Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከፊልሞቹ ጀርባ ስላለው ጉዳትም ይታሰብ!

ነገሩ የሆነው በእንቁጣጣሽ ሳምንት ነው፡፡ ከበዓሉ ሰሞን በአንደኛው ዕለት ዓውደ ዓመቱን ሰበብ በማድረግ ከጥቂት ወዳጆቼ ጋር ሰብሰብ ብለን እንጨዋወታለን፡፡ አንዱ ወዳጃችን ግን ከወትሮ ይልቅ እንደሚያመሽ ለማስታወቅ ወደ ቤቱ ይደውላል፡፡ ባለቤቱን ያናግራል፡፡ ‹‹ስላመሸሁ ይቅርታ ለመጠየቅ፤ ዓውደ ዓመት ነውና የስምንት ዓመት ልጁን ‹‹ምን ይዤህ ልምጣ?›› ብሎ ፈቃዱን ለማወቅ በስልኩ ጫፍ እንድታገናኘው ይጠይቃል፡፡ ለወትሮ የአባቱን ስልክ መደወል ሲያውቅ እየተሽቀዳደመ ለመመንተፍ የሚታገለው ልጅ በዚያች ምሽት ግን ጨምቶ ነበር፡፡ አባቱን ለማናገር እንዳልፈለገ ባለቤቱ ነገረችው፡፡ ‹‹እንዴት አያናግረኝም?›› በማለት ሲጠይቃት ተመለከትነው፡፡ ጤና ስለመሆኑም አረጋገጠችለት፡፡ ቆይቶ እንደተረዳነው አባትና ልጅ በስልክ ላለማውራታቸው ምክንያት ሆኖ የተገኘው በቴሌቪዥን መስኮት ይከታተለው የነበረው ፊልም ነበር፡፡ ልጁ በቴሌቪዥኑ ላይ ዓይኑን ተክሎ ከዘመነኞቹ ፊልሞች አንዱን ይከታተል ስለነበርና ልቡ ስለተሰረቀ፣ ፊልሙን አቋርጦ አባቱን ለማናገር ጊዜ ማጣቱ ለአባት እንግዳ ነገር ነበር፡፡  

ይህ ከሆነ ከሳምንት በኋላ ከወዳጄ ጋር ስንገናኝ እንዳጫወተኝ ልጁን በስልክ ላለማግኝቱ ምክንያት የሆነው የ‹‹ዛራና ቻንድራ›› ፊልም ነበር፡፡ በነገሩ ተበሳጭቶም ስለነበር ፊልሙ የሚተላለፍበትን የሳተላት ጣቢያ አስጠፋ፡፡ ይህ ዕርምጃው በሌሎች የቤተሰቡ አባላት ዘንድ ባይወደድም፣ ትምህርት ከተጀመረ በኋላ ልጆቹ ወደ ፊልም እንዳያዘነብሉ ማሰራጫውን ማቋረጥ እንዳለበት በመወሰን የወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡ በክረምቱ ወራት ወቅት ልጆቹ ፊልሞቹን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ቢያውቅም፣ የተመረጡ ፊልሞችን እንዲያዩ የአባወራነት ትዕዛዝ አስተላልፎ ስለነበር በዚያ ትዕዛዙ መሠረት እየተፈጸመ ይመስለው እንደነበር አጫውቶኛል፡፡

የዘመነኞቹ ፊልሞች ጉዳይ የበርካታ ቤተሰቦች አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ እነ ጥቁር ፍቅርና ዛራና ቻንድራን የመሳሰሉ የውጭ ፊልሞች ጥቂት በማይባሉ ቤተሰቦች ውስጥ አብዮት አስነስተዋል፡፡ የሐሳብ ፍጭት አስከትለዋል፡፡ ሥራ አስፈትቷል ብለው የሚማረሩ እንዳሉም ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ ጣቢያ ባይጀመር ኑሮ በምን እንደበር ነበር? የሚሉ ተመልካቾችንም አፍርቷል፡፡ እንደ እኔ የቴሌቪዥን ማሰራጫው በኢትዮጵያ ሚዲያ ውስጥ ትልቅ አብዮት ፈጥሯል ብዬ አምናለሁ፡፡  አማራጭ ሆኖ መቅረቡንም እገነዘባሁ፡፡ ዕድሜ ሳይለይ ተመልካች ያገኘ ጣቢያ መሆኑን የብዙዎች እምነት ነው፡፡

የፊልሞቹ ተፅዕኖ ምን ድረስ እንደዘለቀ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ያጋጥመኝ ነገር ለዚህ አባባሌ ማረጋገጫ ሊሆን ይችላል፡፡ ለሕክምና በሄድኩበት መለስተኛ ክሊኒክ ውስጥ ያጋጠመኝ ነው፡፡ በክሊኒኩ እንግዳ መቀበያ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ የጀመረውን ፊልም እስኪጨርስ ታካሚ እንዲጠብቀው የሚያሳስብ የሕክምና ባለሙያ መመልከቴ አስገርሞኛል፡፡ ለማንኛውም ክረምቱን እንደ ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያ ያዩ ወላጆች መስከረም ሲጠባና ትምህርት ሲጀመር ልጆቻቸውን ከእነዚህ ሲኒማዎች ማራራቁ ፈተና እየሆነባቸው ነው፡፡ ልጆቻቸው ፊልሞቹን መቼና እንዴት መከታተል እንዳለባቸው ያውጠነጥናሉ፡፡ አንዳንዶቹም ፈጽሞ ወደ መከልከሉ ገብተዋል፡፡ ማየት የሚገባቸውን ፊልም እንዲያዩ መፍቀድ አለብን የሚሉም አጋጥመውኛል፡፡ የማን ዕርምጃ ትክክል እንደሆነ መበየን ቢከብድም፣ ለታዳጊዎች የዕድሜ ክልል የተከለከሉ እንደሆኑ የሚገልጹ ፊልሞች ሳይቀሩ ገደባቸው ተከብሮ እንዳይታዩ የማድረጉ ነገር ሁላችንንም ያሳስባል፡፡ ከሰሞኑ ትምህርት በሚጀመርበት ወቅት ታዳጊዎች የፊልሞቹ ምርኮኛ ሆነው ከቀጠሉ፣ የትምህርትና የጥናት ነገር ችግር ውስጥ እንደሚከታቸው አይጠረጠርም፡፡ ከፊልሞቹ አላቆ አለያም የተወሰነ ጊዜ ተመድቦላቸው እንዲመለከቱ ማድረግ ካልተቻለ ጉዳት ያመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ክልከላ የተደረገባቸው፣ ከወላጆች ዕውቅና ውጭ እያዩ በማስቸገራቸው እንዲጠፋ የተደረገውን ጣቢያ መልሰው በመጫን በድብቅ የሚያዩ፣ ወደ ጎረቤት ቤት እያቀኑ የሚመለከቱ መኖራቸውም ነገሩ ወዴት እያመራ ነው ሳያስብል አይቀርም፡፡

ፊልሞቹ በልጆቻቸው የትምህርት አቀባበል ሥነ ልቦና ላይ ጫና እንዳያደርሱ በመስጋት ከራሳቸው ጋር እየሞገቱ ባሉበት ወቅት፣ የልጆቹን ሐሳብ ይበልጥ ወደ ፊልሞች የሚገፋፋ ሁኔታ እየተፈጠረ በመምጣቱ ወላጆች ልንወያይበት ይገባል ብዬ አሰብኩ፡፡ በተማሪዎች የመማሪያ ደብተር ግብይት ወቅት እየታየ ያለው ድርጊት አሳሳቢ ነው፡፡

የእነ ዛራና ቻንድራ ምስሎች ያሉባቸውን ደብተሮች ወትውቶ ያስገዛ ልጅ፣ የተገዛለትን ደብተር ጎረቤት ላለችው ጓደኛው እያሳየ እሷም በተራዋ ወላጆቿን መቆሚያና መቀመጫ ማሳጣትዋ ከሰሞኑ የታዘብኩት ነው፡፡ የዛራና ቻንድራ ምስል ያለበት ደብተር ይገዛል የሚለውን የልጆች ውትወታ በአወንታዊ ለማስረዳትና ምላሽ ለመስጠት ስትጨነቅና ስትጠበብ የነበረች ወላጅ ታዝቤያለሁ፡፡

ይህ ሁሉ ለምን? መፍትሔውስ? ምን ይሆን እንድል አድርጎኛል፡፡ በዚህ ወቅት በድፍረት ልገልጽ የምፈልገው ነገር እነዚህን ደብተሮች፣ በውጭ ፊልሞች አክተሮች አዥጎድጉደው ወደ ገበያ ያወጡ ድርጅቶች ድርጊታቸው በሕግ የማያስጠይቃቸው ወይም መብታቸው መሆኑ ቢታወቅም፣ የደብተሮቹ ሽፋኖች አገራዊ ገጽታን በሚያሳዩ፣ ክብርና ሞገስን በሚሰጡን ቅርስና ሀብቶቻችን እንዲሸፈኑ የማድረግ ወኔ ማጣት አልነበረባቸውም፡፡ ትውልድ ለመቅረፅ ሁሉም የየራሱ ኃላፊነት አለበት፡፡ የደብተር ሽፋኖቹ የታዳጊዎችን ሥነ ልቦና የሚገነቡ፣ ልጆች ስለ አገራቸው ታሪክ እንዲያስታውሱ  ምስሎች ቢኖሩበት ምን ነበረበት? የአገራችንን ስም ያስጠሩ፣ የአገር ባለውለታዎች፣ ስንት ጉምቱዎችና ምሳሌ የሚሆኑ ዜጎችስ ጠፍተው ይሆን በዛራና ቻንድራ ምስሎች የልጆቻችን ጭንቅላት እንዲያጣበብ የሚፈቀደው? ሁሌም አብሯቸው ከሚውለው  ደብተር ጀርባ፣ ኦማርና አጎቴ ታየርን እንዲመለከቱ፣ ትኩረታቸውንም ወደ እነዚህ ፊልሞች አድርገው ትምህርታቸውን እንዳያስቡ ሊያደርግ ይችላል ብሎ ማሰብ እንዴት አቃተን? በእኔ ዕይታ ነገሩን በዚህ መልኩ እንድገመግመው አድርጎኛል፡፡

ልጆችን ለምርምርና ለፈጠራ የሚያነሳሱ ዓይነ ግቡ ቴክኖሎጂ ቀመስ ምስሎች የሉንም እንዴ? ዛሬ የእነዚህ ፊልሞች ነገር ከቀድሞም የበለጠ ሆኖብኝ እንጂ ከዚህ ቀደም ለገበያ ይቀርቡ የነበሩ ደብተሮችም ማንነታችንን የሚገልጹ አልነበሩም፡፡ የውጭዎቹ መሆን አለባቸው ከተባለም በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በሕክምና፣ በግብርናና በሌሎች የፈጠራ ውጤቶች አንቱ የተባሉ የዓለማችን ድንቅ ሰዎችን ምስል ብናደርግ ልጆች ላይ መልካም ነገር በጫርን ነበር፡፡ ወዲህም ማኅበራዊ ብሎም አገራዊ ግዴታችንን በተወጣን ነበር ብዬ እንዳስብም አድርጎኛል፡፡

አንዳንድ ጊዜ መልካም መስሎን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ የምንፈጽማቸው ተግባራት ተፅዕኗቸው አደገኛ እንደሚሆን ለማሰብ እንዳሁኑ ያለውን ነገር በጥሞና መመልከት ይገባል፡፡ ንግድ ፈጠራም ጭምር ነው፡፡ የተሻለ ሽያጭ ለማግኘት እንዲህ ባደርግ፣ እንዲህ ፈጥሬ ብሠራ ማለትን ይጠይቃል፡፡ የውድድር ጊዜ በመሆኑም ምን ባደርግ አሸንፋለሁ ብሎ ማሰብም ትክክል ነው፡፡ ገበያ እንዲስብ በማድረግ የሰዎችን የልብ ትርታ ማዳመጥ አንዱ መገለጫ ቢሆንም፣ የንግድ ሥራ ማኅበራዊ ኃላፊነት የተላበሰ መሆን እንዳለበት መሳት የለበትም፡፡

እንደ ሚዲያ ባለሙያ አማራጭ መገኘቱን የምስማማበት ቢሆንም፣ ተመልካቾቹ ማናቸው? ብሎ ገደብ ማበጀት ይገባል፡፡ ጉዳይ አጣፍጦ እንዲደመጥ፣ እንዲታይና እንዲነበብ ማድረግ ተገቢ ቢሆንም፣ ሌሎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊና ሌሎች ለሁላችንም የሚጠቅሙ አገራዊ ጉዳዮችን የምንሰማበት፣ የታዳጊዎችን አዕምሮ የሚያበለጽግ፣ የነገ አገር ተረካቢነታቸውን የሚያስታውሱ ለዛ ያላቸው ፕሮግራሞችን መቅረፅ የሁሉም ሚዲያዎችና ባለሙያዎች ኃላፊነት መሆኑን መጠቆሙ አይከፋም፡፡ ስለዚህ ለገበያ ተብለው ከሚደረጉ መሯሯጦች ጀርባ የሚፈጠረውን ተፅዕኖ ማሰብም ተገቢ ይሆናል፡፡ የአየር ሽፋንና የጋዜጣ አምዶች የሚጠይቁ በርካታ ጉዳዮች ያሉብን በመሆኑ፣ ለመዝናኛ ፕሮግራሞች የሚዘረጋው እጅም እዚህም እንዲዘረጋ፣ ለዚህ የሚለፉትም አጋዥ እንዲኖራቸው እናድርግ፡፡ እስኪ እንነጋገርበት፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት