Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው

በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው

ቀን:

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል በመሆንና ዓላማውን ለማስፈጸም በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ላይ ነበሩ የተባሉ አራት ተጠርጣሪዎች፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች ጥላሁን ኢዶሳ፣ አደም ሁሴን፣ ኦሮሚያ ረቡማና ያደሳ ነጋሳ የሚባሉ መሆናቸውን በክሱ ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ በ2005 ዓ.ም. ኬንያ ውስጥ ዲነዲን በተባለ የኦነግ አባል ተመልምለው፣ በኬንያ ሶሎሎ በሚባለው ካምፕ በመግባት ለአንድ ወር ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና መውሰዳቸው በክሱ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጥላሁን ኢዶሳ የተባለው ተከሳሽ ሥልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላ በ2008 ዓ.ም. ኅዳር ወር ውስጥ ወደ ነገሌ ቦረና በመምጣት ኦሮሚያ ክልል ወሊሶ፣ ወለጋ ነቀምትና ዳሌሞበራ ከሚገኙ ጓደኞቹ ጋር በተለያዩ የሞባይል ስልኮች ይገናኝ እንደነበርም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መረጃ በመቀበልና ጓደኞቹንም ጠንክረው እንዲሠሩ መመርያ በመስጠት፣ ማንኛውንም ነገር በጥንቃቄ እንዲሠሩ በመምከር፣ በመሣሪያ ብዛት በማጠናከር ወደ ትግል እንዲገቡ ማሳሰቢያ ሰጥቶ ወደ ኬንያ ሶሎሎ መመለሱን ክሱ ያስረዳል፡፡

ለተከሳሾቹ ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት በኦሮሚያ ጉጂ ዞን ሰባበሩ ወረዳ ዳርሜ ከተማ ሲንቀሳቀሱ መክረማቸውን፣ ጥላሁን የሚባለው ተከሳሽ አሥር ሺሕ ብር ለተልዕኮው መፈጸሚያ ገመቹ አብዬ ከተባለ የኦነግ አመራር እንደተላከለትና በተለያዩ ስልኮች በመጠቀም ወለጋ አካባቢ ከሚኖሩ በርካታ ተጠርጣሪዎች ጋር ግንኙነት እንደነበረው ክሱ ያስረዳል፡፡ ተከሳሾቹ ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ለአሜሪካ ድምፅና ኬንያ ለሚገኙ አመራሮች ሪፖርት ሲያደርጉ እንደነበርም በክሱ ተገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ የኦነግ አባል በመሆን ወታደራዊ ሥልጠና በመውሰድና ወደ ኢትዮጵያ በመግባት፣ የኦነግን ተልዕኮ ተቀብለው አመራርና መረጃ በመስጠትና በመቀበል፣ በሽብር ቡድን ውስጥ በመሳተፍ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1)ን በመተላለፍ ተሳትፈዋል የሚል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ ጠበቃ ቀጥረው መከራከር እንደማይችሉ ክሱን በተረኛ ችሎት ለተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አቅርበው፣ የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመድብላቸው ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ተቀጥረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...