Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየጉራጌ ሴቶች በመስቀል

የጉራጌ ሴቶች በመስቀል

ቀን:

የመስቀል በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ንግሥት እሌኒ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡ ንግሥቲቷ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ቂራቆስ በተባሉ አባት ጠቋሚነት ለማግኘት ደመራ አስደምራ ፍለጋ የጀመረችው መስከረም 17 ቀን እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ የሃይማኖት አባቶችን አሰባስባ በፀሎት እንዲረዷት ጠይቃ፣ ከደመራው በሚወጣው ጢስ ጠቋሚነት መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አግኝታለች፡፡ መስቀሉም ከወራት ቁፋሮ በኋላ ወጥቷል፡፡ ከዚያን ወቅት ጀምሮ  መስከረም 16 ቀን የደመራ ሥነ ሥርዓትና መስከረም 17 የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡

በንግሥት እሌኒ አማካይነት ከተቀበረበት የወጣው መስቀል ክፋይ በሰሜን ኢትዮጵያ በግሸን ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚገኝ ሲሆን፣ በዓሉን ለማክበር ወደ አካባቢው የሚሄዱ በርካቶች ናቸው፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ መስቀል አደባባይ ላይ ከሚካሄደው ታላቅ የደመራ ሥነ ሥርዓት በተጨማሪ በየአድባራቱና በየመኖሪያ ቤት ደጃፍም ደመራ ይደመራል፡፡ ተመሳሳይ አከባባር በሌሎች ከተሞችም ይከናወናል፡፡ በየአካባቢያቸው በዓሉን የሚያከብሩ ሰዎች በአደይ አበባ ያሸበረቀ ችቦ ደመራ አብርተው በነጋታው (በመስቀል በዓል ዕለት) ማለዳ ችቦው የበራበት ቦታ በመሄድ በአመዱ ግንባር ላይ የመስቀል ቅርፅ የመሥራት ልማድም አለ፡፡

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘት እንዳለ ሆኖ በየአካባቢው እንደየማኅበረሰቡ ባህልና ወግም ይከበራል፡፡ ከሌሎች ዐውደ ዓመቶች የመስቀል በዓል በተለየ በድምቀት በሚከበርባቸው አካባቢዎች የብዙ ጎብኚዎችን ትኩረትም ይስባል፡፡ በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በዓለም ቅርስነት የሰፈረውም ለዚሁ ነው፡፡

መስቀል ሲነሳ የጉራጌ ብሔረሰብ ለበዓሉ የሚሰጠው ልዩ ቦታ ተያይዞ ሊወሳ ይችላል፡፡ የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ስለ በዓሉ አከባበር ባዘጋጀው ጽሑፍ መስቀል፣ ‹‹የመስቀል በዓል የጉራጌ ብሔረሰብ የበአላት ሁሉ አውራ ሆኖ ለዘመናት ሲያከብረው የነበረና የሚቀጥልም በዓል ነው፤›› በማለት ተገልጿል፡፡ ከደመራና መስቀል ቀናት በፊትና በኋላም በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች የሚከበረው መስቀል፣ የጉራጌ ተወላጆች ወደቀዬአቸው በመሄድ በአንድነት የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡

የመስቀል በዓል አከባበር ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በተለያየ ሥነ ሥርዓት የሚቀጥል ሲሆን፣ ሴቶች ከበዓሉ ዝግጅት ጀምሮ በልዩ ሁኔታ የሚያከብሯቸው ዕለቶችም አሉ፡፡ መስቀል በጉራጌ ትልቅ በዓል እንደመሆኑ ዝግጅቱም ሰፊ ነው፡፡ የመስቀል በዓል ከተከበረበት ዕለት ጀምሮ ለሚመጣው ዓመት መስቀል መሰናዶ ይጀመራል፡፡ ከትውልድ ቀዬአቸው ርቀው የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ለመስቀል በዓል ቤተሰቦቻቸውን ለመቀላቀል ውሳኔ ላይ የሚደርሱትም ከወራት በፊት ነው፡፡ ተወላጆቹ የአቅማቸውን ያህል ገንዘብ አጠራቅመው ወደ  ትውልድ መንደራቸው ያቀናሉ፡፡

ለመስቀል በዓል ዝግጅት ሲደረግ ሥራ በጾታና በዕድሜ ይከፋፈላል፡፡ በዚህ መሠረት ልጆችና ወጣት ወንዶች ለደመራ የሚሆን እርጥብ እንጨት ከጫካ ለቅመው፣ ከደረቀ በኋላ ይፈልጣሉ፡፡ በዕድሜ ከፍ ያሉት አባወራዎች ደግሞ ለበዓሉ የሚታረዱ ከብቶችን ሳር በመቀለብ ያደልባሉ፡፡

ሴቶች በበኩላቸው ለሚመጣው መስቀል በዓል የሚሆን ቅቤ ማጠራቀም የሚጀምሩት የመስቀል በዓል እንደተጠናቀቀ ነው፡፡ የወራት ዝግጅታቸው ቤት ማሳመርንም ያካትታል፡፡ በዓሉ ሦስት ወራት ሲቀሩት መሰናዶውም ይጧጧፋል፡፡ ወጣት ሴቶች ቤት ቀለም ሲቀቡ፣ የእማወራዎች ድርሻ እንሰት ፍቆ ማዘጋጀትና ጅባ መሥራት ይሆናል፡፡ በተለይ የቡሔ በዓል ከተከበረ በኋላ የመሰናዶውን ፍጥነት ይጨምራሉ፡፡ 

የጉራጌ ሴቶች የመስቀል በዓል መከበር በሚጀምርበት መስከረም 12 ቀን ለምግብ ማቅረቢያ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ከግርግዳ ያወርዳሉ፡፡ ዕለቱ ሌማት ይወርድቦ ቀነ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በዕለቱ የመመገቢያ ቁሳቁሶች እንዲሁም ቤት ይፀዳል፡፡ በየቤቱ አዳዲስ ጅባዎች ይነጠፋሉ፡፡ ቀጣዩ ቀን ወሬት ያሸና ወይም ወልቀነ ይባላል፡፡ ሴቶች የጎመን ክትፎ የሚያዘጋጁበት ሲሆን፣ ከቆት የሚበላበት ዕለት በመባል ይታወቃል፡፡

በጉራጌ ባህል መስከረም 14 ደንጌሳት ይባላል፡፡ የጎመን ክትፎ በሸክላ ጣባ ለመላው ቤተሰብ የሚቀርብበት ዕለት ነው፡፡ በዕለቱ የሚወጣውን ወጪ በሙላ የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ሴቶች ዓመቱን በሙሉ ለመስቀል ባጠራቀሙት ገንዘብ ሙሉ ዝግጅቱን ሸፍነው ቤተሰባቸውን ያስተናግዳሉ፡፡ በደንጌሳት ማታ በየቤቱ ደመራ ይለኮሳል፡፡ ሥርዓቱ የባዮፕ ኧሳት ቀን ይባላል፡፡ ደመራው ሲቃጠል ሴቶች እልልታ ያሰማሉ፡፡ ለበዓሉ በሰላም በመድረሳቸውም ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡

ወከመያ ወይም ጨርቆስ አልያም በሌላ አጠራሩ የእርድማይ የሚባለው መስከረም 15 ነው፡፡ በዕለቱ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሁለትና ከዚያ በላይ የደለበ በሬ ያርዳል፡፡ እርዱ ተጠናቆ የከብት ሥጋ ወደ ቤት እንደገባ ጥሬ ሥጋ በቅቤ ተነክሮ ይበላል፡፡ ቡና በቅቤም ይጠጣል፡፡

የአካባቢው ማኅበረሰብ በኅብረት ደመራ የሚያበራበት የባንዳ ኧሳት ወይም የጉርዝ እሳት የሚባለው መስከረም 16 ቀን ይከበራል፡፡ ዕለቱ በየአድባሩ ደመራ የሚበራበትና ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከናወንበት ነው፡፡ ትልቁን ደመራ የማብራት ሥነ ሥርዓት ሲጠናቀቅ በየአካባቢው መጠነኛ ደመራዎች ይበራሉ፡፡ ደመራው ሥር ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይጨፈራል፡፡

ሥነ ሥርዓቱ ተጠናቆ ወደቤት ከተገባ በኋላ በጣባ ክትፎ ይበላል፡፡ በነጋታው ንቅባር (የከሰል ማይ) የተባለ ሥርዓት አለ፡፡ ሥርዓቱ በአንድ አካባቢ ያሉ ዕድርተኞች ደመራ የተቃጠለበት ቦታ ተሰባስበው ቃል የሚገባቡበት ነው፡፡ በዕለቱ አዳዲስ የዕድር ዳኞች ይሾሙና ካለፈው ዓመት ዳኞች ጋር የኃላፊነት ርክክብ ይካሄዳል፡፡ አዳዲስ የዕድር አባላት ምዝገባም ይኖራል፡፡

መስከረም 18 የፊቃቆማይ ይባላል፡፡ ሴቶች የተለያዩ የስፌት ቁሳቁሶች ለማዘጋጀት የሚውል ስንደዶ መልቀም የሚጀምሩበት ነው፡፡ የአካባቢውን ባህላዊ ዜማ እያሰሙ ስንደዶ ይለቅማሉ፡፡ ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 23 ያለው የጀወጀ  ወይም የጀወቸ አማች መጠየቂያ ጊዜ ነው፡፡

በአማች መጠየቂያ ወቅት ሴቶች ለእናቶቻቸው የፀጉር ቅቤ ለአባቶቻቸው ባርኔጣና ጭራ ይገዛሉ፡፡ ባሎቻቸው ደግሞ ሙክት ይሸምታሉ፡፡ ወቅቱ ልጆች በወላጆቻቸው እንዲሁም ባለትዳሮች በአማቾቻቸው የሚመረቁበትም ነው፡፡

የመስቀል በዓል አከባበርን ከሚያጎሉ ሥርዓቶች መካከል የአዳብና ባህላዊ ጭፈራ ሥነ ሥርዓት ተጠቃሽ ነው፡፡ አዳብና ከመስከረም 16 ቀን እስከ ጥቅምት በዓል ባሉት ቀናት ይከናወናል፡፡ በመገበያያ ቦታዎችና ሌሎችም የጋራ መሰብሰቢያ ቦታዎች አዳበና ሲጨፈር ወንዶችና ሴቶች ሎሚ፣ ብርቱካንና ሸንኮራ አገዳ በመለዋወጥ ይተጫጫሉ፡፡

ወጣቶች ክብ እየሠሩ በሚዘፍኑበትና በሚጨፍሩበት የአዳብና ሥርዓት ብዙዎች የትዳር አጋራቸውን ይመርጡበታል፡፡ አንድ ወንድ ለወደዳት ሴት ሎሚ በመስጠት ፍላጎቱን ያሳውቃል፡፡ የወንዱ ጓደኞች ስለልጅቷ ማንነት አጥንተው ለቤተሰቦቹ ያሳውቃሉ፡፡ ከዛም ለሴቷ ቤተሰቦች ሽማግሌ በመላክ የጋብቻ ሒደቱ ይቀጥላል፡፡

ባጠቃላይ በበዓሉ ዝግጅትና አከባበርም ሴቶች ያላቸውን ጉልህ ሚና ማየት ይቻላል፡፡ የበዓሉ ማኅበረሰባዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም ቀላል አይደለም፡፡ መስቀል በጉራጌ ብሔረሰብ ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሰቦችና አብሮ አደጎች የሚገናኙበት ነው፡፡ በዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበትና ወጣቶች የሚተጫጩበትም ነው፡፡

መስቀል እንደ ዕድር ያሉና ማኅበረሰቡን የሚያስተሳስሩ መስተጋብሮች የሚጠናከሩበት ወቅት ነው፡፡ የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ስለ በዓሉ አከባበር በድረ ገጹ ያሰፈረው መግለጫ፣ በዓሉ የቀዬው ሰው የሚመራረቅበትና ስለቀጣይ ማኅበራዊ ጉዳዮች ዕቅድ የሚወጣበት ነው ይላል፡፡ በዓሉ በአዲስ ዓመት የሚሠሩ ሥራዎች እንዴት መከናወን እንዳለባቸው የሚታቀድበት መሆኑንም ይጠቀሳል፡፡

በመስቀል ስለ ግብርናና ንግድ ሥራ ይወራል፡፡ ወጣቶች ከዕድሜ ባለፀጎች ኃላፊነት ይረከባሉ፡፡ በቢሮው በተዘጋጀው መግለጫ፣ ‹‹መስቀል ወላጆች ለበዓሉ የተዘጋጀውን ከብት ከፊታቸው አቁመው ሻኛውንና ጀርባውን በመዳሰስ ትውልዱን የሚመርቁበት ነው፡፡ ለአገር ሰላምና ብልፅግና ፈጣሪን የሚለምኑበት፣ የተቸገረ የሚጠየቅበት፣ በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉትም ወቅት ነው፤›› በማለት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...