Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከሃያ በላይ ኤርትራዊያን የተሳተፉበት የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ተደረገ

ከሃያ በላይ ኤርትራዊያን የተሳተፉበት የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ተደረገ

ቀን:

በኢትዮጵያና በኤርትራ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ከሃያ በላይ ኤርትራውያን አዲስ አበባ መጥተው ውይይት ተካሄደ፡፡

ሴሌብሪቲ ኢቨንትስ የተሰኘ አገር በቀል ተቋም ያዘጋጀው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ ባለፈው ሳምንት በሐርመኒ ሆቴል ተካሂዶ ነበር፡፡ ከአሁኖቹ በተጨማሪ ወደ ፊት ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብለው ከሚታሰቡ ኤርትራዊያን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ሰፋፊ ስብሰባዎችና ውይይቶች እንደሚደረጉ ተጠቁሟል፡፡ በእነዚህ ግለሰቦች አማካይነትና በሴሌብሪቲ ኢቨንትስ አስተባባሪነት በኤርትራ ተመሳሳይ ውይይት ለማካሄድ መታቀዱም ተገልጿል፡፡

ምሁራንና ታዋቂ ፖለቲከኞች በተገኙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ፣ በእንግሊዝ አገር ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩትና በፖለቲካ ተንታኝነታቸው የሚታወቁት መድኃኔ ታደሰ (ፕሮፌሰር) የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ፕሮፌሰሩ በመነሻ ጽሑፋቸው ላይ እንዳወሱት፣ የሁለቱን አገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማስቀጠል ከታችኛው ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በሁለቱ አገሮች መንግሥታት እየተስተዋለ ያለው ችግር ከፍተኛ እንደሆነ በመጠቆም፣ ችግሩን ለመቅረፍና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ለማስቀጠል ጊዜው አሁን መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መንግሥታት አሁን ካለው የፖለቲካ ትኩሳት አኳያም ጉዳዩን ለመቀበል እንደሚገደዱ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ኤርትራን ወክለው የተገኙት ሰለሞን ገብረ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና ኤርትራ ‹‹አንድ ሕዝብና ሁለት አገሮች›› እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች አሁንም አንድ እንደሆኑ ጠቁመው፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥት ግን ከዚህ በተቃራኒ የቆመ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መሪዎች በተደጋጋሚ በሠሩት ስህተት አንድ የነበሩ ሕዝቦች መከፋፈላቸውን፣ ያለፈው መጥፎም ሆነ ጥሩ ታሪክ ወደ መድረክ መጥቶ ግልጽ ውይይት በማድረግና ካለፈው ስህተት በመማር የሕዝቦችን ግንኙነት ማስጀመር ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሁሉም ስህተት ተደብቆ ሳይቀር ግልጽ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ተደብቆ የሚቀር ነገር መኖር የለበትም፡፡ ከኋላ ተነስተን ያለውን ተቀብለን ወደፊት መሄድ አለብን፡፡ እርስ በርሳችን እየተናቆርን መኖር የለብንም፤›› ብለዋል፡፡

ሌላ አስተያየት ሰጪ በሁለቱም አገሮች መካከል ካለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ባሻገር፣ የአሰብ ወደብን በጋራ እስከመጠቀም የሚደርስ ዕቅድ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራችና የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፣ የውይይት መድረኩን አድንቀው አሁን ባለው የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ባህሪ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ከግብ ከማድረስ አኳያ ፍርኃት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ለዚህ መደላድል የራሱን ችግር ሊፈጥር እንደሚችልም ሥጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለእነዚህና ሌሎች ለተነሱ ጥያቄዎች ፕሮፌሰር መድኃኔ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ታሪክ ስንል መሸፋፈን አይደለም፡፡ እንምረጥ ስንል እንርሳ ማለት አይደለም፡፡ አካዳሚያዊ ውይይቱ ታሪክን ማዕከላዊ አድርጎ ነው የቀረበው፡፡ አፄ ምኒልክ ጋ መሄድ አያስፈልግም፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ጋ አንሄድም፡፡ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ኃይሎችም የየድርሻቸውን ይወስዳሉ፡፡ ግን ከዚያ ትምህርት ወስደን ጥሩ ጥሩውን ወስደን ለመጓዝ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተነሳው የወደብ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡም፣ ‹‹የወደብ ጉዳይ የኮንቴይነር ማመላለሻ ሳይሆን የደኅንነት ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሁለቱን አገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማስጀመር ተነሳሽነቱ የመጣው ከወጣቶች እንደሆነ ጠቁመው፣ ተነሳሽነቱ ከላይ ወደ ታች በነበረበት ጊዜ የተሳካ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማሻሻል በተለያዩ አገሮችና የእምነት ተቋሞች የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም፣ ውጤታማ መሆን እንዳልቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሴለብሪቲ ኢቨንትስ ጉዳዩን የቤት ሥራው አድርጎ ከተንቀሳቀሰ ወራት እንደተቆጠሩና በዚህም የሚያበረታታ ውጤት መገኘት እንደተቻለ፣ የተቋሙ ኃላፊዎች በውይይት መድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡

የሴለብሪቲ ኢቨንትስ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ገብረ ሊባኖስ፣ በሁለቱ አገሮች የምሁራን ውይይት በቀጣይ ሊሠሩ የታሰቡ ዕቅዶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ የሁለቱን አገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማሻሻል ከኢትዮጵያ መንግሥት በጎ ምላሽ እንደተገኘ አስታውሰው፣ ‹‹ጉዳዩን ጫፍ ለማድረስ ኤርትራ ድረስ ሄደን የሁለቱን አገሮች የሕዝቦች ግንኙነት ከማሻሻል በተጨማሪ፣ በመንግሥታት ላይ ሕዝቦች ጫና እንዲያሳድሩ እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡ በቀጣይም ከሁለቱ አገሮች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አርቲስቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ሰዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ሰፋፊ ውይይቶች ለማካሄድ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡ የአሁኑ ጅማሬ ከግብ እንዲደርስም ከኤርትራ ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶችና ሌሎች እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እንደሚደረግና አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ የተጀመረ ሥራ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲሻሻልና የተጀመረው ጥረት ከግብ እንዲደርስ፣ ታዋቂው ባለሀብት አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ አቶ አብርሃም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ሰለብሪቲ ኢቨንትስ አቶ ዳዊትን የሰላም አምባሳደር አድርጎ መሾሙን በውይይቱ መጨረሻ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠቁሟል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...