- ዘንድሮ 345 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሏል
በተያዘው የምርት ዘመን አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ሰብስቦ እንደ ጨረሰ፣ የተለያዩ የውኃ አማራጮችን ተጠቅሞ ወደ መስኖ ልማት እንዲገባ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ ሐሙስ ታኅሳስ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ ከዚህ በፊት አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ጊዜ አምርቶ ረዥም የበጋ ወራትን ያለሥራ ይቀመጥ ነበር፡፡ አርሶ አደሩ ይህንን ልምድ እንዲለውጥና ወደ መስኖ እንዲገባ ጥሪ ተላልፏል፡፡
‹‹የመኸር ሰብሎች ተስብስበው እንደ ተጠናቀቁ አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሙያው፣ የአመራሩ ሁሉ ሙሉ ትኩረት መስኖ ልማት ላይ ይሆናል፤›› ሲሉ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩ የተለያዩ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ አማራጮችን በመጠቀም ረዥሙን የበጋ ወራት አትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም የአገዳ ሰብሎችን እንዲያመርት አሳስበዋል፡፡
በዚህ ትልቅና መሠረታዊ ለውጥ መሠረት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር 3.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በበጋ ያለዝናብ በመስኖ እንደሚለማ ዕቅድ አውጥቷል፡፡ በዚህም 469 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ከወዲሁ ታቅዷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አቶ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ በተያዘው ምርት ዘመን የአየር ንብረቱ መልካም ስለነበርና እንዲሁም ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ በመቅረቡ፣ ይገኛል ተብሎ የታቀደው 345 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ የሚጠቁሙ አመላካቾች ታይተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት በቤንሻንጉል ጉሙዝና በአራቱ ትልልቅ ክልሎች (ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ) በአጠቃላይ 13.7 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለምቷል፡፡ በዚህም መሠረት 345 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ታቅዷል፡፡
‹‹በአጠቃላይ የሚገኘውን ምርት የመግለጽ ኃላፊነት የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ቢሆንም፣ ይገኛል ብለን ያቀድነውን 345 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ የሚያስችል አቋም ላይ እንገኛለን፤›› ሲሉ አቶ ተስፋዬ ገልጸው፣ ‹‹እስካሁን 67.7 በመቶ የሚሆነው ምርት ተሰብስቧል፡፡ የተቀረውንም አርሶ አደሩ በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡ የኤክስፖርት ምርት የሆነው ሰሊጥ ሙሉ በሙሉ ተሰብስቧል፤›› ሲሉ አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል፡፡
መንግሥት በዝቅተኛው የዕድገት አማራጭ የግብርና ዘርፍ በስምንት በመቶ ያድጋል በማለት ግምቱን አስቀምጧል፡፡ በተለይ በ2008 ዓ.ም. ባጋጠመው ሰፊ ቦታ የሚሸፍን ድርቅ ምክንያት የታጣውን የግብርና ምርት ለማካካስ፣ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸው ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ዝናብ በመጠቀም በዓመት አንድ ጊዜ በማምረት ለረዥም ወራት ያለሥራ ስለሚቀመጡ፣ ይህም ብክነት ነው የሚል አቋም በመንግሥት መያዙ ተጠቁሟል፡፡