Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢኮኖሚ ተቋማት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መዋላቸው የኢኮኖሚ ነፃነትን እንደሚጋፋ የአሜሪካ ጥናት ተቋም አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሮች ነፃ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የሚያጠነጥነውና የሊበራል ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለምን የሚያራምደው ሔሪቴጅ ፋውዴሽን የተሰኘው የአሜሪካ የጥናት ተቋም፣ ኢትዮጵያን በአብዛኛው የኢኮኖሚ ነፃነት ከሌለባቸው አገሮች ተርታ ፈረጀ፡፡ መንግሥትም በኢኮኖሚ ተቋማት ያለው የበላይነትና ቁጥጥርም አገሪቱን በዚህ ደረጃ እንድትፈረጅ ማድረጉን፣ የጥናት ተቋሙ ተመራመሪና ምሁር ገልጸዋል፡፡

ላለፉት አርባ ዓመታት በዓለም አገሮች የኢኮኖሚ ነፃነት ላይ ጥናት በማድረግ ሪፖርት ሲያወጣ የቆየው የሔሪቴጅ ፋውንዴሽን ተመራማሪና የኢኮኖሚ ምሁሩ ጀምስ ኤም. ሮበርትስ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት እጅ ረጅም በመሆኑ የፋይናንስ ተቋማት፣ የንግድና የኢንቨስትመንት መስኮች ጫና ውስጥ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

ዓመታዊው የሔሪቴጅ ፋውንዴሽን ሪፖርት ኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ነፃነት የሌላት ካለባቸው ነጥቦች መካከል ደካማ የሕግ የበላይነት መንሰራፋቱ ከሌሎች መመዘኛዎች ይልቅ የጎላው ሆኗል፡፡ ከዓለም አገሮች ታጃኪስታንን ቀድማ 148ኛ ሆና ተቀምጣለች፡፡ ከአፍሪካ አገሮች አኳያም በ37ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ በሪፖርቱ መሠረት የተጨቆኑ ኢኮኖሚዎች ከሚባሉት ተርታ ብዙም እንደማትርቅ ከአገሮች አኳያ ያላት ንፅፅር ያሳያል፡፡

አገሪቱ በአብዛኛው በመንግሥት የበላይነት በተያዙ የመንግሥት ቁጥጥር የበዛባቸው ኢኮኖሚ አውታሮችን እንደምትመራ የሚጠቅሱት ሮበርትስ፣ የግሉ ኢኮኖሚ እንደ ልቡ ለመሥራት የሚቸገርባቸው አሠራሮች ስለሚበዙም ከአሜሪካ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት የነበራቸው ባለሀብቶች ሐሳባቸውን ለመቀየር እየተገደዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት እንደ ባንክና ቴሌኮም ያሉ ተቋማትን በገበያ መር ሥርዓት እንዲተዳደሩና የውጭ ኩባንያዎችም እንዲገቡባቸው አለመፍቀዱን ተችተዋል፡፡

በጠቅላላው በሪፖርቱ እንደሚታየው የመንግሥት የቢሮክራሲ ጥልፍልፍ መሆን እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ እንደሚፈታተነው፣ በዓለም ገበያ መድረክም አገሪቱ የምትዳኝባቸውን የገበያ መርሆዎች ያላከበረ አካሄድ በሰፊው እንደሚታይ ይተነትናል፡፡

በጥናት ሪፖርቱ ዳራ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመሩት ፓርታና መንግሥት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሙሉ በሙሉ በምርጫ ማሸነፉን ካወጀ ጀምሮ ነፃ የኢኮኖሚ ተግባራት አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችንና የሲቪል ማኅበረሰቡን እንቅስቃሴና የገለልተኛና የነፃ ሚዲያ ተቋማትን እንቅስቃሴ የሚገድቡና ከፍተኛ ቁጥጥር የሚያደርጉ ሕጎች መውጣታቸው የአገሪቱን የዴሞክራሲ ምህዳር ይበልጥ እያጠበበው እንደመጣ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ እነዚህ ነጥቦች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ነፃነት ላይ ጫና ማሳደራቸውን ያሳያል፡፡ በጠቅላላው አገሪቱ ከመቶ መመዘኛ ነጥቦች 51.5 በመቶ በማስመዝገብ በአብዛኛው ነፃነት የሌላቸው በሚባሉት ተርታ እንድትመደብ አድርጓታል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች