Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤክስፖርት ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ገበያ በመታጠፋቸው የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ አፈጻጸም ተዳክሟል ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መተግበር በጀመረ በሁለተኛው በጀት ዓመት ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኤክስፖርት አገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ 271 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በዕቅዱ መሠረት በአምስት ዓመት ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፣ የበጀት ዓመቱ በገባ በሁለተኛው ዓመት፣ ሁለት ወራት ውስጥ 16 ሚሊዮን ዶላር በማስገባት የዕቅዱን 88 በመቶ ማሳካት መቻሉን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ መስፍን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊትም አንድ ቢሊዮን ዶላር ከዘርፉ ለማስገኘት ማሳካት የተቻለው ግን ከግማሽ በታች 456 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር፡፡ በየዓመቱ ሲሰበሰብ የነበረው የውጭ ምንዛሪም ከ100 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ነበር፡፡ በወቅቱ ከነበረው አፈጻጸም አንፃር ዕቅዱ ሲገመገም የተጋነነ ነበር ተብሏል፡፡ ለነበረው ደካማ አፈጻጸም የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ማነስ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በሥራ ላይ አለመዋላቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የበጀት ዓመት በሚኖረው አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ የተለያዩ የቀረጥ ማሻሻያዎችና ማበረታቻዎች ለአምራቾች ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም 152 አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ሊፈጠሩ እንደሚገባ ተገልጾ ነበር፡፡

‹‹በመጀመሪያው የዕቅዱ ዘመን የነበሩትን ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም መቅረፍ ተችሏል፡፡ 152 አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ለመፍጠር ታስቦ 90 በመቶ የሚሆነውን ለማሳካት ተችሏል፤›› የሚሉት አቶ ያሬድ፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ማነቆዎች መፈታታቸውን ከተያዘው ዕቅድ በላይ የውጭ ምንዛሪ ለማስገባት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

እሳቸው ይህንን ቢሉም፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመጀመሪያው ዓመት ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ማግኘት የተቻለው የውጭ ምንዛሪ ከተያዘው ዕቅድ በታች በመሆኑ የተያዘው ዕቅድ መከለስ እንዳለበት አመላካች ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመሪያ ዓመት 165 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት የታሰበ ቢሆንም፣ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ማግኘት የተቻለው 71 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር፡፡ ‹‹በመጀመሪያው ዓመት ብዙ ያልተስተካከሉ ነገሮች ነበሩ፤›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ ወደ ሥራው ከገቡ 53 ድርጅቶች መካከል ኤክስፖርት እያደረጉ የሚገኙት 35 ድርጅቶች ብቻ መሆናቸው፣ ምርታቸውን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡ መኖራቸው፣ ወደ ሥራው ለመግባት የሚያስፈልጉ መሬት ለማግኘት ያለው ውጣ ውረድ፣ የግንባታ ሒደት መንጓተትና ሌሎችም የቢሮክራሲ ችግሮች ለተመዘገበው አፈጻጸም አነስተኛ መሆን ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ዕቅዱ የተጋነነ አይደለም ያሉት አቶ ያሬድ፣ ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ይቻላል ብለዋል፡፡ ሌሎችም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ ሲጀምሩ ደግሞ በዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እንደሚሆን ከኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ አብዛኞቹ ድርጅቶች ከአውሮፓ ገበያ ጋር ትስስር ያላቸው በመሆኑ፣ 70 በመቶ የሚሆነው ምርት የሚላከው ወደ አውሮፓ ነው፡፡ በቀጣይ እንደ አጐዋና ኮሜሳ ያሉ ገበያዎች በስፋት ለመጠቀም መታሰቡን አቶ ያሬድ ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪው መስፋፋት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት እንደሆነና በእርሻ ላይ የተመሠረተውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ  በቀላሉ ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን እንደሚቀይረው የተናገሩት የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ፣ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም ማስተዋወቅ ግድ መሆኑን ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በሳሮማሪያ ሆቴል በቅርቡ የሚከፈተውን አፍሪካ ሶርሲንግ ኤንድ ፋሽን ዊክ ኤክስፖን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ በሚሊኒየም አዳራሽ በሚዘጋጀው ኤክስፖ በተለያዩ ጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳትና በቤት ማስጌጥ ሥራ የተሰማሩ ከ20 አገሮች የተውጣጡ 180 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡  

እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ፣ አገር ውስጥ ባለው የገበያ ሁኔታ ተስበው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የማይልኩ ድርጅቶች መኖር፣ በዘርፉ የሚኖረውን ዕድገት ዘለቄታዊነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ድርጅቶች ደረጃውን የጠበቀ ምርት አምርተው ወደ ውጭ መላክ ይኖርባቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን አገር ውስጥ ያለው ገበያም ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን ገዝቶ መጠቀም ይሰለቸውና ይተዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ተቋማቶቹ ከገበያ ውጪ ይሆናሉ፡፡ ይህም ያለውን ዕድገት ወደኋላ ይመልሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች