Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፌዴሬሽኑ ሕጋዊ አስተዳዳሪ ማን ነው?

የፌዴሬሽኑ ሕጋዊ አስተዳዳሪ ማን ነው?

ቀን:

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሁን ያለው አመራር የአገልግሎት ጊዜው ከተጠናቀቀ የወራት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ከአንድ ወር በፊት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተጠራው የፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በአፋር ሰመራ ታኅሣሥ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሚደረገው ምርጫ የአስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና የፌዴሬሽኑ ምርጫ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ታውቋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግለሰቦች ምርጫው እንዲራዘም በአንድም ሆነ በሌላ ከፊፋ ጋር ባላቸው ግንኙነት በተለይም የፊፋን የምርጫ ሥነ ምግባር መነሻ በማድረግ የምርጫውን አካሄድ በመኮነን፣ መራዘም እንዳለበት ለፊፋ ሪፖርት የሚያደርጉ ጭምር እንዳሉ ይነገራል፡፡ በምርጫ ሽግግሩ ምክንያት የፌዴሬሽኑ የዕለት ተዕለት ሥራዎች ብቻ ሳይሆን የተቋሙ ገንዘብና ንብረት ለብክነት እየተደረገ መሆኑ ይሰማል፡፡ ምርጫው እንዲራዘም ከሚፈልጉ ግለሰቦች መካከል አሁን ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ የሚገኙት አቶ ጁነዲን ባሻ አንዱ መሆናቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ እንዲያውም የአቶ ጁነዲን ካቢኔ ከታኅሣሥ 16 ቀን በኋላ ፌዴሬሽኑን የመምራት ምንም ዓይነት የሕግ ከለላ እንደሌለውም እየተነገረ ይገኛል፡፡ አቶ ጁነዲን በሕግና መመርያ ከተሰጣቸው የሥልጣን ገደብ በማለፍ የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ እንዳሰናበቱ፣ በምትኩ ደግሞ ሕጋዊ የሥራ ማስታወቂያ ሳይወጣ ቅጥር መፈጸማቸውን ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች የፌዴሬሽኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አቶ ጁነዲን ባሻን ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ በተለይም በአሁኑ ወቅት የአመራር ለውጥ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ የተነሳ በተቋሙ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ችግሮች እየታዩ መሆኑም ይሰማል፡፡ እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ጁነዲን፡- ፌዴሬሽኑ በበላይነት ከሚያስተናግዳቸው ሊጎች ጀምሮ ሁሉም በታቀደው መሠረት እየተከናወነ ነው፡፡ ከተቋሙ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጀምሮ በሽግግሩ ምክንያት ምንም ዓይነት የአሠራር ክፍተት የለም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር፡- ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ በእግር ኳሱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ በደጋፊዎች መካከል አለመግባባት እየተፈጠረ፣ ከሰው ሕይወት ጀምሮ ከፍተኛ የንብረት ውድመትና ጥፋት ተከስቷል?

አቶ ጁነዲን፡- ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ የሚታየውና የሚሰማው ጥቅል አስተሳሰብ እንደ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነቴ ለኅብረተሰቡ መናገር የምፈልገው በሜዳ ውስጥ በሚከሰቱ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል የቱንም ያህል ቢሆን ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ መቶ በመቶ ነው ባልልም ዘጠና በመቶው ውሳኔዎች ይሰጣሉ፡፡ ቅጣትም እየጎረፈ ነው፡፡ ይህም ያሳስበኛል፡፡ ምክንያቱም በዚህ መልክ ከቀጠልን መጨረሻውስ የሚለው ማለቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚሁ የውድድር ዓመት ወልዋሎ አዲግራትና ፋሲል ከተማ አዲግራት ላይ ሲጫወቱ ረብሻ ተፈጥሮ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ ፌዴሬሽኑ ችግሩን ተመልክቶ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የዲሲፕሊን ዕርምጃ አልወሰደም፡፡ ለወልድያ ከተማና ለመለ ከተማ ወልድያ ላይ ሊደረግ ታስቦ ለነበረው ጨዋታ ከሜዳ ውጪ ለተፈጠረው ረብሻና ውዝግብ አዲግራት ላይ ችግር በተፈጠረበት ወቅት ፌዴሬሽኑ የዲስፕሊን ዕርምጃ ባለመወሰዱ ነው የሚሉ አሉ፡፡  

አቶ ጁነዲን፡- በወልዋሎ አዲግራትና በፋሲል ከተማ ቡድኖች መካከል የተፈጠረውን የዲስፕሊን ክፍተት ተከትሎ ዕርምጃ ለመውሰድ ሪፖርት አልቀረበም፡፡ ረብሻ ነበር ስለመባሉም መረጃ የለኝም፡፡ ይሁንና አሁን አሁን እግር ኳሱ አካባቢ በሚከሰቱ ሁከቶች ራሱን የቻለ ውጪያዊ ገጽታም ያለው ይመስላል፡፡ በተለይ በክልሎች አካባቢ እግር ኳሱን ተከትሎ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችና ውዝግቦች፣ ስፖርቱን ከማጥፋት ያለፈ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ለችግሩ በዋናነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መፍትሔ ስለማይሰጥ ነው ሲባል ይደመጣል፡፡ ጉዳዩ ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ በወልድያ ከተማና በመለ ከተማ ቡድኖች መካከል የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ የሁለቱን ክልሎች ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችን አነጋግሯል፡፡ በንግግሩ ወቅት የተለያዩ የፀጥታ አካላትም ተሳትፈውበታል፡፡ በመርሕ ደረጃ የአማራ ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ምንም ችግር እንደሌለበት፣ ይሁንና ከእግር ኳሳዊ ባህሪ የወጣ ነገር እንዳለ በመሆኑም፣ በጉዳዩ የመንግሥት ድርሻ ትልቅ ሊሆን እንደሚገባ ጭምር በመነጋገር መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ ክልሎቹም በዚሁ አግባብ ተቀብለው ከኅብረተሰቡና በተለይም ከወጣቱ ጋር ተገቢውን ሥራ ሠርተው ውድድሩ እንደሚቀጥል ነው የተስማማነው፡፡ እዚህ ላይ ሌላው እንዲታወቅ የምፈልገው ለአንድ ጨዋታ አራት ዳኞችና አንድ የጨዋታ ታዛቢ ዳኛ ካልሆኑ ፌዴሬሽኑ ተጨማሪ ኃይል አይልክም፡፡ ስለሆነም የክልል የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አካባቢ፣ ዘርና ሃይማኖት የእግር ኳስ ባህሪም መገለጫም ሊሆኑ አይገባም፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል ወዳነሳሁት ነጥብ ልመልስዎት፡፡ የወልዋሎ አዲግራትና ፋሲል ከተማ ጨዋታ ያለዎት መረጃ ጨዋታው በሰላም ተጠናቋል የሚል ነው?

አቶ ጁነዲን፡- እንደ ፕሬዚዳንት ሁሉ ቦታ መገኘት ይኖርብኛል ብዬ አላስብም፡፡ በጨዋታው ዙሪያ ውይይቶች አድርገናል፡፡ ጨዋታው ተረብሾ ጉዳት ደርሷል፣ አልደረሰም የሚለው አልቀረበልኝም፡፡ ሁለቱን ክልሎች ስናወያይም የቀረበ ነገር የለም፡፡ በዕለቱ የነበሩ ዳኞችና ኮሚሽነሮችም ሪፖርት ማድረግ ነበረባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁንም ወደ ቢሮ እንደተመለስኩ ጉዳዩን እጠይቃለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ ስለነበረው የወልዋሎ አዲግራትና ፋሲል ከተማ ጨዋታ ምንም የደረሰዎት መረጃ የለም?

አቶ ጁነዲን፡- እያልኩ ያለሁት የጨዋታው ዳኞችና ኮሚሽነር የጨዋታውን ዝርዝር ጉዳይ አስመልክቶ ወደ እኔ የሚያደርሱበት መስመር አለ፡፡ በዚያ ደረጃ ነው አልደረሰኝም የምለው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ በሚገኙ ብዙኃን መገናኛም ሲነገር አልሰሙም?

አቶ ጁነዲን፡- ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን ተጋኖ የሚነገርበት ሁኔታ ስላለ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያስቸግራል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ዳኞችና ታዛቢ ዳኞች ትክክለኛውን ሪፖርት እንዲያደርጉ መመርያ የሰጠሁበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ዳኞችና ታዛቢ ዳኞች ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ በሰላም ተጠናቋል ብለው ሪፖርት የሚያቀርቡ ስላሉ ማለቴ ነው፡፡ ሌላው ለዚህ መንስዔ ሊሆን ይችላል ብዬ የማስበው እግር ኳስ ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ ወደ ክልል ወርዷል፣ ተደራሽ ሆኗል፡፡ ሆኖም ያንን አጣጥሞ መሄድ የሚያስችል አቅም ደግሞ ገና ነው፡፡ ከአደጋገፍ ጋር ተያየዞ እንዴት ነው የሚል በቂ ግንዛቤ በተለይ ወደ ገጠሩ አካባቢ እንደሌለ ነው የሚሰማኝ፡፡ እግር ኳስና ማኅበራዊ ጉዳዮችን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ኅብረተሰባችን ወደ እምነት ቦታዎች ይዞ የሚገባውን ዓይነት ወደ እግር ኳስም የራሱ መግለጫ በሆነው ማምጣት ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የእርስዎ ካቢኔ የአገልግሎት ጊዜው ተጠናቋል፡፡ አዲስ አመራር ለመምረጥ አስመራጭ ኮሚቴ ተሰይሞ የእርስዎም የኃላፊነት ጊዜ እስከ ታኅሣሥ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ እንዲቀጥል ጉባዔው ወስኗል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ምርጫው እንዲራዘም የእርስዎ ፍላጎት መሆኑ ይነገራል፡፡ ከሆነ ምክንያትዎ ምንድነው? ሌላው የፊፋ የምርጫ ሥነ ምግባር (ኮድ) እ.ኤ.አ. ከ2007 ጀምሮ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወቃል፡፡ ይህንንስ አያውቁትም ማለት ነው?

አቶ ጁነዲን፡- ፊፋ እ.ኤ.አ. ከ2007 ጀምሮ ሥራ ላይ ያዋለው የምርጫ ኮድ እንደኛ ሁሉ በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች የተከሰተ ጉዳይ ነው፡፡ ከምሥራቅ አፍሪካውያኑ ብጀምርልህ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ሱዳን ምርጫ ሊያደርጉ ሲሉ የምርጫ ኮድ ጉዳይ ቀርቦባቸው አስተካክለው ምርጫ አድርገዋል፡፡ በእኛም የተፈጠረው ተመሳሳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የፊፋም እገዛ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት እገዛ? ምክንያቱም ፊፋ ‹‹የምርጫ ሕጌ›› ይኼ ነው ብሎ ሰጥቷል፡፡ ያንን ተከታትሎ ሕጋዊ አካሄዱን መከተል የማን ድርሻ ነው?

አቶ ጁነዲን፡- እውነት ነው እያንዳንዱን የፊፋን ደንብና መመርያዎች ተከታትሎ የመፈጸምና የማስፈጸም ድርሻ ያላቸው ፌዴሬሽኖች ናቸው፡፡ እገዛ ያስፈልገናል ስል እውነታውን ለመሸሸ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- እውነታውን ካመኑ የፊፋን የምርጫ ደንብና አካሄድ ተከትሎ የፌዴሬሽኑን አዲስ አመራር በወቅቱና በጊዜው ማስመረጥ ሲገባ፣ ይባስ ብሎ ተቋሙን ለአላስፈላጊ ወጪ መዳረግ አያስጠይቅም?

አቶ ጁነዲን፡- ምን ተፈጥሮ ነው የተጠያቂነት ጉዳይ የሚነሳው? ቀደም ሲል ለመናገር እንደሞከርኩት ውድድሮችና የፌዴሬሽኑ የዕለት ዕለት ሥራ ላይ ክፍተት አልተፈጠረም፡፡ ስህተት በእኛ አገር ብቻ አይደለም፡፡ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ እየነገርኩህ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ሌሎች ከተሳሳቱ እኛም መሳሳት ይኖርብናል እያሉ ነውን?

አቶ ጁነዲን፡- በፍፁም፣ እያልኩ ያለሁት የምርጫ ኮዱን ምንነት ለመረዳት ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ኮዱ ዓለም አቀፍ ሕግ በመሆኑ ማለት ነው፡፡ ከሕጉ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ ሙያተኞቻችን በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፊፋ የምርጫ ኮድ በፌዴሬሽኑ ተሟልቷል፣ አልተሟላም ወደ ሚለው ዝርዝር ጉዳይ ልንገባ የቻልነው እንዴት ነው? ምክንያቱም ኮዱ ሥራ ላይ የዋለው ከ2007 ጀምሮ ከሆነ፤

አቶ ጁነዲን፡- እውነቱን ለመናገር ጉዳዩ ሊነሳ የቻለው እኛ ጠይቀን አይደለም፡፡ በዚህ ቀን ምርጫ ስለምናደርግ ፊፋ ተወካይ እንዲልክ በጠየቅነው መሠረት፣ ፊፋም ለተወካዩ የመግቢያ ቪዛ እንዲሠራለት ከተነጋገርን በኋላ በመሀል በተደረገ የስልክ ምልልሶች አስመራጭ ኮሚቴ አላችሁ ወይ? የሚል ነገር ተነሳ፡፡ በዚያን ጊዜ በእኛ የተለመደው አስመራጭ ኮሚቴ የምንመርጠው በምርጫው ዕለት መሆኑንና ሲሠራበት የቆየውም በዚሁ አግባብ ስለመሆኑ ጭምር መለስን፡፡ በምላሹም የአስመራጭ ኮሚቴ አስፈላጊነት የግድ እንደሆነ ተገለጸልን፡፡ ይህንኑ እኔ ራሴ ለጉባዔው በግልጽ አስረድቻለሁ፡፡ የተፈጠረውና እውነታውም ይኼው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምርጫው በዚህ መልኩ ተመሰቃቅሎ እንዲራዘም የእርስዎ ፍላጎት አለበት የሚሉ አሉ?

አቶ ጁነዲን፡- ሰዎች የፈለጉትን ሊሉ ይችላሉ፤ እውነታው አሁን የምናገረው ነው፡፡ ምርጫው ቢራዘም ምን የማተርፈው ነገር አለ?

ሪፖርተር፡- ፊፋ ያለው አልፏል በሚል ፌዴሬሽኑ ጉባዔውን በዚያው ቀንና ሰዓት ምርጫ ማድረግ እንደሚችል ይሁንታ ሰጥቶ እንደነበር የሚናገሩ አሉ?

አቶ ጁነዲን፡- ቀደም ሲል ከተናገርኩት በተቃራኒ በተለይ ፕሬዚዳንቱ ሳያውቁት ለፊፋ ደብዳቤ ተጽፎ የመጣ መልስ ነው፡፡ ይኼ ጉዳይ ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ ውሳኔውም ፊፋ ቀደም ሲል ባስቀመጠው ፍኖተ ካርታ መሠረት አስመራጭ ኮሚቴ በመምረጥ፣ ምርጫውም እንዲራዘም በድምፅ ብልጫ እንዲወሰን ነው የተደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- በድምፅ አሰጣጡ ሒደት ከፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ በመነሳት እንደነዚህ የመሰሉ ውሳኔዎች ሲተላለፍ የጉባዔውን ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማግኘት እንዳለበት የተከራከሩ ነበሩ?

አቶ ጁነዲን፡- የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ሳይታይ በእጅ ብልጫ እንዲወሰን ከተደረገ በኋላ ነው በማግሥቱ ጥያቄው የቀረበው፡፡ የተገደበበት ዋናው ምክንያትም ጉዳዩ በክፋት እንዳልሆነ ጉባዔው ስላመነበት ብቻ ነው ውሳኔው እንዲፀና የሆነው፡፡ በዕለቱ የአስመራጭ ኮሚቴ ጉዳይ ሲቀርብ እንደገና ሌላ ውዝግብ ተፈጠረ፡፡ ጉባዔውም በዚሁ ተጠናቀቀ፡፡ በቀጣዩ ጊዜያትም አስመራጭ ኮሚቴ የማይመረጥ ከሆነ ምርጫውን ለ45 ቀናት ማራዘም ጥቅሙ ምድነው? የሚል ነገር ከየአቅጣጫው መደመጥ ጀመረ፡፡ በድጋሚ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲመረጥ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ ሒደቱ ይህን ይመስላል፡፡  

ሪፖርተር፡- አስመራጭ ኮሚቴ በጠቅላላ ጉባዔው በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ሥራውን አከናውኖ ካጠናቀቀ በኋላ፣ የፈረንጆን ገና ምክንያት በማድረግ ምርጫው እንደገና ወደ ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲራዘም ተደረገ፡፡ አሁንም የእርስዎ እጅ እንዳለበት የሚናገሩ አሉ?

አቶ ጁነዲን፡- እውነቱን ለመናገር በእኛ ታኅሣሥ 16 በፈረንጆች የገና በዓል (ዲሴምበር 25) እንደሚሆን አስመራጭ ኮሚቴውም ይህንኑ እንዲያውቅ እኔ ራሴ መናገሬ እውነት ነው፡፡ ይህንኑ ለአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለአቶ ዘሪሁን መኰንን ነው የነገርኳቸው፣ በኮሚቴው በኩል ተለዋዋጭ ውሳኔ ከምናስተላልፍ በዚያው በቀኑ ብናደርግ ይሻላል ብለው ያንኑ ውሳኔ ለፊፋ አሳውቀዋል፡፡ እንደገና ዲሴምበር 25 የፈረንጆች ገና ከሆነ ፊፋ ተወካይ እንዴት ሊልክ ይችላል? የሚል ነገር ከራሱ ከአስመራጭ ኮሚቴው ተነሳ፡፡ ጉዳዩም ለፊፋ ተገልጾለት ተወካይ እንደማይልክና ለአንድ ሳምንት ያህል ቢራዘም የተሻለ እንደሚሆን መልስ ሰጠ፡፡ ፊፋ ከፈረንጆች ገና አንድ ሳምንት በኋላ ባለው እንድናደርግ ምክረ ሐሳብ ሰጥቶም ነበር፡፡ ይሁንና ይህ ቀን ደግሞ በኛ የገና በዓል የሚከበርበት በመሆኑ እንደገና ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲሆን ይህንኑ ፊፋ እንዲያውቀው ተደርጎ ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው ምርጫው እንዲራዘም የተደረገው፡፡  

ሪፖርተር፡- በፈረንጆች የገና በዓል ወቅት ቦትስዋናዊው የፊፋ ኃላፊ ለምርጫው መገኘት እንደሚችሉ የጻፉት ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ደርሷል የሚሉ አሉ?

አቶ ጁነዲን፡- ማፊ ዴቪድ የተባሉ የፊፋ ተወካይ የጻፉት ደብዳቤ የሚለው ታኅሣሥ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሚደረገው ምርጫ አይደለም እንደሚገኙ የተናገሩት፡፡ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 30 እንጂ ዲሴምበር 25 አለመሆኑን ጭምር አሳውቀዋል፡፡ ደብዳቤውን መመልከት ይቻላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይኼ ሁሉ መመሰቃቀል በእርስዎ ምክንያት የሚሉት ምንድነው?

አቶ ጁነዲን፡- አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ምርጫው ስለመደረጉ አሁን ባለው ሁኔታ እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

አቶ ጁነዲን፡- ይኼ የአስመራጭ ኮሚቴው ኃላፊነት ነው፡፡ እምነቴን ከሆነ ምርጫው የማይካሄድበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትልቁ የሥልጣን አካል ማን ነው?

አቶ ጁነዲን፡- ጠቅላላ ጉባዔው፡፡

ሪፖርተር፡- ጉባዔው እርስዎ በፕሬዚዳንትነት ለሚመሩት ካቢኔ ፌዴሬሽኑን እንዲያስተዳድር ሥልጣን የሰጠው እስከ ታኅሣሥ 16 ቀን ድረስ ነው፡፡ አሁን ምርጫው ወደ ጥር 5 ቀን መሸጋገሩ ተነግሯል፡፡ በዚህ መሀል ፌዴሬሽኑ ሕጋዊ ባለቤት የለውም፡፡ የሀብትና የንብረት ውድመት ቢከሰት ተጠያቂው ማን ነው?

አቶ ጁነዲን፡- ጉባዔው እስከ ታኅሣሥ 16 ብቻ አልወሰነም፡፡ በመርሕ ደረጃ የምርጫውን መራዘም ካፍም ሆነ ፊፋ እስከተቀበሉ ድረስ፣ የምርጫ አስፈጻሚውም ተቀብሎታል፡፡ ይኼ አካል ምርጫውን የማራዘም ሥልጣን እንዳለው መዘንጋት የለብንም፡፡ ጉባዔው የእግር ኳስ የበላይ አካል መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ለዚህ ጊዜ እኛስ ብንሆን እንዴት ነው ተቋሙን ለአደጋ የምናጋልጠው?

ሪፖርተር፡- የምንነጋገረው ስለ ጉባዔው ሥልጣንና ስለመተዳደሪያ ደንብ እንጂ ስለእምነትና ክህደት ነውን?

አቶ ጁነዲን፡- ይገባኛል፣ በእኔ እምነት በዚህ 15 ቀን በማይሞላ ጊዜ ሥልጣን የሚፈልግ አካል ያለ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ችግር ቢፈጠር እርስዎም ሆኑ ሌሎች አመራሮች ተጠያቂ የሚሆኑበት የሕግ አግባብ አለ?

አቶ ጁነዲን፡- ምንም የሚፈጠር ነገር አይኖርም፡፡ በቀናነት እናስበው ከተባለ ምርጫ እስኪፈጸም ተቋሙን ሜዳ ላይ ጥለን የምንሄድበት አግባብ አይታየኝም፡፡ እጃችን ላይ ያለውን ነገር በሥነ ሥርዓት እናስረክባለን፡፡ ይልቅስ ለምርጫ የሚቸኩሉ አካሎች ለምን ተብሎ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ የሚገርመው ምርጫው ለ45 ቀናት እንዲራዘም ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ለስድስት ወር፣ ለሁለት ወርና ለሦስት ወር እንዲራዘም የጠየቁ እንደነበሩ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እኔ ነኝ 45 ቀናት በቂ ነው በሚለው ስምምነት ላይ እንዲደረስ ያደረግኩት፡፡

ሪፖርተር፡- በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 36 ተራ ቁጥር ሁለት መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ የመጥራት ኃላፊነት የፕሬዚዳንቱና የዋና ጸሐፊ መሆኑን ይደነግጋል፡፡

አቶ ጁነዲን፡- እውነት ነው፡፡ አሁንም ጥር 5 ቀን ለሚደረገው ምርጫ ለጉባዔ አባላት ጥሪ እየተደረገ ያለው በፌዴሬሽኑ በኩል ነው፡፡ አስመራጭ ኮሚቴውም ይህንኑ አምኖበታል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ወገኖች ሥልጣኑ የአስመራጭ ኮሚቴ ነው የሚሉ እንዳሉ ግን አውቃለሁ፡፡ ይሁንና ከምርጫ ጋር ተያይዞ ከአመራሩ ጀምሮ በአጠቃላይ ተገቢ ያልሆነ ጩኸት እንዳበዛን ይሰማኛል፡፡ እግር ኳስ የአንድነትና የፍቅር መድረክ እንጂ ለአላስፈላጊ ጫጫታና ትርምስ መዋል የለበትም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሽግግሩም ሰላማዊ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ከዚህ በላይ መናገር ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ከምርጫው ጋር በተፈጠረ ውዝግብ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ ስንብቱ ብዙዎቹ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ሳያውቁት በእርስዎ ብቻ እንደተወሰነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ከደንብና መመርያ አኳያ ያስኬዳል?

አቶ ጁነዲን፡- ይኼ አብረው ወስነው በጎን ራሳቸውን እንደሌሉበት አድርገው ለማውራት የወሰኑ ካልሆነ በዋና ጸሐፊው ስንብት የሁሉም አመራሮች ስምምነት አለበት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዋና ጸሐፊው ቀደም ሲል አሞኛል በሚል መልቀቂያ አስገብተዋል፡፡ እንዲያውም በግሌ ጠቅላላ ጉባዔው እስኪያልፍ እንዲቀጥሉ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡ እንደማይችሉ ደግመው አረጋግጠውልኝ ነው የተሰናበቱት፡፡

ሪፖርተር፡- ስንብቱ ላይ የሁሉም አመራሮች ይሁንታ አለበት እያሉን ነው?

አቶ ጁነዲን፡- በነገራችን ላይ የጽሕፈት ቤቱን ጉዳይ በተመለከተ ኃላፊነቱ የፕሬዚዳንቱ ብቻ እንደሆነ በደንባችን አለ፡፡ እኔም ባደርገው ሕጉ ይፈቅድልኛል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ጉዳዩ የመጣው ግን ከራሳቸው ከባለ ጉዳዩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዋና ጸሐፊውን እንዲተኩ የተደረጉት ተጠባባቂ ጸሐፊ ሲቀጠሩ በእርስዎ ፍላጎት ያለማስታወቂያ መሆኑ ይነገራል?

አቶ ጁነዲን፡- እውነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከመንግሥት የሠራተኛ ቅጥር ሕገ ደንብ አኳያ የእርስዎ ውሳኔ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ጁነዲን፡- የእናንተን ተቋም ጨምሮ ለሴቶች ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት፣ ሴቶችን ለኃላፊነት ማብቃት ተገቢ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአሁኗ ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ በአካዴሚክ አቅማቸው ብቻ ሳይሆን በፊፋና ካፍ ደረጃ ተገቢው የእግር ኳስ ዕውቀት የቀሰሙ በመሆናቸው ኃላፊነቱ እንዲሰጣቸው አድርጌያለሁ፡፡ ጉዳዩም በቃለ ጉባዔ ለሥራ አስፈጻሚ እንዲቀርብ ጭምር ተደርጎ ነው ቅጥሩ የተፈጸመው፡፡

ሪፖርተር፡- በእሳቸው ደረጃ የበቁ ሌሎች እንስቶች ለኃላፊነቱ እንመጥናለን፣ ማስታወቂያ ወጥቶ ለሁሉም እንስቶች ዕድሉ ሊሰጥ ይገባ ነበር የሚሉ ጠያቂዎች ቢመጡስ?

አቶ ጁነዲን፡- በዚህ ደረጃ አልተመለከትኩትም፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲልም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሆነ በሌሎች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ያገለገሉትን ግምት ውስጥ በማስገባት ያደረግኩት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ውሳኔው ሕገወጥ ነው ብሎ ከሥራ አስፈጻሚው ጭምር ጥያቄ ያቀረበልኝ የለም፡፡  ዛሬ ለምን እንደተነሳም ሊገባኝ አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ በሽግግር ላይ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ተጠባባቂ ጸሐፊዋን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ብዙውን ጊዜ በውጪ ጉዞ መጠመዳቸው ይነገራል፡፡ ይህስ ለፌዴሬሽኑ የሀብት ብክነት ምክንያት አይሆንም?

አቶ ጁነዲን፡- ከሰሞኑ ወደ ካይሮ የተደረገውን ጉዞ የተመለከትክ ከሆነ ካፍ ራሱ በጠየቀው መሠረት የተከናወነ ነው፡፡ ከዚህ ወጪ የሆነ ነገር የለም፡፡ እግር ኳስ አካባቢ የተለመደ ስለሆነ ብዙም ትኩረት አልሰጠውም፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የእግር ኳስ ታሪክ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንቶች ውስጥ ተደጋጋሚ የውጭ ጉዞ በማድረግ እርስዎን የመጀመርያ የሚያደርጉ አሉ?

አቶ ጁነዲን፡- ለሥራ ካልሆነ ለግል ጉዳዬ የትም ሄጄ አላውቅም፡፡ ይኼ ፌዴሬሽኑን ለሁለተኛ ጊዜ ለማገልገል የምርጫ ዘመቻ ላይ ስላለሁ የተፈጠረ ማዘናጊያ ነው፡፡ የውጪ ጉዞ ባደርግም በካፍና ፊፋ ወጪ እንጂ በፌዴሬሽኑ የሄድኩበት አገር የለም፡፡ ባይገርምህ ከሰሞኑ ወደ አንጎላ አቀናለሁ፡፡ የሌሎች አገሮች ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች በዚሁ አግባብ የሚስተናገዱ ከሆነ ለምን የኢትዮጵያ ወንጀል ተደርጎ እንደሚነገር በራሱ ግልጽ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በቀድሞው የካፍ ፕሬዚዳንት ኢሳ ሐያቱ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የጨዋታ ኮሚሽነር ሆነው መሥራትዎ ይነገራል፡፡ ኮሚሽነር ለመሆን የዳኝነት ሙያ አይጠይቅም?

አቶ ጁነዲን፡- ካፍ ሥልጠና ሰጥቶኛል፡፡ ስህተት ከሆነም ለምን መዳቢውን አትተቹም? እርግጠኛ ነኝ ይኼ ጥያቄ የመጣው እኛ ለምን አልሄድንም ከሚሉ ወገኖች ነው፡፡ ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች የፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች ተመሳሳይ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለምን በመጥፎ ጎኑ እንደሚታይ አይገባኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ቃል በገባለት መሠረት የራሱን ሕንፃ ለመግዛት ጨረታ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ ፊፋ ቃል የገባው ገንዘብ የግዥው ሒደት ከተጠናቀቀ በኋላ ፌዴሬሽኑ በሚያቀርበው ትልመ ሐሳብ መሠረት ነው፡፡ ይሁንና ትልመ ሐሳቡ የዘገየው ከኮሚሽን ጋር በተያያዘ አለመግባባት መሆኑ ይነገራል፡፡ ምን ይላሉ?

አቶ ጁነዲን፡- ጨረታው ሁለት ጊዜ ወጥቷል፡፡ የመጀመርያው ፊፋ ገንዘቡን በጊዜ ባለመልቀቁ ሲስተጓጎል፤ በሁለተኛው ጨረታም ቢሆን እስካሁን ፊፋ ገንዘቡን ሊለቅልን አልቻለም፡፡ ከዚህ ውጪ የኮሚሽን ጉዳይ ስለሚባለው የማውቀው ነገር የለም፡፡ እንደተባለው ፊፋ ሕጋዊ ጨረታ አድርጋችሁ ገንዘቡን እለቃሁ ማለቱ እውነት ነው፡፡ በአፈጻጸም ላይ ግን ክፍተት አለው፡፡ በሌላ በኩል አገልግሎቱን ያጠናቀቀ ኮሚቴ ይህን የሕንፃ ግዥ መፈጸም የለበትም የሚሉ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...