በበሊሕ ላማ
በአሮጌው ዓመት እዚህ አገር ላይ ከደረሰ የፀጥታ ችግር ጀርባ ሕግዴፍ-ሻዕቢያ አለበት ያልተባለበት አጋጣሚ ቢኖር ከጋምቤላ ሕፃናት በታፈኑና ከብቶች በተዘረፉ ወቅት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ አርባ ምንጭም፣ አሩሲም፣ ጎንደርም፣ ምዕራብ ሸዋም… ብቻ በየትኛውም አቅጣጫ ከነበሩ የዘንድሮ ፖለቲካዊ ቀውሶች ዙሪያ የአስመራው መንግሥት እጁን በረጅሙ ስለማስገባቱ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ እርግጥ ነው የኤርትራ መንግሥት የተለያየ ግብና ህልም ላላቸው ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ኃይሎች በአደባባይ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ተደጋፊዎቹም ይህንን አስተባብለው አያውቁም፡፡ ይልቁንም እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍም በአደባባይ ሲያወሩ ተደምጠዋል፡፡ እነዚሁ ቡድኖችም ሆኑ ራሱ ሻዕቢያ ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ምኞታቸውን ለማሳካት መጣደፋቸው አይቀርም፡፡ ፀረ ኢሕአዴግ አቋማቸው ብቻ አንድ የሚያደርጋቸው ከአምስት በላይ ቡድኖች ኤርትራ የተቀመጡት በአስመራ መንደሮች ውስጥ ጋራዥ ለመክፈት አይደለም፡፡ አንድ ቀን ጠብ የሚል ነገር ቢኖር ብለው ነው፡፡ እናም የትኛውንም አጋጣሚ መጠቀማቸው የማይቀር ነው፡፡
እኛ የዚች አገር ዜጎች ግን አንድ ወፍራም ጥያቄ ማንሳት ይገባናል፡፡ ያቺ ትንሽ አገር፣ ዝቅተኛ የጦር አቅምና የሕዝብ ቁጥር ይዛ ይህንን ግዙፍ መንግሥትና አገር እንዴት እንዲህ ልታሸብር ቻለች? አርባጉጉ ላይ ለሚፈጠር ግጭት፣ ጎንደር ላይ ለሚኖር አመፅ፣ ምዕራብ ሸዋ ላይ ለሚተኮስ ጥይት በሙሉ ተጠያቂው ሻዕቢያ ከሆነ እኛም መንግሥታችንን እንዲህ ስንል መጠየቅ አለብን፡፡ ‹‹በአራቱም ማዕዘናት ለመግባት የሚያስችለውን ቀዳዳ ባትከፍትለት ኖሮ፣ ጠንካራ የፀጥታ ጥበቃ ቢኖርህ ኖሮ፣… ሻዕቢያ ዕድሉን ታገኝ ነበርን? ከሰሜን እስከ ደቡብ የተነሱ ጥያቄዎች በሙሉ ጀርባቸው ሻዕቢያ ነው ከተባለ፣ ሻዕቢያ ከአስመራ ተነስታ ጎንደርንም አልፋ፣ ወለጋንም ተሻግራ…አምቦ እስከምትደርስ ድረስ አንተ የማንን ጎፈሬ ታበጥር ነበር? ይህስ ማንቀላፋትህ የአገር ሀብት የሆነውን የደኅንነት ተቋማችንንና መከላከያችንን እንዳናምነው አያደርገንም ይሆን?›› ማለት ቢኖርብን ነው፡፡
የእኛ መንግሥት ሁሌ ‹በጎቼን ቀበሮ በላብኝ› እያለ ጎረቤቶቹን ሲያታልል ኖሮ መጨረሻ ላይ የእውነት ሲበሉበት ረዳት እንዳጣው ውሸታም እረኛ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ከጎንደር እስከ አርባ ምንጭ፣ ከኮንሶ እስከ አምቦ… ሁሌም ሻዕቢያ አፈነ፣ ተኮሰ፣ ገደለ፣ አሸበረ… እያለ የሚዘፍናትን ሙዚቃ (ሙዚቃዋ እውነትነት ቢኖራትም ቅሉ) ሕዝብም ሰልችቶ ነገርየውን የሁለት አገር ጉዳይ ሳይሆን፣ የሁለት መንግሥታት ቀጣናዊና ታሪካዊ ቁርሾ እንዲሁም አብሮ አደጋዊ መናናቅ አድርጎ የሚቆጥር ማኅበረሰብ መብዛቱ አይቀርም፡፡
ሌላኛዋ የተሰለቸች ነጠላ ዜማ ‹ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንወስዳለን› የምትለዋ ነች፡፡ ‘ተመጣጣኝ’ ሲባል ምን ማለት ነው? የእነሱ ዓላማ የአዲስ አበባው መንግሥት እንዲወገድ እስከ ቀራኒዮ የሚደርስ ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ‘ተመጣጣኝ’ ዓላማ የአስመራውን ሥርዓት እስከመቀየር ይደርሳልን? ወይስ ፆረናን አያልፍም? ወይስ ሁለት ጥይት ሲተኩሱ ሁለት መተኮስ? 50 ኢትዮጵያውያንን አፍነው ሲወስዱ 50 ኤርትራውያንን ጠልፎ ማምጣት? ይህንን እንኳ ያብራራ ባለሥልጣን እስካሁን የለንም፡፡
የሆነ ሆኖ ይቺን ከአሥር ዓመት በላይ የተጠቀማትን ፋሽን ወደመጣችበት መልሶ አዲስና ገቢራዊ ሥልት መጠቀም ይገባዋል፡፡ የመጀመሪያውና ዋነኛው መላ ለአገራዊ ቀውሶች ፈጣንና የሠለጠነ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በቀጥታ በኤርትራ ላይ የሚተገበር ሥራ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ አዲስ ዘዴ ኤርትራን መውረር ላይሆን ይችላል፡፡ ለሁሉም ቀውስ ሻዕቢያን ከመክሰስም በላይ፣ ከተመጣጣኝ ዕርምጃም በላይ መሆን ግን አለበት፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይ ከወዲሁ ካልታሰበ የነገዋ ኤርትራ አስፈሪ ነች፡፡
የወደፊቷ ኤርትራ
ኤርትራ በምዕራቡ ዓለምም ሆነ በዓረቡ ወገን ከኢትዮጵያ በበለጠ ተመራጭ ነች፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ስትራቴጂክነትን የታደለች አገር ናት፡፡ ይህ ደግሞ ዝም ተብሎ የሚወራ ሳይሆን የሚታይ ነው፡፡ ከዓለማችንን ነዳጅና ሸቀጥ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው የሚጓጓዘው በቀይ ባሕር ነው፡፡ ይህ ባሕር በቀጥታ ከስዊዝ ቦይ ጋር ይገናኛል፡፡ ይህ ቦይ ደግሞ ምዕራቡን ዓለም ከእስያ ጋር የሚያገናኝ ትልቅ የንግድ መሥመር ብቻ ሳይሆን በሜድትራኒያን ባሕርና በዓረብ ባሕረ-ሰላጤ ያለውን የአሜሪካ ባሕር ኃይል የሚያገናኝ ነው፡፡ ቦዩ ተጠሪነቱ ለግብፅ ነው (ኤርትራንና ግብፅን አንድ የሚያደርጋቸው ዋነኛ አጀንዳ ደግሞ አለ፡፡ ከኢትዮጵያ ጥቅም በተቃራኒ የቆመው ፍላጎታቸው)፡፡ ቀይ ባሕር ደግሞ ኤርትራን በብዙ ኪሎ ሜትሮች የሚያዋስን ነው፡፡ ባሕሩ የደኅንነትና የወታደራዊ አጀንዳዎች ማንፀሪያም ነው፡፡ ይህንን ባሕር ለመቆጣጠር ሲባል ኤርትራን የማይፈልጋት የለም፡፡ ከአሜሪካ እስከ ኢራን፣ ከአውሮፓ ኅብረት እስከ ዓረብ ሊግ … ከኤርትራ ጋር መወዳጀት ይፈልጋሉ፡፡
ለዚህ እማኝ ይሆነን ዘንድ በቅርቡ የመንግሥታቱ ድርጅት ያወጣውን ሪፖርት መመልከት ይበቃል፡፡ የድርጅቱ የሶማሊያና የኤርትራ ታዛቢ ቡድን ባሳለፍነው ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ (2008 ዓ.ም.) ይፋ ባደረገው ሰነድ፣ የኢሳያስ መንግሥት ለአልሸባብ ድጋፍ ስለማድረጉ የሚያሳይ ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል፡፡
በዚያው ሰሞን ይኼው ታዛቢ ቡድን ያወጣው ሌላ ዘገባ ደግሞ፣ የአስመራ ባለሥልጣናት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ስለተሰማሩ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲከሰሱ የሚያሳስብ ነበር፡፡ ሆኖም የቡድኑ ምክረ ሐሳብ ይተገበር የነበረው የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት ሲያፀድቁት ነበርና ወደ ምክር ቤቱ ያመራው ይኼ ጉዳይ፣ በቻይናና በአሜሪካ ውሳኔ (ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን) ውድቅ ተደርጓል፡፡
ከላይ ያሉትን ሁለት ነጥቦች በተን አድርጎ ማየት ያሻል፡፡ ቡድኑ ‹‹ኤርትራ አልሸባብን ስትደግፍ የሚያሳይ ማስረጃ አላገኘሁም›› ማለቱ ለአስመራ እፎይታ ነው፡፡ ይህ ቀነ ገደብ ያልተቀመጠለት ማዕቀብ ሊነሳ የሚችልበት ዕድል እንዳለ የሚጠቁም ነው (ኤርትራ ላይ ማዕቀብ የተጣለው ለአልሸባብ ድጋፍ ታደርጋለች በሚል መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ በአንድ በኩል የሶማሊያው ጽንፈኛ ቡድን እየተሸነፈ መሄድ እነ ኢሳያስ አፈወርቂ ሳይወዱ በግድ ያደርጉታል ተብለው የተከሰሱበትን ድጋፍ እንዲያቋርጡ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ በሌላ ወገን ከኤርትራ ጋር መወዳጀት የሚሻ ሁሉ የነ ኢሳያስን ለአልሸባብ ድጋፍ አለማድረግ በማሳያነት በመጥቀስ ማዕቀቡ እንዲነሳ ሊወተውት ይችላል፡፡
ሁለተኛው ነጥብ አሜሪካና ቻይና ለምን የታዛቢ ቡድኑን ምክረ ሐሳብ ውድቅ አደረጉት የሚለው ነው፡፡ እነዚህ አገሮች በአፍሪቃ ቀንድ ግልጽ ፍላጎት አላቸው፡፡ ዋሽንግተን የቀጣናው የፖለቲካ ካራ ከእጇ እንዳይወጣ ትሻለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ከ1,300 ኪሎ ሜትር በላይ የባሕር ድንበር ያላትን ኤርትራን መምረጧ የማይቀር ነው፡፡ ቻይናም በቀላሉ መግባትና መውጣት የሚያስችሉ ወደቦች ያሏትን ኤርትራን ለንግድና ለኢንቨስትመንት አብዝታ ትሻታለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ማዕቀብ የተባለ እንቅፋት እንዲያጥራት አትፈልግም፡፡ ቤጂንግ በዓለም የደኅንነትና የሰላም ጉዳይ ላይ መሪ ለመሆን ከአሜሪካ ጋር ለገባችበት ትንቅንቅ፣ ተፈጥሯዊ ስትራቴጂክነት ያላትን ኤርትራን መሣሪያ ማድረግ አትጠላም፡፡ እናም የኤርትራን ማዕቀብ አላስፈላጊነት ሁለቱ አገሮች ከተስማሙበት ነገሩ ሁሉ ያልቅለታል፡፡ ከላይ የተጠቀሰውን የሁለቱን አገሮች ውሳኔ ለማዕቀቡ መነሳት ምልክት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡
እነዚህ አገሮች የኤርትራን ሁናቴ ከሰብዓዊ መብት አያያዝና ከዴሞክራሲያዊነት አንፃር መዝነው ማዕቀቡ እንዳይነሳ ያደርጋሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ በአንድ በኩል አሜሪካ ጥቅሟ እስከተከበረ ድረስ (የፖለቲካዊና የወታደራዊ ስትራቴጂክነት ጥቅሟ) ለአገሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ ሕገ መንግሥታዊነት፣ ወዘተ የሚባሉ ጽንሰ ሐሳቦችን እንደ ቅድመ ሁኔታ አታስቀምጥም፡፡ ለዚህ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ወዳጆቿን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዓለማችን ሰብዓዊ መብቴችን በመጣስ አንደኛ አገር የንጉሣውያኑ ምድር ሳዑዲ ግንባር ቀደም የአሜሪካ አጋር ነች፡፡ ቻይና ደግሞ በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የማይገባ የውጭ ጉዳይ መርሆ ያላት በመሆኗ፣ የኤርትራን ወዳጅነት ያለቅድመ መመዘኛ እንድትቀበለው ያደርጋታል፡፡
ማዕቀቡ ሊነሳ የሚችልበት ሌላም ፍንጭ አለ፡፡ የኤርትራ መንግሥት የየመን ሁቱዎችን ለመደምሰስ በሳዑዲ ዓረቢያ እየተመራ የመን የገባውን ቡድን ተቀላቅሏል (በእርግጥ ኤርትራውያን ያስተባብላሉ)፡፡ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ግን የሻዕቢያ መንግሥት ከሁለት ሺህ በላይ እግረኛ ሠራዊት ወደ የመን መላኩን ደጋግመው ዘግበውታል፡፡ ከዚያም ባሻገር የአሰብ ወደብን ዓረቦቹ ዘለግ ላሉ ዓመታት በሊዝ መያዛቸው፣ ሳዑዲ መራሹ ቡድን ለፀረ ሁቱ ዘመቻ የሚያሠለጥንበትን ቤዝ ከኤደን ወደ ኤርትራ ማሻገሩ፣ ኤርትራ ከነ ሳዑዲ የገንዘብ፣ የጦር መሣሪያና የነዳጅ ድጎማ እያገኘች መሆኗ (ሳዑዲ የጦር መሣሪያውን የምታገኘው ከአሜሪካና ከብሪታኒያ መሆኑ ይሰመርበት)፣ አደባባይ ላይ የዋለ እውነት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ (በሌላ ቋንቋ ማዕቀቡ ሲጣስ) ማዕቀቡን የጣሉት እነ አሜሪካም ሆኑ የመንግሥታቱ ድርጅት አይተው እንዳላየ መሆናቸው፣ ማዕቀቡ ከኤርትራ አናት ላይ ገለል ሊል የሚችልበት ዋዜማ ላይ እንደደረሰ የሚጠቁም ነው፡፡
ባሳለፍነው ክረምት የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ለደቡብ ሱዳን ተጎጂዎች የሚያስፈልገውን አንድ ሺሕ ሜትሪክ ቶን የዕርዳታ እህል ያጓጓዘው በምፅዋ ወደብ ላይ ነው፡፡ ይህ እ.ኤ.አ ከ2006 ወዲህ የመጀመሪያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ኤርትራ ለቀጣናው የሰብዓዊ መብት ግልጋሎቶች ወደቦቿን ክፍት አደረገች ማለት ዓለም አቀፍ ወዳጆቿን (ከመንግሥታትም ሆነ ከረድኤት ተቋማት ጋር) ለማብዛት እየተንደረደረች ነው ማለት ነው፡፡ እነሱም በዚህ ደረጃ ጠቀሜታዋን ከተረዱት የኤርትራ ማዕቀብ እንዲነሳ ጫና ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ (እነ አሜሪካ እንኳን የኤርትራን ማዕቀብ የኩባንና የኢራንንም አንስተዋል)፡፡ ስለዚህ የወደፊቷ ኤርትራ ማዕቀብ የተነሳላትና በጉልበተኞቹ አገሮች የምትመረጥ የመሆን ዕድል ያላት ነች፡፡
ኤርትራና የአውሮፓ ኅብረት
በእርግጥ የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት በውሳኔ ተለያይተውም፣ ተራርቀውም አያውቁም፡፡ እናም ኅብረቱ በኤርትራ ላይ ከአሜሪካ የተለየ አመለካከትና ፖሊሲ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይልቁንም በተግባራዊነት የብራሰልሱ ድርጅት ከአሜሪካም የቀደመ ሥራ ሠርቷል፡፡
የኤርትራ መንግሥት ባሳለፍነው ጳጉሜን 3 ቀን 2008 ዓ.ም. 18.7 ሚሊዮን ዩሮ ከአውርፓ ኅብረት አግኝቷል፡፡ ይህ ገንዘብ በኤርትራ ስድስት ቦታዎች ላይ የጠብታ መስኖን ለማልማት የሚውል ነው፡፡ ይህንን ሥራ ለማከናወን ደግሞ በዘርፉ የሚያስመሰግን ልምድ ያላቸው የእስራኤል ኩባንያዎች ውል ተፈራርመዋል፡፡ ‹‹የኤርትራን ግብርናና የምግብ ዋስትና ለማገዝ›› በሚል መርሐ ግብር ከኅብረቱ የተለቀቀው ይኼ ገንዘብ ብራሰልስና አስመራ እየተናበቡ ስለመሆኑ አስረጂ ነው፡፡ በኅብረቱ የኤርትራ ጉዳዮች ኃላፊ ፔሬ ፊሊፔ እንደተናገሩት እ.ኤ.አ. ከ2013 አንስቶ የኤርትራን አርሶ አደሮች ምርታማነት ለመጨመር ለአገሪቱ መንግሥት የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ሲያደርግ ከርሟል፡፡ የዚህ አዝማሚያ የሁለቱን ወገኖች የወደፊት ግንኙነት የሚጠቁም ነው፡፡ ኅብረቱ ያደረገው የንዘብ ድጋፍም ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡
በአገሪቱ ሁለተኛ ሰው በአቶ የማነ ገብረአብ (የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የፖለቲካ አማካሪ) የተመራ የልዑካን ቡድን በመስከረም ወር መግቢያ ላይ ወደ ጀርመን አቅንቶ ነበር፡፡ ይህ የሆነው ኅብረቱ ሚሊዮን ዩሮዎችን ለአስመራው መንግሥት ከሰጠ በኋላ ነው፡፡ ወደ በርሊን የመሄዳቸው ምክንያትም በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ የአውራነት ሚና ካለው የጀርመን መንግሥት ጋር ለመወያየት ነበር፡፡ በዚህም ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢኮኖሚ ሚኒስቴር ጋር ተገናኝተዋል፡፡ የጀርመን ቆይታቸውም በመግባባት ላይ የተመሠረተና ለወደፊት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በጋራ ለመከወን በመስማማት የተጠናቀቀ መሆኑን አቶ የማነ ለጀርመን መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ጀርመን ኤርትራን በቅን ልቡና ተቀበለቻት ማለት 27ቱም የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ተቀበሏት ማለት መሆኑን መጠርጠር ያስፈልጋል (የአንገላ መርከል አስተዳደር በኅብረቱ ውስጥ ያለውን ጉልበት ልብ ይሏል)፡፡ ስለዚህ ኅብረቱም የኤርትራ ማዕቀብ እንዲነሳ መፈለጉ አይቀርም፡፡ የዚህ ፍላጎት ምክንያት ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ከላይ እንደተገለጸው የአውሮፓ ኅብረትም የኤርትራን ስትራቴጅካዊነት ይፈልገዋል የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የኤርትራ ስደተኞች ናቸው፡፡ ለኅብረቱ አባል አገሮች የስደተኞች ነገር ራስ ምታት መሆን ከጀመረ ቆየ፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ዜጎቻቸው ወደ አውሮፓ ይሻገራሉ ከሚባሉ አገሮች ውስጥ ኤርትራ ከመጀመሪያዎቹ ተርታ ትጠቀሳለች፡፡ እናም ኅብረቱ ከኤርትራ ባለሥልጣናት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ይህንን ራስ ምታቱን ማስታገስ ይፈልጋል፡፡ በአጭር አገላለጽ የኤርትራ ስደተኞችን ቁጥር ለማቃለል ከአስመራው መንግሥት ጋር መቀራረብ ለኅብረቱ ወሳኝ ነው፡፡
ኤርትራና የዓረብ ሊግ
ኢሳያስ አፈወርቂ ገና ከትጥቅ ትግሉ ዘመን ጀምሮ ከዓረቡ ዓለም ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ወዲ አፎም ምንም እንኳ የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኝ ቢሆኑም ጀለቢያ ሳይቀር እየለበሱ መስጂድ ገብተው ከዓረብ ጎበዛዝት ጋር ይዶልቱ እንደነበር ድርሳነ ሳሕላቸው ይተርካል፡፡
ይህንን ጉዳይ በአገር መሪነታቸው ዘመን ጠንከር አድርገውት ቀጥለዋል፡፡ ኤርትራንም የዓረብ ሊግ ታዛቢ አባል አድርገዋታል፡፡ ላለፉት 20 ወራት በየመን የሚካሄደውን ጦርነት ከነሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ሆነው መቀላቀላቸውም ለዚሁ ለዓረቡ ዓለም ያላቸውን ታማኝነት የሚያሳይ ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት አስመራ ከምዕራቡ ዓለም ያጣችውን ድጋፍ ለማካካስ ከዓረቡ ዓለም ጋር የሙጥኝ ማለቷ የጠራራ ፀሐይ ሀቅ ነው፡፡ አቶ ኢሳያስ በተደጋጋሚ የዓረብ ሊግ አባል አገሮችን መጎብኘታቸው (ወደ ሱዳን ካርቱም፣ ወደ ግብፅ ካይሮ፣ ወደ ሳውዲ ሪያድ፣ ወደ ኳታር ወዘተ መመላለሳቸው) ከእነዚሁ የሰሜን አፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ ወዳጆቻቸው ጋር ያላቸውን ሽርክና ለማጠናከር አልመው ለመሆኑ ዕሙን ነው፡፡ እነዚህ አገሮችም ለኤርትራ ነዳጅ፣ ገንዘብና የጦር መሣሪያ ከመደጎምና ከማበደር አልፈው ወደብ በሊዝ እስከመከራየት ደርሰዋል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የአሰብ ወደብን ለሰላሳ ዓመት በሊዝ ተከራይታዋለች፡፡ በዳህላክ ደሴት ላይ ሰፍሮ የነበረው የኢራን ጦርም እነ ኢሳያስ የሺዓውንም የሱኒውንም አገር አሟጦ ለመጠቀም እያደረጉ ያሉትን መውተርተር ያመለክታል፡፡ በእርግጥ ኢራኖች በየመን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላና ከሳዑዲ ጋር የውክልና ጦርነት ውስጥ ተፋፍመው ከገቡ ወዲህ (ሁቱዎች በኢራን የሚደገፉ ሺዓዎች ናቸው) ዳህላክ ደሴትን ትተው ወጥተዋል፡፡ እሥራኤል ዛሬም ምፅዋ ላይ አለች፡፡
ይህን ኤርትራ በዲፕሎማሲ ያመጣችው ሳይሆን ተፈጥሯዊ ስትራቴጅክነቷን ተጠቅማ ያገኘችው ዕድል ነው፡፡ ከኤርትራ የተሻለ ጥቅም እንደሚያገኙ በሚገባ የተገለጠላቸው እንደ ኳታር ያሉ አገሮችም ኤርትራን ከጠላቶቿ ለማስታረቅ ጥረት ሲያደርጉ እየታዩ ነው፡፡ ባሳለፍነው ዓመት የመጨረሻ ወራት በኳታር አደራዳሪነት ኤርትራ የጅቡቲ እስረኞችን ፈትታ ሰጥታለች፡፡ ይህ የኳታር ጥረት ተጠናክሮ ከቀጠለ ሁለቱን አገሮች ወደ ወዳጅነት ማምጣቱ አይቀርም፡፡ የኳታር መንግሥት ይህንን ሁሉ የሚያደርገው ኢትዮጵያን ብቻዋን ለማስቀረት በማሰብ መሆኑን መጠርጠር ያስፈልጋል (ኢትዮጵያና ኳታር ሄድ መጣ የሚል የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው ይታወቃል)፡፡ በየመን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሁቱ አማፅያን ሽንፈትና በነ ሳዑዲ ዓረቢያ የበላይነት የሚጠናቀቅ ከሆነ (አዝማሚያው እንደዚያ ይመስላል) ለኤርትራ ፍሰሐ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢሳያስ መንግሥት የወታደሮቹን ደም እየገበረ ያለው እሱ የሚፈልገው ቡድን ወደ ሥልጣን እንደሚመጣ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ሥጋት መሆኑ አይቀርም፡፡ የወደፊቷ የመን ከአዲስ አበባ ይልቅ ጎረቤቷን አስመራን ልትመርጥ ትችላለች፡፡
የኢትዮጵያ አማራጮች
አፍሪቃዊቷ ሰሜን ኮሪያ የሚል መጠሪያ የተሰጣት ኤርትራ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የነበራት መገለል ከተቋጨ የምሥራቅ አፍሪቃ የኃይል ሚዛን ይቀያየራል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የአስመራው መንግሥት ውጫዊ ትኩረት ካገኘ፣ በኢትዮጵያ ላይ ለሚያስበው እኩይ ድርጊት መልካም ፖለቲካዊ ታኮ (political buttress) እንደሚሆንለት ዕሙን ነው፡፡ ኃያላኑ አገሮችም ቢሆኑ ጥቅማቸው እስከተጠበቀ ድረስ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያን ለመውረር ቢነሳ ሃይ አይሉትም፡፡ ይህ ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያ በየመን ወረራ ስትፈጽም እነ አሜሪካ ድጋፍ ሲያደርጉ እየተስተዋለ ያለ ተሞክሮ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ላዘመተችው የውክልና ጦርነት (proxy war) በቂ የፋይናንስና ዓለም አቀፋዊ ይሁንታ ልታገኝ ትችላለች፡፡ በኢሕአዴግ ላይ የሚነሳው ተቃውሞ አገራዊ መልክ ይዞ ቢቀጥልና ግንባሩ በኃይል የመገርሰስ ዕድል ቢገጥመው እነ አሜሪካ ሁለተኛ አማራጭ (plan B) ማሰባቸውና ማቀዳቸው አይቀርም፡፡ ይህንን አማራጭ ሊያገኙ የሚችሉት ደግሞ አስመራ ላይ ከተጠራቀሙት ቡድኖች መካከል መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ ኤርትራ ለምታዘምታቸው ፀረ ኢትዮጵያ ‹አርበኞች› ሳይታሰብ የኃያላኑን ድጋፍ የምታገኝበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡
ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ኢትዮጵያ አማራጮቿን አሟጥጣ መጠቀም ይገባታል፡፡ እነዚህ አማራጮች ምንድን ናቸው የሚለው ጉዳይ ዓብይ ነጥብ ነው፡፡ መቼም ሰላማዊ ድርድር የሚባለው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ቁጥር አንድ የፖለቲካ ዘዴ (political technique) አስመራ ላይ ሻዕቢያ፣ አዲስ አበባ ላይ ኢሕአዴግ እስካሉ ድረስ የማይታሰብ ነው፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ግልጽ መናናቅና መጠላላት ተጠናውቷቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለጠረጴዛ የሚበቃና የሚቀራረብ ሐሳብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ እናም ይኼኛው አማራጭ ለጊዜው ገቢራዊ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ከመርፌ ቀዳዳም የጠበበ ነው፡፡
ፕሮፌሰር አሌክስ ዲ ዎል ከሳምንታት በፊት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከማዕቀቡ በኋላ ስላለችው ኤርትራ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችው አማራጭ የለም፡፡ ይህ የአገሪቱ መንግሥት ጉዳዩን አርቆ እንዳላየው የሚያመለክት ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን የኤርትራ ማዕቀብ እንዲራዘም ለማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መንግሥት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ኤርትራ ከዓረቡ ዓለም ጋር እያደረገች ያለችው ሽርጉድ (ከላይ በዝርዝር እንደተመለከተው) የተጣለባትን ማዕቀብ የሚጥስ መሆኑን የሚያስገነዝብ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ዘንድ መሥራትና ማሳመን ይገባዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት እስካሁን አልሸባብን በይፋ አለማውገዙም፣ ኢትዮጵያ የኤርትራን ማዕቀብ ለማስቀጠል ለምታደርገው ጥረት እንደ አንድ ማጣቀሻ ሊያገለግላት ይችላል፡፡ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2017 ወርቃማ ዕድል (golden opportunity) አላት፡፡ ይህ አጋጣሚ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የመሆኗ ነገር ነው፡፡
ባሳለፍነው ሐምሌ በኒውዮርክ በተካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ የድርጅቱ ጉልበተኛ ክንፍ በሆነው የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ እ.ኤ.አ. ከጥር 2017 አንስቶ ባሉት ሁለት ዓመታት እንድትቆይ የሚያስችላትን የ185 አገሮች ድምፅ አግኝታለች፡፡ የዚህ ምክር ቤት አባል መሆን ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዱ፣ በምክር ቤቱ ውስጥ የራስን ጉዳይ የመወያያ አጀንዳ አድርጎ ማስያዝ ማስቻሉ ነው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ በሚኖራት የምክር ቤቱ ቆይታ የኤርትራን ማዕቀብ የማራዘሙን ጉዳይ ትኩረት ሰጥታ ልትከውነው ይገባል፡፡ አሁን ግን ይህ ዘላቂ መፍትሔ አይደለም፡፡ እናም የአዲስ አበባ ባለሥልጣናት የረጅም ጊዜ ዕቅድ ማስቀመጥና አሁን ካለው ‹ሰላምም ጦርነትም የለም› ከሚለው መርሆ የተሻገረ ገቢራዊ ሐሳብ ሊያስቡ የሚችሉበት ጊዜ የቀረበ ይመስላል፡፡ ይኼ ገቢራዊ ሐሳብ በኤርትራ ያሉ የኢሳያስ መንግሥት ተቃዋሚዎችን (እንደ የቀይ ባሕር አፋሮች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን) ማጠናከርና አለም አቀፋዊ ድጋፍ እንዲኖራቸው ማገዝ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህንና ሌሎች መንገዶችን አጢኖ መሄድ የማይችል የኢትዮጵያ መንግሥት ካለ ግን ኤርትራ የተባለች ትንሽ አገር የቀጣናውን ግዙፍ የፖለቲካ መዘውር እጇ ማስገባቷ የማይቀር ነው፡፡ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ ክፉ በማሰብ ዕድሜያቸውን የፈጁት አቶ ኢሳያስም ከመቐሌ እስከ ሞያሌ ሊፈነጩ የሚችሉበት አጋጣሚ አይፈጠርም ብሎ መከራከር አይቻልም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡