Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናካቶሊክ መንግሥት አገራዊ ቁስሎችን የማዳንና ዕርቅ የማውረድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠየቀች

ካቶሊክ መንግሥት አገራዊ ቁስሎችን የማዳንና ዕርቅ የማውረድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠየቀች

ቀን:

  • የሃይማኖት መሪዎች ያለምንም አድልዎ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ድምፃቸውን እንዲያሰሙም ጥሪ ቀርቧል

በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች የኢትዮጵያን ህልውናና የሕዝቡን አንድነት ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥሉ ስለሆነ፣ መንግሥት አገራዊ ቁስሎችን የማዳንና ዕርቅን የማውረድ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አሳሰበች፡፡

ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ያሳሰባት ቤተ ክርስቲያኒቱ በካቶሊካውያን ጳጳሳት 34ኛ መደበኛ ጉባዔዋ ከመከረች በኋላ፣ ሐሙስ ታኅሳስ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ አማካይነት መግለጫውን ሰጥታለች፡፡

ለአገሪቱ 2009 ዓ.ም. ፈታኝ እንደነበረ ዘንድሮም ሁኔታው የማኅበረሰቡን አብሮነትና አንድነት በአደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን፣ በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በተነሱት ግጭቶች በጠፋው የሰው ሕይወት ማዘኗን የገለጸችው ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ የመንግሥት አካላት ማንኛውንም ዓይነት ልዩነት ወደ ጎን በመተው ሕዝብንና አገርን ለማዳን ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው አሳስባለች፡፡ የካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ በማሳሰቢያው፣ ‹‹የውስጥ ልዩነት እንኳን ቢኖራችሁ የግጭት መልክ ይዞ ወደ ሕዝብ እንዳይወርድ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድታደርጉ እናሳስባለን፤›› ብሏል፡፡

መግለጫው አያይዞም የመንግሥት አካላት ማንኛውንም ልዩነት በውይይትና በድርድር በመፍታት፣ የውይይት መድረክ እንዳይዘጋ አስፈላጊውን መስዋዕት በመክፈል፣ አገሪቷን ከውድቀት፣ ሕዝብንም ከሞትና ስደት የመታደግ ከባድ ሞራላዊና መንግሥታዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡

በብሔርተኝነት የሚገለጹ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ማንነት የሚፈታተኑ ግጭቶች እየተከሰቱ፣ በርካታ ወገኖች ለሕልፈት ሕይወት፣ የተረፉት ደግሞ ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል ብላለች ቤተ ክርስቲያኒቱ፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች እነዚህን የብዝኃነት እሳቤዎችን ተከትለው የሚነሱ ጥያቄዎችን በጊዜና በአግባቡ አለማስተናገድ የሚፈጥረው የፍርኃት ጫናና የእርስ በርስ ጥርጣሬ ቢስተዋልም፣ የሰው ልጅ ሕይወት ግን ከማንኛውም ጥያቄና ፍላጎት በላይ እግዚአብሔር የሰጠው ክቡር ስጦታ ስለሆነ፣ በሰው ሕይወት ላይ የሚመጣው አደጋ ፍፁም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ብላለች፡፡

በተመሳሳይ የፍቅርና የወንድማማችነት መገለጫ መሆን የሚገባቸው የስፖርት ውድድሮች የጥላቻና የተቃርኖ መገለጫዎች መሆናቸው፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዕውቀት መገብያ ማዕከል መሆን ሲገባቸው የግጭትና የሕይወት መጥፊያና የንብረት ማውደሚያ ማዕከል ሆነው መታየታቸው የሚያስቆጭ መሆኑንም ገልጻለች፡፡

የሃይማኖት አባቶች የሰላምና የእርቅ መሣሪያ በመሆን በየአካባቢያቸውም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣  የሰው መብት እንዲከበር ያለፍርኃት የጥፋት ኃይሎችን መገሰጽ እንደሚጠበቅባቸው፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ አካላትን፣ ማኅበረሰቦችን፣ የመንግሥት አካላትን፣ ያለምንም ወገናዊነትና ፍርኃት፣ ተግሳጽ የሚገባውን በመገሰጽ ይቅርታ መጠየቅ ያለበትን እንዲጠይቅ፣ ይቅርታ መስጠት ያለበት እንዲሰጥ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ  እውነትን መሠረት ያደረገ እርቀ ሰላም እንዲሰፍን የነቢይነት ኃላፊነትን መወጣት ይገባል ሲሉ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሚፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ቋንቋንና የዘር ሐረግን በመከተል ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ የጥፋት ኃይሎች በሕዝብ ላይ የባሰ ትርምስና ጉስቁልና እንዳያስከትሉ፣ መንግሥት ጥበብ የተሞላበት የሕዝቡን ታሪካዊ አንድነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅነት በመጪው ሐምሌ ወር በአዲስ አበባ በሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባዔዎች ኅብረት (አመሰያ) ጉባዔ፣  ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቀጣናው እየታዩ ያሉ የብሔርተኝነት ጉዳዮች ወደ ዘረኝነት ሊያመሩ የሚችሉ አዝማሚያዎች አጀንዳው እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡  ጉባዔው የሚያውጠነጥነው ‹‹በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ሕያው ብዝኃነት፣ ሰብዓዊ ክብርና ሰላማዊ አንድነት ለአመሰያ አገሮች›› የሚል መሪ ቃል መሆኑን፣ የምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባዔዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ገልጸዋል፡፡

ከሐምሌ 6 እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚካሄደው ጉባዔ  የአመሰያ አባል አገሮች ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣  ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራና ታዛቢ አገሮች ማለትም ጂቡቲና ሶማሊያ እንደሚካፈሉ ታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...