Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በቀደም ዕለት በሞባይል ስልኬ የጽሑፍ መልዕክት ደረሰኝ፡፡ ስልኬ ድምፅ አሰምቶኝ ስከፍተው በባለ አራት አኀዝ ቁጥር አድራሻ የያዘ መልዕክት ነው የመጣው፡፡ ምን ይሆን ብዬ ስከፍተው በአማርኛ ቋንቋ ሲነበብ የሚረዱት በላቲን ፊደሎች የተጻፈ ነው፡፡ መልዕክቱ በአጭሩ የሚለው ‹‹ሲኖትራክ ያሸንፉ! ሞባይል፣ ቲቪ፣….›› በማለት ሦስት ብር በመክፈል መሳተፍ እንደምንችል ያግባባል፡፡ እኔ በበኩሌ ኢትዮ ቴሌኮም የማልፈልገውን ነገር ለምን እንደሚልክብኝ በጣም ነው የምናደደው፡፡ ይህ የግለሰቦችን መብት የሚዳፈር ድርጊት እንደሆነ አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ መልዕክት መቀበል እንደምፈልግ ጠይቆኝ ካልተስማማሁ በስተቀር ምንም ዓይነት ነገር እንዲልክብኝ አልፈልግም፡፡ ይህንን የምለው ራሴን ወክዬ ነው፡፡

ወደ መልዕክቱ ስመለስ ግን ይህንን ዕጣ በሞባይል ስልክ የጽሑፍ መልዕክት እየላኩ የሚያግባቡን ሰዎች ምን ማለት ፈልገው ነው? ከመቼ ወዲህ ነው በሲኖትራክ፣ በቲቪ፣ በሞባይል ስልክ ወይም በሌላ ቁሳቁሶች በሎተሪ ዕጣ የደረሰው ሰው ኢንቨስተር የሚሆነው? ይሁን እንበል ዕጣው ደረሰኝ፡፡ ያገኘሁትን ዕድል እኔ ነኝ የምወስንበት? ወይስ በደረሰኝ ዕጣ ኢንቨስተር እንድሆን ግዴታ አለብኝ? ግዴለም ይህም አጉል ክርክር ነው ይባል፡፡ ግን በእንዲህ ዓይነት ፈጽሞ አሳማኝ ባልሆነና ትዝብት ላይ የሚጥል ማግባቢያ ኢንቨስተር መሆን ይቻላል እንዴ? ኢንቨስትመንት እኮ የከፍተኛ ልፋትና የሥራ ውጤት መሆኑ ቀርቶ በየቦታው ባልሆነ መንገድ ሲተረጎም በጣም ይደብራል፡፡ በተቻለ መጠን አቀራረቡ ላይ እርማት አድርጎ የሚያዋጣ ከሆነ ሥራውን መቀጠል ሲቻል፣ ለትዝብት የሚዳርጉ አባባሎችን ማረም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይኼ  የእኔ ምክር ነው፡፡

በአገራችን በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው (ሬዲዮና ቴሌቪዥን) የምናያቸውና የምንሰማቸው ማስታወቂያዎች የቁጥጥር ያለህ የሚሉ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የማስታወቂያ ሕግ ወጥቶ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ ማስታወቂያዎች እንዴት መነገር እንዳለባቸውም በዝርዝር ተደንግጓል፡፡ ማስታወቂያዎች አታላይነት፣ አደናጋሪነት፣ ሕገወጥነትና የመሳሰሉት አላስፈላጊ ባህሪያት እንዳይኖሩዋቸውም በሚገባ በሕጉ ውስጥ ሠፍሯል፡፡ አንዱ የቢራ ፋብሪካ ይነሳና የነገሥታቱ ዘመን ውስጥ ከቶን ከነባራዊ ሕይወታችን ጋር የማይገናኝ ድርሳን ይዞ ይቀርባል፡፡ ሌላው የአራዳነት ወይም የከተሜነት ብቸኛ ወኪል ሆኖ ይቀርባል፡፡ እኔስ ያለው ደግሞ የባህል፣ የወግና የታሪክ መናኸሪያዎች አጋፋሪ ነኝ ይላል፡፡ በዚህ መሀል ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን እየሰሙና እየተመለከቱ ስላሉ ለግላጋ ወጣቶችም ሆነ ታዳጊዎች ማሰብ ቀርቷል፡፡ የይስሙላ ይሁን ወይም የግዳጅ ጫና ‹‹ከ18 ዓመት በታች አይሸጥም›› የሚል ታርጋ ይለጠፋል፡፡ በቃ፡፡

ከዚሁ ከማስታወቂያ ወግ ሳንወጣ ፓስታ፣ ሳሙና፣ ዳይፐር፣ ወዘተ ከአንጋፋ ማስታወቂያ ሠሪዎች እስከ ተለማማጆቹ ድረስ የሚያቀርቡልን በትወና ወይም በሙዚቃ ካልሆነ ዕርም ሆኗል፡፡ እኔ በበኩሌ በተለይ ብዙዎቹን ማስታወቂያዎች በቴሌቪዥን ሳያቸው የሚታዋወቁትን ምርቶች ለመጥላት እየተገደድኩ ነው፡፡ ማስታወቂያ ቀላልና ዘና በሚያደርግ አቀራረብ በዕውቀትና በጨዋነት ሲቀርብልን መልዕክቱን በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል፡፡ አለበለዚያ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ የቀረቡት ወይዛዝርትና አካኋናቸው ላይ ቀልባችንን ስንረሳው ሁሉም ነገር ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ አንጋፋዎቹ የማስታወቂያ ለፋፊዎች ሁሉም ነገር ውስጥ እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ እያሉ ሲያሰለቹን ሌላ ሐሳብ ውስጥ ጭልጥ ብለን በዚያው እንቀራለን፡፡ በዚህም የተነሳ የማስታወቂያ ማስነገሪያ ጊዜዎች የቤተሰብ ጉዳይ መወያያ እየሆኑ የድራማና የሙዚቃ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡

የማስታወቂያ ነገር ሲነሳ እግዚአብሔር ነፍሱን ይማረውና ተስፋዬ ካሳ የቀለደው አይረሳኝም፡፡ እስካሁን ድረስ ከአገሪቱ ኮሜዲያን ተርታ በቁንጮነት የማሠልፈው ተስፋዬ፣ ጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን ባዘጋጀው አንድ ሥራ መድረክ ላይ የቀለደው እንዲህ ነው፡፡ ‹‹ልጅ ከእናቱ ቤት ወጥቶ ለብቻው መኖር ሲጀምር ማዘር ብቸኛ ሆነች ይልና ቴሌቪዥን ይገዛላቸዋል፡፡ እሳቸውም ልጃቸውን መርቀው ቴሌቪዥናቸውን መከታተል ይጀምራሉ፡፡ አንድ ቀን ልጃቸው ‘እማዬ ቲቪው እንዴት ነው?’ ይላቸዋል፡፡ እናትም ‘ልጄ ተባረክ፡፡ ገንዘብህን አውጥተህ በገዛህልኝ ብዙ ነገር እያየሁ ነው፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ነጋ ጠባ መዘፍዘፍ፣ ነጋ ጠባ መዘፍዘፍ’ ይሉታል፡፡ ‘ምንድነው እማዬ? ምንድነው የሚዘፈዘፈው?’ በማለት ይጠይቃቸዋል፡፡ ‘ልጄ አንተማ ቴሌቪዥን ነበር የገዛህልኝ፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ? ሰዎቹ ጠዋት ማታ ሳሙናቸውን ለማስተዋወቅ እየዘፈዘፉ ሲጨፍሩ ቴሌቪዥኔን ሳፋ አደረጉት’ ብለው ነገሩት፤›› ብሎ እዚያ ሥነ ሥርዓት ላይ የነበርነውን በሳቅ አንፈራፍሮን ነበር፡፡

ይኼ 20 ዓመት የሞላው ቀልድ ቢሆንም ዛሬም ሳሙና እየዘፈዘፉም ሆነ ፓስታ እየቀቀሉ የመውረግረግ ፋሽን አላለፈበትም፡፡ በዚህ ዘመን ዓለም ከደረሰበት ሥልጣኔና ዕድገት አኳያ፣ ከአስተሳሰብ ዕድገት አንፃር፣ ከዕውቀትና ክህሎት መዳበርና ከአዲሱ ትውልድ ለውጥ ፈላጊነት መንፈስ ጋር የሚሄዱ አቀራረቦች ያስፈልጉናል፡፡ በጣም አሰልቺና እጅ እጅ የሚሉ ጊዜ ያለፈባቸው ቀልዶች፣ ተረቦች፣ ዲስኩሮችና ትርክቶች እንደተረሱ ሁሉ፣ አሁን ደግሞ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ አሰልቺ ማስታወቂያዎችንና የፕሮግራም ዝግጅቶችን መተው የግድ ይላል፡፡ በዲጅታል ዘመን አናሎግ የሆኑ ነገሮች እንደማይሠሩ ሁሉ ከዘመኑ እኩል መራመድ ተገቢ ነው፡፡ አቀራረባችን ቀላል፣ ግልጽና ምቹ ሲሆን ተቀባይነታችን ይጨምራል፡፡ ጥራት የሌላቸውና የሰው ቀልብ የማይስቡ አቀራረቦች ለጊዜው ይመስል እንጂ ገበያው አይፈልጋቸውም፡፡ ዊንስተን ቸርችል በአንድ ወቅት፣ ‹‹በወጣትነቱ ሶሻሊስት ያልሆነ ሰብዓዊ ርህራሔ የለውም፣ ያ ሰው ግን በ40 ዓመቱ ኮሙዩኒስት ሆኖ ቢገኝ አዕምሮ የለውም፤›› ያለው የሰው ልጅ በዘመን ውስጥ ተለዋዋጭ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡

(ሲራክ አልአዛር፣ ከወሎ ሠፈር)  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...