጆርናሎች ላይ ተጠቅሷለ፡፡ በእንግሊዝ ከልብ ሕመም ጋር በተያያዘ አማካሪ የሆኑት ፋርማሲስት ሔለን ዊሊያምስ እንደሚሉት፣ በአገሪቱ የጤና ዘርፍ ኃይለኛ የሕመም ማስታገሻዎችን የመተው አዝማሚያ እየተስተዋለ መሆኑንና በንፅፅር የኢቦፕሮፊን የጎንዮሽ ጉዳት አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ የሕመም ማስታገሻ አጠቃቀም እንዴት ይታያል? ሰዎች ሲያማቸውስ ወደ ሕክምና የመሄድ ልማዳቸው እንዴት ነው? ድንገት እስትንፋስን ፀጥ ስለሚያደርገው የልብ ሕመም አስበው ያውቃሉ? ልብዎ እንዴት ነው?

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...