Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ውድቀት እያስከፈለ ያለው ዋጋ

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ውድቀት እያስከፈለ ያለው ዋጋ

ቀን:

በያሲን ባህሩ

      ከትውልድ ቅብብሎሽ ይልቅ በጥቂት ቀያሾቹ ላይ የተንጠለጠለ፣ ሁሉን አሳታፊ የፖሊሲና ስትራቴጂ ለማውጣት ቢሞከርም በአተገባበር ተጠልፎ ሊወድቅ ያለ፤ ወይም ስትራቴጂው እየነጠፈና ፈታኝ ሕዝባዊ ተግዳሮት እየገጠመው የሚሄድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ሥርዓት ማንቀላፋትን የሚያነቃው ምንድነው? የሚል ጥያቄ መሰንዘር ወቅታዊው የአገራችን አጀንዳ ነው፡፡ ታዳጊ ዴሞክራሲን በሚገነባ አገር ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር ዋነኛው መሠረትና የዘላቂ መፍትሔው ፈለግ እንደሆነ ማውሳትም የዚህ ጽሑፍ መነሻና መድረሻ ነው፡፡

       በዚህ መነሻ  የአገራችንን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ኢሕአዴግን የተጫጫነው የቅቡልነት ዕጦት ወደ መዘርዘር አንገባም፡፡ በእርግጥ መርህ የማያከብሩና ሕዝባዊ ዓላማውን የሳቱ ካድሬዎች መብዛት፣ ሕዝቡ እያሳደገ የመጣው ፍላጎት (በተለይም የዴሞክራሲ መስፋትና የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ጥያቄ) ተፅዕኖ በርትቷል ልንል እንችላለን፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን  ገዥው ፓርቲ  የማለለትንና የተገዘተለትን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ አውራ ፓርቲ የተባለው፣ የለየለት ጠቅላይነት ላይ  በመቆሙ ነው፡፡ ይህም  አስደንጋጭ የሚባል  ዋጋ እያስከፈለው መሆኑን መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ 

በአገራችን ታሪክ ውስጥ ትንሽ  የማይባል አሻራ ያሳረፈው ኢሕአዴግ  (በውስጡ መደማማጡ እንደ ተስተጓጎለ በግልጽ እየታየ ነው) ግን በበሽታ ላይ እንደሚገኝ፣ ወይም የአገሪቱ የፖለቲካ ንፍቀ ክበብ እንደ በረሃ ንዳድ በሚያንዘረዝር ቆፈን ውስጥ መወሸቁን ለመናገር ጠንቋይ መሆን የሚያስፈልግ አይደለም፡፡

ይህ አጉል ክስተት ደግሞ ከብዙ መንገላታትና ችግር በኋላ ቀና ማለት የጀመሩትን የአገራችንን ሕዝቦች  የሚጎዳና  የጋራ ቤታችንንም የሚያዳክም ስለሆነ፣ እንደ አንድ ዜጋ የመሰለኝንና የማምንበትን ሐሳብ ወደ መሰንዘር ለመግባት መርጫላሁ፡፡ ከሁሉ በላይ ሁኔታው የዜጎችን ለዘመናት የዘለቀ አብሮነትና አንድነት እያናወጠ፣ በመንደርተኝነትና በጥላቻ መንፈስ መናቆር እንዲፈጠር ማድረጉ ሁላችንንም ሊያነቃና ሊያስደነግጥ ይገባል ባይም ነኝ፡፡

      የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚባለው የመቻቻል፣ የመደራደርና የመወዳዳር የዴሞክራሲ ፈርጥ እንደ እኛ ላሉ የማንነት፣ የአስተሳሳብና አመለካከት ብዝኃነት ለታጨቀባቸው ሕዝቦች እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ያውም ኢትዮጵያዊያን በየማንነታቸው ከጥንት እስከ ዛሬ መሪና አዛዥ  የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ስለሆኑ፣ ክብርንና ነፃነትን አጥብቀው ስለሚሹ ቢደራጁም፣ ባይደራጁም የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶች እንደሚኖራቸው አለመጠርጠር የዋህነት ነው፡፡ ስለሆነም በአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ ስም ምልዓተ ሕዝቡን ወጥ በሆነ የግራ ዘመም አስተሳሳብ ለመወከል መሞከር አደጋ እያስከተለ መጥቷል፡፡ ‹ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር› የሚለውን የዴሞክራሲ መርሆም በመጋፋት ላይ  ነው፡፡  

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት፣ ሁሉም በአገራዊ ምርጫ የሚወዳደሩበትና የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ እኩል ዕድል የሚያገኙበት ሥርዓት  እንደ መሆኑ፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ዋስትና ማግኘቱ መልካም ነበር፡፡ ይሁንና በኢሕዴግ ራስ ወዳድነትም ይባል በዴሞክራሲ ተቋማት እንጭጭነትና ከተፅዕኖ ነፃ አለመሆን በገቢር ፈቀቅ አለማለቱ ብዙ ጣጣ እያስከተለ ነው፡፡ ለወደፊቱም ዘላቂና ሁሉን አቀፍ መፍትሔ ተበጅቶ በአገሩ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ውስጥ ባዕድ እየሆነ ያለውን ሰፊ ኃይል ማሳተፍ ካልተቻለ፣ ፈተናው ከዚህም በላይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

በመሠረቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በሕጋዊና ሰላማዊ  መድረክ  የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች፣ ራሳቸውን ችለው ወይም ግንባር ፈጥረው መንግሥት ለመመሥረት የሚችሉበት ሥርዓት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ግንባር ፈጥሮ ማሸነፍና ሥልጣንን መጠቅለል፣ ለዚህ የሚያበቃ ድምፅ ለማግኘት ካልተቻለ ደግሞ ጥምር መንግሥት መመሥረት የሚቻልበት አሠራር ያለበት ነው፡፡ ስለሆነም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊነትን የሚከተሉ ፓርቲዎች ጠንካራ ዓላማና አገራዊ አጀንዳ  እስከያዙ ድረስ እንደ መልካም አማራጮች እንጂ፣ ጠላት ተደርገው ሊቆጠሩ አይገባም፡፡ ባለተራ መንግሥታት መሆናቸውም ከግምት ሊገባ ይገባል፡፡ ከቀደመው ታሪካችን አንስቶ ሲንከባለል የመጣው የጥላቻ መንገድ ግን ይኸው እስከዚህኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ተገዳዳሪን በጠላትነት የሚያስፈርጅ  እንጂ፣ እንደ አማራጭ የሚመለከት ሊሆን አልቻለም፡፡

በታዳጊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገና በሁለት አሥርት ዓመታት ይህ  ለምን  አልተወገደም ባይባል እንኳን፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ የተቃውሞ ፖለቲካው አስኳል ተገፍቶ፣ ተገፍቶ በስደት ዓለም እየባዘነ፣ ይኸው ኃይልም ጽንፈኝነትና ጥላቻን ብቸኛ አማራጭ እያደረገ በአገር ውስጥም ሥርዓት አልበኝነትና ብሔርተኝነት አየሩን እየሞሉት አለፍ ሲልም ሕዝቡ ሳይደራጅና ሳያስፈቅድ ለአመፅ እየተነሳ፣ ወዘተ. በዚህም ላይ “ሁሉን ልጨምድድ ወይም ልጣ!” ብሎ የተነሳው ኢሕአዴግ መዳከም ሲጀምርና ሕዝቡ “ዞር በል!” ሲለው አደጋው እየከፋ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡ ሰላም በነበረችው አገር ሞት፣ ስደትና ንብረት ውድመት እንደ ቀላል የሚቆጠሩ ሲሆኑ፣ እንዲሁም በነፃነት መንቀሳቀስና ወጥቶ መግባት ፈታኝ መሆን ሲጀምር  የት ልንደርስ እንችላለን የሚለው ጉዳይ ያሳስባል፡፡ 

በመሠረቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን በታማኝነት የሚተገብሩ አገሮች ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች መካከል አንዱ ብቻ ተነጥሎ የፓርላማ አብላጫ ድምፅ የሚያገኝበት ዕድል ጠባብ ነው፣ የለም ሊባልም ይችላል፡፡ ስለዚህ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅም ለማበጀት ሲሉ ጥምረት ይፈጥራሉ፡፡ ታዲያ እኛ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ መጠፋፋትና ጥላቻን፣ ቂም በቀልና በተዛባ ታሪክ መናቆር አልፋና ኦሜጋ አድርገን እስከ መቼ ልንቀጥል ይሆን ብለን ማሰብ አለብን፡፡

ለዚህም ኢሕአዴግ በቀዳሚነት ሌሎች ፓርቲዎችም በተከታይነት ራሳቸውንና ሕዝቡን በመያዝ ካልፈተሹ ውጤቱ መክፋቱ አይቀሬ ነው፡፡ መንግሥትም እንደ አገር መሪነቱ ሚናውን ሳያደበላልቅ በሆደ ሰፊነት የለውጥ መዘውር ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ስለዚህ አስቸኳዩ ዕርምጃ መሆን ያለበት የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ማስፋት፣ አሳሪ ሕግና መመርያዎችን መፈተሽ፣ የሐሳብ ነፃነትን ያለገደብ ማረጋገጥ፣ በፖለቲካ እምነትና በሐሳብ መዘዝ የታሰሩ ዜጎችን በምሕረትም ይባል በሌላ መንገድ መፍታት፣  ብሎም ለሰጥቶ መቀበል አገራዊ ድርድር ራስን ማዘጋጀት ሊሆን ይገባል፡፡

 በእርግጥ በተቃውሞ ፓርቲዎች ንፍቀ ክበብ ረገድ ያለው ትብትብም ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ እስካሁን በተጨባጭ እንደታየው በአገሪቱ በየምርጫ ዘመኑ ለክልልና ለፌዴራል ሥልጣን የሚወዳዳሩ ከ60 እስከ 70 የሚደርሱ የብሔር ፓርቲዎች ሕዝብ የሚያማልል የጋራ አጀንዳ ሲያቀርቡ አልታዩም፡፡

አብዛኛዎቹ (ጥቂት የማይባሉትንም ራሱ ኢሕአዴግ ጠፍጥፎ እንደ ሠራቸው ይታማሉ)  በምርጫ ወቅት ከምርጫ ቦርድ የሚበተንን ጥሬ (ፍርፋሪ) ከመልቅም ያለፈ ሚና ስለሌላቸው ሕዝብ የሚያዝንባቸው ናቸው፡፡ አገርንና አጠቃላይ ሕዝብን ለማገልገል ከመነሳት ይልቅ  በብሔር አጀንዳ መወሸቅንም እንደሚያስቀድሙ የምንመለከተው ነው፡፡ ስለሆነም እንኳን ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ሊያግዙ ይቅርና በራሳቸው ዓላማ ሥር ተሠልፈው በድርጅታዊ መዋሀድ ላይ የተመሠረተ ተወዳዳሪነትን መፍጠር  አልቻሉም፡፡

እውነት ለመናገር ከአንድነትና ከኅብረት ይልቅ መለያየትና ጥላቻ የተበተባቸው፣ አንዳንዶቹም በጡረተኛ የ1960ዎቹ ፖለቲከኞች የጥርጣሬ መንፈስ የተወጠሩ፣ እንዲሁም በዓላማ ፅናት አልባ ወጣቶችና ምሁራን ዕጦት የሚወቀሱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም ገና በፓርቲ ሥልጣን ሽኩቻ ታምሰው የግለሰቦች ፓርቲ እስከ መባል የወረዱ መሆናቸው ሲታይ ለመንግሥትም ቢሆን እንዴት አመቺ ያልሆነ ፀረ ዴሞክራሲ ቅፍቅፍ እንደ ተደቀነበት አመላካች ነው፡፡ ሕዝብንም ተስፋ በማስቆረጥ አማራጭ ቁዘማ ውስጥ የሚከት ሁኔታ ነው፡፡ 

እንዲያውም አንዳንዶቹ ኅብረ ብሔራዊነት በመላበሳቸውና ጉምቱ ፖለቲከኞችን በመያዛቸው ተስፋ የተጣለባቸው (እንደ መድረክ፣ መኢአድ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓ. . .) መኖራቸው እንጂ ሕዝቡም የበለጠ ተስፋ ቆርጦ  ወደ መባከን ይገባ እንደ ነበር ጥርጥር የለውም፡፡

ይሁንና እነዚህም በየጊዜው ከውስጥና ከውጭ በሚነሳ ተፅዕኖ ሲከፈሉና ሲበተኑ ማየት፣ የአገሪቱ የተቃውሞ ፖለቲካ ንፍቀ ክበብ የገጠመውን ያልታከመ ወረርሽኝ  ለመገንዘብ ይረዳል፡፡ በዚህ ላይ ምሁራኑና ባለሀብቱ ከዳር ቆመው ለውጥን በመሻት ወይም በከፋ አድርባይነት በመውደቃቸው አዲስ ፊትና የተሻለ ተገዳዳሪ ለማግኘት አዳጋች ሆኗል፡፡ የብዙው ተገዳዳሪ መነሻም ጥላቻ እየሆነ መምጣቱ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ መዳከም የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ለማለት ይቻላል፡፡

       ከዚህ አንፃር በአገሪቱ ባለፉት 26 ዓመታት እንኳን ለሥልጣን የሚወዳደር የተቀዋሚ ፓርቲ ሊገነባ ይቅርና ገዥው ፓርቲ ራሱ ችግር ሲገጥመው ታግሎ የሚያስተካካል ተቀናቃኝ ኃይል አለመኖሩንም አረጋጋጧል፡፡ ይህ ሁኔታ ኢሕዴግንም “እኔ ብወርድ ማን አለና አገር ትቆማለች? ያው ትፈርስ እንደሆነ እንጂ. . .” የሚል ግብዝነት ውስጥ ከቶታል፡፡ ይህም ቀስ በቀስ ወደለየለት ፀረ ዴሞክራሲያዊነት (ሥልጣን ወይም ሞት) ወይም ባልተደራጀ የሕዝብ ትግል ወደ መደነቃቀፍ አዘቅት ውስጥ እንደሚከተው፣ የሌሎች ጎረቤት አገሮችን ተሞክሮ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡

አሁንም ሕዝቡ በፈቃዱና በጉልበቱ (በተለይም ወጣቱ) የፖለቲካ ምኅዳሩን ከፍቶ በአደባባይ እየተፋለመ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ በብሔር እየተፈላለገ (በተለይ ከሰሞኑ የሚታየውን ነገር በጥሞና ለመረመረው ድንጋጤውን ያንረዋል) ወደ መጋጨትና ስሜታዊነት እየገባ ያለው፣ በዚሁ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አለመጠናከር መዘዝ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡

እንደ አንዳንድ ተንታኞች አባባል አሁን በአገሪቱ እየተከሰተ ላላው የመልካም አስተዳዳር ዕጦት፣ የዴሞክራሲ መብቶች መታፈንና የኢኮኖሚና ሥልጣን ክፍፍል ኢፍትሐዊነት አንዱ  መንስዔ  የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታው ውድቀት ነው፡፡ ስለሆነም ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ መላው ሕዝብም ለዴሞክራሲያዊነትና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ማበብ መነሳት እንዳለበት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በምሁራኑ በኩል ያለው የከፋ አድርባይነትና አያገባኝም በሚል መንፈስ (የሰሞኑ የአማራ ክልልና የኦሮሚያ ክልል የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጅምሮች በጎ ናቸው)፣ እጅ እግርን አጣጥፎ መቀመጥ አገር እንደ ማፍረስ ተቆጥሮ መወገዝ አለበት፣ ይገባልም፡፡

በመሠረቱ  ለእኛ ዓይነቱም ሆነ ለሌላው ታዳጊ አገር ከባለ አንድ ወይም ከባለ ሁለት ፓርቲ ሥርዓቶች ይልቅ የተሻለው የብዙኃን/መድበለ ፓርቲ ሥርዓት  መሆኑ በተግባርም የተረጋጋጠ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ሊሳካ የሚችለው በሰበብና በገደብ ሳይሆን በትክክለኛው ዴሞክራሲያዊነት፣ በአገር ጉዳይ የጋራ ኃላፊነትን በመውሰድ፣ እንዲሁም ሕዝብን አደራጅቶ ለማነቃነቅ በነፃነት በመንቀሳቀስ ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ 

ይህች አገር የሁላችንም እንደ መሆኗ  የምሁራኑን፣ የባለ ሀብቱንና የሠራተኛውን የነቃና የተደረጃ ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ አጠናክሮ መጀመር ግድ ይላል፡፡ በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ  ግን  ይህ የዴሞክራሲ  ፈርጥ  ከብልጭ ድርግም አልፎ በለውጥ አዙሪት ውስጥ የገባ ጉዳይ አለመሆኑ፣  ሁሉንም አገር ወዳድ ዜጎች ሊያስጨንቅና ሊያስቆጭ ብቻ ሳይሆን ለለውጥ ሊያነሳሳ  ይገባል፡፡ የኢሕአዴግ የሁሉም ነገር አድራጊ ፈጣሪ ነኝ ወይም የችግሩ ሁሉ መፍትሔው እኔ ነኝ የሚለው የግትር መንገድም ሊገታ የሚገባው ነው፡፡ 

እውነት  ለመናገር የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ከስም አልፎ በገቢር ሁሉን ካሳተፈ፣ በአንድ ወይም በሁለት ፓርቲ ሳይወሰን በርካታ የተደራጀ አመለካከትና አቋም ያላቸውን ፓርቲዎች የሚያቅፍ በመሆኑ ተመራጭ ነው፡፡ ይነስም ይብዛም የሕዝቡ  ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀትና የመቃወም መብቶች ብቻ ሳይሆን የሥልጣን ባለቤትነቱንም የሚያረጋጋጥ ነው፡፡ እያንዳንዱ ፓርቲ የመራጩን ሕዝብ ድምፅ ለማግኘት ስለሚፎካካር የተሻለና ተወዳዳሪ የሆነ ፓርቲ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ፣  በሥልጣን ላይ ያለውም ለሕዝብ በመጨነቅ እንቅልፍ አጥቶ እንዲያድር ያደርገው  ነበር፡፡ ታዲያ ይኼ የሠለጠነ አካሄድ እንዴት ሊጠላ ይችላል? መደናቆር ካልሆነ በስተቀር፡፡

በተለይ ግን አንድ ነጠላ ፓርቲ የፓርላማውን፤ የሕግ ተርጎሚውንና የአስፈጻሚውን ሥልጣን ያለገደብና ያለተቀናቃኝ እንዳይዝ ለማድረግ እውነተኛ  የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጥሩ ብቻ ሳይሆን ግሩም  ነው፡፡ በአገራችን ከምርጫ 2007 በኋላ እንኳን  ከገዥው ፓርቲ የተለየ አንድም አማራጭ ሊስተናገድበት የሚችል አለመሆኑ፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ግንባታ ውድቀት ማመለካቱ ብቻ ሳይሆን የሐሳብና የአመለካካት  ብዝኃነት በታጨቀበት ምድር ሕዝብን ድምፅ አልባ ማድረግ ከፍ ያለ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ አገርንም ወደ ጉዳት የሚወስድ ነው፡፡

 እርግጥ እዚህ ላይ የፖለቲካ ድርጅት የመሠረቱ አመራሮችና አባላት ኃላፊነትም ከፍተኛ እንደሆነ መጤን አለበት፡፡ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለመጠቀም የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዋነኛነት የሕዝብ ድምፅ ለማግኘትና ለመመረጥ ያለማቅማማት መሥራት አለባቸው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል ነፃነት  እንደሚሰጥ መገንዘብና በተግባር ዕውን እንዲሆን መታገልም  ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ይህን መብት የሚከለክልና የሚያግድ ምንም ዓይነት ሕገወጥ ኃይል እንዳይኖር መታገል ያስፈልጋል፡፡

በየትኛውም የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚተገብር አገር ውስጥ ፓርቲዎች  ይናገራሉ፣ ይጽፋሉ፣ አቋማቸውን ለሕዝብ ያሳውቃሉ፣ ከሌላው ፓርቲ የሚሻሉበትን አማራጭ አቅርበው በሚዲያ ይከራከራሉ፡፡ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ግንባር ይፈጥራሉ፡፡ መድረክም ሆነ ኅብረት መጠርያው ምንም ይሁን ምን ይሰባሰባሉ፡፡ ድምፅ አግኝተው ከተመረጡና መንግሥት ከመሠረቱ ገዥ ፓርቲ ወይም መሪ ፓርቲ  መሆን ይችላሉ፡፡ በእኛ አገርስ ለምን ይህን መጀመር ተሳነን? እስከ መቼስ አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ በዜሮ ድምር የፖለቲካ ጨዋታ መቀጠል ይቻላል? ብሎ መጠየቅ የወቅቱ ትውልዳዊ ኃላፊነት ነው፡፡

        የተፎካካሪ ፓርቲዎች መዳከምና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሕይወት አልባ መሆን፣ የገዥውን ፓርቲ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ያበረታል፡፡ በተፈጥሮው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ድርጅት እንኳን ቢሆን ግልጽነትና ተጠያቂነትን እየዘነጋ፣ የሕዝብ ጥያቄንና መብትን እየደፈቀ በራሱ ጥገኞች ጥንጣን ተበልቶ እንዲገነደስም ያደርገዋል፡፡ ካልሆነም በለየለት ድርቅናው ገፍቶበት አገር እንዲበተን ያደርጋል፡፡ እንግዲህ እኛንም ከዚህ ያውጣን ነው! ሌላ ምን ይባላል?

በዚህ ዓይነቱ ድክመት ውስጥ የገባ የየትኛውም አገር አገዛዝ  በመንግሥት ሀብት የፓርቲውን ሥራ ይሠራል፣ ቁልፍ በሆኑ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የራሱን ፓርቲ ካድሬዎች ያለ ችሎታና ብቃታቸው በብቸኝነት ይሾማል፣ ሕገ መንግሥት ቢጻፍም ያሻውን የመተግበር መዋቅር ይዘረጋል፡፡ ሕዝብ አይደመጥም፣ የብሔርና የመደብ (ቢያንስ ማኅበራዊ መሠረቴ የሚለውን ጥቅም በማስቀደም) ልዩነትን አይገታም፣ ራሱንና የራሱን ደጋፊዎች ብቻ ከመስማት አይወጣም፡፡

ከዚያም አልፎ ውሰጠ ድርጅት ዴሞክራሲው እየከሳ ሥርዓት አልበኝነት ይንሰራፋል፡፡  ይህ አካሄድ ደግሞ ለሕዝባዊና አገራዊ  ፖለቲካ ፀር ነው፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ሌላውን ሳይንቅ፣ ቀረብ አድርጎ ራሱን ፈጥኖ በመፈተሸ  አሁኑኑ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በማሳተፍ ቆም ብሎ መፍትሔ ማምጣት አለበት፡፡ የተሸከመው ሕዝባዊና አገራዊ አደራም ይህን እንዲያደርግ ግድ  ይለዋል፡፡       

በአጠቃላይ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ለአገራችን ፖለቲካ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያመጣ  መጠራጠር ዓይንን ጨፍኖ ራስን ወደ ገደል እንደ መወርወር ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም ከአስመሳዩ የፖለቲካ ትግል በመውጣት በውድድር፣ በሠለጠነና በሰላማዊ መንገድ ለሥልጣን የሚያበቃ የፖለቲካ ትግል እንዲጠናከር ያለፍርኃት ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥታዊው ቁልፍ በእጃቸው እንዳለ ተገንዝብው ዘላቂውን መንገድ የማበጀት ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ይህ ሳይደረግ  ቀርቶ  በተለመደው ግትርነትና ቅንነት የጎደለው የፖለቲካ አካሄድ፣ ወይም በወታደራዊ ኃይል መፍትሔ ለማምጣት መሞከር ግን ታሪካዊ ተወቃሽነትን የሚያስከትል ጥፋት መጋበዝ ብቻ ሳይሆን፣ ለማንም የማይበጅ መዘዘኛ ዋጋ የሚያስከፍል እንደሆነ መረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...