እነሆ መንገድ። መንገዱን ተናጋሪ ሞልቶታል። አንዱ ሲጨርስ አንዱ ይተካል። አንዱ ሳይጀምር ሌላዋ አቋርጣ፣ ቆርጣ ትቀጥላለች። ዘንድሮ ቆርጦ በመቀጠል የወግ ዲግሪ የጫኑት ተማርን ከሚሉት በዝተዋል። መንገዳችንም ያንን ለትዝብት አልፎ እየሰጠ ያስጉዘናል። ውሎ ማደር እስከሆነልን ድረስ ለጠዋት ትዝብት ለማለዳ አያድርስ የምንሰማው ዜና አናጣም። ከግራ ከቀኝ ከላይ ከታች ትርምስና እርግጫ የሚበዛው ይኼ ጎዳና የእግዚኦታ ታሪክ ሲቀምር ፀሐይ ወጥታ ውላ ታዘቀዝቃለች። ‹በመሸው ጎዳና ፀጥ ባለው መንገድ፣ እንወዝወዝና አብረን እንሰደድ› ሆኖ ግጥሙና ዘፈኑ፣ ሲነጋ የተቋጠረ ትልም ሲመሽ አላልቅ ሲል ዘፈን፣ አብዮት፣ ግጥም፣ እሳት ይጭራል። ስለዚህ ለአገሬ ባይ ሁሉ ይገጥማል። ያቺም ትገጥማለች። እነዚያም ይዘፍናሉ። አገሩ ከዘፈንና ከልግጫ ውጭ የሐሳብ ኮንሰርት አላስተናግድ ብሎ መንገዱ ነግቶም መሽቶም ያው ፅልመት የዋጠው አውድማ ይመስላል።
“አንተ ቶሎ ቶሎ ጫን እንጂ። ቤት ደርሰን ችቦ እናበራለን እኮ?” ይሉታል አንድ አባወራ ወያላውን። “በደቦ ያበራነው አይበቃም እንዴ? በተወደደ ኑሮ ለምን ብቻውን ችቦ ያስበራዎታል?” ይላቸዋል። “አንድያው! ወሬ ሲሆንማ አንደኛ ናችሁ፤” ብለው ሰውዬው ሲያጉተመትሙ ቆዩና፣ ‹‹አሁን የኑሮ ውድነትና ችቦ ማብራትን ምን ያገናኛቸዋል? የዋጋ ንረትንና ደመራን ምን ያገናኛቸዋል? ከመንግሥት ጋር ስንጣላ ለማየት ካልሆነ በቀር?” አሉት ወያላውን። “እንዴት አይገናኝም? በተወደደ ችቦ በየቤቱ እሳት ሲለኮስ ነውር አይደለም እንዴ? የእህል ብቻ አይደለም የችቦም ግፍ አለው፤” ሲል ተሳፋሪዎች በሳቅ ፈረሱ። “ወይ አፍ? እንዲያው ይኼን አፋችሁን ይዛችሁ በየመንገዱ ባክናችሁ ትቀሩ?” ሲሉት፣ “ፓርላማ ከመግባት መንገድ ላይ መቅረት አይሻልም? ማለቴ ዘንድሮ እኮ የመንገዱን ያህል ፓርላማው እሳት አያነድም፤” ብሎ አስጨበጨበን። የአንዳንዱን ሰው ሐሳብና ዕውቀት ሥራው ሲሸፍነው ማየት መቼም አለመታደል አይደል?
ጉዟችን ተጀምሯል። መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ወጣቶች ሳቅና ሁካታ ጆሮ ይበሳል። “ኧረ ድምፅ. . . ድምፅ በዛ. . .” ይላል ወያላው። “ቴሌቪዥን መሰልንህ እንዴ? ይኼኔ እኮ በሪሞት የምንሠራ ቢሆን አታፍርም ‹ሚውት› ታደርገን ነበር፤” አለው አንደኛው። አሁንም ትርጉም አልባ ሆሆታ ናኘ። ወያላው ‘አልነጋገርም’ ብሎ ዝም አለ። “የቴሌቪዥንን ነገር ካነሳህስ? አለ አንደኛው ወደ ወዳጁ ዘወር ብሎ፣ ‹‹ዛሬ ማታ አንጋፋው ኢቢሲ ደመራውን አስመልክቶ ምን ብሎ ዜና የሚሠራ ይመስልሀል?” ሲል ጠየቀው። ያኛው ድምፁን አጎርንኖ ከአራምባ እስከ ቆቦ በተራራቁ ዘገምተኛ ቃላት ዓረፍተ ነገር እየመሠረተ፣ “ዘንድሮ የተከበረው የደመራ በዓል የአገሪቱን ዘላቂ ልማትና ዴሞክራሲ ለማስቀጠል ያለው አቅም ከፍተኛ ነው ሲሉ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ ይልለሃላ፤” ብሎ ሆዱኔ ይዞ ሳቀ።
“ምንድነው ዛሬ ሰው ሁሉ ከሳቅ ትምህርት ቤት ነው እንዴ የተለቀቀው?” ትለኛለች ሦስተኛው ረድፍ ላይ ከጎኔ የተሰየመች ወይዘሮ። “እኔ እኮ እነዚህ ‹አንዳንድ› የሚባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የት ይሆን የሚኖሩት?” ይላል የወዲያኛው። “ምን ለማለት ነው? እዚሁ ነዋ። ይልቅ እንደ እሱ ከምትል ለምን አንድኛውን አንዳንድ የሚባል ክፍለ ከተማ አይመሠረትላቸውም በል?” አለው። “ኧረ እውነትህን ነው። እንደዚህ ሆደ ሰፊ፣ ሁሉን ነገር በታጋሽነትና በተስፈኛ ልቦና የሚመለከቱ የመላዕክት እኩዮች አንድኛውን ክፍለ ከተማ መሥርተው እኛንም ቢያካትቱን እንዴት ጥሩ ነበር?” ሰትል አጠገባቸው የተሰየመች ወጣት፣ “አይ ጊዜ. . . ሰው እንደ አሜሪካኖች ሆሊውድ የሚባል የፈልም መንደር ይመሠርታል እንጂ የዜና መንደር ይመሠርታል? ብትል፣ “ፊልም ሆነ ዜና ምንድነው ለውጡ?” ብለው አባወራው ወያላው ላይ ያፈጣሉ። የማይፈጠጥበት ላይ ስናፈጥ ዜናና ፊልሙ ተደበላለቀብን ዘንድሮ!
ጉዟችን ቀጥሏል። ጋቢና የተሰየመ ወጣት ፌስቡክ ሲጎረጉር ቆይቶ ቀና አለ። “ኧረ በስንቱ ልሳቅ?” እያለ ይሳለቃል። ሾፌሩ፣ “ምን ተገኘ?” ይለዋል። አንድ ምስኪን ታዳጊ የወዳደቁ ዕቃዎች ለቃቅሞ ከበሮ ሲጫወት ያያል። “ማን ፖስት ቢያደርገው ጥሩ ነው? ኢቢሲ!” ሲል ሁሉም ስልኩን ላጥ ላጥ አድርጎ አውትቶ ፌስቡኩን ከፍቶ ኮሜንት ማንበብ ጀመረ። አንዱ፣ “ተሰጥኦ ካለ ሌላው አይቸግርም የሚሉን እኛ ነው ድራመሩን?” ይላል። “ልጁማ ልጅ ነው። ምን ያውቃል? እኛን ነው እንጂ። ሥራ አጣሁ ብሎ ሰበብ ከመደርደር ኮብልስቶን መደርደርም ሥራ ነው ነው እኮ ነገሩ፤” ይላል ሌላው። “አቤት ቀናነት እንዲህ ራቀን በቃ”? ሲሉ አባወራው፣ “የተማረ ሥራ አጥ ከበዛ ወዲህ መሰለኝ የባሰብን፤” ትላቸዋለች ከጎናቸው የተሰየመች። “አንቺ ለመሆኑ ተመርቀሻል?” አሏት። “ያውም በሙዚቃ ነዋ፤” አለቻቸው። “ሙዚቃ? ለሙዚቃ ስትይ ዲግሪ አጠናሽ?” አሉ አፋቸውን ከፍተው፡፡
“ታዲያ ዘንድሮ የሚያስበላ የሚያስበላው ነገር ሁሉ በኮኔክሽን ተይዟል። እንደምንም አንድ ዜማ አቀናብሬ ወይም አቀንቅኜ እዚያው የፈረደባት አሜሪካ ሄጄ እቀራለሁ ብዬ ነዋ። ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው ላሰበበት. . .?” ብትላቸው ሐቲታቸው ተበልቶ ድርቅ እንዳሉ ቀሩ። ‹‹አባት ምነው?” አለ ወያላው ደንግጦ። “እንጃ ልጄ እዚህ ግራ ጎኔ ሥር ይወጋኛል። ከዚህ በላይ መአት ሳልሰማ ሊሸኘኝ ነው መሰል?” ሲሉት፣ ‹‹ኧረ እንደሱማ ብሎ ነገር እዚያው የሚሸኙበት ይሸኛሉ እንጂ፣ እኔ ታክሲ ውስጥ ከምሸኘው ሰው ሌላ የሚሸኝ የለም፤” ብሎ ተቆጣ። ይኼኔ ነው ቀና ብለው በእርጋታ፣ “አትቆጣ! ሞትን በቁጣ አታባርረውም ታዛምተዋለህ እንጂ፤” ያሉት። ወይ ቅኔ!
ወያላው ሒሳብ ተቀብሎ ሣንቲም እየቆነጠረ መልስ ይመልሳል። መካከለኛው ረድፍ ላይ ሁለት ወጣቶች ስለሱስ ያወራሉ። “ኧረ የኢንተርኔት ሱስ ሊገለኝ ነው?” ይላል አንደኛው። “የፌስቡክ ሱስ አትልም?” ያሳጣዋል ሌላው። “አንተ ደግሞ! ብለህ ብለህ በሰው ሱስ መቅናት ጀመርክ?” ሲል ጨዋታውን የጀመረው፣ “በል በል ባሳደገን ባህላችን እንዳትመጣ። ስንፈጠር ባገኘነው ሁሉ እንደቀናን እንድንኖር የታዘዝን ነን። ይኼ ሁሉ ሰው ርስት ተነጥቆ እንዳልጎደለበት አንገቱን ደፍቶ የሚኖረው ለምን ይመስልሃል? የማይወረሱ፣ የማይከለከሉ፣ የጠመንጃ አፈሙዝ የማይደነቅባቸው ሀብቶች ስላሉት ነው እሺ? ምን ሌማቱ ባዶ ቢሆን በቅናት፣ በሀሜት፣ በጥርጣሬ፣ በወሬና በአሉባልታ ጎተራው ያልሞላ በባትሪ ብትፈልግ እንደማታገኝ እወቅ፤” ልጁ ሲናገር እንደ ማስፈራራትም ይቃጣዋል።
“ምን ባትሪ አስገዛህ ፀሐይ እያለችልህ?” ሲል ጎልማሳው ወዲያ ጋቢና ከተሰየሙት እንስቶች አንደኛዋ፣ “ስለየትኛዋ ፀሐይ ነው የምታወራው?” እያሉ መጨረሻ የተቀመጡት ተንሾካሾኩ። “አዛውንቷ ሆሆ! ስንት ፀሐይ ኖሯል? አንድ መስላኝ?” ብለው ተደናገጡ። “ምን አውቄ እማማ! ዘንድሮ የማይሰማ ጉድ የለም። ምናልባት አልሰማን እንደሆን እስኪ አንዳችሁ ‘ጉግል’ ላይ፣ ‘ፀሐይም እንደ ሰው በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት ተከፋፍላ ከሆነ’ እስኪ ሰርች አድርጉና ንገሩን?” ትላለች። ምነው ቴክኖሎጂ እያደር የነገርና የትንግርት ወንፊቱን እያሻሻለ ሲጓዝ ስለራሳችን የምንፈለፍለበት መሣሪያ ነፈገን አያስብልም ይኼ? ይኼ?
ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። “ዕፎይ ተገላገልኳችሁ” ይላል ወያላው። “ምን አደረግንህ? ይኼን ያህል?” አንዲት ወጣትነት። “ከግብርና መር ኢኮኖሚ አለመውጣታችን ነው እንጂ ምን ያላደረጋችሁኝ ነገር አለ ዘንድሮ? እንደ በለፀጉት አገሮች ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ያላት አገር ብትሆን እኮ በዕለተ ደመራ በዚህ አፋችሁ አያይዛችሁኝ ነበር፤” ሲል ነገሩ ወዲያው ገባን። “ተው የሰው ስም አታጥፋ። ዘንድሮ ብሶት ከመናገርና ጥያቄ ከማቅረብ የተረፈን በጩኸታችን ዝናና ክብር የሚገዙ ራስ ወዳዶች የፖለቲካ ትርፍ ነው። አንተም ከነዚያ ወገን እንዳትሆንና እንዳናኮርፍ፤” አሉት አዛውንቱ። “እኔ እኮ ያልኩት በዚህ አፋችሁ እንዲህ በነፃነት ያሻችሁን ስታወሩ በቴክኖሎጂ ስላለ የዳበረ አገር ቢሆን እናንተን ሳይሆን እኔን ነበር ከነታክሲዬ አፍሶ የሚወረውረኝ ነው ያልኩት። ለልማት እንጂ ለወሬ ማደራጀት እኮ ገና አይፈቀድም፤” ሲል፣ “በል ዝም በል የማታውቀውን አታውራ፤” አለችው አንዷ ነገረኛ፡፡
“እኛን የሰለቸን ይኼ ይኼ ነገር ነው። አገራቸው ላይ ቁጭ ብለው በዕውቀትና በማስተዋል በኃላፊነት ያሻቸውን የሚናገሩ እከሌ እከሌ የሚባሉ ሰዎች ባሉባት አገር፣ መንግሥት እንዲህ እንደ ጭራቅ እንደ ሰይጣን የሚሳልበት ምክንያት አይገባኝም። ነው የትናንቱ የደርግ ጠባሳ አልሻረልንም? ምንድነው እንዲህ በሹክሹክታ፣ በሽሙጥና በሐሜት ፍቅር ክንፍ ብሎ እያዩ አለማየት? ለምንድነው ዓይናችን ሥር ያለውን ገሀድ የማናየው? የትኛው አገርስ ነው በአንድ ሌሊት ተገንብቶ፣ ተስማምቶ፣ ተፈጣጥሞ ያደረው? ምንድነው ግን እንዲህ ለዲስኩርና ለአሉሽ አሉሽ ቀዳዳ ስንቦረቡር መኖር? ኧረ አያምርብንም በቃ፤” ብላ ልክ ልካችን ነግራን ስታበቃ ታክሲያችን ጥጓን ይዛለች። ዲስኩርና ፖለቲካ ለየቅል። አወዳደቄን ብቻ ሳይሆን አወራረዴን አሳምረው ታክሲ ላይም ይሠራል ጎበዝ! መልካም ጉዞ!