መስከረም 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን ለማድረግ አቅዶ የነበረው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማጣራው ነገር አለ በማለቱ ጉባዔው ተራዘመ፡፡
ምርጫ ቦርድ መስከረም 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔው እንዲራዘም በመጠየቁ ሰማያዊ ጠቅላላ ጉባዔውን መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማድረግ ማቀዱን፣ የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ሰብሳቢ አቶ አበራ ገብሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጐላ በበኩላቸው፣ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲራዘም ፓርቲውን ቦርዱ የጠየቀው ከፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በቀረበ ቅሬታ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹የፓርቲው ፕሬዚዳንት ውጭ አገር ነበሩ፡፡ እርሳቸው አገር ውስጥ ባልነበሩበት ወቅት ሌሎች ጠቅላላ ጉባዔው እንዲካሄድ ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱም ሲመጡ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፤›› በማለት አቶ ወንድሙ አስረድተዋል፡፡
‹‹እኔ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ጠቅላላ ጉባዔው በደንቡ መሠረት መካሄዱን፣ ጉባዔ ለመጥራት የተሄደበት መንገድ ትክክል ነው ወይ የሚለውን ለማየትና ችግር እንዳይኖርበት ለማድረግ ለተወሰነ ጊዜ አሸጋግሩት ብለናቸዋል፤›› ብለዋል፡፡
የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን መስከረም 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትና ሌሎች አካላት ጉባዔውን ከማደናቀፍ ተግባር እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ኢንጂነር ይልቃል፣ ‹‹አንድ ሰው ጠቅላላ ጉባዔውን ሊያደናቅፍ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እነርሱ ጠቅላላ ጉባዔውን ሲጠሩም ሆነ ምርጫ ቦርድ ጉባዔውን ሲያግደው እኔ ምንም አላውቅም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ይህ ሁሉ ነገር ያጋጠማቸው አመራሩን አግልለውና ሕጋዊውን ነገር ባለመከተላቸው ነው በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም ፓርቲው ከአንድም ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ በዚያ ሒደት ውስጥ ከየትኛውም አቅጣጫ እንዲህ ዓይነት ነገር አልመጣበትም ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድም ቢሆን የእኛን ጉባዔ ሊያግደውም ሆነ ሊያስቆመው አይችልም፡፡ ለዚህ ሁሉ ነገር ያበቃቸው ሕጋዊውን ሳይሆን አቋራጭ መንገድ በመከተላቸው ነው፡፡ እኔ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራና በጉባዔው ችግሮች እንዲፈቱ እፈልጋለሁ፤›› ሲሉ ኢንጂነር ይልቃል አስረድተዋል፡፡
በትክክል ሁሉም ሰው የሚሳተፍበት ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚካሄድ ቃል ገብተዋል፡፡