Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትኧረ ለመሆኑ ኪራይ ሰብሳቢነት ምንድን  ነው? ኪራይ ሰብሳቢውስ ማነው?

ኧረ ለመሆኑ ኪራይ ሰብሳቢነት ምንድን  ነው? ኪራይ ሰብሳቢውስ ማነው?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

የአገር ልጆች ሲተርቱ ‹‹ሰው ኑሮውን ይመስላል›› ይላሉ፡፡ የምሳሌው ትርጓሜ ድህነትም ሆነ ጌትነት ዝርዝሩን ቁመና ላይ ይጽፋል ማለት ነው፡፡ የገበሬና የወዛደሩ የኑሮ ቆፈንና አሳር የፊት ቆዳው ላይ፣ ግንባርና መዳፉ ላይ ይቆጠራል፡፡ የጌታ ድሎትም እንዲሁ ነው፡፡ ‹‹አፍ ሲያብል ገላ በላሁ ይላል››፡፡ ምቾት ዓይንና ገላ ላይ ይታተማል፡፡ የትኛውም የኑሮ ዘይቤ ህሊናም ላይ እንዲሁ እያንዳንዱን ነገሩን ያትማል፡፡ የተገላቢጦሽ ግን አይደለም፣ ሐሳብና ምኞታችን ስለሰበክነው ወደ ኑሮነት አይሸጋገርም፡፡ ‹‹አትስረቅ፣ ክፉ አትሥራ፣ . . . ወዘተ›› ሲሰበክ ስንት ዘመኑ! ስብከቱን በየቀኑም ሆነ በየሳምንቱ እንጠጣዋለን፡፡ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ትንሽ ኃፍረትና ፀፀት ብጤ እንድንቀማምስ ወይም በአፍአዊ ጨዋነት ገመናን ለመሰወር ከመጥቀሙ ባሻገር እጅግም ኑሯችንን አላረመም፡፡ ክፉ ሥራውም፣ ሌብነቱም በተለያየ ደረጃና ሥልት እንደ ጉድ ይካሄዳል፡፡ በተሰባኪው ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሰባኪዎቹ ውስጥም፡፡

ኢሕአዴጋዊ ገዥዎቻችን ተራማጅ ነን ይላሉ፡፡ እስከምናውቀው ድረስም ተራማጅነታችው የማርክሳዊነት ጀርባ ያለው ነው፡፡ የማርክሳዊ ተራማጅነት አንዱ የአስተሳሰብ ዓምድ፣ የሰዎች ማኅበራዊ ህሊና ብዙ ትውፊታዊና ቀኖናዊ ዝግንትል ሊኖረው ቢችልም፣ በመሠረቱ በማኅበራዊ ህልውና የሚቃኝ ነው የሚል ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ መሠረት ሰው በየጊዜው የሚቀርፀው ግንዛቤ ተወላገደም ተጠናገረም፣ የማኅበራዊ እውነታና ግንኙነት መነሻ አለው፡፡ ተግባራዊ አኗኗር ዋነኛ የህሊናው ገሪ ነው፡፡ ማኅበራዊም ሆነ ግለሰባዊ ህሊና ከዕውናዊ ኑሮ ጋር ባልተዋወቀና በማይግባባ መዓት ነገር ቢጎሰር ጉስሩ በኑሮ ትግል ውስጥ የማደናበር፣ ጥምዝምዝንና ደፋ ቀናን የማብዛት ተፅዕኖ ይፈጥራል፣ ወይም ነባራዊ ኑሮን የማይወጋ አፍአዊ ኳኳቴ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡

- Advertisement -

እውነታን እየበረበረ ሊሆን የሚችለውንና የማይችለውን (የአዲስ ዕድገት አላቦችን ብርታት ከፀሮቹና ከእንቅፋቶቹ ብርታት ጋር አገናዝቦ) የተረዳ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መርሐ ግብር፣ የአሮጌ ባህል ግሳንግስን የሚገለባብጥና መላውን ሕዝብ አንድ ላይ የሚቀዝፍ የለውጥ ኃይል መሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ የእኛ አገሮቹ ‹‹ተራማጆች›› ሥፍራቸው የት ነው? ‹‹ጥገኝነትን/ኪራይ ሰብሳቢነትን ነጋ ጠባ እንታገላለን፤›› ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ይህ ልፍለፋቸው ለጥገኞች ዘረፋና መደበቂያ የማይመች እውነታ በመፍጠር ተግባር የተመራ ነው? ወይስ ለምጥመጣ የሚመች ሁኔታን አቅፎ የያዘ ባዶ ኳኳታ ነው?

እስኪ እውነቱን እንነጋገር “ጥገኝነት/ኪራይ ሰብሰቢነት” የሚባለው ነገር ምንድን ነው? “ኪራይ ሰብሳቢ/አሳዳጅ” ከኢኮኖሚ ሳይንስ ጋር ትንሽም ያህል ትውውቅ ለሌለው ሰው በሁለት ምክንያት ሊያደናግር ይችላል፡፡ አንደኛ ቃሉ ያዘለው ከተራ ልብታ የዘለለ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ሁለተኛ ስያሜው ጤናማ የሆነ ኪራይ ሰብሳቢነትን ጤናማ ካልሆነው ለመለየት አያግዝም፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁለት ትልልቅ ሥራዎች ይካሄዳሉ፡፡ አዲስ ምርት (እሴት) የማምረት ተግባር አንዱ ነው፡፡ አንጋሬ ለፍቶ ልዩ ልዩ ቆዳ ነክ ነገሮችን (ጫማ፣ ቦርሳ፣ ጓንት፣ የመሳሰሉትን) ለማምረት ይውላል፡፡ የተመረቱት አዳዲስ ቁሳቁሶችና ፈላጊያቸው አጠገብ ለአጠገብ ላይገናኙ ይችላሉ፡፡ በተወሳሰበ ኅብረተሰብ ውስጥ አምራችና ገዥ ከመራራቅም ባለፈ ላይተዋወቁ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴ አዲሱ ዕቃ አባብሎም ቢሆን ራሱን ማስተዋወቅና ፈላጊዎችን ማፍራት ሊያስፈልገው ይችላል፡፡ ዕቃን የማስተዋወቅ ሥራ የአገልግሎት ኪራይ ያስከፍላል፡፡ ዕቃውን ከተመረተበት ሥፍራ አንስቶ የመጓጓዣ ወጪውን ሁሉ ችሎ ፈላጊው ሊያገኝ የሚችልበት ገበያ ድረስ አድራሹና ሻጩም ለዚያ አገልግሎቱ ኪራይ ይቀበላል፡፡

የተለያየ ሥራ ሠርቶ ትርፍ ለመፍጠር የሚሻ ሰው ለዚያ የሚሆን ገንዘብ ሳይኖረው ሲቀር፣ የተቀመጠ ገንዘብ ካለው አካል ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሠርቶበት ለመመለስ ይበደራል፡፡ ለዚያ አገልግሎት ደግሞ ዋናውን ከመመለስ ባሻገር ኪራይ (ወለድ) ይከፍላል፡፡ ዋናውን ከእነ ወለዱ መክፈል የሚችለው የተበደረውን ገንዘብ ዕላፊ ገንዘብ እንዲወልድ አድርጎ ከሠራበት ነው፡፡ ገንዘብ ተበድረው መሥራት የሚሹ ሰዎች ማን የሚከራይ ገንዘብ አለው እያሉ በመናወዝ ችግራቸውን አይወጡትም፡፡ አንድ ባለገንዘብ ግለሰብም የስንትና ስንቱን ገንዘብ ፈላጊ ፍላጎት በራሱ የገንዘብ አቅም መሸፈን አይችልም፡፡ ይህንን ክፍተት የደፈኑት ባንኮችና መሰሎቻቸው ናቸው፡፡ ባንኮች ሥራ የፈታና አስተማማኝ ማስቀመጫ የሚሻ ገንዘብን እየሳቡ በማሰባሰብና ለተበዳሪ በማቅረብ፣ ተበዳሪ ከሚከፍው ወለድ ላይ ለአስቀማጩ የተወሰነ ኪራይ ይከፍሉና ራሳቸውም ለሰጡት የማስቀመጥና የማበደር አገልግሎት ኪራይ ይወስዳሉ፡፡

የጤና ሁኔታችንን ለማወቅ ወይም ሕመም ሲያገኘን ወደ ሐኪም እንሄዳለን፡፡ የሕክምና ሰዎች ሙያዊ አገልግሎታቸውን ያከራያሉ፡፡ ታካሚዎችም አገልግሎታቸውን ለተወሰነ ጊዜ እንከራያለን/እንገዛለን፡፡ ይህን በመሰለ አኳኋን የምንከራያቸው ነገሮች ቁጥር ሥፍር የላቸውም፡፡ መኖሪያ ቤት፣ መነገጃ ቤት፣ መጓጓዣ፣ የሥራ መሣሪያዎች፣ የዋስትና አገልግሎት፣ የመዝናኛ አገልግሎት፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉትን ዕቃዎችንም ሆነ አገልግሎቶችን የመገበያየት ተግባሮች በዘመናችን ኑሮ ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡

ግብይይት ውስጥ አስፈላጊም ተገቢም ያልሆኑ (ወደ ስርቆትና ነጠቃ ያዘነበሉ) ግንኙነቶችም አሉ፡፡ በቀላል ምሳሌ እንጀምር፡፡ የእንጀራ ጋገራ ንግድ የሚያካሂዱ ነጋዴዎች ከተራ ነዋሪ የተለየ የኤሌክትሪክ ኃይል ቆጣሪ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ቆጣሪ ግብሩም ታሪፉም ለየት ይላል፡፡ ነጋዴዎቹ ጭማሪዋን ገንዘብ ላለማውጣት ሲሉ የጋገራ ሥራቸውን በተራ ቆጣሪ ማካሄድ ይቀጥላሉ እንበል፡፡ የመብራት ኃይል የጥገና ሠራተኞች በተራ ቆጣሪ የሚካሄድ የጋገራ ንግድ መኖሩን ሲያውቁ ፍትፍት የጥቅም ቀዳዳ አገኙ ማለት ነው፡፡ ብልሽት እያዳገመ ኃይል ሲቋረጥ ነጋዴው የማይደማው ደነዝ ከሆነ ቢያመለክትና ደጅ ቢጠናም ዝም ይሉታል፡፡ ባለጉዳዩ የእነሱን መለገም ለአለቃ ቢያሳጣ ጉድ ተገልጦ ቅጣትና ቆጣሪ አስቀይሮ ያልፈለጋትን ተጨማሪ ወጪ መክፈል ልትመጣ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ መግባት ካልፈለገ ደግሞ በተበጠሰ ቁጥር ለጠጋኞቹ የተወሰነ ገንዘብ መሸጎጥ ግዱ ይሆናል፡፡ ለነጋዴው የቱ ያዋጣዋል የሚል ነገር ውስጥ ሳንገባ፣ በጉርሻ ሰጪና በተቀባይ መሀል ያለውን የኪራይ ግንኙነት እንመልከት፡፡ በምሳሌያችን ውስጥ ያሉት የጥገና ሠራተኞች የሙያ ኃላፊነታቸውን ለሕገወጥ ተግባር አከራይተው ጉርሻ ይቦጭቃሉ፡፡ ነጋዴውም ወደ መንግሥት ሊገባ ይችል ከነበረ ገንዘብ ላይ ለጠጋኞቹ የተወሰነ አካፍሎ ለራሱ ያስቀራል፡፡ በዚሁ ዓይነት አኳኋን ግብርና ታክስ ትመና ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችና ነጋዴ ከተገቢው በታች የሆነ ግብርና ታክስ በመተመን፣ አማካይነት ሕገወጥ/የአቋራጭ ገቢ የሚካፈሉበት ሁኔታ አለ፡፡ እንደ ጠጋኞቹ ኃላፊነቱን ለሕገወጥ ሥራ ያከራየ የግብርና የታክስ ሠራተኛም ሆነ፣ ሠራተኛውን በጉቦ ተከራይቶ ከትልቅ ክፍያ ያመለጠ ነጋዴ ሁለቱም ያልለፉበትን ገቢ መጣጮች ናቸው፡፡ ሁለቱም ኪስ ውስጥ የገባው ገቢ ደግሞ ወደ መንግሥት መግባት ከነበረበት ገቢ የተመነተፈ ነው፡፡ ከውጭ ዕቃ በማስመጣት ሥራ ውስጥም በኮሚሽን ክፍያ ተደልሎ ወይም ብዙ በማትረፍ ስግብግብነት ተጠምዶ ኮሾ ወይም አልባሌ ምርት ሕዝብና ኢኮኖሚያችን ላይ እንዲደፋ የሚደረግበት፣ የእኛም መንግሥታዊ የጥራት ቁጥጥርና የሸማቾች የራስ በራስ ጥበቃ አቅም ደካማ በመሆኑ ከውስጥ ሆኖ ያዘረፈም ከውጪ ሆኖ የዘረፈም ኩባንያ የሚያመልጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ በመላክ ንግድም ውስጥ ጥራት የጎደለውን ምርት በጉርሻ ሸፋፍኖ በማሳለፍ፣ የወጪ ንግዳችን የጠራ ምርት የመላክ ፅናት እንዳይኖረው የማድረግና በዚሁ ምክንያት በሚከተል የስም መጉደፍ ንግዱ እንዲበደል የማድረግ ጥፋት ይፈጸማል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ አዘርፎ የመዝረፍ ድርጊቶችን እየተሹለከለኩ የሚሠሩ ግለሰቦች የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሕይወት ባለበት ጊዜም ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

የክረምት ጎርፍ የውስጥ ለውስጥ መሄጃው ተደፍኖ አስፋልት መንገድ ላይ የተንጣለለበትና መሻገሪያ የከለከለበት ሁኔታ በተፈጠረበት ሰዓት፣ ችግሩን የአጋጣሚ ኪራይ ማግኛ የሚያደርጉ (በጀርባ እያዘሉ ለማሻገር ኪራይ የሚያስከፍሉ) ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በዚያው ዓይነት የሆነ ሸቀጥ ጠፍቶ ዋጋው ሲተኮስም በእጥረቱ ምክንያት የምትከሰተዋ የዋጋ ቅጣይም፣ የእጥረት ችግር ተሻግሮ ሸቀጡን ለማግኘት የተከፈለች ኪራይ ነች፡፡ የዚህ ዓይነት ዕላፊ ዋጋ ከጊዜ ጊዜ ሊያጋጥም ይችላል፡፡

መግዣና መሸጫ ዋጋን ሊቀይሩ የሚችሉ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ የመገበያያ ገንዘብ መውደቅ/መጠንከር፣ የግብርና የታክስ ለውጥ፣ የንግድ ውድድር መጥበብ፣ የአቅርቦት እጥረት/መትረፍረፍ፣ ወዘተ፡፡ ኢኮኖሚው ጉልህ መረበሽ እስካልደረሰበትና የተረጋጋና ጤናማ ሕይወት እስካለው ድረስ፣ የሚነግዱት ሸቀጥ ከመጋባቱ በፊት መጠባበቂያን እያሟሉ ትንንሽና ተባራሪ ዝባቶችን በሚያቻችል የተረጋጋ ዋጋ መገበያየት በንግድ ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ ኢኮኖሚው በውስጣዊም ሆነ በውጪያዊ ምክንያቶች ሲረበሽና የአቅርቦትን አስተማማኝነት ዜጎች ሲጠራጠሩ ወደ ሽሚያ ያመራሉ፣ ሽሚያም ዋጋ ሰቀላን ይጠራል፡፡ ሸማቾች በሥራ ገበታቸው ላይ የመቆየታቸውንና የገቢያቸውን ዘላቂነት ሲጠራጠሩ የገንዘብ አጠፋፋቸውን ይቆነጥጣሉ፣ ገበያ ውስጥ ፈላጊ የለሽ ዕቃ ይበረክታል፡፡ ከውጭ የሚገባ የኃይል ምንጭ (ነዳጅ) ዋጋው ሲሰቀል የሌሎች ሸቀጦችንንና ግልጋሎቶችን ዋጋ ያስወድዳል፡፡ ግርግርና ጦርነት የኢኮኖሚ ተግባርን ሲያሰነካክል፣ የገበያ ሸቀጥን እየተሻማ አላስይዝ ሲል፣ በደፈናው ኢኮኖሚው በፖለቲካ ሽኩቻዎችና በልዩ ልዩ አሻጥሮች ሲጠመድ የተረጋጋ የገበያ መስተጋብር ድራሹ ይጠፋል፡፡ ቀውስ ባለበት ጊዜ የሚከሰተው የገበያ መታወክና መንገብገብ የአቋራጭ ጥቅም አነፍናፊዎችን ያራባል፡፡ እኛን አበሳ ሲያስቆጥሩን የኖሩት ከዚህ ዓይነት አለመረጋጋትና ከመዥገራዊ ሥርዓት የሚራቡ ተባዮች ናቸው፡፡ አንዳንዶችን እንጎብኝ፡፡

ስለምጥመጣ ከታሪካዊ ጀርባችን ጥቂት ነገሮች

በኢትዮጵያ ላይ የኖረው ቅድመ ደረግ ሥርዓት፣ መዋዋጥና መዘማመቱ ማለቂያ አጥቶ ለረዥም ዘመናት አገሪቱንና ሕዝቧን ሲያቃጥልና ሲመነጥር የኖረ ነው፡፡ በዘመቻ አማካይነት በመስፋፋቱና በጥቅለላው አይሎ መንሰራፋት የቻለው አፄያዊ አገዛዝ ከእነተዋረዱ በጦረኛነቱም በቅንጦቱም ጥሪት አንካችነት ባህርይው ነበር፡፡ ከጭቃ ሹምና ምስለኔ አንስቶ እስከ ላይ መሳፍንታትና ንጉሠ ነገሥቱ ድረስ ያለው ቅጥልጥል ሁሉ ህልውናቸው በተለያየ መልክ ግብርናን የተጣባ (የባላገሩን የሥራ ፍሬ የሚመገምግ) ነበር፡፡ አፄው/መሳፍንቱና መኳንንቱ የሚምነሸነሹበት ሀብት፣ በድግስ የሚያድፋፉት፣ በዘመቻ የሚከሰክሱት፣ ቤተ እምነት በማሠራት መፅደቂያ የሚያደርጉት፣ ወደ አገር ውስጥ ለመጣ ፈረንጅም ሆነ ፈረንጅ አገር ጉብኝት ሄደው ለትንሹም ለትልቁም የሚሸልሙት ሽልማት ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባላገሩ የሚመጠጥ ነበር፡፡

 የባላገሩ ዕዳ ቻይነት ባፈራው ሀብት ብቻም የተወሰነ አልነበረም፡፡ በረዥሙ የመዘማመት ታሪክ ውስጥ “አለኝ የምትለውን የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ይዘህ ና! የደረሰ ልጅህን አስከትለህ ለዘመቻዬ ተነስ” ሲባል ውትድርና ውስጥ የሚገባ፣ ዘማች ሠራዊት ሲለቀቅበት ቀለብ የሚችል፣ ወራሪ ሠራዊት ካሸነፈም ከሀብትና ንብረቱ መዘረፍና ዶጋ አመድ መሆን ባለፈ፣ ራሱ ከእነ ነፍሱ ተዘርፎ በባርነት ሊነዳና እየተሸጠ ወደ ሲሳይ ሊቀየር የሚችልበት ዕድል ሁሉ ነበር፡፡

ከዘመቻ በመለስ ባለ ኑሮውም ውስጥ፣ ባላገሩን ማቃፈፊያው ሥልትና ያቃፋፊው ብዛት በአጭር ጽሑፍ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በተለያየ ስም የሚጣለው የግብር ዓይነት ብርካቴ፣ በዓይነትም ሆነ በገንዘብና በጉልበት መልክ ክፍያ የሚፈጸምባቸው ቀዳዳዎች መብዛት አይነሳ! (በበዓላት ጊዜ፣ ጌቶች/እሜቴ ወልደው፣ ድረው ደስታቸው ሲሆን፣ ወይም እንግዳ ሲመጣባቸው፣ ሐዘን ሲደርስባቸው፣ ጌቶች/ እሜቴ በጉዞ ሲያልፉ፣ እንግድነት ሲመጡ፣ ከጉዞ በሰላም ሲመለሱ ሁሉ በባዶ እጅ እጅ አይነሳም፡፡)

አንዳዴ የባላገሩ አበሳ አስቆጣሪ ከሐበሻ ጌታም አልፎ ይሄድ ነበር፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያዎች ውስጥ ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረው ናትናኤል ፒርስ በጊዜው ያየውን፣ የሰማውንና የኖረውን ሕይወት በማስታወሻ አስቀርቶልናል፡፡ ሐበሻ አግብቶ ከመውለድ፣ ትግሪኛ ከመልመድና በባዶ እግር ከመጓዝም በላይ መኳንንትነት ተዋህዶት የነበረው ናትናኤል ፒርስ በአንድ ወቅት የሚከተለውን ድርጊት ፈጽሞ ነበር፡፡ የትግሬ አካባቢን ገዥነት በአንድ ጌታ ሥር ማቆየት ተስኖ ግዛት የተቃረጡ ገዥዎች ይዘማመቱ በነበሩበት በዚያ ወቅት፣ ፒርስ የራስ ወልደ ሥላሴ ባለሟል ሆኖ ጉዞ ያደርግና የሆነ ሥፍራ ሲደርስ በአካባቢው የራስ ወልደ ሥላሴ እርሻና ከብት ጠባቂ የነበረ ሀብታም ገበሬ እንዲቀበለው ሰው ይልካል፡፡ ገበሬው ሴት ልጁን ልኮ የለሁም ያስብላል፡፡ የሐበሻ አዕምሮ የዘለቀው ፒርስ የራስ ንብረት ያለጠባቂ መቅረቱ ያሳሰበው መስሎ አባቷ እስኪመለስ እሱ ሊጠብቅ ይወስንና ምግብና ቤት እንድታሰናዳ ነግሮ ልጅቷን ይሰዳል፡፡ ማምለጫ ያጣው አባት ተጨንቆ ይመጣል፡፡ ፒርስ ፊት ነስቶ የሠራውን ጥፋት ለራስ እንደሚነግር ይዝትበታል፡፡ ገበሬው ድንጋይ ተሸክሞ ይቅርታ ሲለምን የፒርስ ወታደሮች አሥር ወይፈን ካሳ ካልሰጠ ይቅር እንዳይል ያሳስቡታል፡፡ ገበሬው ለፒርስ ሁለት ሙክት፣ ለወታደሮቹ ራት በማቅረብ ሊክስ ቢማፀንም ፒርስ ያንሳል አለው፡፡ ገበሬው በሁለት ሙክት ላይ አንዲት መሲና ላም ጨምሮ ቢያመጣም አይሆንም ብሎ መለሰው፡፡ በመጨረሻ የተቀለበ ወይፈንና ሙክቶቹን አቅርቦ ካሳው ተቀባይነት አገኘ፣ ከዚያ በላይ እቤቱ አስገብቶ ሲያበላና ሲያጠጣ አመሸ፡፡ (ዘመነ መሳፍንት፣ ትርጉም ብርሃኑ በላቸው፣ ገጽ 101-2)፡፡

ባላገሩ በገዛ የደስታና የሐዘን ድግሱም ቢሆን ወደደም ጠላ ከቦጫቂ አያመልጥም ነበር፡፡ ክርስትና፣ ሠርግና ተዝካር ሲደግስ እንደ ዕርዱ ዓይነትና እንደ ድግሱ ዓይነት የሥጋ ብልትና የጠላ ቀረጥ የመስጠት/የመላክ፣ የማብላትና የማጠጣት (ለምሳሌ፣ ለምስለኔ፣ ለጭቃ ሹም፣ ለቄስ፣ ወዘተ) ግዴታ ነበረበት፡፡ ግዴታውን አለማሟላት ቅጣት ያስከትልም ነበር፡፡ ተፈላጊ አገልግሎት ሰጥቶ ኪራይ የማስከፈል ግንኙነት ያለበት በሚመስለው በአንድ ዙር የማያበቃ ፍታት የማስፈታት ኃላፊነት ውስጥ የማራቆት ገጽታም ነበር፡፡ ፍታት ሀብት ለሌለው ጥሪት አድራቂ እንደነበር፣ አንዲት የትግሬ ሴት ሟች ባሏን እስከ ስድስት ወር ፍታት ለማስፈታትና ተዝካር ለማውጣት ሁለት የእርሻ በሬዎቿን በመሸጧ ምክንያት ማሳዋን ከማሳረስ ወደ ማስቆፈር እንደ ዞረች ናትናኤል ፒርስ ተርኮልናል (የተጠቀሰው ገጽ 108፣9)፡፡ ከመቅሰፍት እናድናለን /እንፈውሳለን፣ ወዘተ የሚሉ ደብተሮችና ጠንቋዮች በፊናቸው የባላገሩ ጥሪት መጣጮች ነበሩ፡፡

ባለገሩ ጉዳይ ኖሮት ወደ ምድራዊ ጌቶቹ አቤት ሲልና ደጅ ሲጠናም ሆነ በአማላጅ በኩል ሲሄድ ገጸ በረከት ማቅረብ ነበረበት፡፡ ዳኝነት ፈልጎ ቢሄድ ተከራክሮ ቢረታ እንኳ አጥፍቶ ከመቀጣት እጅግም የማይርቅ የሚሆንበት ሁኔታ ነበር፡፡ ተመስገን ገብሬ ‹ሕይወቴ› በተሰኘ ጽሑፉ እንደሚተርክልን በራስ ኃይሉ ቤት ጸሐፊ በነበረ ጊዜ ባለጉዳይ ደጅ ጠኚ ጉዳዩን ሲያጽፍ ለራስ ኃይሉ መታያ አንድ ብር፣ ጸሐፊ አሳምሮ እንዲጽፍለት አንድ ብር፣ አጋፋሪው ራስ ዘንድ እንዲያቀርበው ደግሞ የአቅራቢ መታያ ሌላ ብር መክፈል ይጠበቅበት ነበር፡፡ የማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀልንና የመርስኤ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ ሥራዎችን ብናገላብጥ ደግሞ ከዚህ የባሱ ነጠቃዎችንም እናገኛለን፡፡

የገባር ጭሰኛው ሥርዓት ዘመናዊ ቀመስ ቢሮክራሲና ደመወዝተኛነት እያበጀ በመጣም ጊዜ ቢሆን የጸሐፊ፣ የወረዳ ገዥ፣ የአውራጃ ገዥና የአገረ ገዥም ሆነ የዳኛ ደመወዝ በጣም አነስተኛ ነበርና ኑሯቸው ይደራጅ የነበረው በመታያ/በገጸ በረከት መልክ በሚካሄድ ምጥመጣ ነበር፡፡ አንዳንዱ አማላጅነት ቤትና መሬት እስከ መቀበል ይጨክን ነበር፡፡ የዳኝነትና የጉዳይ ትኮሳ አካሄድና ውጤት፣ በሚያስገኘው ገቢ ስባትና ክሳት ይወሰንም ነበር፡፡ ይህንን መሳዩን የጉዳይ አፈጻጸም ከእነ መታያና ድግሳ ድግሱ በቤተ ክህነት ውስጥም እናገኘዋለን፡፡ ምድራዊ ጌቶች/ሹሞች ዘንድ ለመድረስና ልባቸውን ለማራራት የሚካሄደው የደጅ ጥናትና የምልጃ ኪራይ “ልመናዬ ከሰመረ . . .  አገባለሁ” በሚል ወደ ሰማዩ ጌታም ተሸጋግሯል፡፡

የኃይለ ሥላሴን ፍፁማዊ አፄነት የተካው የደርግ ሥርዓት የአልቅታዊ ምጥመጣ መፍያ በመሆን ረገድ በኢትዮጵያ የአገዛዞች ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ሥርዓቱ ለዚህ የአንደኝነት ማዕረግ ሊበቃ የቻለውም አንዳቸው ለአንዳቸው መዘዝ በሆኑ ሦስት ምክንያቶች ነበር፡፡ አንደኛ ሶሻሊስት ነኝ ባይና በስተኋላም የአንድ ፓርቲ ፖለቲካን የተጎናፀፈው ወታደራዊ ቢሮክራሲያዊ አድራጊ ፈጣሪነት፣ የኅብረተሰቡን ሕይወት እስከ ትንንሽ የችርቻሮ ንግድና እስከ መኖሪያ ቀዬ ድረስ ትብትብ ውስጥ እንዲወድቅ አደረገው፡፡ ሁለተኛ ድንፋታን፣ ስድብንና ጥፊን ሁሉ ያካተተ አዛዥ ናዛዥነትን የሚረጭ “አብዮታዊ” ሽርጉድ (ስብሰባ፣ ቅስቀሳ፣ ሠልፍ፣ የክብረ በዓል ዝግጅት፣ የስንቅ ዝግጅት፣ ወታደራዊ ምልመላ፣ ወዘተ፣ ወዘተ) ዕለታዊ ኑሮንና የኢኮኖሚ ተግባራትን የሚረብሽ፣ የሰው ኃይልን፣ የሥራ ጊዜንና ጥሪትን የሚሻማ፣ እንዲያውም ከምንም ነገር ቅድሚያ የሚሰጠው ሆነ፡፡ ሦስተኛ የሁለቱ ድምር ውጤት የመላ አገሪቱ የሥራ እንቅስቃሴዎች በእጥረት፣ በሰው መጓደል፣ በጥራት የለሽነት፣ በብልሽት፣ በመንቀርፈፍ፣ በደጅ አስጠኝነትና በሠልፎች የተሞሉ እንዲሆኑ አደረገ፡፡

እነዚህ እንደ መዓት የፈሉ ችግሮች ደግሞ፣ ከችግር ማምለጫ ቀዳዳ የሚፈልጉ ባለጉዳዮችና ማምለጫ ቀዳዳዎችን የሚያውቁ/የሚቆጣጠሩ ሰዎች አቋራጭ የኪራይ ጥቅምን በጉቦና በኮሚሽን መልክ የሚለዋወጡባቸው ገበያዎች ሆኑ፡፡ ባሉ ችግሮች ከመነገድ ታለፈናም በየአቅጣጫው የችግር ኬላ ፈጥሮ ኪራይ ለመመጥመጥ ሲባል ምን መሰናክል ልፍጠር እየተባለ ሸቀጥ ደብቆ ሐሰተኛ እጥረት መፍጠር፣ ሰነድን ደብቆና ከሥራ ገበታ ላይ ዘወር ብሎ እንግልትን መፈብረክ እንደወርረሽን ተባዛ፡፡ የጓዳ መንገድና የጉቦ ድርድር የሌለበት ነገር ታጣ፡፡ የስልክና የውኃ መስመር ማስገባት፣ ማስጠገን፣ የሕክምና ተራ ማግኘት፣ መድኃኒት ማግኘት፣ ዶሴ አስፈልጎ ማግኘትና ማንቀሳቀስ፣ ትምህርት ቤት ማግኘት፣ የሚያበላ የሥራ ቦታ ላይ መመደብ፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ ሕይወት ከተራ ዘበኛ እስከ መንግሥት ሹምና የግል ባለሀብት ድረስ ተባይ ባፈራ አኗኗር እንደ ተወረረ ሁሉ፣ አገሪቱም የሶቪየት ካምፕ ጥገኛ ነበረችና በተለያየ መልክ ይካሄድ ለነበረ የወጪ ቡጥቦጣ ተዳርጋ ነበር፡፡ ቀጥሎ የመጣውንና እስካሁን እንዳየነው ከደርግ ግማሽ መንገድ የራቀውን የኢሕአዴግ አገዛዝ የብቻ ርዕስ አስይዘን እናተኩርበት፡፡

ርዕዮተ ዓለማዊ ኳኳቴና ተግባር በኢሕአዴግ አገዛዝ

ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ያልነበረ የብዙ ፓርቲዎችን ታሪክ ቢያስጀምርም፣ ደርግ ኢሠፓ ብቸኛ የሕዝብ መሪ ነኝ ይል እንደነበር ሁሉ ራሱም ያንን ሚና በውድም በግድም ተክሏል፡፡ ኢሠፓ ብቸኛ ገዥ እንደነበር ሁሉ እሱም እስካሁን ብቸኛ ገዥ ሆኖ ኖሯል፡፡ የመደራጀትና የመናገር ነፃነት ለመፈንጠቅ ቢደፍርም፣ እሱም እንደደርግ በብዙኃንና በሙያ ማኅበራት ስም በተሠሩ የቢሮክራሲ ቅጣዮች የኅብረተሰብን ነፃ እንቅስቃሴ አደንዝዟል፡፡ ተኪ የለሽ የሕዝብ መሪነቱም እንደ ደርግ ያላጨበጨበን በጥቅም የሚቀጣና ሰሚ በሌለው ፕሮፓጋንዳ የሚነዘንዝ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳ ከደርግ ጋር ሲተያይ እንዲያውም በጡጦ የመስጠት ያህል መድረሻ የሚያሳጣ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችን እንዳይሞቱ እንዳይሽሩ አድርጎ የማያፈናፍነው ገዥነቱም አሀዳዊነትን በፌዴራላዊነት ከመቀየሩ፣ በመድበለ ፓርቲ “ውድድር” ከመቀሸሩና ብዙ ብሔርተኛ ቅርፆችን ከማበጀቱ በቀር ከአምባገነንነት መውጣት ያልቻለ ነው፡፡ መብቶችን የሚያብለጨልጨው ይህ አምባገነንነት ጠለቅ ብለው ሲያዩት በእጅጉ ሚስጥራዊነትና የመረጃ አፈና የጠናበት፣ እስከ መንደርና ግቢ ድረስ የዘለቀ ፖሊሳዊ (ፀጥታዊ) ጅማቱ የበረታ ነው፡፡

በኢኮኖሚው ረገድም ኢሕአዴግ የመንግሥታዊ ቢሮክራሲውን የቀድሞ የይዞታ አግበስብሴነትንና አዛዥነትን በጣጥሶ የግሉ ዘርፍ እንዲንቀሳቀስ ያደረገ ቢሆንም፣ ዛሬም በመሬት ላይ ያለተቆጣጣሪነትና ያለተጠያቂነት ከማዘዝ አንስቶ፣ መንግሥታዊ የኢኮኖሚ አውታራት ባለቤትነትና አንቀሳቃሽነቱ ግዙፍ ነው፡፡ ቴሌኮምን፣ አየር መንገድን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንና የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ከመሳሰሉትና በስኳር ልማት ኮርፖሬሽንና በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ውስጥ ከተካተቱ የኢኮኖሚ ተቋማት ባሻገር፣ በክልል መንግሥታት ሥር ያሉ በክልላዊ ፓርቲ ወገንተኛነት የሚመሩ የፋብሪካ፣ የፋይናንስና የአገልግሎት ንግድ ተቋማትም አሉ፡፡ ዛሬም መንግሥት ቤት አከራይ ነው፡፡ ዋና የቤት ገንቢ በመሆንና የጋራ መኖሪያ ቤትን በረዥም ጊዜ ክፍያ የመግዛት ዕድልን በማንጠልጠል የኅብረተሰቡ የገንዘብ ቁጠባ ዋና አሰባሳቢና አንቀሳቃሽም መንግሥት ነው፡፡ በተስፋፉት የፌዴራል/የየክልል መንግሥታዊ ልዩ ልዩ መረቦቹ በኩልም ሆነ በግንባታ ፕሮጀክቶቹ በኩል ዋና ሥራ ቀጣሪም ነው፡፡ የጥቃቅንና የአነስተኛ ሥራዎች አደራጅ፣ የገበያ ትስስር አፈላላጊ (ይበልጡን ከመንግሥታዊ ግንባታዎች ጋር በማያያዝ)፣ ከአነስተኛ ደረጃ ሥራዎች ‹‹አስመርቆ›› ወደ “ኢንቨስትመንት” አስተላላፊም መንግሥት ነው፡፡ በመንግሥታዊ አካልና በዩኒየኖች በኩል በሚካሄድ ግዥና ሽያጭ አማካይነት የግብርና ውጤቶችን ዋጋ የመቆጣጠር ሥራንም ያከናውናል፡፡

ከክልል አንስቶ እስከ ፌዴራል ድረስ ባለ የሥልጣን መንበር ላይ የሚላወሱት ብሔርተኛ አዕምሮዎችና ድርጅታዊ ገመዶች እንደ መሆናቸውም፣ የትኛውም መስክ (ከሥራ ፍለጋ እስከ ሥራ ከፈታ፣ ከትምህርትና ሥልጠና ዕድል እስከ አስተዳደርና ፍትሕ ሥራ ድረስ) ለብሔርተኛ አድልኦ የተጋለጠ ነው፡፡ በተግባርም ሲደረግ ቆይቷል፣ ዛሬም መቁረጫ ያጣ ችግር እንደሆነ ነው፡፡

ከኃያላን አገሮች ጋር ያለ ግንኙነትን በተመለከተ የደርግ ዘመኑ የከፋ የውጭ ጥገኝነት የተሰበረ ቢሆንም፣ ዛሬም ገና ያልተላቀቀን የዕድገት ኋላቀርነት ከጥገኝነት ለማምለጥ የሚያስችል አይደለም፡፡ የጥበብ (የቴክኖሎጂ) እና የካፒታል እጥረት ወደ ታላላቆቹ አገሮች ለማንጋጠጥ ያጋልጣል፡፡ በዚህ ላይ በሕዝብ ድጋፍ እጥረት ጭራሽም በቅዋሜ መዋከብን ባለመፍታት በውጭ ካሉ የአገሪቱ ልጆች ሊገኝ የሚችለውን ያህል የውጭ ምንዛሪ አለመሳብ፣ እንዲሁም በውስጥና በውጭ ያሉ የአገሪቱን የፈጠራ፣ የሐሳብ አፍላቂነትና የሙያ አቅሞች በሩቅና በቅርብ አሰባስቦ የመጠቀም እጥረት የውጭ ጥገኛነትን ያባብሳልና ዛሬም የኢትዮጵያ ዕርምጃ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ጋር ደፋ ቀና የሚል ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ልዩ ልዩ ንግድ ውስጥ እየተሹለከለኩ ጥቅምን የማስከበር ልምድ ማነስ ለመታለልና ለመበለጥ (በኢንቨስትመንት፣ በአዕምሮ ንብረት ጥበቃ፣ በገቢ ዕቃዎች የጥራት ዋስትና፣ በፋይናንስ፣ በንግድ፣ ወዘተ) እንደሚያጋልጥ ሁሉ፣ አንገት በሚያስደፋው ጥገኝነት ውስጥ መሆንም እያወቁ ለመሞኘት ያጋልጣል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ከውጭ በገቡና አገልግሎት እየሰጡ ባሉ የመኪናና የስልክ ዓይነቶች ላይ የታየን የጥራት መጓደል አነፍንፎ ኪሳራ የሚያስተፉበትንም ሆነ ዕቃ የሚያስመልስበትን ዓይነት፣ ልበ ሙሉ ውልና ዕርምጃ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ደካማ አገር በጌቶቹ አገሮች ኩባንያዎች ላይ ለመውሰድ ይከብዳታል፡፡ በአቅም ማነስ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ አቅራቢም፣ ቴክኖሎጂ አቅራቢም፣ ገንቢና ተካይም አንድ አገር የሆነበት ግንኙነት ውስጥ ሲወደቅ ነፃ ሆኖ እንደ ሥራ አኮናታሪ ጥቅምን የማስጠበቅ ጥንካሬ ይሰለባል፡፡ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ባላት የልማት ግንኙነት አንዱ ፈተናዋ ይህ ነው፡፡

እስቲ የአቋራጭ ጥቅም አሳዳጅነትን እንመልከት

ከሁሉ በፊት ማኅበረሰባዊ ዝምድናን መሠረት ባደረገ ፖለቲካዊ መቦዳዳን አማካይነት የበደል ታሪክ ቁጭትንም ሆነ አኩሪ የትግል ገድልን እየነካኩ የሕዝብን ድጋፍ መሸመት፣ ለአቋራጭ ጥቅም አሳዳጅነት ጥሩ ከለላ ከመሆኑ ሌላ በብሔርተኛ ቅስቀሳ የሚታፈሰው ድጋፍ ራሱ አቋራጭ ገቢ ነው፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ በድሉ ዋዜማና አጥቢያ የሥልጣን ገጸ በረከትን ደቅኖ፣ ብሔረሰባዊ ገመዶችን የተከተሉ ጭፍራ ድርጅቶችን እንዳረባ ሁሉ፣ የእሱ ጭፍሮችም ሆኑ በተቃዋሚነት የቆሙት ብሔርተኛ ቡድኖች የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰብንና ዕቅድን መታወቂያቸው በማድረግ፣ በዚያ የሕዝብን ተስፋና አመኔታ የማሸነፍን ከባድና ረዥም መንገድ ሸሽተው በብሔረሰብ ገመድ በኩል ሲሮጡ የአቋራጭ/ያልተለፋበት ገቢ (ድጋፍ) ሰብሳቢዎች መሆናቸው ነው፡፡ ዛሬም በብሔርተኛነት ፖለቲካ የሚነግዱ ቡድኖች ሁሉ የአቋራጭ ድጋፍ ጥቅመኞች ናቸው፡፡

የአቋራጭ ገቢ መጠጣና የዘረፋ ሽሚያ ዋና ጎሬ ብሔረሰባዊ ወገንተኝነት ሊሆን የቻለውም፣ በአገሪቱ የተዘረጋው ዋናው የፖለቲካ መነገጃ ብሔርተኛነት ስለሆነና ከክልሎች እስከ ፌዴራል ድረስ ሥልጣኑን የዋጡት ብሔርተኞች ስለሆኑ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ገዥ ቡድኖች በሕወሓት መንገድ ጠራጊነት የፈጠሯቸው የሀብት ቅርምት የሚካሄድባቸውና ፓርቲያዊ ጡት አባት ያላቸው ክልላዊ ኩባንያዎችም፣ አቋራጭ መንግሥታዊ አድልኦ በተለያየ መልክ የማግኘት ዕድል እንዳላቸውና እንደሚኖራቸው በፓርቲ ሰዎች እስከ መመራት የዘለቀ የፖለቲካ ቀረቤታቸው የሚመሰክርላቸው፣ ለገዥ ፓርቲ መንግሥት ነክ የኪራይ ሰብሳቢነት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪነት ሌሎች ተፎካካሪዎችን በልጠው ባለብዙ ደንበኛ ከመሆን፣ አድካሚ ጎዳና ውጪ የብሔሬ/የክልሌ ሀብት በሚል መመዘኛ አማካይነት ገዥ የማፍራት ባህርይን በመያዛቸውም የአቋራጭ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

የኢሕአዴግ ገዥ ቡድኖች የተቀባይነት ዕድገት በፕሮግራማቸው ፋይዳ ላይ ብቻ ያልተንጠለጠለ፣ የሥራ ዕድል ከማግኘት አንስቶ ልዩ ልዩ ጥቅሞችን በቀላሉ ከማግኘት ጋር ሁሉ የተቀራረበ መሆኑ፣ በመንግሥት ሥራ ላይ የተሠማሩ ዕድገትና ሹመት ፈላጊዎችንና በየስብሰባው ሠልጣኝና አሠልጣኝ እየሆኑ ውሎ አበል መግመጥ የሚያጓጓቸውን ብዙ ሰዎች ወደ ፓርቲ አባልነት ከመሳብ አልፎ፣ ገና በትምህርት ገበታ ላይ ያሉትንም በተስፋ አጨብጫቢ ለመሆን አብቅቷል፡፡ በግል ባለሀብቶች በኩልም ከግብር እና ቀረጥ አንስቶ እስከ መሬት ድረስ ልዩ ልዩ ጥቅሞችን በመፈለግ “በደጋፊነት” ለጠፍ ማለትን አስከትሏል፡፡ የጋራ ቤት በማግኘት ዕድል ውስጥ የሚሰጥ ቅድሚያ (በመቶኛም ሆነ በሌላ መልክ) የዚሁ ዓይነት ሚና አለው፡፡ የምርጫ ዓመት ሲደርስ የተደረጉ ሕገወጥ ግንባታዎችን ወደ ሕጋዊነት የማዞር ሥራዎች፣ በነዋሪዎች በኩልም የምርጫ መቅረብን በመንተራስ በገዥው ፓርቲ የድጋፍ ፍላጎት ለመጠቀም ተብለው ሲደረጉ የነበሩ “መንግሥታችን ለሕዝብ አሳቢ ሆኖ እያለ፣ እኛም የመሬት ግብር ሁሉ ሳናጓድል…”     እያሉ ሕገወጥ ግንባታዎችን ሕጋዊ የማስደረግ ብልጠቶች ሁሉ የእከክልኝ ልከክልህ ዘይቤዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ ደግሞ መንግሥታዊ የብድር፣ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅራቢነት፣ የቴክኖሎጂ ዕገዛ፣ በጥቃቅንና በአነስተኛ ሥራዎች የማደራጀት፣ በግብር ዕፎይታና በገበያ ትስስር የመጥቀም መድረኮች ገበሬው፣ ወጣቶችና ሴቶች ገዥውን ፓርቲና መንግሥት እንዲጠጉ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ መስተጋብሮች ውስጥ የሚገኙት ጥቅሞች የፖለቲካ መተሻሸት ባይደረብባቸው እንኳ ጥቅሞቹ ራሳቸው እንደ ውለታ አስቡኝ የሚል አንድምታ የማስተላለፍ አቅም አላቸው፡፡ ተጠቃሚዎቹም “መንግሥታችን” እያሉ ደጋፊ መምሰልና በምርጫ ጊዜ ውለታ መክፈል ድርሻቸው እንደሆነ ይገባቸዋል፡፡

ከዚህ በጎደለ ደግሞ፣ “የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ ሕዝብ ውስጥ በማስረፅ” እና “ወቅታዊ ሁኔታዎችን በማስገንዘብ” ሽፋን የፓርቲ ድጋፍን የማስፋፋትና ብሶት/ቅዋሜ የማብረድ ዘመቻ አለ፣ ያውም ከውሎ አበልና ከግብዣ ማጣፈጫ ጋር፡፡ እነዚህን የመሳሳሉ ነገሮች፣ የነዳጅ ድንግል ሀብትን ለአልሚ በረዥም ዘመን አኮናትሮ ከዚያ ከሚገኝ የኪራይ ገቢ ላይ ኅብረተሰብን በመደጎም የመሸበብ ብልጠትን በሌላ መልክ ከማከናወን ጋር የተመሳሰለ ባህርይም አላቸው፡፡ ከስብሰባ ጋጋታውና ከሌላ ሌላው “ልማታዊ” የድጋፍ መንገድ በተጨማሪ የፕሮፓጋንዳ አውታሩ አለ፡፡ ያ ሁሉ ተደርጎም የሚኖረው የድጋፍ እጥረት ደግሞ በፀጥታ አውታራት የተስፋፋ መዳፍ ይጣጣል፡፡ በአጭሩ የሕዝብ ሀብት በአዕምሮ አጠባም በኩል ሆነ በአፈና በኩል ገዥነትን ለማዝለቅ ይውላል፡፡

ከዚህ በተለየ ዓላማ (የዝና ጥምን ለማርካትም ሆነ ቅምጥልነትን በማብለጥ) የቀበጠ ሕንፃ ለመሥሪያ/ለመከራያ፣ የተንደላቀቁ ቢሮዎች ለማደራጃና አገልግሎቶችን ለማሟያ የሕዝብ ሀብትን ማዋል፣ የበጀት ዓመት ደርሶ ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና ተመላሽ እንዳይሆን በምኑም በምኑም ማድፋፋት ገና ያልተገፋ ችግር ነው፡፡ የሕዝብ ቁጠባ አግበስባሹ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ እያሠራው ያለውን ረዥም ፎቅ ያመጣው የቢሮ ችግር ወይስ የዝና ችግር? ብለን ብንጠይቅ፣ ይኼው ባንክ ለ2010 ዓ.ም.  ያሳተመውን ቅብጥ ያለ ባለ ወረቀት ቦርሳ የቀን መቁጠሪያ ብንመለከት ስለዚሁ ገመና ፍንጭ የምናገኝ ይመስለኛል፡፡

በመንግሥት ቤት ውስጥ ግለሰባዊ የአቋራጭ ጥቅም አባራሪነት

በደርግ ዘመን የተባዙት ልዩ ልዩ የአቋራጭ ጥቅም መንገዶች ከፓርቲያዊ ትስስር ጋር ጎሰኛ መሳሳብን አዛምደው ዛሬም በኑሯችን ውስጥ ይታያሉ፡፡ እንጠቃቅስ፡፡

የመንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነትን ለግል ጥቅም ማደኛ ማዋል፣ የሕዝብ አገልግሎት ሥራን እንደ ውለታ ማየትና “ለውለታ” ወሮታ መፈለግ፣ የሥራ ድርሻን እንደ ውለታ እያከራዩ ገቢ ማግኛ ማድረግ፣ ከዚህም ባለፈ የአገልግሎትን አካሄድ አስቸጋሪ እያደረጉ (ደጅ ጥናትን፣ የወረፋ ሠልፍን፣ ማልመጥን፣ የሥራ ማጓተትን እያራቡ) ጉርሻ መቀፍቀፊያ ማድረግ፣ የጉርሻ ተጋሪ ባይሆኑም ያለ ደንብ አልሠራም፣ ወዘተ በሚሉ ዓይነት አስባቦች ሥራን እያወላከፉ ባለጉዳዮችን ለኪስ አላቢዎች ማጋለጥ፣

የደመወዝ ጭማሪ፣ ዕድገት፣ ለመስክ ሥራ መውጣት፣ የሥራ ዝውውር፣ ወደ ውጭ አገር ለሥራ ጉዳይም ሆነ ለትምህርት የመላክ ዕድል ዛሬም ከመጠቃቀሚያነት አለመፅዳት፣

በመንግሥት ወጪ በመላላክም ሆነ በኢንተርኔት ወይም በውስጥና በውጭ የትምህርት ተቋም ውስጥ ገብቶ ከተማሩ በኋላ ይህንን ውለታ የሚመልስ የሥራ ፍሬ አለማበርከት፣ ጭራሽ ዕዳን እንደ ተሸከሙ ወደ ውጭ መሹለክ ዛሬም አለማሳፈሩ፣

የመንግሥት ሥራን እያካሄዱ ባሉበት ሥፍራ እግረ መንገድን በትርፍ ጊዜ የግል ጉዳይን ማካሄድ ጤናማ ነው፡፡ የግል ጉዳይን ለመሙላት ተብሎ የሽፋን ሥራ (ወደ መስክ ከመውጣት እስከ ውጭ አገር ጉዞ ድረስ) ማመቻቸት ግን የሙስና ተግባር ነው፣ ይህም አለ፡፡

ከፍተኛ ትምህርትን የተመለከተ የሙያ ብቃት ምዘና ሲመጣም፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንደ ሱቅ እየቀፈቀፉ በሠለጠነ የሰው ኃይል ጥራት፣ በትምህርት ቁሳቁስና በሥነ ዘዴ ያልተሟላ ግልብልብ ትምህርትና ሥልጠና በማራባት አጥፊነት መንግሥትን ዋና ተጠያቂና የማካካሻ ሥልጠና ባለ ዕዳ በማድረግ ፈንታ፣ ብቃቴ ለምን ተለክቶ ብሎ መቃወምም የአቋራጭ ጥቅመኝነት መገለጫ ነው፡፡ 

የመንግሥትን የውስጥና የውጭ አገር ዕቃ ግዥ በተጋነነ ዋጋ/ኮሚሽን መመንተፍ፣ የሥራ ስብሰባዎችን የተሻለ መዝናኛና ተጎብኚ መስህቦች ካሏቸው ሥፍራዎች ጋር ማገናኘት፣ ጥቅማ ጥቅም ለመቃረም ቀዳዳ ከሚሆኑ ድግሳ ድግሶች፣ ከካኒቴራና ከኮፍያ ግዥዎች ጋር ስብሰባዎችን ማዛመድ፣ ከዚህም አልፎ ለጥቅም ሲባል ሥራው ከሚሻው በላይ ስብሰባ፣ ኮንፈረንስና ሥልጠናን ማመላለስ በከልካይ መመርያ የማይበገር ዘይቤ እንደሆነ ነው፡፡

የመሬት ምሪትን/ኪራይን የሥውር ጥቅም መተሳሰቢያ ማድረግ፣ የመንግሥት ግንባታዎችን የሁለት ወገን የዝርፊያ ማሳ አድርጎ መቦጥቦጥም ይኼው እስከ ዛሬ አልሸነፍ ያለ ችግር ነው፡፡

ኅብረተሰብ ላይ ያሳረፈው አሻራ

የኢሕአዴግ አገዛዝ ያላቃለለውና ራሱም ያራባው የአቋራጭ ጥቅም አዚም ከመንግሥት ቤት ተሻግሮ ኅብረተሰብን ከባለፀጋ እስከ መናጢ ድረስ በጥቅል ማንቀዙም የችግሩ ሌላ ገጽ ነው፡፡

በተለይ የመሬትና የቤት ባለይዞታነት የሁሉንም ቀልብ የጨመደደና ሁሉንም የሚያቅነዘንዝ የአቋራጭ ጥቅም መሻሚያ መስክ በመሆን ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ለዚህ ማዕረግ ያበቃውም የመሬትና የቤት አቅርቦት ለኑሮም፣ ለንግድ ሥራም መሠረታዊ መሆኑ፣ በአገሪቱ ያሉ የመሬትና የቤት ማግኛ ቀዳዳዎች ጠባብ መሆናቸውና ሁሌም ተትረፍርፎ ያለው የቦታና የቤት ጥያቄ ባለመሬትና ባለቤት መሆንን ለታሪክ የሚተኮስ ኪራይንና የሽያጭ ዋጋን ማፈሻ ስላደረገው ነው፡፡ ትርፍ አመንጪ የልማትና የንዋይ ተቋማትን (በተለይም የቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የመሰሉ ግተ – ብዙ ተቋማትን) ከመያዝ ባሻገር በኪራይ መልክ የሚካሄድ የመሬት ሽያጭ ጌታ በመሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጎረቤቶቹ ከእነ ኬንያ የሚለይ መሆኑን አስተውሎ እነሱ የደረሱበት የግብር አሰባሰብ ምጣኔ ላይ እኔም ካልደረስኩ ከሚል ፉክክር ይልቅ፣ የበጀት ብክነትን ካስወገደ አጠቃቀም ጋር በፍትሐዊነት የላቀ፣ የደቃቆችን ተፍጨርጫሪነትና ዕድገት የሚያግዝ የግብር ሥርዓት መዘርጋት ችግር እንደሆነበት ሁሉ፣ መሬትና ቤትን በሽያጭ በማገላበጥ ዝቆሽ ትርፍን በለመዱ ሰዎች ዘንድ የሚታይ መቅነዝነዝም ወደ አስካሪ ሱስ የተቀየረ ይመስላል፡፡ ከእነሱ ዝቅ ብለን የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታን ብንወስድ፣ መንግሥት ባደረገው የዋጋ ጭማሪ ላይ አንድ ሰሞን ተካሂዶ የነበረው ጫጫታ የዚያው ብጤና ይሉኝታን ቀቅሎ የበላ ነበር፡፡ የልማት አውታራት በተሟሉበት መሀል ከተማ ውስጥ ወይም ለመሀል ከተማ በቀረበ አካባቢ የተሠራ የጋራ ቤትን መንግሥት በተወቀሰበት “ውድ” ዋጋ ማግኘት፣ ለእያንዳንዱ “ባለ ዕድል” የንግድ ኩባንያ አደራጅቶ ከመስጠት በላይ ነው፡፡ ኩባንያ አያያዙን ካላወቁበት ወደ ኪሳራ ይቀየራል፡፡ እነዚህን ቤቶች መግዛት ማለት ግን ገና ገዥዎቹ እጅ ሲገቡ የትናየት ዋጋቸው የሚተኮስና ከጊዜ ጊዜ በሚያድግ ኪራይ ብቻ በሌሎች ኪስ የነበረ ገንዘብን ወደ ራስ ኪስ እየመጠጡ ማዛወሪያ መኪኖችን መረከብ ማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የገንዘብ ማተሚያ መኪና ለሚሰጥ የዞረበት መንግሥት ታዲያ ወቀሳ ሊሰነዘርበት ቀርቶ ምሥጋናስ አያንሰውም!! (ይህንን የምለው የመንግሥትን የዋጋ ጭማሪ አበጀህ ለማለት ሳይሆን አካሄዳችን የቱን ያህል መንገድ እንደሳተ ለመጠቆም ነው፡፡)

የምርጫ 97 ማግሥት ከሥልጣን የመንሸራተት አደጋን ባሳየ ጊዜ የኢሕአዴግ ሰዎች አዲስ አበባ ላይ መሬት ወደ መሻመት ሲዞሩ ለማየት የተቻለው የትኛውም ሰው በፖለቲካ ተገን፣ በጎሰኛ ትስስርና በወፍራም ጉቦ በኩል በራሱም ሆነ በተወላጅና በዘመድ ስም የከተማ መኖሪያ ቦታ ተቀብሎ ወይም ገዝቶ በማቆየት፣ ከተቻለም የተወሰነች ግንባታ አክሎባት ለመሸጥ የሚያደራው ከዚያ የሚገኘው ውጤት ሕይወትን የሚቀይር ስለሆነ ነው፡፡ አጭበርብረሃል ተብሎ መነጠቅ በማያጋጥምበት ሕጋዊነት የጋራ ቤትን በተናጠል ለማግኘት ሲባል የተጋቡ የውሸት የሚፋቱት፣ እጮኛሞች በየፊናቸው የተመዘገቡት የጋራ ቤት ዕጣ ለሁለቱም እስኪደርስ ጋብቻቸውን የሚያዘገዩት፣ ውርስ ተቀባዮች በውርስ የተገኘ ቤትን ስም ከማዘዋወር የሚያቆዩት፣ ሙልጭ ያሉ ድሆች በባዶ ኪስ ለጋራ ቤት ተመዝግበው በቅድሚያ የሚጠየቀውን ክፍያ የገቡበት ገብተው አሟልተው ቀሪውን በኪራይ ለመሸፈን የሚደፍሩት፣ እንዲህ ያለ ውድ ዕድል ያገኘ ደሃ ዘመድን ዕድሉ እንዳይመክንበት ዘመድ አዝማድ የሚረባረበውም፣ ቀደም ብሎ እንደተባለው የዚህ ዓይነት ዕድልን አግኝቶ ማሳለፍ የሎተሪ ሽልማት አሸናፊነትን ሳይወስዱ የማቅለጥ ያህል ስለሆነ ነው፡፡ በተከራይነት ለረዥም ዘመን የኖሩበትን ቤት በጉርሻ ሰነድ አስጠፍቶና አስቀይሮ ወደ ግል ይዞታ ለማዞር፣ ወይም በግል መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ያለችንና በትርፍ ቤትነት ወደ መንግሥት የገባችን ቤት ከተከራዩዋና ከቀበሌ ሰዎች ጋር በደህና ገንዘብ ተደራድሮና ሰነድ አስተካክሎ ከግል መኖሪያ ቤት ጋር ለመቀላቀል ደከመኝ የማይባልበት ልፋት የሚለፋው፣ ተከትሎ የሚመጣው ጥቅም የዋዛ ስላልሆነ ነው፡፡ መንግሥት በቅዋሜ በተወጠረበትና በተሸበረበት ወቅት የሚሟሟቅ ተገቢ ካሳ ሳይከፈለን የሚል ሮሮና ጫጫታ በድፍኑ እውነተኛ በደልን ብቻ የሚያንፀባርቅም አይደለም፡፡ በአያያዝ የደረሰ መራገፍን እንዳለ በካሳ ማነስ ላይ መላከክ እንዳለ ሁሉ፣ የፖለቲካ ድጋፍ የተጠማ መንግሥት በቀላሉ ይሸነፍልናል በሚል ብልጠት ካሳ የማይመለከታቸውም መከሰታቸው የሚነግረን አጋጣሚው የማይታለፍ መሆኑን ነው፡፡

በነጋዴው በኩል ከደርግ ጀምሮ በትንሽ ሰበብ የዕቃዎችን መሸጫ ዋጋ በመቀጠል ወይም መጠንና ብዛት በማሳነስ፣ ወይም በሁለቱም ዘዴ ውድነትን በመፍጠር መዝረፍ ዛሬም ድረስ የቁጥጥርና የቅጣት ልፊያ የማይበግረው ተግባር እንደሆነ ነው፡፡ ከደርግ ጊዜ እስካሁን ያለው ንግድ ሁሌም ትኩረትና ጥረቱ ስንጥቅ ትርፍ በማግኘት ላይ ነው፡፡ ስስትን/ራስ ወዳድነትን ሊታፈርበት የማይገባ የብልህ ንግድ እስትንፋስ አድርጎ መፈላሰፍ እንደመጣ ሁሉ፣ ሥልጣኔ ተብሎ እነ ታይዋንና ቻይና አካባቢ ያለውን የስመኛ ሸቀጦችን ነገረ ሥራና ምልክት የተመሳሰሉ አልባሌዎች በመሥራት/በማቅረብ ማጭበርበር፣ ጽሑፋዊንም ሆነ ድምፃዊና ምሥላዊ የፈጠራ ሥራዎችን እያባዙ መስረቅ፣ የመንግሥት ሐኪም ቤት መስተንግዶን አስመራሪ እያደረጉና እያላሸቁ ተገልጋዮችን ወደ ግል ንግድ መግፋት፣ በግል የሕክምና ንግድም ውስጥ (በመንግሥት ሐኪም ቤቶች ውስጥ ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ የሚሰጥ ንግድ ቀመስ የሕክምና ሥራን ጨምሮ) የምርመራ ትዕዛዞችን ለገቢ ማወፈሪያ ሲባል የማበራከት ብልጠት ተደርጎ ተይዟል፡፡

የአገር ውስጥና የውጭ ታዳሚ የሚጎርፍባቸውን ወቅታዊ ክብረ በዓላትን ጠብቆ የባህላዊ ቁሳቁሶችን፣ የምግብና የመኝታ ዋጋ በመተኮስ መመንተፍ ከቱሪዝም ንግድና የአካባቢ ኢኮኖሚን ከማጎልበት ጋር ተምታቶ፣ ሃይ ባይ ከማጣትም በላይ የሚኮረጅና የሚቀናበት ሆኗል፡፡

የእጥረት ኢኮኖሚ ከልታሞችን ሲያድቆሰቁስ ለጥቂቶች ደግሞ የሲሳይ ጡት መሆኑ የተለመደ ነው፡፡ ድሆች በስንት ሠልፍና ርኩቻ ያገኙትን የፍጆታ ሸቀጥ በጭማሪ ዋጋ በመሸጥ የሚገኘው ገቢ የሚብስ ጉርስን ገዝቶ የከፊል ረሃብ ኑሯቸውን ለመደለል የሚስችላቸው ሲሆን፣ የሚሸጡትን ይዘው መሽትሽት ሲል ወደ ጉልት ብቅ ይላሉ፣ ወይም በዘንቢል አድርገው ወደ ሱቅ ያመራሉ፡፡ ስኳር፣ የፓልም ዘይትና የፉርኖ ዱቄት የዚህ ዓይነት ግልጋሎት ዛሬም እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እጥረቱ ለረዥም ጊዜ የሚቀጥል ሲሆን፣ የተወደደ ሸቀጥ የት ተሠልፌ በምን ቀዳዳ አግኝቼ በትርፍ ሸጬ ብሎ ማሰብ ሥራ ሆኖ እግርን ያኳትናል፣ ገትሮ ያውላል፡፡ የቧንቧ ውኃ ማስቀዳትና መኖሪያ ቤትን ቆርሶ ለኪራይ ማዋልም የዚህ ዓይነት አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ተከራይ እያስወጡና እያስገቡ ከጊዜ ጊዜ የኪራይ ገቢን ማሳደግን ደሃውም በኑሮ የደረጀውም ተጠቅሞበታል፣ ዛሬም ይጠቀምበታል፡፡

አንዳንድ ከንቱዎች ታዲያ ቴሌቪዥን ላይ ወጥተው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ውኃ እስከ ማስቀዳትና እስከ ቡና ቤት አስተናጋጅነት ድረስ የሰፋ ስለመሆኑ በማውራት፣ መንግሥትን ያገዙ ወይም እንጀራቸውን የጋገሩ ይመስላቸዋል፡፡ ምን ይበጃል የሚል ጥያቄ ሲመጣም በደፈናው መታገል ያስፈልጋል ከማለትና የማስተማርን/የቁጥጥር “መፍትሔን” ከመሰንዘር ያለፈና የንቅዝት መፍለቂያ የሆኑ ሥርዓታዊ ችግሮችንና መቃለያቸውን የማሳየት አቅም የላቸውም፡፡ የኢሕአዴግ ሰዎችስ ቢሆኑ፣ “ኪራይ ሰብሳቢነት/ጥገኝነት” የሚሉትን የአቋራጭ ጥቅም አባራሪነት እንታገላለን ሲሉ ከማጥ ውስጥ ሳይወጡ ለመራመድ ከመሞከር የተሻለ ሥራ እየሠሩ ይሆን?!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...