Saturday, May 25, 2024

ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖራትን ጥቅም ለመወሰን የተረቀቀው አዋጅ ላይ የተጠራው ሕዝባዊ ውይይት ተቋርጦ ተላለፈ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

  • የኦሮሚያ ክልል አመራሮችና የፓርላማ አባላት ጫና አሳድረዋል
  • አቶ አባዱላ ገመዳ ውይይቱ እንዲቀጥል ያደረጉት ጥረት አልተሳካም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደርና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖራትን ጥቅም ለመወሰን በተረቀቀው አዋጅ ላይ በጋራ የጠሩት የሕዝብ ውይይት ዓርብ ታኅሳስ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማው ዋና አዳራሽ የተሰየመ ቢሆንም፣ ከኦሮሚያ ክልል በተወከሉ አመራሮች ተቃውሞ ተስተጓጉሏል፡፡

ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ የተጀመረው ውይይት፣ ውይይት መካሄድ የለበትም በሚሉ የኦሮሚያ ክልል አመራሮችና የኦሕዴድ የፓርላማ አባላት የአካሄድ ጥያቄ፣ እንዲሁም ቋሚ ኮሚቴዎቹ ኃላፊነታችንን እንወጣበት በማለታቸው መግባባት አቅቶ ከአንድ ሰዓት በላይ ቆይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የሻይ ዕረፍት ወስደው ከተመለሱ በኋላ የኢሕአዴግ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎች አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴና አቶ አባዱላ ገመዳ፣ እንዲሁም ሌሎች ምክክር አድርገው ስምምነት ላይ ሲደረስ፣ የቋሚ ኮሚቴዎቹ አመራሮች ውይይቱ ከዚህ በኋላ ቢጀመርም በአንድ ቀን ማለቅ የማይችል በመሆኑ ለሌላ ጊዜ ቢተላለፍ ብለው ባቀረቡት ሐሳብ ላይ ከመግባባት ተደርሶ ውይይቱ ተበትኗል፡፡

ውዝግቡ ለምን ተፈጠረ?

የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደ ሰንበት መድረኩን የከፈቱበት አዳራሽ ውስጥ ከሦስት መቶ በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተው ነበር፡፡ በረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘካሪያስ ዘኮላ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ፣ ለተሳታፊዎችና በውይይቱ ለመሳተፍ ለተገኙ የፓርላማ አባላት፣ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወካዮች ዕድል እንደሚሰጡ ገልጸው ክፍት ሊያደርጉ ሲሞክሩ፣ በመድረኩ አካሄድ ላይ በርካቶች ጥያቄ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

ከበርካታ እጆች መካከል ዕድል ያገኙት የኦሮሚያ ክልል ካቢኔ አባልና የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ነበሩ፡፡ አቶ አዲሱ ባነሱት ሐሳብ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የኦሮሞ ሕዝብ እንደሆነ ጠቁመው፣ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ያለበትን ችግር ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ከ600 ሺሕ በላይ ኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፖች እየማቀቁ እኛ ተረጋግተን ገንቢ ሐሳቦችን መስጠት አንችልም፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፓርላማው ይህንን ረቂቅ አዋጅ ሲመራ በጥድፊያ ወይም ሰፊ የሕዝብ ውይይት ሳይደረግበት እንደማይፀድቅ አቅጣጫ ስጥቶ መሆኑን በማስታወስ፣ ቋሚ ኮሚቴው የኦሮሞ ሕዝብን ሳያወያይ ሊፀድቅ ስለማይገባ፣ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ቋሚ ኮሚቴውን ጠይቀዋል፡፡

አቶ አዲስ ያነሱት ጥያቄ ከሞላ ጎደል የሁሉም ተሳታፊዎች ጥያቄ ሆኖ በመገኘቱ ሰብሳቢው አቶ ጴጥሮስ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ ይህ ሕዝባዊ ውይይት ሐሳብ ለመሰብሰብና ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር እንጂ ለማፅደቅ አለመሆኑን፣ ይህ ውይይት ተካሄደ ማለት ቀጣይ ውይይት አይኖርም ማለት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ የፀጥታ ችግሩ ቋሚ ኮሚቴውን እንደሚያሳስበው፣ ነገር ግን ቋሚ ኮሚቴው በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት የመወጣት ግዴታ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ይህ የአቶ ጴጥሮስ ማብራሪያ ግን ተሳታፊዎችን ማሳመን ባለመቻሉ ተጨማሪ የአካሄድ ጥያቄ ተነስቷል፡፡ የአካሄድ ጥያቄውን ያነሱት የኦሕዴድ የፓርላማ አባል ግርማ መኮንን (ዶ/ር) ናቸው፡፡

‹‹በምክር ቤቱ የአሠራር ደንብ መሠረት ቋሚ ኮሚቴው የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ ሳያወያይ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ጠራ፡፡ ሕዝብን እንቅልፍ እየነሳ ያለ ችግር እያለ በልዩ ጥቅም አዋጅ ላይ መጣደፍ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተመሳሳይ ሐሳብ አንስተዋል፡፡

የተጠራው መድረክ በዚህ ውዝግብ ውስጥ እያለ በድንገት አቶ አባዱላ ገመዳና በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ወደ አዳራሹ ይገባሉ፡፡

በመጨረሻ ላይ የተነሳውን ሐሳብ ይዘት ብቻ እንዳዳመጡ በመናገር አስተያየት መስጠት የጀመሩት አቶ አባዱላ፣ ይህ ረቂቅ አዋጅ በጥድፊያ መፅደቅ የሌለበትና በየደረጃው ሕዝቡን በሰፊው በማወያየት መዳበር እንዳለበት ምክር ቤቱ ተግባብቶ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ለቋሚ ኮሚቴ መመራቱን አስረድተዋል፡፡ አዲሱ የሥራ ዘመን ከተጀመረ በኋላ ሕዝባዊ ውይይቱ በተነሱት ችግሮች ምክንያት መዘግየቱን እንደሚረዱ፣ ነገር ግን ዛሬ የተጀመረው ውይይት መቋረጥ አለበት ተብሎ የተነሳው ሐሳብ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹እንደዚህ ያሉ የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎት የሚነኩ ረቂቅ ሕጎች ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው በመሆኑ ቋሚ ኮሚቴዎች ዝርዝር ምልከታ በሚያደርጉበት ወቅት ከባለድርሻ አካላት፣ ወይም ከሕግ አውጪ ባለሙያዎች በመነሳት ውይይቱን በመጀመር ወደ ሕዝብ ውይይት ይወርዳሉ፡፡ በቂ ውይይት ተደርጎበታል ብለው ሲያምኑም የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባሉ፤›› በማለት የሥነ ሥርዓት ደንቡን ከተሞክሯቸው በማጣቀስ አብራርተዋል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ረቂቁ ከየትኛውም ቦታ ቢጀመር እንኳን ውይይት ይቁም ብሎ መከራከር ተገቢ አለመሆኑን፣ በኦሮሚያ ያለውን ችግርና አለመረጋጋት፣ እንዲሁም የፓርላማውን ሥራ ደባልቆ መመልከት ተገቢ አይደለም ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በዚህ ምክረ ሐሳብ መሠረት ውይይቱን ለመጀመር ሰብሳቢው ቢሞክሩም የባሰ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ ተሳታፊዎች አቶ አባዱላ ባቀረቡት ምክር እንደማይስማሙ ገልጸዋል፡፡

ሁኔታው ብስጭት ውስጥ የከተታቸው የሚመስሉት አቶ ጴጥሮስ፣ ‹‹የጠራናችሁ የቋሚ ኮሚቴውን ሥራ እንድትደግፉ እንጂ ሥራውን እንዳይሠራ እንድትወስኑ አይደለም፤›› በማለት ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈው ለሻይ ዕረፍት ውይይቱን በትነዋል፡፡

ውይይቱ በሻይ ዕረፍት ተወስኖ ሰብሳቢዎችና የተወሰኑ ተሳታፊዎች ከአዳራሹ ሲወጡ፣ በርካቶች ግን በአዳራሹ ቀርተው በኦሮሚኛ ቋንቋ ሲመካከሩና አቋም ሲይዙ ነበር፡፡ በአዳራሹ የቀሩትን ተሳታፊዎችም ሆነ ኮሪደር ላይ የነበሩ ሌሎች የኦሮሚያ ክልል አመራሮችን ሲመክሩና ሲያግባቡ የነበሩት አቶ አባዱላ ሰሚ አላገኙም፡፡

ከሻይ ዕረፍት በኋላ ውይይቱ ከተሳታፊዎች የተነሳውን ጥያቄ ሳይቀበል የሚቀጥል ከሆነ፣ ሁሉም አዳራሹን ጥለው ለመውጣት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ይህንን ያጤኑት የቋሚ ኮሚቴው አመራሮች ከሻይ ዕረፍት በኋላ፣ ‹‹የቀረው ጊዜ ውይይቱን ለማስጠቀል በቂ ባለመሆኑ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ›› በማለት አማራጭ ሐሳብ በማቅረባቸው ስምምነት ላይ ተደርሶ ውይይቱ ተበትኗል፡፡ በውይይቱ መጨረሻ ላይ አስተያየት የሰጡት አቶ አስመላሽ የሕዝብ ሐሳብ ሳይካተት የሚፀድቅ ሕግ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -