በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ አገር በቀል ኩባንያዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለውን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት ኮሚቴ አቋቁሞ ጥናት ቢያስጠናም፣ በጥናቱ ላይ ተመርኩዞ እስካሁን ውሳኔ ባለመስጠቱ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን አመለከቱ፡፡
በሁለቱ ክልሎች በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ30/70 የብድር ፖሊሲ መሠረት ከሁለት ዓመት በፊት መሬት ወስደው ኢንቨስት ቢያደርጉም ብድር ማግኘት ባለመቻላቸው ለችግር ተዳርገዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተለይ በመሬት ዘርፍ ላለው መጠነ ሰፊ ችግር በ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር መስጠት እንዲያቆም፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ደግሞ መሬት መስጠት እንዲያቆም ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት ጥናት እንዲጠና ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፣ ሲካሄድ የቆየው ጥናት ከወራት በፊት መጠናቀቁን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
የጋምቤላና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሀብቶች እንደገለጹት፣ ለልማት ባንክ ብድር እንዲሰጣቸው ካመለከቱ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለሀብቶቹ በተለይ ከ2007 ዓ.ም. በፊት ብድር ማግኘት ያልቻሉት በመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በአጠቃላይ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዕርምጃ ለመውሰድ ጥናት እንዲካሄድ መወሰኑ በበጎ የሚታይ ቢሆንም፣ በጥናቱ ላይ ውሳኔ ባለመስጠቱ ግን ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ አንዱ ተወልደ ብርሃን ኃይሌ እርሻ ልማት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ከጋምቤላ ክልል አበቦ አካባቢ አንድ ሺሕ ሔክታር መሬት ቢፈቀድለትም የተረከበው 500 ሔክታር መሬት ነው፡፡
የድርጅቱ ባለቤት አቶ ተወልደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር እንዲፈቅድ ጥያቄ ያቀረቡት ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት መስከረም 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡
‹‹ብድሩ ሁለት ጊዜ በመሬት መደራረብ ምክንያት፣ ሁለት ጊዜ በፖሊሲ ለውጥ ምክንያት ሳይፈቀድ ቀረ፤›› በማለት የገለጹት አቶ ተወልደ፣ ‹‹ሦስት ጊዜ ለውሳኔ ቀርቦ ውሳኔ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ በመጨረሻ ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ብድር እንዲቆም በማለቱ እስካሁን በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፤›› ሲሉ ጉዳዩ ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል፡፡
‹‹ልማት ባንክን አምነን ገንዘባችን አፍስሰናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፋጣኝ ጉዳያችንን ሊያዩልን ይገባል፡፡ ገንዘባችንን መሬት ላይ በማፍሰሳችን ልንበረታታ ነው የሚገባን፤›› ሲሉ አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡
ክብሮም ገብረየስ የእርሻ ልማት ድርጅትም ተመሳሳይ አቋም አለው፡፡ የድርጅቱ ባለቤት አቶ ክብሮም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመሬት መደራረብ ምክንያት መጀመሪያ የተሰጣቸው መሬት ቀርቶ ሌላ 500 ሔክታር መሬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 105 ሔክታር መሬት መንጥረው ወደ ሥራ ቢገቡም፣ ብድር ማግኘት ባለመቻላቸው ለችግር መዳረጋቸውን አቶ ክብሮም ይናገራሉ፡፡
‹‹ብድር ለማግኘት ሁለት ዓመት ተመላልሻለሁ፡፡ ጂማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምዕራብ ቅርንጫፍ ኦፊሰሮች ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት ችግሩ የእነሱ እንዳልሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የባንኩ ኃላፊዎች ባለቤት እንዳልሆኑ ይናገራሉ፡፡ ዋነኛው ባለቤት የሆነው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለምን አፋጣኝ ምላሽ አይሰጥም?›› ሲሉ አቶ ክብሮም ይጠይቃሉ፡፡
ከጋምቤላ በተጨማሪ የቤንሻንጉል ጉሙዝ እርሻ ኢንቨስተሮችም ተመሳሳይ ችግር እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ ሰለሞን ለይኩን እርሻ ልማት ድርጅት በቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ቤንጉ ቀበሌ አንድ ሺሕ ሔክታር መሬት ተረክቦ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ የድርጅቱ ባለቤት አቶ ሰለሞን እንደገለጹት፣ መሬቱን በ2006 ዓ.ም. መጨረሻ ተረክበው በሙሉ ኃይላቸው ወደ ሥራ ለመግባት የጀመሩት ፕሮጀክት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር አልቻሉም፡፡
‹‹በሌሎች አገሮች መንግሥታት ለእርሻና ለኢንዱስትሪ ከወለድ ነፃ ብድር ያቀርባሉ፡፡ እኛ ዘንድ ግን ይህ ቀርቶ ባለው ሕግ እንኳ መስተናገድ አልቻልንም፤›› ሲሉ በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ብድር እንዲቆም ያደረገው ከ43 በላይ ቦታዎች ተደራርበው ለባለሀብቶች በመሰጠታቸው፣ በአንድ መሬት ሁለት ኢንቨስተሮች የተለያየ ብድር በማግኘታቸው፣ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ብድር ከወሰዱ በኋላ እየተሰወሩ በመሆናቸው ምክንያት እንደሆነ መንግሥት መግለጹ ይታወሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የፀጥታ፣ የመልካም አስተዳደርና የገበያ ትስስር ችግሮች በመኖራቸው፣ እነዚህን በጥናት ለመመለስና የአሠራር ለውጥ ለማድረግ መሆኑን ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ይጠቁማል፡፡
ባለሀብቶቹ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያለበቂ ሥራ ማሳለፋቸውን አመልክተው በ2009 ዓ.ም. የግብርና ምርት ዘመን የተሻለ ሥራ ለመሥራት የግድ ብድሩ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የተካሄደው ጥናት ቢጠናቀቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለባቸው የሥራ መደራረብ ምክንያት ውሳኔ አልተሰጠበትም፡፡