Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‹‹አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ››

‹‹አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ››

ቀን:

በጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

ከሰሞኑ ኢሕአዴግ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ያስፈልገኛል ማለቱን ሰምተናል፡፡ ካለንበት የፖለቲካ ቀውስ ለመውጣት ለውጥ ያስፈልጋል ብለን ለምናምን ሁሉ፣ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ተሃድሶ ያስፈልገኛል ማለቱን በአዎንታዊ መልኩ ልናየው የሚገባ ቢሆንም፣ ‹‹ጥልቅ›› የተባለው ተሃድሶ በአስፈላጊው ደረጃ ‹‹ጥልቅ›› አይሆንም የሚለው ሥጋት ደግሞ ነገሩን ሁሉ በጥርጣሬ እንድናይ ግድ ይለናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ኢሕአዴግ ተሃድሶ ያስፈልገኛል ወደሚለው ድምዳሜ ሲደርስ መነሻ የሆነው ትንታኔ ነው፡፡

ትንታኔው ጥልቀት ሳይኖረው መፍትሔና ተሃድሶው ጥልቀት ሊኖረው አይችልም፡፡ እንደ ኢሕአዴግ ትንታኔና ግምገማ ለገባንበት የፖለቲካ ቀውስ ዋነኛው መንስዔ ባለሥልጣናት ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ማስቀደማቸው ነው፡፡ በፌዴራልና በክልል ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰጣቸው ባለሥልጣናት ለተሰጣቸው ኃላፊነት ብቁ ካለመሆናቸውም ባሻገር፣ በሥልጣናቸው ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ የግል ሀብት ማካበት ይመርጣሉ የሚለው የኢሕአዴግ ወቅታዊ አቋም ‹‹ተሃድሶ ያስፈልገናል›› ለሚለው የድርጅቱ ውሳኔ መነሻ ሆኗል፡፡

ኢሕአዴግ የሹማምንቱን አግባብ ያልሆነ የግል ጥቅም የማሳደድ አባዜና የብቃት ችግር ዘግይቶም ቢሆን ማመኑ መልካም ነው፡፡ ሆኖም ተሃድሶው በእውነትም ጥልቅ ተሃድሶ እንዲሆን በቅድሚያ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት እንዲህ ያለ ዝንባሌ የሚታይባቸው ለምንድነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የሕዝብ ሀብት የሚመዘብሩና የጉቦ ቀበኛ የሆኑ ባለሥልጣናት ከላይ እስከታች የበዙት ለምን እንደሆነ ሳንረዳ ይህንን ችግር መቅረፍ አንችልም፡፡ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ›› እንዳሉት ነው ነገሩ፡፡

እንደ እኔ አመለካከት የኢሕአዴግ ሹማምንት ዘንድ በስፋት የሚታየው በመንግሥት ሥልጣን የግልን ጥቅምና ሀብት የማደራጀት ችግር መንስዔ የሆኑ ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች አሉ፡፡ በእርግጥም መንስዔዎቹ እነዚህ ብቻ ናቸው ባልልም ተደርገው ሊታዩ የሚችሉት እነዚህና ተያያዥነት ያላቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡

አንደኛው ምክንያት ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሕዝብ ድጋፍና ተቀባይነት የሌለው ፓርቲ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኢሕአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን ለመገደብና ለመቆጣጠር አስፈላጊ የሆኑ ሕጋዊና ተቋማዊ መዋቅሮችን ክፉኛ ማዳከሙ ነው፡፡ ላለንበት ቀውስ መንስዔ ናቸው በማለት ከላይ ያስቀመጥኩዋቸውን እውነታዎች ለመረዳት ምርጫ 97ን ተከትሎ የሆነውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው ምርጫ 97 በአንፃራዊነት የኢሕአዴግ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሻለ ነፃነት አግኝተው ከኢሕአዴግ ጋር የተወዳደሩበት ምርጫ ነበር፡፡

የኢሕአዴግ መሪዎችም ከምርጫው በፊት ባደረጉት ‹‹ተሃድሶ›› እና በኢኮኖሚው ላይ በታየው መነቃቃት የተነሳ በምርጫው ሕዝብ ይደግፈናል ብለው በተስፈኝነት የገቡበት ምርጫ ነበር፡፡ ሆኖም የምርጫ ፉክክሩ ተጧጡፎና ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነታቸው ከፍ እያለ መጣ፡፡ ምርጫውም እጅግ አወዛጋቢ በሆነ መልኩ ተጠናቀቀ፡፡ ከዚያ በኋላ ኢሕአዴግ በዴሞክራሲያዊ ዓውድ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መወዳደርን እርም ብሎ ብቻውን ሮጦ ብቻውን ‹‹የሚያሸንፍበትን›› ዓውድ ለመፍጠር ሥራዬ ብሎ ተንቀሳቀሰ፡፡

በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ኢሕአዴግ ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች ውስጥ አንዱ የአባላቱን ቁጥር በብዙ እጥፍ ማሳደግ ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች ሲታሰሩና ሲዋከቡ በአባልነት ለሚመለመሉ ደግሞ የተለያዩ መደለያዎች ቀረቡ፡፡ ሥራ፣ ትምህርት፣ ብድርና ሌሎችም በመንግሥት ‹‹ችሮታ›› የሚገኙ ጥቅምና ዕድሎች ለፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ብቻ የሚሰጡ ሆኑ፡፡

ኢሕአዴግ ብዙዎችን በጥቅም አባብሎ አባላቱ አደረገ፡፡ ይህ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንና ብዙዎቻችን ያየነውና የማንካካደው ነገር ይመስለኛል፡፡ የፓርቲ አባላት ያልሆኑት ሲገፉ የፓርቲ አባል ለሆኑና ‹‹ንቁ ድጋፍ›› ለሚሰጡ ደግሞ በምላሹ ኑሮ ሲመቻች፣ ሲደላደል ታየ፡፡ ታዲያ ኢሕአዴግ በዚህ ሒደት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላት ሰብስቦ፣ እነዚህን አባላቱን ሹመት ሰጥቶ ሲያበቃ ʻየግል ጥቅም አሳዳጅ ናቸውʼ ብሎ ማማረሩን ምን ይሉታሉ? እንክርዳድ ዘርቶ ስንዴ አይታጨድም፡፡

በአገር ደረጃ ነፃ ህሊናን ጠላት አድርጐ በአበል፣ በሥራ ዕድል፣ በትምህርት ዕድል፣ በሥልጣንና በጥቅም ደልሎ ብዙዎች ያላመኑበትን ‹‹አሜን!›› እንዲሉ ያደረገ ፓርቲ አባላቱ ‹‹እበላ ባይ›› ሆነው ቢገኙ ሊገረም አይገባም፡፡ የነፃነትና የዴሞክራሲ ዕጦት፣ አምባገነንነትና ጭቆና አድርባይነትን በእጅጉ ያስፋፋሉ፡፡ አስመሳይና እበላ ባዩ እንዲህ ባለው ሥርዓት ከፍ ከፍ እያለና እየተመቸው ይሄዳል፡፡ ኢሕአዴግ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ጉልበትና እበላ ባይነትን የሥልጣኑ ምሰሶዎች አድርጐ ቆይቷል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ፉክክር የተገኘ የሕዝብ ይሁንታ ስለሌለው ደጋፊና አባል የሚያስጠጋውና የሚሰበስበው በሥልጣን ተጠቅሞ ሀብት የማጋበስ ዕድል እየሰጠ ነው፡፡

በተለይም ለኢሕአዴግ ተቃውሞ በሚበዛባቸው ክልሎች የኢሕአዴግ አካል መሆን የራሱ የሆነ ማኅበራዊ ዋጋ የሚያስከፍል፣ የሚያስነቅፍና የሚያስተች ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ውግዘት አልፈውና ችለው ብዙዎች የድርጅቱ አባል እንዲሆኑ ኢሕአዴግ ለአባላቱ ሥልጣናቸውን ለግል ጥቅማቸው እንዲያውሉ መፍቀድ ነበረበት፡፡ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ድርጅቱና አባላቱ የተዋዋሉት ውል አባላቱ ባያምኑበትም ኢሕአዴግ እንዲደግፉ ሲያስገድድ፣ ሕዝብ በድለውም ቢሆን ሀብት እንዲያካብቱ ‹‹መብት›› ሰጥቷቸዋል፡፡

መሬት እንደ ከረሜላ የቸረቸሩት ሹመኞች ኢሕአዴግ አባል ሲያደርጋቸው አባል የሆኑት ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጥሟቸው ወይም ኢሕአዴግ እኔ ለወጣሁበት ሕዝብ የሚያስብና የሚጨነቅ፣ የሚጠቅም ፓርቲ ነው›› ብለው አይደለም፡፡ እየበላህ ደግፈኝ የሚለውን ግብዣ ሲታደሙ ህሊናን ከቤት ትተው ነው፡፡

ስለዚህ ኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ለማድረግ እውነት ከወሰነ ለእበላባይነት ፖለቲካ ምቹ የሆነውን አምባገነናዊ ዓውድ ማስወገድ አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ አድርባይነት ከዋነኞቹ የኢሕአዴግ የሥልጣን ምሰሶዎች አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው ዋነኛ ምሰሶ ጉልበት ነው፡፡ ይህ እውነታ ካልተለወጠ ሹመኛና ባለሥልጣን ቢለዋወጥም ችግሩ ይቀጥላል፡፡ አገሩ ነፃ ካልሆነ፣ የዜጐች መሠረታዊ የዜግነት መብትና ነፃነቶች ካልተከበሩ፣ የሥልጣን ምንጭ በእውነትም የሕዝብ ይሁንታ ካልሆነ፣ ካለንበት ቀውስ አንወጣም፡፡ የ‹‹ተሃድሶው›› አቅጣጫ ከሹም ሽር አልፎ ወደ ችግሩ ሥር፣ ወደ ዋነኞቹ መንስዔዎች የሚያስኬድ መሆን አለበት፡፡ ሕዝቡ በመረጠውና በወደደው የሚተዳደር ካልሆነ፣ ነፃነቱን እንደተነፈገ ከቀጠለ ያለንበት ቀውስ እየባሰ ይሄዳል፡፡

የሕዝብ ይሁንታ የሌለው መንግሥት ጥቂቶችን በጥቅም ገዝቶ፣ ብዙኃኑን አስፈራርቶ ከመኖር ውጪ አማራጭ የለውም፡፡ በቅርቡ እንዳየነው ደግሞ ይህ አካሄድ፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ሰፊ የብሔር ብዝኃነት ባለበት አገር የሚያዛልቅ አይደለም፡፡ በጥቅም የተገዙት እየተገባበዙ፣ እየዘረፉ፣ ሕዝብን እያማረሩና እየበደሉና የመሳሰሉትን እየፈጸሙ አመፅ ይበዛል፡፡ ስለሆነም ከቀውሱ ለመውጣት እበላ ባዮች ላይ ከመዝመት በፊት እበላ ባዮችን ያበዛውን አምባገነናዊ ዓውድ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዓውድ ሲለወጥ ታዲያ የፓርቲውን የሥልጣን ሞኖፖል ማሳጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ታዲያ ፓርቲው አባላቱን ከግል ጥቅማችሁ ይልቅ የሕዝብ ጥቅምን አስቀድሙ ብሎ እንዳሳሰበ፣ ፓርቲውም ከድርጅቱ በሥልጣን ከመቆየት ፍላጐት ይልቅ የአገር ጥቅምና ህልውና ካስቀደመ ሥልጣኑን ከተፎካካሪዎቹ ቢጋራ ቅር ሊሰኝ አይገባውም፡፡ የተሃድሶው ጥልቀትና ሀቀኝነት መለኪያ ይኼ ነው፡፡ ካልሆነ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ›› ነው ነገሩ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...