‹‹ከአንድ ዓመት በላይ በፖለቲካ ግጭት ያሳለፉ አገሮች ወደነበሩበት ለመመለስ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል›› ዶ/ር ተስፋቸው ታፈረ፣ የኢኮኖሚ ምሁር
በኢትዮጵያ የተከሰቱት ፖለቲካዊ ችግሮች አሁን ካሉበት ደረጃ ከመባባሳቸውና አገሪቱንና ሕዝቦቿን ለጉዳት ከመዳረጋቸው በፊት እንዲፈቱ፣ የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የንግድና የልማት ጉባዔ ባልደረባና የኢኮኖሚ ምሁር አሳሰቡ፡፡
በተመድ የንግድና ልማት ጉባዔ የአፍሪካ፣ ያላደጉ አገሮችና የልዩ ፕሮግራሞች ክፍል የቀድሞው ዳይሬክተርና የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶ/ር ተስፋቸው ታፈረ በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የወቅቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዳይባባስና ይበልጥ ጉዳት እንዳያደርስ ችግሮች በመነጋገር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
ከፖለቲካዊ አንድምታው ይልቅ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ላይ አስተያየታቸውን መስጠት እንደሚፈልጉ የገለጹት ምሁሩ፣ የፖለቲካው ትኩሳቶች በቶሎ ካልተፈቱ ግን አገሪቱ ያገኘቻቸውን የኢኮኖሚ ለውጦች ልታጣ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል፡፡ በፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ለዘመናት ልፋት የጠየቁ ለውጦች ሊጠፉ እንደሚችሉና መልሶ ለማገገም በርካታ ዓመታትን ሊጠይቅ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡
በተቃውሞ ሠልፎች፣ በብጥብጥ፣ በመንግሥት ግልበጣ ሙከራዎች፣ በእርስ በርስ ግጭትና በሌሎችም ፖለቲካዊ አለመግባባቶች የሚከሰቱ ፖለቲካዊ ቀውሶች የሚያስከትሏቸውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች በሚመለከት የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ጥናት ማድረጉን፣ በጥናቱ መሠረት አገሮች ምን ያህል ጫና እንደሚደርስባቸው መረጋገጡን አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ የፖለቲካ ግጭት የተከሰተባቸውና ከአንድ ዓመት በላይ ቀውሱ የቆየባቸው አገሮች፣ ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚገመት የንግድ ዕድልና አቅማቸውን እንደሚያጡ አስረድተዋል፡፡ አገሮቹ በገቡበት ቀውስ ምክንያት መነገድ እንደሚሳናቸውም አብራርተዋል፡፡ ‹‹ከአንድ ዓመት በላይ በፖለቲካ ግጭት ያሳለፉ አገሮች ወደነበሩበት ለመመለስ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕልፈትና መጎዳት ብሎም መታሰርና ለንብረት መውደም ምክንያት የሆነው የፖለቲካ ቀውስ ከተቀሰቀሰ ወደ አንደኛ ዓመቱ እየተጠጋ ይገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በቅርቡም በ22 ኩባንያዎች ላይ ለደረሰው ጉዳት መንግሥት የካሳ ክፍያ ለመፈጸም ጥናት በማካሄድ ላይ መሆኑን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ዶ/ር ተስፋቸው ባቀረቡት ትንታኔ መሠረት፣ መንግሥታት የፖለቲካ አለመረጋጋቶችን ለመፍታት ሰፊ ጊዜያቸውን በሚያውሉበት ወቅት ለኢኮኖሚ ጉዳዮች የሚሰጡት ትኩረት አነስተኛ ስለሚሆን፣ የአገር ልማትና ዕድገት ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖም እየጎላ እንደሚመጣ ጠቅሰዋል፡፡ በሶሪያ እየደረሰ ያለውን ውድመት በዋቢነት የጠቀሱት ምሁሩ፣ አገሪቱ ከገባችበት አዘቅት በመውጣት ቀድማ ወደነበረችበት ደረጃ ለመመለስ ምን ያህል ዓመታት ሊፈጅባት እንደሚችል ማሰቡ ቀላል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ተስፋቸው ሰሞኑን በዓለም ዙሪያ የተለለቀውንና በየዓመቱ የሚሰናዳውን የተመድ የንግድና የልማት የጥናት ሪፖርትና ውጤቶቹን ለማስተዋወቅ ከጄኔቭ በመምጣት በአዲስ አበባ ተገኝተው ነበር፡፡ ዶ/ር ተስፋቸው በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ዋና ፀሐፊ አማካሪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ዓለም ከምን ጊዜውም ይልቅ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡
ለመኖር አስከፊና አስፈሪ እየሆነች በመጣችው ዓለም የአገሮች የአኮኖሚ ዕድገት ይጠበቅ ከነበረው በታች ማሽቆልቆል ማሳየቱን፣ የዓለም የንግድ እንቅስቃሴም እየተዳከመ መምጣቱን የሚያሳየውን ሪፖርት ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ነዳጅና ብረትን ጨምሮ በርካታ ሸቀጦች የዋጋ ማሽቆልቆል አሳይተዋል፡፡ የግብርና ምርቶች በተለይ በተቀባይ አገሮች ፍላጎት ማጣት ምክንያት ዋጋቸው በመቀነሱ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የወጪ ንግድ ገቢ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ይታመናል፡፡ የአፍሪካ አገሮችን ጨምሮ በርካቶች ያልታሰበ ኢኮኖሚ ዕድገታቸው ዘገምተኛ እንዲሆን ያስገደዱ በርካታ ፖለቲካዊ ክስተቶች የተስተናገዱበት ወቅት ሲሆን፣ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት ከሚጠቀሱት መካከል እንደሚጎላ የተመድ የንግድና የልማት ሪፖርት አመላክቷል፡፡