Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቀድሞ ፍትሕ ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታ ለእነ አቶ መላኩ ፈንታ የመከላከያ ምስክርነት...

የቀድሞ ፍትሕ ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታ ለእነ አቶ መላኩ ፈንታ የመከላከያ ምስክርነት ሰጡ

ቀን:

በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል በመዝገብ ቁጥር 141352 ላይ መከላከያ ምስክሮቻቸውን በማሰማት ላይ የሚገኙት፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ የቀድሞ ፍትሕ ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታን በመከላከያ ምስክርነት አሰሙ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ለአቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ መከላከያ ምስከር ሆነው ዓርብ ታኅሳስ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀርበው የመሰከሩት፣ የቀድሞ የፍትሕ ሚኒስትር አቶ ብርሃን ኃይሉና ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ናቸው፡፡

ምስክሮቹ በመከላከያ ምስክርነት የቀረቡት፣ እነሱ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. መንግሥት የታክስ ሥወራን ለመቆጣጠር በ1,000 ነጋዴዎች ላይ ጥናት ሲያደርግ፣ ከዘጠኝ እስከ አሥር የሚሆኑ ነጋዴዎች አራጣ ማበደራቸው በመታወቁ ባለሥልጣኑ ክስ እንዲመሠርትባቸው ውክልና ሲሰጠው፣ የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ከበደ ተካተው የተላኩ ቢሆንም፣ ከአቶ መላኩና አቶ ገብረ ዋህድ ጋር ባላቸው የጥቅም ግንኙነት እንዳይከሰሱ አድርገዋቸዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ ላይ መከላከያ ምስክርነታቸውን እንዲያሰሙ መሆኑን፣ አቶ መላኩ በጠበቃቸው አማካይነት ጭብጥ አስይዘዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ ብርሃን በእውነት ለመመስከር ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ በሰጡት ምስክርነት እንደገለጹት፣ የፍትሕ ሚኒስትር ሆነው የሠሩት ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡ እሳቸው በሠሩባቸው ዓመታት መንግሥት በ1,000 ነጋዴዎች ላይ ጥናት አላደረገም፡፡ ሐሳቡም ሆነ ዕቅድም አልነበረውም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የታክስ ሥራውን ለመከላከል በ1,000 ድርጅቶች (ባለሀብቶች) ላይ ጥናት ማድረጉን እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ጥናቱን ሲያደርግ ሰባት ባለሀብቶች ከፍተኛ ገንዘብ (ሀብት) እንዳላቸው በማወቁ፣ የገንዘቡ ምንጭ ከየትና ምን እንደሆነ ለማወቅ ተጨማሪ ጥናት ሲያደርግ፣ አራጣ ሆኖ እንዳገኘው መስማታቸውንም አቶ ብርሃን መስክረዋል፡፡ በመሆኑም አራጣ ወንጀል ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ ክስ ለመመሥረት ሥልጣን ስለሌለውና ሥልጣኑ የፍትሕ ሚኒስቴር በመሆኑ ውክልና መጠየቁን አብራርተዋል፡፡

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አራጣ በማበደር ከባንክ ወለድ በላይ ከፍተኛ ወለድ እንደሚያስከፍሉ የደረሰባቸውን ሰባት ተጠርጣሪዎች በመግለጽ፣ ውክልና እንዲሰጠው በባለሥልጣኑ የዓቃቤ ሕግ ዋና ዳይሬክተር በነበሩት አቶ እሸቱ ወልደ ሰማያት አማካይነት ማቅረቡን አቶ ብርሃን መስክረዋል፡፡ አቶ እሸቱ ጥያቄውን ያቀረቡት ለሚኒስትር ዴኤታው አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ብርሃን፣ በአቶ ብርሃኑ ፊርማ ውክልናው ለአቶ እሸቱ መሰጠቱንና ለእሳቸው በግልባጭ እንዲያውቁት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በተሰጠው አራጣ አበዳሪዎችን የመክሰስ ውክልና ውስጥ የአቶ ከተማ ከበደ ስም ተካቶ ስለመላኩ ተጠይቀው፣ አቶ ከተማን በሚመለከት ስለመሰጠቱ እንደማያስታውሱ፣ ነገር ግን በተገለጸው ዝርዝር ውስጥ እንዳልተካተቱና ተካተው ቢሆን ኖሮ በዝርዝሩ ውስጥ ይታዩ እንደነበር በመግለጽ አለመካተታቸውን መስክረዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ ፀጋዬም ቀርበው በሰጡት ምስክርነት፣ መንግሥት በ1,000 ነጋዴዎች ላይ ምንም ዓይነት ጥናት እንዳላካሄደ፣ ጥናቱ የተካሄደው በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሆኑን ገልጸው፣ በጥናቱ አራጣ አበዳሪዎችን በማግኘቱ፣ ክስ ለመመሥረት ከፍትሕ ሚኒስቴር ውክልና መውሰዱን አስረድተዋል፡፡

ውክልናውን በስማቸው ጠይቀው (ባለሥልጣኑን ወክለው)፣ ፈርመው የወሰዱት አቶ እሸቱ መሆናቸውን አረጋግጠው፣ ውክልናውን ፈርመው የሰጡት እሳቸው መሆኑንም መስክረዋል፡፡ ለሚኒስትሩም በግልባጭ ማሳወቃቸውንም አክለዋል፡፡ የመክሰስ ውክልና ሲሰጥ በቀረበላቸው ዝርዝር ውስጥ የአቶ ከተማ ከበደ ስም መካተት አለመካተቱን ተጠይቀው፣ የቀረበላቸው የሰባት ሰዎች ዝርዝር መሆኑንና በዚያ ውስጥ የአቶ ከተማ ስም እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

ምስክሮቹ ምስክርነታቸውን እንዳጠናቀቁ ዓቃቤ ሕግ በተለይ ለአቶ ብርሃን ኃይሉ መስቀለኛ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር ለባለሥልጣኑ በሰጠው ውክልና ላይ ከሰባቱ ተጠርጣሪዎች ጋር አቶ ከተማን ስምንተኛ አድርጎ ቢልክ ኖሮ፣ ክስ ሊመሠረትባቸው ስለመቻሉና አለመቻሉ ሲጠይቅ ተከሳሾች ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ከላይ በጭብጥ ያስመዘገቡትን ክስ ዓቃቤ ሕግ አቅርቦና አስመስክሮባቸው፣ እንዲሁም ተከላከሉ እንዲባሉ አድርጎ በመስቀለኛ ጥያቄ እንዴት ‹‹ቢሆን ኖሮ›› የሚል ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል የሚል ተቃውሞ አቶ መላኩ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ በብይን ይመዘናል እየተባለ ቀደም ብሎ የተሰጠ ምስክርነት ሳይመዘን መታለፉን በማስታወስ፣ ‹‹ቢሆን ኖሮ›› የሚለው ጥያቄ በችሎቱ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ፣ የመከላከያ ምስክርነት ማሰማታቸው ጥቅም እንደሌለው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

ሌላው በመከላከያ ምስክርነት የቀረቡት የቀድሞ የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዓቃቤ ሕግ የነበሩትና በእስር ላይ የሚገኙት አቶ መርክነህ ዓለማየሁ ናቸው፡፡ አቶ መርክነህ እንደመሰከሩት፣ የተቋሙ ሥልጣን የሚመነጨው ከተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 587/2000 ነው፡፡ ሥልጣኑም የታክስና ጉምሩክ ወንጀሎች ሲከሰቱ ይከሳል፡፡ በሥራ ሒደት በሌላ ተቋም ሥልጣን ሥር የሚወድቁ የወንጀል ግኝቶች ሲያጋጥሙት ውክልና ወስዶ ይከሳል፣ ይከራከራል፣ ያስወስናል፡፡ ነገር ግን ለመመርመር አይነሳሳም፣ አይመረምርም፡፡ በ2001 ዓ.ም. በተደረገ ጥናት አራጣ አበዳሪዎች በመገኘታቸው ከፍትሕ ሚኒስቴር ውክልና ወስዶ መክሰሱንና ማስቀጣቱን ገልጸዋል፡፡ አራጣ በማበደር ከባንክ ወለድ በላይ ወለድ ሲያስከፍሉ የነበሩት አቶ አየለ ደበላ፣ አቶ ከበደ ተሠራ፣ አቶ ሌንጫ ዘገየን ጨምሮ ሰባት ግለሰቦች መከሰሳቸውን ጠቁመው፣ አቶ ከተማ ከበደ ግን በዝርዝሩ ውስጥ እንደሌሉና በሳቸውም ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር የተሰጠ ውክልና እንዳልነበረ መስክረዋል፡፡ በባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ ሥራ ውስጥ የአቶ መላኩም ሆኑ የአቶ ገብረ ዋህድ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት እንደሌለበት፣ ከማንኛውም ነገር ነፃ ሆኖ ይሠራ እንደነበርና ከተፅዕኖ ነፃ መሆኑን አክለዋል፡፡

ለአቶ ከተማ ከበደ መከላከያ ምስክር ሆነው የተቆጠሩት አቶ ባህሩ አብርሃ ለመመስከር የቀረቡ ቢሆንም፣ የቀረበላቸውን ጥያቄ ‹‹አላውቅም፣ አልሰማሁምና አብሬ አልነበርኩም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን የአቶ ከተማ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳመለከቱት፣ ምስክሩ ከአቶ ከተማ ጋር በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል  ታስረው ብዙ ሚስጥሮችን ለአቶ ከተማ መናገራቸውንና በምርመራ ወቅትም ለፖሊስ የሰጡት ቃል የተመዘገበ መሆኑን ገልጸው፣ ሰነዱ እንዲታይላቸው አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሰነዱን እንደሚያየው አስታውቋል፡፡ ሌሎች አራት የመከላከያ ምስክሮች ለአቶ መላኩ፣ ለአቶ ገብረ ዋህድና ለአቶ ከተማ ቀርበው ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡  

ምስክሮቹ አቶ ጥሩነህ በርታ በወቅቱ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የኢንተለጀንስ ቡድን መሪ፣ አቶ ቁምላቸው ሻምበል የኢንተለጀንስ ሠራተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከታክስ ሥወራ ጋር በተያያዘ ስለተደረገ ክትትልና ከፍተኛ ገቢ እያንቀሳቀሱ አነስተኛ ግብር ስለሚከፍሉ ሰዎች ጥናት ተደርጎ እንደተደረሰባቸው መስክረዋል፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩም ለባንኮችና ለውል ክፍል በጻፏቸው ደብዳቤዎች የተገኙ የብድር ሰነዶችና የባንክ ስቴትመንት ማስረጃዎች የገንዘቡ ምንጭ አራጣ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከንግድ ድርጅቶቻቸውና ከመኖሪያ ቤታቸው በብርበራና በፍተሻ የተገኙ ማስረጃዎች ተተንትነው ክስ እንዲቀርብባቸው ለምርመራ ቡድን እንዲተላለፍ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡ የክትትል ሥራው በዋናው ዳይሬክተርና በበላይ አካል ቁጥጥር የሚደረግበት ስለሆነ፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከመርማሪዎች ጋር ፍተሻና ብርበራ እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡ የክትትሉን ሥራ ሚስጥራዊነት ለመጠበቅ፣ ዓቃቤ ሕግም ሆነ ሌላ ወገን ጣልቃ የማይገባበት መሆኑንና ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ ጉዳዩ ለዓቃቤ ሕግ እንደቀረበ መስክረዋል፡፡

አቶ ጥሩነህ እንደገለጹት፣ ለክትትልና ለምርመራው መነሻ የነበረው ከታክስ ሥወራ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ብቻ ነበር፡፡ በሒደት ግብር የማይከፍሉና አነስተኛ ግብር የሚከፍሉ ተጠርጣሪዎች የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ ምንጩ አራጣ መሆኑን የሚያመለክት ማስረጃ ከቀረበ በኋላ፣ አቶ መላኩ ለባንክና ለውል ክፍል ማስረጃ እንዲላክ በተጻፈው ደብዳቤ፣ የምርመራና የክትትል ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ አቶ ከተማ ከበደ ወይም ልጃቸው ትዕግሥት ከተማ እንዳልነበሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

አቶ ደግአደረገ ሥዩም የተባሉ አማራ ልማት ማኅበር የጽሕፈት ቤት ኃላፊም እንደመሰከሩት፣ ማኅበሩ የመክፈቻ በዓል ያከበረው ጥቅም 15 ቀን 2002 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ነው፡፡ በዚሁ ዕለት አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ከተማ ከበደ እንዳልነበሩ ተናግረዋል፡፡ ጥር 28 ቀን 2002 ዓ.ም. ባህር ዳር በነበረው የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ግን መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ የምሳ ግብዣ የተደረገው በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት እንጂ ዓባይ ምንጭ ሆቴል እንዳልነበረም መስክረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ታኅሳስ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በወጣው ዕትም አቶ መላኩ ፈንታ በቁጥጥር ሥር በነበሩበት ጊዜ መርማሪ፣ ‹‹አቶ ከተማ ከበደን ያልከሰስከው ለአማራ ልማት ድርጅት አሥር ሚሊዮን ብር ስለሰጠህ ነው፤›› የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው እንደነበርና አቶ ከተማ የምስክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ ግን፣ አሥር ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ለመስጠት ቃል እንዳልገቡ ገልጸው ነበር፡፡ አቶ ከተማ በምስክርነት እንዳረጋገጡት፣ በአማራ ክልል በሚሰጣቸው ባዶ ቦታ ላይ በአሥር ሚሊዮን ብር ወጪ ትምህርት ቤት ለመሥራት ቃል መግባታቸውን ነው፡፡ ለትምህር ቤት ግንባታ የሚውል መሬትም እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ጠይቀው ማግኘት ስላልቻሉ፣ የተባለውን ትምህርት ቤት መሥራት አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸው ነበር፡፡ በተጨማሪም አቶ መላኩ ፈንታ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ፕሮቶኮል ጠብቆ በየግብዣው ላይ መታየትና የድርሻን ወስዶ መሄድን እንደማይቀበሉ አስረድተው፣ የእሳቸው ድጋፍ የማይለያቸው ከሆነ፣ ተቋሙን በኃላፊነት መምራትና የታክስ ሪፎርም ጥናት ለማካሄድ ፈቃደኛ መሆናቸውን፣ ያቀረቡት ሐሳብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ሥራ መግባታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...