Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የመላውን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች መፍታት የሚቻለው በትክክለኛ ቁመና ላይ በመገኘት ብቻ ነው!

  በሩን ዘግቶ ለበርካታ ቀናት ስብሰባ የተቀመጠው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መሰንበቻውን በመሀል ባወጣው መግለጫ፣ ራሱን በመገምገም ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የሚመጥን ድርጅታዊ ቁመና ለመያዝ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ በአገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተመለከተ ባደረገው ግምገማም የችግሮቹ ዓይነተኛ ባህሪያትና ዋነኛ መንስዔዎች ላይ ዝርዝር ውይይት መደረጉን፣ ለችግሮቹም የማያዳግምና መሠረታዊ የሆነ መፍትሔ እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡ ለተፈጠሩት ደም አፍሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅቱ አመራር ድክመት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም አምኗል፡፡ ይህንን ግርድፍ መግለጫ በመተንተን በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ በአገሪቱ ባለፉ ሦስት ዓመታት እየታዩ ያሉ ችግሮች ከቀን ወደ ቀን ብሶባቸው የአደጋ ሥጋት ሲያንዣብብ፣ ድርጅቱ ራሱን በራሱ ለማደስና ወደ ትክክለኛው መስመር ለመመለስ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› መጀመሩን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ በዚህም መሠረት ለሕዝብ በርካታ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ቃል ቢገባም፣ ተሃድሶውም ሆነ ምላሹ ጥልቀት ስላልነበረው አገሪቱን መልሶ አዘቀት ውስጥ ከቷታል፡፡ ቃልና ተግባር አልገናኝ ብለው ሕዝብና መንግሥት ተቃቅረዋል፡፡ ለአገሪቱ እንግዳ የሆነ  የብሔር ግጭት ተቀስቅሶ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጭምር ለብልቧል፡፡

  ሕዝብ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ግልጽ ሆነው ሳለ በኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች መካከል በተከሰተው አለመተማመንና ጥርጣሬ ሳቢያ ውሉ ያልታወቀ ሽኩቻ ተጀምሮ፣ ለዜጎች ሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል፡፡ እንኳንስ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶችን አስከብሮ አገሪቱን ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመምራት ቀርቶ፣ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በተጨማሪ አጋር የሚባሉት ጭምር የሚሳተፉበት አደገኛ ትንቅንቅ ታይቷል፡፡ ከላይ እስከ ታች ተደረገ የተባለው ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› መክኖ ‹ኪራይ ሰብሳቢ›፣ ‹ኮንትሮባንዲስት›፣ ‹ትምክህተኛ›፣ ‹ጠባብ›፣ ወዘተ. በመባባል በተገኘው አጋጣሚ በመወራረፍና በመፈራረጅ ሕዝብና አገርን አደጋ ውስጥ የሚከት ሥርዓት አልበኝነት ተፈጥሯል፡፡ እርስ በርሱ ተፋቅሮና ተሳስቦ በመኖር የሚታወቅ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ውስጥ አለመተማመን በመፍጠር ማጋጨት የተለመደ ሥራ ሆኗል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሕዝባችንን የጋራ እሴቶች የሚንዱ በብልግና የታጀቡ ስድቦች ተሰምተዋል፡፡ በአገሪቱ ሕግ የሌለ እስኪመስል ድረስ በጠራራ ፀሐይ ንፁኃንን የገደሉና ያፈናቀሉ ጠያቂ የለባቸውም፡፡ በተደጋጋሚ መንግሥት አጣርቶ ለሕዝብ ያሳውቃል ቢባልም የውኃ ሽታ ሆኗል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሕዝብ እንዴት መንግሥትን ወይም ኢሕአዴግን እንዲያምን ይጠበቃል?

    ኢሕአዴግ በታሪኩ ይታወቅ የነበረው በጠንካራ ግምገማውና ባጠፉት ላይ ደግሞ በሚወስደው ምሕረት የለሽ ዕርምጃው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚታወቅበትን ጠንካራ ጎን ለአድርባይነትና ለአስመሳይነት በማጋለጡ ራሱን አረንቋ ውስጥ ከቷል፡፡ ከደጋፊነት ወደ አባልነት በገፍ የተሸጋገሩ አባላቱ ከመነሻው ሥልጣንና ጥቅም ፈላጊዎች በመሆናቸው፣ ድርጅቱ ቆሜለታለሁ ይለው የነበረውን ሕዝባዊነት ገደል ውስጥ ከቶታል፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ከሥልጣን ወደ ሥልጣን የሚንጠላጠሉ ብልጣ ብልጦች በኔትወርክ በመደራጀት የራሳቸውን ጥቅም ከማጋበስ የዘለለ አገራዊ ፋይዳ ስላልነበራቸው ድርጅቱን አሽመድምደውታል፡፡ ድርጅቱ ራሱ ይህንን ያምናል፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ግምገማዎችን እያደረገ ራሱን ማጥራቱን ቢናገርም፣ ቃልና ተግባር ሊገናኙ ባለመቻላቸው ራሱንም አገሪቱንም አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መጓደልና በሙስና ላይ ብቻ ይሳበብ የነበረው ችግር አድማሱን አስፍቶ ሌሎች ጥያቄዎችን አስከትሏል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግጭቶች የሚቀሰቀሱትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሕዝብ የተታለለ ሲመስለው የሥርዓቱን ህልውና አይፈልግም፡፡ ወጣቶች ምሬቱ ከመጠን በላይ ሲሆንባቸው ማንኛውንም አማራጭ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ችግሮችን ለማስተንፈስ ሲባል ብቻ የሚወጡ አገም ጠቀም መግለጫዎችም የባሰ ችግር ይፈጥራሉ እንጂ ፋይዳ የላቸውም፡፡ በብልጣ ብልጥነት ራስን ወቅሶ ለማድበስበስ መሞከር ትርፉ ቀውስ መፍጠር ብቻ ነው፡፡

  ሕዝቡንም ሆነ አገሪቱን ከቀውስ መታደግ የሚቻለው በአንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እሱም ለሕዝብ ፍላጎት መገዛት፡፡ የሕዝብ ፍላጎት ደግሞ የተሟላ ሰላም፣ የተሟላ ዴሞክራሲና የሁሉንም ሕዝብ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር ልማት ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት ከገዥው ፓርቲ ጀምሮ ለሕግ የበላይነት መገዛት የግድ ይላል፡፡ ለዚህ  ደግሞ በሕጉ መሠረት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማክበር አፈናን ማቆም፣ ዜጎች በመረጡት የፖለቲካ ድርጅት የመደራጀት መብታቸውን ዕውቅና መስጠት፣ የንግግርና የጽሑፍ ነፃነትን በተግባር ማረጋገጥ፣ ከአድልኦ የፀዳ የሥራ ሥምሪትና ዕድገት እንዲኖር ማድረግ፣ ዜጎች በመረጡት ሥፍራ የመኖር፣ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ማክበር፣ በዜጎች መካከል እኩልነት እንዳይኖር የሚያደርጉ ብልሹ አሠራሮችን በፍጥነት ማስወገድ፣ በሕጉ መሠረት ብቻ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲከናወን የሚያስችል ምኅዳር በፍጥነት መክፈት፣ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የተላቀቁ መንግሥታዊ ተቋማት እንዲኖሩ ማመቻቸት፣ የፓርቲና የመንግሥት ሥራን የመደበላለቅ መጥፎ አባዜን ማስወገድ፣ በሥልጣን መባለግ የሚነሱ አመራሮችን ለሕግ ማቅረብና ተጠያቂ ማድረግ፣ በአጠቃላይ ለሕዝብና ለአገር የማይጠቅሙ ብልሹ ድርጊቶችን በቁርጠኝነት በማጥፋት ሕዝባዊ ሆኖ መገኘት የግድ ይላል፡፡ ኢሕአዴግ ከገዥ ፓርቲነት በተጨማሪ በትክክለኛ ምርጫ ተሸንፎ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊሆን እንደሚችል ማመን ይኖርበታል፡፡

  አሁን ላሉ ችግሮች ዋነኛ መሠረት ኢሕአዴግ በራሱ አጋፋሪነት ከዛሬ 23 ዓመታት በፊት ሥራ ላይ የዋለውን ሕገ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንድ ሦስተኛ ክፍል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ላገኙ መሠረታዊ መብቶች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ እነዚህ መብቶች ከወረቀት ጌጥነት ባለማለፋቸው ግን ለዓመታት የተጠራቀሙ ብሶቶች በየአቅጣጫው እየገነፈሉ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት ይቀጠፋል፣ አካል ይጎዳል፣ ንብረት ይወድማል፣ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ቀውስ ይደርሳል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፣ ‹. . . በየደረጃው ያለው አመራር ከሞላ ጎደል የዚህ ድክመት [የደም አፋሳሽ ግጭት] ተጋሪ ቢሆንም፣ ሥራ አስፈጻሚው የዚህ ችግር ዋነኛ ባለቤት መሆኑንና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ እየተሸረሸረ ችግሮችን በቁጭት መንፈስ ከመፍታት ይልቅ፣ የእርስ በርስ ንትርክ ላይ እንደሚያተኩር መግባባት ላይ ተደርሷል፤›› ብሏል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም አደረግኩ ያለው ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ችግር እንደነበረበት ነው፡፡ አመራሩ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማጣቱ፣ እርስ በርሱ በመጠራጠር ሳቢያ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ መሸርሸሩን መግባባት ላይ ከተደረሰበት፣ ችግሩ ምን ያህል ፅኑ እንደነበር ያመለክታል፡፡ ይህ መግባባት ትክክል እንደሆነ በተግባር የማሳየት ኃላፊነት የኢሕአዴግ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት የተባሉት ሁሉ በተግባር አልታዩምና፡፡

  የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አንድ ላይ መቆም አለባቸው፡፡ ከፖለቲካ ሥልጣንና ይህ ሥልጣን ሊያስገኛቸው ከሚችሉ ጥቅማ ጥቅሞች በላይ ማሳሰብ ያለበት የአገርና የሕዝብ ህልውና ነው፡፡ ሥልጣን በአቋራጭ መያዝም ሆነ አገርንና ሕዝብን እያተራመሱ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረገው ሙከራ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው አገርን ነው፣ ሕዝብን ነው፡፡ ይህ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ የሥልጣን ጥመኞች የግጭት ሰለባ እንዳይሆን፣ አገር ደግሞ ለቀውስ ተዳርጋ የማትወጣበት አዘቀት ውስጥ እንዳትገባ መላ መፈለግ አለበት፡፡ አሁን ጊዜው የማስመሰልና የማድበስበስ ሳይሆን፣ እውነቱን መነጋገሪያ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በቀና መንፈስ በመቀራረብ ሁሉንም ወገን የሚያስማማ ብሔራዊ የውይይት መድረክ መፈጠር አለበት፡፡ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ምሁራን፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ሠራተኞች፣ ኅብረተሰቡን የሚወክሉ የተለያዩ አደረጃጀቶች፣ ወዘተ. ከፖለቲካ ወገንተኝነትና ከፍርኃት በመላቀቅ ለአገር የሚጠቅም መፍትሔ መጠቆም ይኖርባቸዋል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉና የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች ሳይቀሩ አስተዋጽኦዋቸው መፈለግ አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም ይታይበት የነበረውን የበላይነትና የአዛዥነት ካባውን አውልቆ ለሠለጠነ ውይይት ራሱን ማስገዛት አለበት፡፡ ራስን መውቀስ ጥሩ ነገር ሆኖ ሳለ ወቀሳውን ለሕዝብ ፍላጎት አለማስገዛት ግን በታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ቁመና ላይ መሆኑን በተግባር የማሳየት ፈተና ቀርቦለታል፡፡ የመላውን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች መፍታት የሚቻለውም በትክክለኛ ቁመና ላይ በመገኘት ብቻ ነው! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

  በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

  ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

  በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

  ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

  በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የሱዳንን የፖለቲካ ቀውስ ይፈታል የተባለው የሱዳን ጄኔራሎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት

  የሱዳን የጦር መኮንኖችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ሲቪል...

  ፈጠራና ቴክኖሎጂ የተሳሰሩበት ዓውደ ርዕይ

  በአበበ ፍቅር ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንትን በማስመልከት የተለያዩ   የፈጠራ...

  ‹‹የወደፊቷ ዓለም ዲጂታል ትሆናለች ሲባል ሰውን ማዕከል ማድረግ አለበት››

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሪስ፣ በኢትዮጵያ በተካሄደው...

  መልካም ምኞት የተገለጸለት የዓለም እግር ኳስ ንጉሡ ፔሌ

  በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዘው የዓለም እግር ኳስ ንጉሡ...

  ‹‹እኔ እኮ ብቻዬን አይደለሁም››

  አንድ አዋቂ ወደ ሌላ አዋቂ መኖሪያ ሄዶ እንዲህ ብሎ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ንፁኃንን ከአጥቂዎች መከላከል ነው!

  በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ንፁኃን ያለ ኃጢያታቸው የሚጨፈጨፉበት ምክንያት ብዙዎችን ግራ ከማጋባት አልፎ፣ የአገርና የጠቅላላው ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳሰበ ነው፡፡ መንግሥት...

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...